>
5:29 pm - Sunday October 10, 3019

አስረውህም ይፈሩሃል...!!! (በዲ/ን ዐባይነህ ካሴ)

አስረውህም ይፈሩሃል…!!! 

በዲ/ን ዐባይነህ ካሴ  

አይሁድ ጌታን ከሰቀሉት በኋላ ርደተ መቃብሩንም ዐይተዋል። ግን እነሣለሁ ስላለ ፈርተውታል። በመቃብሩ ላይ ከብዙ ሰው በቀር በኹለት እና ሦስት ሰው ጉልበት በማይነቃነቅ ድንጋይ መቃብሩን ዘጉት።
ፍርሃታቸው ናረ እንጅ አልበረደም። እናም በማኅተም ለብጠው አተሙት። እኛ ታሽጓል እያልን እንደምናትመው። አሁንም አልበቃቸውም። የመቃብሩ ቦታ በቅልብ ወታደር ጡንቻ፣ ጦርና ጎራዴ እንዲጠበቅ አደረጉ። ይህ ሁሉ ድርብርብ ግን የጌታን ትንሣኤ እንኳንስ ሊያስቀረው ጥቂትም እንኳ ሊያዘገየው አልቻለም። እንደተናገረ ተነሣ።
እስክንድር ነጋ ኢትዮጵያ ከምትፈልጋቸው ጥቂት ልበ ቅኖች አንዱ ነው። ለሀገር ትንሣኤ ስለሠራ ፈሩት። በጣም እጅግ በጣም ስለፈሩት በአዲስ አበባ ጉዳይ ጦርነት እንግጠምህ አሉት። እርሱ ግን ከብዕር በቀር አንዳችም የለውም። የማይካደው ግን ብእሩ እሳት ይተፋል። ተሐዋሲ ያቃጥላል። አንደበቱ የሰላም ወተት ያፈልቃል። ልትቀጣው ቀርቶ ልትቆጣው ያሳሳሃል።
ስለፈሩት በለንቋሳ ክስ አሰሩት። አስረውትም ምሥክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ካልተሰሙ በሚል እስከ ሰበር ሰሚ ጉዳዩን ሲያንከባልሉት ሲያጉላሉት ቆዩ። አስረውትም ስለፈሩት ጊዜ ማራዘሚያ ሲሹ ይህን አደረጉ። ስምንት ወራት እንደዋዛ አለፉ። በእነርሱ ቤት በትልቅ ድንጋይ መግጠማቸው ነው።
የማይሰበረው እስኬ ብረቱ አንገቱን አልደፋም። እውነት አርነት ያወጣችውን የትኛውም የምድር ሲኦል አይውጠውም። በወኅኒ ሳለ ደመቀ። ጎላ እያለ እንደ ማለዳ ፀሐይ እየቆየ ፈነጠቀ። ፀሐይዋን እንጋርዳት ያሉ በወኅኒው ውስጥ ካለው እስር ቤት ሌላ ውስጠ ውሳጤ እስር ቤት አመጡ።
እነ ስብሐት ነጋን በጠባቧ ክፍል ውስጥ ወስደው ደረቡበት። ካሰሩትም በኋላ እንደገና ማሰራቸው ነው። ጠባቂ ማኖራቸው። ስብሐት በጣም ከሚጠሉት ሰው ጋር መታሰራቸው ጥቅሙ ለእርሳቸው ነው። ያተርፉበታል። እርሱ አይጠላቸውማ! እኩይ ግብራቸውንና አሳባቸውን እንጅ ሰዎቹን ጠልቶ አያውቅም። ሲያሳድዱት ከኖሩት ጋር መገናኘታቸው ግን ትልቅ የታሪክ ክስተት ኾኖ ታይቶኛል። አብረው ከሰነበቱ እስክንድር ይፈውሳቸዋል። እስራታቸውን የፈያታይ ዘየማን ያድርግላቸው።
አስረውህም ይፈሩሃል! አንተ የጽናት ግንብ አሁንም ይበልጥ ያጽናህ!
Filed in: Amharic