>

"...የተናቀች ከተማ በአህያ ትወረራለች...!?!" (ሔቨን ዮሐንስ)

“…የተናቀች ከተማ በአህያ ትወረራለች…!?!

ሔቨን ዮሐንስ

ድሮ የመንግስት ዋነኛ ተቃዋሚ በመባል የሚታወቅ አንድ ግለሰብ ከጃንሜዳ እሰከ መሐል አራዳና ከዚያም እስከ ላጋር ድረስ አሥራ ሁለት አህዮች እየነዳ ሲሄድ ሰዎች ጠጋ እያሉ “የምን አህዮች ናቸው” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ “ኢትዮጵያን ይመሩ ዘንድ የተሾሙት አሥራ ሁለቱ ሚኒስትሮቻችን ናቸው” ይል ነበር አሉ፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ያደረጉት ኢትዮጵያዊ ማን እንደሆኑ አልተገለፀም፡፡ የዶክተር #ጆንሰንን “ራስ ሴላሥ” ወደ አማረኛ የመለሱት #ብላታ_ሲራክ ኀሩይ ወልደ ሥላሴም እንዳልሆኑ አረጋግጫለሁ፡፡
እሳቸው (#ብላታ) ባይሆን የሚታወቁት የአባ ገብረ ሃናን ታሪክ ደግመው ነው። በቤተ መንግስት ግብር ላይ ወጣወጡን በሙሉ በሱፍ ልብሳቸው ላይ በማፍሰስ (የተጋበዘው ልብሴ ነው) በማለታቸው ነው፡፡ #መንግስቱ_ገዳሙ ደግሞ የዚያን ዘመን ሰው ስላልሆነ ድርጊቱ ለእርሱ አልተሰጠም፡፡ መንግስቱ ይልቁን ቢታወቅበት የሚያምርበት፤ አንድ ምስኪን ኢትዮጵያዊ ለአንዲት ጥጋበኛ አህያ እጂ ሲነሳ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህንን ምስል እንደ አዲስ አራተኛ መጽሐፌ ሽፋን እጠቀመዋለሁ ምክንያት የሃሳብ ጥልቀት፤ የሰውየው አስተሳሰብ አድማስ ስፋት የሚደንቅ ስለሆነ ይህንን የምሰርቅበት ዋና አላማ ይህንን ጦማር አንብባችሁ ስጨርሱ ትረዳላችሁ። #መንግስቱ አንድ ምስኪን ኢትዮጵያ ወጣት ለአንድነት ጥጋበኛ አህያ እጅ ሲነሳ ያለውን ሃሳብ በምስል መጽሐፍ ላይ አውጥቶታል። የመጽሐፉን ስያሜ “#ከማን_አንሼ” ብሎታል፡፡ ለማንኛውም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በገዢዎቹ ተደስቶ ስለማያውቅ “አህዮች” ሲላቸው ኖሯልና ጥያቄው ማን ነው ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲህ ያላቸው? የሚል ይሆናል፡፡
አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ያቋቋሙትን የጥንቱን ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ስታገላብጡ በወቅቱ እሳት የላሰ ጋዜጠኛ ይባል የነበረው #ተመስገን_ገብሬ በእነዚያው አሥራ ሁለት ሚኒስትሮች (የአዲሱ ትውልድ ገዥዎች) ላይ መዓቱን ሲያወርድ ታነባላችሁ፡፡ “#አጋሰሶች” ይላቸዋል፡፡ “ከአህያ” ትንሽ አሻሽሏቸዋል ወይስ አብሷቸዋል ማለት ይሆን? “እነዚህ አሥራ ሁለት ሚኒስትሮች ከአጋሰስ በታች ናቸው፡፡ አጋሰስ እንኳ ድግስ በሚኖርበት ጊዜ ጌሾም፣ በርበሬም፣ እህልም ይጭናል፡፡ ለሌላም ሸክም ይጠቅማል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ከአጋሰስ በታች ናቸው” እያለ ይጽፍ ነበር፡፡ ይህ ሰው ዛሬ በኢትዮጵያ ቢኖር ኖሮ የመንግስት ሹማምንቶችን ምን ይላቸው ነበር? ትውልደንስ? ብለን ብናስብ ከስድብ አልፎ በትር ይዞ ሁሉ የሚወጣ ይመስለኛል።።።
ኤረ ወዲያ ነው እኛስ ከትናንት ትውልድ ጋር ልንነፃፀር አንችልም ዝም ብየ ቀደም ብለን ወደ ጠቀስናት እንስሳ ልመልሳችሁ እንገደዳለሁ፤ ወደ አህያዋ፡፡ የአጤ ምኒልክ ጋዜጠኛ ይባሉ የነበሩትን #ደስታ_ምትኬን አንድ ታላቅ ሰው ያናገራቸውን ቃል በቃል አስቀምጠው እነሆ:- ‹‹#ደስታ_ምትኬን ከሰላሳ አምስት ዓመት በፊት መላልሼ አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ጋዜጣና በመነን መጽሔት ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ አባት ጋዜጠኛ ደስታ ምትኬን ባንገርኃቸው ቁጥር ስለሚኒልክና ስለ ጣይቱ እያነሱ፣ መንፈሳቸው እየተረበሸ ልቅሷቸውን ስለሚያስነኩት ቀልድ ወደሚመስል ነገር እወስዳቸዋለሁ፡፡ ‹‹ሚኒስትሮቹን በአህያ የመሰላቸው ማን ነበር?›› እላቸዋለሁ፡፡ ‹‹አረጀሁና ስሙ ጠፋኝ›› ይሉኛል፡፡ ‹‹በአህያ የተመሰሉት እነዚያ ገዥዎች አልተቃወሙምን?›› አልኳቸው፡፡”
“ጋዜጠኛ ደስታ እየሳቁ “አንድ ላይ ተሰብስበው ለአልጋ ወራሸ አቤቱታ አቀረቡ እየተባለ ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ ቀደም ሲልም ራሳቸው አልጋ ወራሸ የእነዚያን ሰዎች አሰራር እንደማይፈቅዱት ያውቁ ስለነበር ያቀረቡት አቤቱታ “በሥላሴ አርአያና አምሳል የተፈጠርነው ሰዎች አህያ ተባልን ብለው ነበር ስሞታ ያቀረቡት ይባላል፡፡ አልጋ ወራሹ ፈጣን አዕምሮ ያላቸው ሰው ነበሩና “አህያ በሥላሴ አምሳል አልተፈጠረችም፡፡ በሰይጣን አምሳልና አርአያ ነው የተፈጠረችው ካላችሁ ማስረጃችሁን አምጡና ሰውየው ይቀጣል አሉ ይባላል” በማለት አጫውተውኛል፤ መሬቱ ይቅለላቸውና፡፡” ሲሉ በማዘን ትናትን ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።
ተረባና ቅኔማ ትናንት ትውልድ ላይ ቀረ ሃሃሃሃ፤ ዛሬማ አልቃሽና ሙሾ እየየ ብቻ ነው ያለው። አንድ አንባቢ ለጦማር አዘጋጅ ያቀረበው ጥያቄ “ወያኔዎች አዲስ አበባን የወረሩት በሺህ አህዮች እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ አህዮቹ የት ደረሱ?” የሚል ነበር፡፡ የጦማር መልስ “ከየመኪናው ገቢና ውስጥ ናቸው” የሚል ነበር፡፡ ይበል! ይበል! እኔ ብሆን ኖሮ “በየቢሮው ገብተዋል” ነበር የምለው፡፡ ያው ነው፡፡ #ስልቻን_ቀልቀሎ -#ቀልቀሎን_ስልቻ! ዋናው ነገር በዚያ ሁሉ የጊዜ ርዝማኔ መካከል አህያ የፖለቲካ እንስሳችን ሆና መቆየትዋ ነው፡፡ #የአዲስ_አበባ ልጆች ደግሞ አንድ አዲስ ተረብ ብጤ አውጥተው እንደነበር ይነገራል፡፡ የዛሬን አያድርገውና ንቁ ተሳታፊ ነበሩ በፓለቲካው ለማለት ነው! እናም ያ ተረባቸው እንዲህ የሚል ነበር
“#በሁለተኛው_አብዮት” ማለትም በወያኔ ዘመን ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡ እንስሶች እንዲሸለሙ (በአሥረኛው ዓመት በዓል ላይ) ተወሰነና ኮሚቴ ተቋቋመ አሉ፡፡ የኮሚቴው ዋና ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ሆኑ፣ እንደ አራዶች ተረብ፡፡ ብዙና አወዛጋቢ የማጣራት ተግባር ተካሂዶ በመጨረሻ ላይ ግመል፣ ውሻና አህያ ስለ ቀሩ ክቡርነታቸው ዘንድ እየቀረቡ አስተዋጾዋቸውን በዝርዝር እንዲያሰሙ ተደረገ፡፡”
“በዚሁ መሰረት #ውሻ ቀረበና ለወያኔ ያለውንና የነበረውን ታማኝነት አብራራ፡፡ “የአብዮታችን ምልክትና ተምሳሌት መሆንዋን በምናምነው በግመል ላይ ስትጮኸ ስለነበረ ወድቀሃል” ይሉታል፡፡ ቀጥሎ አህያ ትመጣለች፡፡ ለወያኔ አብዮት ከመነሻው አንስቶ ያበረከተችውን አገልግሎት በዝርዝር አቀረበች፡፡ በበረሃና በጫካ ስትሰጥ የባጀችውን ልዩ ልዩ ውለታ አብራርታ ነገረቻቸው፡፡ ክቡርነታቸው ግን “አንች መሸለም ለሐሜት ያጋልጠናልና በአደባባይ የሚደረገውን ግርግር እንተወው፡፡ እና ያሰብነው ግመልን ለመሸለም ነው” ይሏታል፡፡ በዚህ ጊዜ አህያ ‹‹…ድሮስ ቢሆን እናንተ ለወገኖቻችሁ መች ትመቻላችሁ? ለእኛ ሲሏችሁ ምቀኝነታችሁ ይገርማል…” አለች እያሉ አራዶች ተረባቸውን በቅኔ አቅርበዋል።
አሁንም ከአህያ አልራቅንም? ትላልቅ ሰዎች ማለትም ሊህቃኖች የህውሃትን መንግስት የሚገልፁት አህያ_ገዥዎች ወይስ ገዥ_አህዮች? እንበላቸው እያሉ ለመሪዎቹ ያላቸውን ንቀት ይገልፁ ነበር። እኔ በሁለቱም አባባል ደስ አይለኝም፡፡ ከሆነ ደግሞ ምንም ለማድረግ አይቻልም፡፡ ሰዎች በየጊዜው ቀልድ ይፈጥራሉና ወያኔ ወገኖቻችን እንደ ራስ ተፈሪ ሚኒስትሮች “በሥላሴ አርአያ የተፈጠረነውን ሰዎች አህያ አሉን” እንዳላሉ ተስፋ አለኝ፡፡ “አህያ በሳጥናኤል አምሳል” ለመፈጠረዋ ደግሞ ማስረጃ ለማምጣት አይችሉም፡፡ በነገራችን ላይ የታህሳሱ አብዮተኛ መንግስቱ ንዋይ “#የተናቀ_ከተማ_በአህያ_ይወረራል” በሚል ጥቅስ ይታወቃሉ፡፡
ይህ አባባል እንደ ውብ ቋንቋም፣ እንደ ንግርትም እየተነገረ እነሆ ግንቦት 20 ቀን 1983 አዲስ አበባ የነበራችሁ ሰዎች እንደምታስውሱት ሥፍር ቁጥር የሌላቸው አህዮች በአምስቱም የአዲስ አበባ ከተማ በሮች በመግባት የከተማይቱን ነዋሪዎች ቁጥር አሻቅበውት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳ አህዮቹ ወደ አመሻሹ ላይ ከተማውን ለቅቀው ወጥተዋል ቢባልም መንፈሳቸው ግን ከቀድሞ ተጠቃሚዎቻቸው ዘንድ ቀርቷል፡፡ በዚያን ሰሞን የወይዘሮ ገነት ዘውዴ የትምህርት ሚኒስትርነት እንቅፋት አጋጥሞት እንደነበር ተከታትለናል፡፡ በምክር ቤት ውስጥ ለራሳቸው ነፃነት ሰጥተው የሚሟገቱ አንድ ተቃዋሚ ሴቲቱ ለዚህ ታላቅ ስራ ብቃት እንደሌላቸው፣ እስካሁንም በፀረ ወጣትነትና በፀረ ትምህርት አቋማቸው ብዙ ችግር እንደ ፈጠሩ በማንሳት ሹመታቸውን ይቃወማሉ፡፡ አቶ መለስ በተለመደው ቁጣቸውና ግልምጫቸው “የፈለግነውን መንገደኛ፣ የፈለግነውን ድንጋይም ቢሆን ለማስቀመጥ እንችላለን” ብለው መደንፋታቸው አይዘነጋም፡፡ ከዚህ አነጋገር የምንገነዘበው ያው እስካሁን የምናውቀውን ሐቅ ነው፡፡ ዛሬስ የፈለጉትን መንገደኛ እና የፈለጉትን ድንጋይ የሚያስቀምጡ መሪዎች የሉንም ወይስ?
ዝም ብየ ወደ መለስ ንግግር አንድምታ ልግባ አንደኛ “ድንጋይም፣ አህያም፣ ግመልም” በኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ሊይዝ ይችላል ማለት ነው፡፡ መለስ ናቸው ያሉት የሚሉት፡፡ ሁለተኛ፣ ይህች አገር የተወሰኑ ግለሰቦች “ግዛት” መጫወቻና የግል ንብረት ናት፡፡ ሦስተኛ፣ ገዥዎቻችን ትናንትም ዛሬም ማንም የማይጠይቃቸው #ምሉዕ_በኩለሄ ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ አገር ያለው ችግር ሁሉ የሚፈታው በእነሱ የእይታ አድማስ፣ በእነሱ አመለካከትና በእነሱም እምነት አንጻር ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ በመሆኑ የቁጣቸው፣ የቀለሃቸው፣ የሰደፋቸውና የሰይፋቸው ሰለባ መሆን አለበት፡፡ እንደማለት ነበር፤ ኦ ሀይል እግዚአብሔር በኪነ ጥበብ አነሳልን። የዛሬዎቹስ ከትናንቶቹ ምን ተምረው ይሆን?
ክፍል ሁለት ይቀጥላል።
Filed in: Amharic