>
8:56 pm - Tuesday June 6, 2023

የኢሳያስ ነገር ለምን ጆን ጋራንግን ያስታውሰኛል? (አሰፋ ሀይሉ)

የኢሳያስ ነገር ለምን ጆን ጋራንግን ያስታውሰኛል?

አሰፋ ሀይሉ

 

አሜሪካ የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ የነበረውን ዶ/ር ጆን ጋራንግ የፈጠረችው ደቡብ ሱዳንን ገንጥሎ፣ ሱዳንን ሁለት ቦታ እንዲከፍልላት ነበር፡፡ ኢትዮጵያም፣ ኬንያም፣ ኡጋንዳም፣ ብዙዎችም ከአሜሪካ ጎን ተባብረው በመጨረሻ ሱዳን እጇን ሰጠች፡፡ አልበሽር አማራጭ አልነበረውም፡፡ ከጆን ጋራንግ ጋር በሰላም ስለሚገነጠሉበት ሁኔታ መወያየት ጀመረ፡፡ 
 
በመሐል ግን ሁለቱም የሆነ እውነት የተገለጸላቸው ይመስለኛል፡፡ የአሜሪካ ዋነኛ ዓላማ ለሱዳን ህዝቦች ዕድገትና ብልጽግና ተቆርቁራ ሳይሆን፣ እስላማዊ ነው ብላ የምታስበውን የሰሜን ሱዳን መንግሥትና ህዝብ በምትችለው ሁሉ ለመቆራረጥና ለማሽመድመድ ነበር፡፡ ያንን የተረዳው የደቡብ ሱዳኑ ነፃ አውጪ ጆን ጋራንግ ባለቀ ሰዓት የሱዳንን ህዝብ ሁለት ቦታ ከመክፈል የተሻለ ሶስተኛ አማራጭ ተከሰተለት፡፡ 
 
ጆን ጋራንግ ከአልበሽር ጋር ባደረጋቸው ተከታታይ ውይይወቶች የደቡብ ሱዳን ህዝብ በሪፈረንደም ፍላጎቱን እንዲገልጽ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ ያንን አለመቀበል አይችልም ነበር የካርቱም መንግሥት፡፡ ነገር ግን በውይይቶቹ መሐል ጆን ጋራንግ ሰሜኑ እስልምናውን ይዞ፣ ደቡቡም ክርስትናውን ይዞ፣ የሀይማኖት ነጻነትን ለህዝባቸው ሰጥተው፣ የህዝቦቹን እኩልነት አክብረው፣ ሁለቱም የሀገራቸውን የተፈጥሮ ሀብት በጋራ እያለሙ፣ በፍትህ ተካፍለው በአንድ ባንዲራ ሥር በፍቅር መኖር የሚችሉበት አማራጭ ለአጠቃላዩ የሱዳን ህዝብ ከሁሉ የተሻለው አማራጭ መሆኑ የተገለጸለት ይመስለኛል፡፡ 
 
እና ጆን ጋራንግ ለዓመታት ሲፋለመው ከነበረው ዋነኛ ጠላቱ ከአልበሽር ጋር መሻረክና መወዳጀት ብቻ ሳይሆን፣ ለሚዲያዎችም በተደጋጋሚ ስለ አጠቃላዩ የሱዳን ህዝብ ያለውን ራዕይ በግልጽ መናገር ጀመረ፡፡ በተለይ ወደ መጨረሻ ላይ አሜሪካኖቹን በጣም ያበሳጨ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጠ ጆን ጋራንግ፡- 
 
‹‹በነገራችን ላይ ይህን ሁሉ ዓመት ከሰሜኑ መንግሥት ጋር 
የተዋጋነው ደቡብ ሱዳንን ለመገንጠል አይደለም፣ ዋናው 
ዓላማችን እኩልነት፣ ፍትሃዊ የሀብትና የዕድል ክፍፍል 
እንዲኖር፣ የሁሉም ሱዳናዊ መብት በእኩል እንዲከበር 
ነው፣ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች የሚከበሩበትን መንገድ 
ካገኘን፣ መገንጠላችንን ልንተወው ሁሉ እንችላለን፣ 
መገንጠል የኛ ዋነኛ አጀንዳ አይደለም!›› 
 
ይህን ንግግር ሲናገር ዓለም ጉድ አለ፡፡ በተለይ ስንት ዓመት ሙሉ ቀኝ እጃችን ብለው የደገፉት አሜሪካኖች ሰማይ የተደፋባቸው መሰሉ፡፡ ይህ የሆነው በ2005 ነው፡፡ ይህ ከሆነ ከጥቂት ወራት በኋላ (በሐምሌ ወረ) ዶ/ር ጆን ጋራንግ በሄሊኮፕተሩ እየሄደ ሳለ፣ በአየር ላይ በግል ጠባቂው ከኋላው በማጅራቱ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አለፈች፡፡ 
 
ከህልፈቱ በኋላ የጆን ጋራንግን ሥልጣን ምክትሎቹ ሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር ተቀራመቱት፡፡ ጋራንግ በሞተ በ5 ዓመቱ የደቡብ ሱዳንን ‹‹ሪፈረንደም›› አካሄዱ፡፡ ከእስላማዊቷ ሰሜን ሱዳን የተለየች ራሷን የቻለች የደቡብ ሱዳን መንግሥት በይፋ ተመሠረተች፡፡ እና ትልቋ ሱዳን ሁለት ቦታ ተከፈለች፡፡ 
 
እስካሁን የሚገኝ ትልቅ – እንደ ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ከፍ አድርጎ የደቡብ ሱዳንን ክርስትያኖች ሲያሻግራቸው የሚያሳይ የሚመስል ኃውልት – ለጆን ጋራንግ ቆሞለታል በጁባ፡፡ በስሙ ቤተዘመክርና ሌሎችም የተለያዩ ሃውልቶች ቆመውለታል፡፡ ያነሳው አስገራሚ ሃሳብ፣ እና የአሟሟቱ ጉዳይ ግን ተረስቶ ቀረ፡፡ 
 
የኤርትራንም ነገር ሳስብ የደቡብ ሱዳኑ ነገር ይመጣብኛል፡፡ ብዙውን የኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ታሪክ ብዙዎቻችን ስለምናውቀው ልለፈው፡፡ እና ኢሣያስ አፈወርቂ ከ3 ዓመት በፊት ይመስለኛል (አብይ አህመድ ከመምጣቱ ጥቂት ወራት በፊት) ስላደረገውና ስላስደነገጠኝ ነገር ላንሳ፡፡ 
 
ኢሣያስ በአፍሪካና በመላው ዓለም ለሚገኙ ሀገራት የዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች በሙሉ (ተመድንና አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ) ባሰራጨው ኦፊሴላዊ ደብዳቤ ላይ – 
 
‹‹ እኛን (ኤርትራን) እና ኢትዮጵያን ያጣላችን፣ 
እና እያጣላችን ያለችው፣ አሜሪካ ናት፣ 
ሌላ የሚያጣላን ምንም ይህ ነው የምንለው 
ምክንያት የለንም!›› 
 
በማለት ለዓለም አወጀ፡፡ ዓለም ጉድ አለ፡፡ አሜሪካኖች በድፍረቱ ተገርመው (እና ተናደው ይመስለኛል) ኤርትራን ‹‹የአፍሪካ ሰሜን ኮርያ››፣ ኢሣያስን ደሞ ‹‹የአፍሪካው ኡን›› (ኪም ጆንግ ኡን) ብለው በየጋዜጦቻቸውና ሚዲያዎቻቸው ተሳለቁበት፡፡ 
 
እንዳልኩት ግን ያ የኢሣያስ መግለጫ በሕይወቴ እጅግ ከደነቁኝ ነገሮች አንዱ ነበር፡፡ ይሄ ሰው ብዙ ዓመታት ኖሮ ኖሮ በመጨረሻ እውነቱ ተገለጸለት? ወይስ ምን አስቦ ነው? እንዴት ይህን ሊል ቻለ? ብዬ ደጋግሜ አስቤያለሁ፡፡ ያ የኢሳያስ ደብዳቤ እስካሁም ገርሞኝ አላባራም፡፡ ወደፊትም ሲያስገርመኝ ይኖራል፡፡ 
 
በመሐል አብይ አህመድ መጣና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ተሻረከች፡፡ ስምምነቱ ብዙ ግልጽነት ቢጎድለውም ኢሣያስ አፈወርቂ ግን በሚዲያዎች ሲጠየቅ እየደጋገመ:- 
 
‹‹እኛን የሚያስጨንቀን የድንበር ጉዳይ አይደለም፣ 
ባድመ ዕድሜ ልኳን ልትቀር ትችላለች፣ የኢኮኖሚና 
ንግድ ጉዳይም አይደለም ዋናው፣ ከኢትዮጵያኖች 
ጋር ወንድማማቾች ነን፣ አሁን ሁለቱን ህዝቦች 
የሚያቀራርብ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ጀምረናል፣ 
ወደ ኋላ የሚመልሰን ምንም ነገር የለም፣ ሌላው 
ከዚያ የሚቀጥል ይሆናል!›› 
 
እያለ ነበር የሚናገረው፡፡ ይሄ ሰው ስንት ዘመን ኖሮ ኖሮ – ባለቀ ሰዓት – ገረመኝ በእውነቱ፡፡ እና ፈራሁለት፡፡ የጆን ጋራንግን እጣ ፈንታ እያሰብኩ፡፡ 
 
ሰሞኑን ታዲያ የአሜሪካኖቹን – በተለይ ያኔ የኢሳያስንና የመለስን እጅ ይዞ ኢትዮጵያን ሁለት ቦታ የከፈለውን ስምምነት ያፈራረመው የሲ አይ ኤ ልዑክ የሄርማን ኮህንን – መጠን ያለፈ መንጨርጨርና መቅበዝበዝ ስመለከት – እነዚህ ሰዎች ምን ሆነዋል? ማለቴ አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ዳግም መቀራረብ እጅግ የረበሻቸውና ወደ የት ሊያመራ ይሆን ብለው በእጅጉ የተጨነቁ ይመስላሉ፡፡ 
 
በእርግጥ አሜሪካኖቹ የእኛ ሰብዓዊ አያያዝ ጉዳይ አያስጨንቃቸውም ማለት አይደለም፡፡ ሊያስጨንቃቸው ይችላል፡፡ የአሁኑ መቅበዝበዛቸው ግን ከዚያም ከፍ አለብኝ፡፡ እና የተረበሹ ይመስላሉ፡፡ ሌላ ቀርቶ በእነርሱ (በዶናልድ ያማማቶ) ጥቆማ ሥልጣን ላይ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳለንም የዘነጉት ይመስላሉ ከንዴታቸው የተነሳ፡፡ 
 
እና አብይ አህመድ የቱንም ያህል የኢትዮ ኤርትራን ፍቅርና መቀራረብ ለማምጣት ቢጥር – እና በዚህ በኩል ብዙ የሚያስመሰግኑት ጥረቶች ያደረገ ሰው ቢሆንም – ከመነሻው ግን በአሜሪካኖቹ ጥቆማ ወደ ሥልጣን የመጣ ሰው መሆኑን እያሰብኩ – አንዳንዴ – ለዚህ ለኢሣያስ እፈራለታለሁ፡፡ በሆነ አጋጣሚ ሳያስበው – የአብይን እጅ ጠምዝዘው – ኢሣያስን ጉድ እንዳያደርጉት እሳቀቃለሁ፡፡ ጆን ጋራንግን ደጋግሞ እያስታወሰኝ፡፡ አይ ኢሣያስ፡፡ ባለቀ ሰዓት እንዲህ አንጀታችንን ትበላው? 
 
የሆነ ሆኖ – ለኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች አንድም ጥይት የማይተኮስበት – እውነተኛ ሠላምና ወዳጅነት እንዲወርድልን ከልብ እመኛለሁ፡፡ ሁልጊዜም በህልሜም በእውኔም የምመኘው አንድ ነገር ቢኖር – አንድም ሀበሻ እናት – ለአንዲትም ቀን – ልጄ ተገደለብኝ፣ ልጄ ቆሰለብኝ፣ ልጄ ተቆረጠብኝ፣ ልጄ ታሰረብኝ ብላ የማታነባበት የማያልቅ የሠላምና የፍቅር ዘመን እንዲመጣልን ብቻ ነው፡፡ የባሩድ ጭስ ጠፍቶ፣ የእጣን ጭስ የህዝባችንን ማጀት የሚሞላበት ቀን እንዲያመጣልን የሁልጊዜ ምኞቴ ነው፡፡ ለዚያ ፈጣሪ ይርዳን፡፡ 
 
መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic