>

ከሕገ ወጡ የሕወሐት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት ከመንግሥት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ ...!!! (ኢ .ፕ. ድ)

ከሕገ ወጡ የሕወሐት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት ከመንግሥት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ …!!!

ኢ .ፕ. ድ

*…የፍርድ ቤት መያዣ ከወጣባቸው ከፍተኛ የሕውሐት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ ጥሪ ቀረበላቸው
***
በሕገ ወጥ ጥቃቱ እና ተያያዥ በሆኑ የወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተጠረጠሩ እና በዚህም መነሻ የፍርድ ቤት መያዣ ከወጣባቸው ከፍተኛ የሕውሐት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱ የመጨረሻ ጥሪ ቀረበ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ከሕገ ወጡ የሕወሐት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት ከመንግሥት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ በሚል ባወጣው ጥሪ ላይ እነደተገለጸው፤ እነዚህ ወገኖች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እና መኖሪያቸው በመመለስ ማኅበረሰቡን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
“በዚህ መንገድ ከአጥፊው ቡድን ተለይተው ወደሰላማዊ ኑሯቸው የሚመለሱ የክልሉ ተወላጅ ዜጎች፣ የትኛውም የሕግ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው፣ ከአጥፊ ተግባራት ተቆጥበው፣ ወደ ሥራቸው እና ኑሯቸው በሰላም መሠማራት ይችላሉ” ተብሏል።
እነዚህን ዜጎች በመልካም ሁኔታ በመቀበል እንዲተባበሩ እና የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ለየሚመለከታቸው የጸጥታ፣ የአስተዳደር እና የሕግ አስከባሪ ተቋማት አስፈላጊው መመሪያ ተሰጥቷቸዋል ያለው ማሳሰቢያው፤  የጥፋት ቡድኑ አካል ሆነው በተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የፍርድ ቤት መያዣም የወጣባቸው ከፍተኛ የሕወሐት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች፣ በሰላም እጃቸውን ለሕግ አስባሪ ተቋማት እንዲሰጡ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።
“እነዚህ አመራሮች እስከዛሬ ከደረሰው ሀገራዊ ጥፋት እና ጉዳት በመማር፣ ለፍትሕ ራሳቸውን በማቅረብ፣ ተጨማሪ ሀገራዊ ኪሣራ እንዳይደርስ እና በከንቱ የዜጎች ደም እንዳይፈስ የበኩላቸውን በጎ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ መንግሥት ጥሪ ያቀርባል” ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ማሳሰቢያ ገልጿል።
ይሄንን የሚያደርጉ ከፍተኛ የሕወሐት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ራሳቸውን ከከፋ ቅጣት፣ ወገናቸውን ከመጎሳቆል ይታደጉታል፤  ይሄንን የመጨረሻ ጥሪ ተጠቅመው ራሳቸውን ለፍትሕ በማያቀርቡ የሕወሐት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ግን፣ ሕግ በሚፈቅደው ሁሉም ዓይነት መንገድ ሕግ ለማስከበር ሲባል አስፈላጊው ሁሉ የሚፈጸም መሆኑን ቀድመን እንገልጻለን ሲልም ነው የጽህፈት ቤቱ ማሳሰቢያ የገለጸው።
Filed in: Amharic