በቅድሚያ የአዲስ አበባ ህልውና ለኢትዮጵያ ንቅናቄ በቴዎድሮስ አበባው*በቅፅል ስሙ በቴዲ ቡናማው እና በየጊዜው በማንነታቸው የዘር ፍጅት ወንጀል በተፈፀመባቸው ዜጎች ሁሉ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ የሙዋቾችን ነብስ ፈጣሪ በአፀደ ገነት እንዲያኖር፤ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው ኢትዮጵያዊም መፅናናትን እንዲሰጥ ልባዊ ምኞቱን ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በህወሀት መራሹ ገዢ ቡድን የተጫነበትን አስከፊ የመከራ እና የጨቁዋኝ ተጨቁዋኝ ትርክት እምቢኝ ብሎ ከከፋፋዩ እና አምባገነኑ ፋሽስታዊ አገዛዝ ለመላቀቅ የሞት ሽረት ትግል አድርጎ በታላቅ ተጋድሎ ስርዓቱን ገፍትሮ ለመጣል ከመቃብር አፋፍ ላይ አድርሶት እንደ ነበር እሙን ነው። ነገር ግን በህውሀት ጉያ ተፈልፍለው ያደጉት የለውጥ ሀይል ነን ባዮች ከስም የአንድነት ፖለቲካ አራምጅ ነን ባይ የፖለቲካ ደላሎቻቸው ጋር በመሆን በቅቤ አፋቸው እያማለሉ የመዲናችን የአዲስ አበባ ሕዝብንም ሆነ የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ ከድጥ ወደ ማጡ አሸጋግረውት ህልውናውን እጅግ አደጋ ላይ ጥለውታል።
ከህፃን እስከ አዋቂ ያሁሉ ዋጋ የተከፈለለት እና ዜጎች ከህውሀት መራሹ ኢህአዲግ የአልሞ ተኳሾች ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጠ እንደቅጠል በመርገፍ ዋጋ የከፈለለት ትግል ለጨፍጫፊዎች ለውጥ እንዳል ነበርም ንቅናቄያችን ጠንቅቆ ያውቃል ። ነገር ግን ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ሞት እረክሷል ፤የእሬሳ ክምርም በየጊዜው ማየት ልማዳችን ሆንዋል፤ዜጎችን በማንነታቸው እያሳደዱ ቆራርጦ መጣል፣ከነ ህይወታቸው በእሳት ማቃጠል የስርዓቱ ዋነኛ መገለጫ ተግባሩ ሆንዋል፤ ዜጎች ተቆራርጠው ኩላሊታቸው የሚበላበት፤ሆድ እየተቀደደ ፅንስ የሚወጣበት፤ህፃናት ጭምር ወጥተው የማይገቡበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይሁን እንጅ የወገን ደም የማይከረፋቸው የዚህ ገዢ ቡድን የፖለቲካ ደላሎች አዲስ አበቤውን ጨምሮ ዜጎች በማንነታቸው እየተሳደዱ እየረገፉ ባሉባት ሐገር ዛሬም አሻጋሪው የለውጥ ሃይል እያሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ሲቆምሩ ይታያሉ።
ነገር ግን ህልውናውን ለማጥፋት እርብርቦሽ የሚደረግበት አዲስ አበቤውም ሆነ ንቅናቄያችንን ጨምሮ በማንነቱ የሚሳደደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ የለውጥ ሀይል በሚል ስም የሚነግደው ፅንፈኛ ገዢ ቡድን በንፁሀን ደም የተጨማለቀውን የኦነግ አራጅ ድርጅት ከነመሳሪያው እየተግተለተለ ገብቶ የሐገሪቱን ቁልፍ ቦታዎች እንዲይዝ ሲፈቅድ እና ሲስማማ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት እንዳልቆመ ጠንቅቀን ተረድተናል።
አዲስ አበባ “ ኬኛ” የሚል የዘመናት ትርክታቸውን እና ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ህልማቸውን እውን ለማድረግ በጥምር እየፈፀሙ ያሉት አረመኔያዊ ተግባርም የዚሁ ማረጋገጫ ነው።
የአዲስ አበባ ህልውና ለኢትዮጵያ ንቅናቄ አዲስ አበባ ኢትዮዽያዊነትን አጣምራ የያዘች ፤ የኢትዮዽያ ህብር ፤ የራስዋ የሆነ መገለጫ ታሪክ ፣ ባህል እና የተለያዩ እሴቶች ያልዋት የአዲስ አበቤዎች እና የመላው ኢትዮጵያዊ ርዕሰ መዲና እንጅ ጊዜ ሰጠን የሚሉ ፅንፈኞች ልዩ ጥቅም ሊጠይቁባት የሚገባት ከተማ አለመሆንዋን በፅኑ ያምናል ።
ይሁን እንጅ ይህንን ሀቅ ሰልቅጠው የዋጡ የኦነጋዊው/ኦዴፓ (ብልፅግና) ፅንፈኛ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ከቻሉ የሌላውን ኢትዮጵያዊ የዜግነት መብት እየጨፈለቁ ግዛት ማስፋፋት እና በኦሮሞ ስም የአገዛዙን የበላይነትን ማስቀጠል ፤ ያ ካልተቻለ ደሞ ትልቅዋን ኦሮሚያ ለመገንባት ቅድሚያ የኢትዮጵያዊነት ማሰሪያ ውል የሆነችውን አዲስ አበባን ቅርፅ እና ይዘትዋን በዲሞግራፊ ቅየራ መለወጥ እና ማጥፋት የሚል ለማንም የማይበጅ ደም አፋሳሽ እና ሐገር አፍራሽ ኦነጋዊ ዓላማቸውን እየተገበሩ ይገኛሉ።
አዲስ አበቤው በእነዚህ እኛ እናውቅልሀለን በሚሉት ፅንፈኞች አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገባት እና የኖረባት ከተማ እስከማትመስለው ድረስ የአንድን ጎሳ ለማንገስ በሚደረግ እኩይ ሴራ ባህሉን ፤ ቁዋንቁዋውን፣ እሴቱን፣ ሐብት የማፍራት መብቱን ሁሉ ተነጥቆ ተፈጥሮ ያደለችውን የሰውነት መብት ተገፎ ህልውናው አደጋ ላይ ወድቅዋል፤ በማንነቱም እየተሳደደ በየጊዜው አሰቃቂ የግድያ ወንጀልም እየተፈፀመበት መገኘቱም የዚህ ውጤት ነው።
የቴዲ ቡናማውን ጨምሮ የሌሎችም የመጨፍጨፍ ምክንያት ይሄንኑ የፅንፈኛውና የተረኛው ገዢ ቡድንን አካሄድ ተጠይፈው ኢትዮጵያዊነታቸውን ይዘው ህልውናዋ አደጋ ላይ ለወደቀው የአዲስ አበባ ህዝብ ፀንተው መቆማቸው ነው።
የአዲስ አበባ ህልውና ለኢትዮጵያ ንቅናቄም አገዛዙ ይህንን ሁሉ ግፍ እና በደል ፤ የዘር ፍጅት ወንጀሎችን እና በኢትዮጵያዊነት ላይ የተነጣጠሩ ጥቃቶችን በማናለብኝነት እንዲፈፅም ድፍረት እና ወኔ የሰጠው ኢትዮጵያዊው በአንድነት አለመቆሙ እና ያለመደራጀቱ ብቻ ሳይሆን የኦነጋዊው/የኦዴፓ/ብልፅግናን አደገኛ አካሄድ እና አፍራሽነትን አስቀድሞ የተረዳውን ታላቁ የነፃነት ታጋይ እና የፅናት ተምሳሌት የሆነውን እስክንድርን፣ስንታየሁን፣አስቴርን፣አስካለን እና ሌሎችም የነፃነት ታጋዮቹን ያለስማቸው ስም እየሰጠ እስርቤት ወርውሮ ሲያሰቃያቸው በጋራ ቆሞ ታግሎ ማስፈታት አለመቻሉ ነው!!!
ስለዚህ ንቅናቄያችን ይህ ስርዓት ፍትሕ ተጠይቆ የማይገኝበት እና በህግ አካላቱ ላይም የተጣለው ተስፋ ፈፅሞ ተሟጦ ከዜሮ ድምር በታች በመሆኑ ማንኛውም ሰው የቴዲን የአሟሟት ሁኔታ በግልም ሆነ በቡድን ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል እና የአገዛዙን አደገኛ አካሄድ ተገንዝቦ እራሱንም ሆነ ሐገሩን ከተመሳሳይ ጥቃት እንዲጠብቅ እና እንዲከላከል አ.ህ .ኢ.ን ያሳስባል።
ማሳሰቢያ:-የአዲስ አበባ ህልውና ለኢትዮጵያ ንቅናቄ በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፤ለቴዲ ቡናማው እጮኛ እና ቤተሰቡ እንዲሁም ለስፖርት አፍቃሪዎች በሙሉ መፅናናትን እየተመኘ በዚህ አጋጣሚ በቴዲ ቡናውማው ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እና በማንነት ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ሳለ የስርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች የአገዛዙን ገበና ለመሸፈን ሲሉ ሕዝብን ለማደናገር ከሚነዙት የሀሰት መላምቶች እንዲታቀቡ እና በንፁሀኖች ደም መቆመራቸውን እንዲያቆሙ ያሳስባል።
አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊነት ማሰሪያ ውል ናት!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!
ከአህኢን ጽ/ቤት
መጋቢት :-2013