>
5:13 pm - Thursday April 18, 9776

አሜሪቃ ሄይቲና ጦቢያ (መስፍን አረጋ)

አሜሪቃ ሄይቲና ጦቢያ

 

መስፍን አረጋ


ሩሲያ ዶናልድ ትራምፕን በመደገፍ በፕሬዘዳንታዊ ምርጫችን ጣልቃ ገባችብን በማለት አሜሪቃኖች ማለቃቀስ – ይልቁንም መነፋረቅ – ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡  በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ፣ በተለይም ደግሞ በምርጫ ጣልቃ በመግባት ግን ራሷን አሜሪቃንን የሚስተካከል ቀርቶ እግሯ ጫፍ የሚደርስ የለም፡፡  

ለምሳሌ ያህል የሩሲያው ቦሪስ የልትሲን (Boris Yeltsin) በ1996 ዓ.ም ድጋሚ ለመመረጥ ሲነሳ፣ የነበረው የሕዝብ ድጋፍ 6% ብቻ ስለነበር፣ በትክክለኛ ምርጫ እንደማያሸንፍ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡  ቦሪስ የልትሲን ግን ሩሲያን በማሽመድመድ አሜሪቃን ብቸኛ ልዕለኃያል (sole superpower) ለማድረግ ቁልፍ ሚና የተጫወተ ያሜሪቃ ቡችላ ስለነበር፣ ድጋሚ መመረጡ ላሜሪቃ ወሳኝ ነበር፡፡ 

ስለዚህም የወቅቱ ያሜሪቃ ፊምበር (president) ቢል ክሊንተን (Bill Clinton) በአይ-ኤም-ኤፍ (IMF) በኩል 10 ቢሊዮን ዶላር ሩሲያ ላይ አፍስሶ፣ ሪቻርድ ድሬስነርን (Richard Dresner) የመሳሰሉ እውቅ የፖለቲካ አማካሪወች የልትሲነን እንዲያማክሩ ሩሲያ ላይ በይፋ አሰማርቶ፣ በመጨረሻ ደግሞ እሱ ራሱ መስኮብ ድረስ በመሄድ አንዱን እጩ (የልትሲንን) የሚደግፍ አድሏዊ ንግግር አድርጎ፣ የምርጫው ዘመቻ ሲጀመር ውራ (የመጨረሻ) የነበረው የልትሲን የቅርብ ተፎካካሪውን በ 13% በልጦ በማሸነፍ እንዲመረጥ አድርጓል፡፡  ምርጫው እንደተጠናቀቀ ደግሞ ያሜሪቃው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስትሮብ ታልቦት (Strobe Talbot)  “ምርጫው ነጻና ፍትሓዊ ነው”  የሚል መግለጫ ተሸቀዳድሞ አውጥቷል፡፡  ለመምረጥ የሚችሉ አዋቂወች (adults) ቁጥር 500ሺ ብቻ በሆነባትና በየልትሲን ትእዛዝ ያለ ርህራሄ በተቦነበችው (bombed) በቸቺኒያ (Chechnya) ውስጥ፣ ቁጥራቸው ካንድ ሚሊዮን የሚበልጥ መራጮች በምርጫው ተሳትፈው 70 በመቶወቹ (70%) የልትሲንን መረጡ የተባለለት ምርጫ በምንም ዓይነት አተያይ ነጻና ፍትሓዊ ሊሆን እንደማይችል የተገነዘቡት ሚካኤል ሜዶውክሮፍትን (Michael Meadowcroft) የመሳሰሉ የምርጫ ታዛቢወች ደግሞ በበላዮቻቸው ማስጠንቀቂያ አፋችውን ለመያዝ ተገደዋል፡፡

ዲሞክራሲ ከኔ ወዲያ ላሳር የሚለው ያሜሪቃ መንግሥት የዲሞክራሲ ማሰሮ (ገንቦ) ቢከፍቱት ተልባ ነው፡፡  ላሜሪቃ መንግሥት ዲሞክራሲ ማለት ያሜሪቃን (በተለይም ደግሞ የነጭ አሜሪቃን) ጥቅም ማስከበሪያ መንገድ እንጅ በራሱ ግብ አይደለም፡፡  ማናቸውም የሌላ አገር መንግሥት ያሜሪቃን ጥቅም ለማስከበር ሽንጡን ገትሮ የቆመ፣ ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት የሚል ያሜሪቃ ሎሌ ከሆነ፣ የቱንም ያህል አምባገነን ቢሆንም ያሜሪቃ ሎሌነቱን እስከቀጠለ ድረስ አገዛዙ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡  ያገሩን ጥቅም ካሜሪቃ ጥቅም የሚያስቀድም መንግሥት ደግሞ፣ የቱንም ያህል ዲሞክራቲክ ቢሆንም፣ ከተቻለ በተጭበረበረ ምርጫ እንዲወድቅ፣ ካልተቻለ ደግሞ በጡጫ ወይም በርግጫ እንዲገረሰስ ይደረጋል፡፡  ለዚህ ደግሞ አያሌ ምሳሌወችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

በነጻና ፍትሓዊ ምርጫ ተመርጦ የኢራንን ጥቅም ለማስቀደም (በተለይም ደግሞ የራሷን ዘይት በራሷ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ) ቆርጦ የተነሳሳው የጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ሙሰዲቅ (Mohammed Mossadeq) ዲሞክራሲያዊ መንግሥት በሲ-አይ-ኤ (CIA) ቀጥተኛ ተሳታፊነትና በቢቢሲ (BBC) ሐሰተኛ ዜና (fake news) ነዥነት ባፋጣኝ ተወግዶ፣ በምትኩ ያሜሪቃው ሎሌ የኢራኑ ሻህ አምባገነኑ ሙሐመድ ፓህላቪ (Mohammed Reza Pahlavi) ተተካ::  

ዲሞክራቱ መላፍሪቀኛ (panafricanist) ፓትሪስ ሉሙምባ (Patrice Lumumba) ለሌሎች ጥቁር ብሔርተኞች (black nationalists) መቀጣጫ እንዲሆን በሲ-አይ-ኤ ቅጥረኞች በጭካኔ ተገድሎ፣ በምትኩ አምባገነኑ ጎጠኛ ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ (Mobutu Sese Seko) ተተከለ፡፡  በዮሐንስ አሪስታይድ (Jean-Bertrand Aristide) የሚመራው ዲሞክራሲያዊው የሄይቲ (Haiti) መንግሥት፣ የሲ-አይ-ኤ ሰላዮች በመሩት መፈንቅለ መንግሥት ተገለበጠ፡፡   

ራሷ አሜሪቃ ውስጥ ደግሞ፣ ቀድሞውንም በተለያዩ ሰበቦች የተገደበ የነበረውን ያሜሪቃ ጥቁሮችን የመምረጥና የመመረጥ መብት ይበልጥ ለመገደብ ያሜሪቃ ሴናተሮች (በተለይም ደግሞ ሪፓብሊካኖች) ደፋ ቀና ማለታቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል፣ በተለይም ደግሞ በነጭ ላዕልተኞች (white supremacists) ከሚፈቀረው ከትራምፕ አስተዳደር ሽንፈት በኋላ፡፡    

እነዚህ ሁሉ የሚመሰክሩት ያሜሪቃ ዲሞክራሲ ከመሠረቱ የነጭ፣ በነጭ፣ ለነጭ መሆኑን ነው፡፡  ያሜሪቃን ብሔራዊ መዝሙር የደረሰው ፍራንሲስ ኬይ (Franics Scott Key)፣ ያሜሪቃ ጥቁሮች በባርነት በሚማቅቁበት ዘመን አሜሪቃን የነጻወች አገር (the land of the free) ለማለት የደፈረው፣ ያገሪቷ ሥሪት የነጭ፣ በነጭ፣ ለነጭ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡  ከንግሊዝ ቅኝ ገዥወች ጋር ተዋግቸ በማሸነፍ ነጻ ሪፓብሊክ መሠረትኩ በማለት ከመኩራራት አልፎ የሚታበየው ያሜሪቃ መንግሥት፣ የሄይቲ ጥቁሮች ከባርያ ፈንጋዮች ጋር ተፋልመው በማሸነፍ የመሠረቱትን ነጻ ሪፓብሊክ በመንግሥትነት ለማወቅ ስልሳ (60) ዓመታት የፈጀበትም ምክኒያት ይሄው ያገሪቷ ሥሪት ነው፡፡  

በነገራችን ላይ ያሜሪቃ አብዮት (American revolution) እና የሄይቲ አብዮት (Haitian revolusion) ሁለቱም አብዮቶች ቢሆኑም፣ ክብደታቸው ግን ሰማይና መሬት ነበር፡፡  ያሜሪቃ ያብዮት ጦርነት (american revolution war) የተካሄደው፣ ከራሴ አገር ሰወች ጋር እዚሁ አሜሪቃ ቀርቸ፣  የህንዶቹን መሬት ቀምቸ በመስፈር ልበልጽግ ወይስ የንግሊዝን ንጉሥ ጥቅም ለማስከበር በያገሩ የምዘምት ቅጥረኛ እንደሆንኩ ልቅር እያለ ከሚዋልል፣ ልቡ ከተከፋፈለ ከራስ ወገን ጋር ስለነበር፣ ተግዳሮቱ እምብዛም ነበር፡፡  ያሜሪቃ አብዮት ቁስል ባጭር ጊዜ ውስጥ ሽሮ፣ እንግሊዝና አሜሪቃ ሥር ጓደኞች (special relationship) የሆኑበትም ምክኒያት ይሄው ነው፡፡  በሌላ በኩል ግን፣ የሄይቲ አብዮት የባርነት ሰንሰለትን ለመበጣጠስ፣ የጭቆና ቀንበርን ለመሰባበር ስለነበር፣ ያብዮተኞቹና የባርያ ፈንጋዩ ትግል የሞት ሽረት ትግል ነበር፡፡  የሄይቲ አብዮት ቁስል በየጊዜው እያመረቀዘ፣ ሄይቲና ፈረንሳይ በየጊዜው የሚናቆሩትም በዚሁ ምክኒያት ነው፡፡                           

ወዳገራችን ወደ ጦቢያ ስንመለስ ደግሞ፣ ያሜሪቃ ያፍሪቃ ፖሊሲ የተመሠረተው በሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) እሳቤ ላይ መሆኑን እንረዳለን፡፡  ሮማን ፕሮቻዝካ (Roman Prochazka) ጥቁሩ አደጋ (die Schwarze Gefahr) የተሰኘውን መጽሐፍ ከዘጠና አመታት በፊት (1929 ዓ. ም) በጀርመንኛ የጻፈ፣ በታላቁ የአድዋ ድል አንጀቱ የቆሰለ ነምሳዊ (Austro-Hungarian Empire) የናዚ ባላባት (baron) ነበር፡፡   ይህ መጽሐፍ በጣልያንኛ አደገኛዋ ጥቁሯ ጦቢያ (Abissinia pericolo nero) በሚል ርዕስ የተተረጎመ ሲሆን፣  Abissinia: The Powder Barrel የሚለውን የእንግሊዘኛ ትርጉም ደግሞ ደበበ እሸቱ ጦቢያ፣ የባሩድ በርሜል በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ መልሶታል፡፡  የመጽሐፉ ፍሬ ሐሳብ ደግሞ በጥቁርነታቸው የሚኮሩት፣ የጥቁር አንበሶቹ (black lions) አገር የሆነችው ጦቢያ፣ ለነጭ ዘር መቅሰፍት ስለሆነች፣ ባገር በቀል ጎጠኞች ተጎጥጉጣ መገነጣጠል አለባት የሚለው ነው፡፡  

The numerous tribes who inhabit the Ethiopian state are being forcibly kept from European colonialism by Abyssinian rulers whose aim is to act as champions of all black people so as to attack and destroy Western culture.

የጦቢያን አያሌ ብሔረሰቦች የነጭ ባርያ የመሆን ምርጫቸውን የነፈጓቸው፣ ዓላማቸው በነጭ የባህል  (እና የሐይማኖት) መቃብር ላይ የጥቁርን ልዕልና መገንባት የሆነው የሐበሻ መሪወች ናቸው፡፡

Roman Prochazka (Abyssinia: The Powder Barrel, Vienna, 1935)

 ለምሳሌ ያህል የሮማን ፕሮቻዝካ ደቀመዝሙር (disciple) የሆነው፣ ያሜሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያፍረቃ ወንበር ሃላፊ የነበረው ኸርማን ኮኸን (Herman Cohen)፣ የባሕርዳሩን ክስተት በተመለከተ 

”Faild coup in #Ethiopia’s Amhara state was an attempt by ethnic nationalists to restore Amhara hegemony over all of Ethiopia that existed for several centuries prior to 1991.  That dream is now permanently dead.”

‹‹ባማራ ክልል ውስጥ የተካሄደው ያልተሳካው የመንግሥት ግልበጣ (ወያኔ ጦቢያን እስከተቆጣጠረበት) እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ለምዕተ ዓመታት ሰፍኖ የነበረውን ያማራ የበላይነት ለማስመለስ ያማራ ብሔርተኞች ያደረጉት ሙከራ ነበር፡፡  ይህ ህልማቸው ለዘለዓለም አሸለበ፡፡››

በማለት በትዊተር ገጹ ጽፎ ያማራን ሕዝብ በተመለከተ ያለውን እኩይ እይታ በግልጽ አስቀምጦ ነበር፡፡

ያሜሪቃ መንግሥት የመላው ዓለም ጥቁሮች (በተለይም ደግሞ ያሜሪቃ ጥቁሮች) ነጭን ድል ባደረገችው በጦቢያ ከመኩራት ይልቅ እንዲያፍሩባትና የነጭን የበላይነት በጸጋ እንዲቀበሉ፣ ጦቢያን አሳፋሪ ለማድረግ፣ ማድረግ ያለበትን ሁሉ ያደርጋል፡፡  በጥቁርነታቸው እየኮሩ የጦቢያን ጥቅም የሚያስቀድሙ አገር ወዳድ ጦቢያውያን ስልጣን እንዳይዙ፣ ከያዙም እንዳይቆዩ፣ ከቆዩም ሰላም አግኝተው ዓላማቸውን እንዳያሳኩ ሊጋርጥ የሚችለውን ጋሬጣ ሁሉ ይጋርጣል፡፡  መለስ ዜናዊን የመሰለ ፀራማራ ቡችላ ሲያገኝ ደግሞ ቡችላውን ባስፈላጊው ዘዴ ስልጣን አስጨብጦ፣ ቡችላነቱን እስከቀጠለ ወይም ደግሞ ከሱ የተሻለ ቡችላ እስከተገኘ ድረስ የስልጣን ዘመኑን ያረዝምለታል፡፡

የዘመናችን ፀራማራ ደግሞ በጦቢያ ፍርስራሽ ላይ የኦሮሞ አጼጌ (Oromo empire) ለመመሥረት ቆርጦ የተነሳው፣ የኦሮሙማ አጀንዳ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው፣ ቃላባዩ ኦቦ ዐብይ አሕመድ ነው፡፡   አብይ አህመድ ላይ ላዩን ጦቢያ፣ ጦቢያ ቢልም ውስጥ ውስጡን ግን ኦሮሚያ፣ ኦሮሚያ የሚል ኦነጋዊ መሆኑን በጦቢያ ቤተመንግሥት ውስጥ ቤተኞች የሆኑት አሜሪቃኖች አያውቁም ማለት ከየዋህነት አልፎ ቂልነት ነው፡፡  ወያኔና ኦነግ አማራን ላሰርት ዓመታት ሲጨፈጭፉ እንደነበሩና ዐብይ አህመድ ደግሞ ጭፍጨፋውን በገደል ከመወርወር ወደ ማረድ ከፍ እንዳደረገው በደንብ ያውቃሉ፡፡  ስላማራ መታረድ ግን ውግዘት ይቅርና ስሞታ እንኳን አሰምተው አያውቁም፣ ይመቻቸዋልና፡፡  ወያኔው አቶ ስብሃት ነጋ በግልጽ እንደተናገረው፣ አሜሪቃኖች ዐብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን ከፍተኛ ጫና ያደረጉበት ምክኒያት ማንነቱን በደንብ ስለሚያውቁና አጀንዳው ስለተመቻቸው ነው፡፡  ስለዚህም ፀራማራው ዐብይ አህመድ ያሜሪቃ ቡችላነቱን እስከቀጠለ ድረስ፣ አገዛዙ እንዲቀጥል አሜሪቃ አስፈላጊውን እገዛ ታደርግለታለች፡፡  

አስፈላጊውን ስልጠና አሜሪቃ ውስጥ ወስዳ ወደ ጦቢያ የተመለሰችው ቡርቱካን ሚዴቅሳ ደግሞ አብይ አህመድ ከወዲሁ እንዲያሸንፍ ያደረገችበትን የይስሙላ ምርጫ ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የምትራወጠው፣ ባሜሪቃ የሚደጎመውን የምርጫ ቦርድ እየመራች፣ አሜሪቃ ዘውሪው በሚላት አቅጣጫ እንድትዘውር ባሜሪቃ ሹመኞች በተሰጣት መመርያ መሠረት ነው፡፡      

ለማጠቃለል ያህል በነጭ ላዕልተኞች (white supremacists) እይታ፣ ኢትዮጵያ ለነጭ ላዕልተኞች ሰላም የማትሰጥ የአፍሪቃ ሄይቲ ስለሆነች (The Haiti of Africa)፣ የጦቢያን ጥቅም በማስከበር የመላ አፍሪቃን ጥቅም ለማስከበር አርአያ (role model) የሚሆን አገር ወዳድ (patriotic) መሪ ጦቢያን መምራት የለበትም፡፡ 

የሄይቲ ጥቁሮች፣ የነጭን የባርነት ሰንሰለት በጣጥሰው፣ የጭቆና ቀንበሩን ሰባብረው የመጀመርያውን የጥቁር ሪፓበሊክ  (first black republic) ከ217 ዓመታት በፊት (በ 1804 ዓ.ም) በመመሥረታቸው፣ ካሜሪቃ መንግሥት ጥርስ ውስጥ ገብተው እድሜ ልካቸውን በድህነትና እየማቀቁና በብጥብጥ እየተሳቀቁ፣ የላቲን አሜሪቃውያን መሳቂያን መሳለቂያ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል፡፡  ጦቢያውያን ደግሞ የነጭ ላልተኞችን (white supremacists) መሠረተቢስ ትርክት አድዋ ላይ ድባቅ በመምታት ለጥቁሮች (በተለይም ደግሞ ላሜሪቃ ጥቁሮች) የነጻነት አርአያ ስለሆኑ፣ ካጋም እንደተጠጋ ቁልቋል ዘላለም እንዲያለቅሱ ምዕራባውያን (በተለይም ደግሞ አሜሪቃ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ) ወስነውባቸዋል፡፡ 

ጥቁሮች ራሳቸውን ማስተዳደር አይችሉም ለማለት እንዲመች፣ የመጀመርያውን የጥቁር ሪፖብሊክ የመሠረተቸው ሄይቲ ያሜሪቃ አህጉር የመጨረሻ ድኻ መሆን አለባት፡፡  ቅኝ መገዛታቸው ጥቁሮችን ጠቅሟቸዋል ለማለት እንዲመች ደግሞ፣ ቅኝ ያልተገዛችው ጦቢያ ያፍሪቃ አህጉር የመጨረሻ ድኻ መሆን አለባት፡፡    

ያሜሪቃ የጦቢያ ፖሊሲ የሮማን ፕሮቻዝካን (Roman Prochazka) አስተምህሮ (doctrine) ከሚያቀነቅኑ ከነጭ ላዕለተኞች (white supremacists) ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ተላቆ ከሥር ከመሠረቱ እስካልተለወጠ ድረስ፣ ወይም ደግሞ ጦቢያውያን ባንድም በሌላም መንገድ ከምዕራባውያን ተጽእኖ ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ነጻ እስካላወጡ ድረስ፣  ነጻ ምርጫና ትክክለኛ ዲሞክራሲ ለጦቢያውያን የሕልም እንጀራ ናቸው፡፡   በመሆናቸውም መለስ ዜናዊንና አብይ አህመድን የመሰሉ ፀራማራ የነጭ ቡችሎች እንጅ፣ ለጦቢያ ጥቅም የቆመ አገር ወዳድ ጦቢያዊ፣ የጦቢያን በትረ ስልጣን አይጨብጥም፣ ቢጨብጥም መቸም ሰላም አያገኝም፡፡         

Mesfin Arega

mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic