የተቋም እና የአውራ መሪ ጠኔ!
ያሬድ ሀይለማርያም
አገር ማበላሸት ቀላል ነው። በሺ አመታት የተገነባችን አገር በከሸፋ ፖለቲከኞች እጅ ለአሥርት አመታት በመቆየቷ ይሄው በእኛ እድሜ እየተንኮታኮተች እያየን ነው። ወያኔና ሻቢያ የጀመሩት አገር የማፈራረስ የሸር ፖለቲካ በኤርትራ መገንጠል አላበቃም። ዛሬ ያለንበትን የተመሰቃቀለ እና ግራ የሚያጋባ ሁኔታም ፈጥሯል። የዛሬው ምጥ ትግራይ የምትባል ሌላ ብጣሽ አገር ለማዋለድ የሚደረግ ትርምስ ይመስላል።
ክፉ እና የአፈና አገዛዝ አንዱ ጠባሳው አገር በተቋም እና ለማህበረሰብ መሪና ምሳሌ በሚሆኑ ሰዎች አጦት እንድትላሽቅ ማድረግ ነው። ተቋም እና ሰው አልባ በርሃ ማድረግ። ክፉ አገዛዝ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋምትን ማጥፋት ብቻ አይበቃውም። በቀላሉ እንዳይፈጠሩም ማድረግ ይችላል። ምሳሌ የሚሆኑ፣ ማህበረሰቡ እንደ መሪ የሚያያቸው እና የሚያከብራቸው፣ በመንፈስ ልዕልናቸው ከፍ ያሉ፣ በእውቀታቸው የላቁ፣ ፍርሃትን ያሸነፉ እና አድር ባይነትን የተጠየፉ መሁራንን ዱካቸውን እየተከተሉና እያሳደዱ ማጥፋት ብቻም አይበቃውም፤ በእነሱ ምሳሌ ሌላ መሪ እንዳይፈጠር ከትምህርት ፖሊሲው አንስቶ በሁሉም መስክ የከሸፈ ትውልድ እንዲፈጠር ማድረግም ይችላል።
ኢትዮጽያ ባለፉት 50 ዓመታት የገጠሟት ክፉ አገዛዞች ተቋም አልባ አድርገዋታል። ከ60ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ የጀመረው ምሁር ጠል የሆነው ፖለቲካችን አገሪቷ መቼም ልትተካቸው የማትችል ምርጥ ልሂቃንን እየሰለቀጠ መጥቶ የነጮችን የቅኝ ግዛት ወረራ የተቋቋመችውን ብቸኛ አፍራካዊት አገር ድንቁርና ከፉኛ በተጫናቸው ካድሬዎች ቅኝ አስተዳደር እንድትወድቅ አደርጓታል። ኢትዮጵያ ዛሬም በካድሬዎች ቅኝ አስተዳደር የወደቀች አገር ነች። ካድሬዎቹ ስማቸው ይቀያየር እንጂ የክሽፈት ፖለቲካ የባህሪ ልጆች ናቸው።
ምሁሮቿን ያዋረደች፣ ያሰደደች፣ ያመከነች፣ ሰልቅጣ የዋጠች አገር ከርሃብና ከጠኔ፣ ከእርስ በርስ ግጭት፣ ከዘር ሽኩቻ፣ ከጦርነት እና ከሁከት እንዴት ነጻ ትሆናለች። ሀገር በዜጎቿ ጥንካሬ ደሀ ሆናም ትጸናለች። ልትበለጽግ እና ወደ ስልጣኔ ማማ መምጣት የምትችለው ግን በምሁራኖች ሳይንሳዊ እውቀት እና ምርምር ብቻ ነው። ምሁር የማያፈልቅ እና ምሁር ጠል የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት የሰው እና የተቋም በርሃ የሆነች አገር ነው የሚፈጥረው። ኢትዮጵያ ዛሬ በዚህ በርሃ ከተዋጡ ጥቂት አገሮች አንዷ ነች።
ዛሬም ይህን በርሃ በምሁራን እና በጠንካራ ተቋማት ለማለምለም ፍላጎት ስለመኖሩ ብዙ ምልክት አለመታየቱ ያስፈራል። ይሄ ደሞ ኢትዮጵያ በተቋም እና በመሪ ጠኔ የምትሰቃይበትን ዘመን ያረዝመዋል።
ምሁራን ፖለቲካውን አትፍሩት። ዋጋ ቢያስከፍልም ይች አገር ያለ ሀቀኛ ምሁራን እርብርብ አትድንም። የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአገሪቷ ምሁራን እጅ ካልገባ የመከራው ዘመን ይረዝማል።
ከልባቸው የአገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት በፖለቲካ ውስጥ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ እየከፈሉ ለሚታገሉ ምሁራን አክብሮቴ የላቀ ነው።
ቸር እንሰንብት!