>
5:33 pm - Friday December 6, 1191

የኢሳያስ አፈወርቂን ቃለ መጠይቅ የአማርኛ ትርጉም በቅናት እርር ድብን እያልኩ አዳመጥኩት...!!! (ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ)

የኢሳያስ አፈወርቂን ቃለ መጠይቅ የአማርኛ ትርጉም በቅናት እርር ድብን እያልኩ አዳመጥኩት…!!!
ጋዜጠኛ የትነበርክ ታደለ

 ኢሳያስ ከራሱ ሀገር አልፎና ተርፎ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግሮች መንስኤና መፍትሄዎች በመረጃ ይተነትናል። ስለ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ችግሮችና ከኋላ ስላሉ ገፊ ምክኒያቶች ያስረዳል። በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤ ዙርያ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ጥቅም ያልተከበረበት የሀያላን ሀገራት አሰላለፍ መጨረሻው ምን ሊያስከትል እንደሚችል ይናገራል። የአባይ ወንዝ ተፋሰስና በዚያ ዙርያ ያሉ አለማቀፍ ፍላጎቶች እንዲሁም ዛሬ ኢትዮጵያ ስለገባችበት የህዳሴ ግድብ አጣብቂኝ መነሾውን አንድ ሁለት እያለ ችግሩን ከነመፍትሄው ለማሳየት ይሞክራል። በጠቅላላው ኢሳያስ አፈወርቂ አንድ የሀገር መሪ ብቻ ሳይሆን አንድ በእድሜ ብዛትና በምርምር የበሰለ ተመራማሪ ሳይንቲስት ለተማሪዎቹ እንደሚያስተምር ያህል እየተሰማኝ በቅናት ተሞልቼ አደመጥኩት። “መች ነው እንዲህ ያለ ሀገራዊ ጉዳዮችን አብራርቶና አፍታቶ ለዜጎች የሚናገር ውስጡ ያለውን እውቀት ዜጎች ውስጥ መጨመር የሚችል መሪ የነበረን?” ብዬ በቁጭት ብዙ ዘመን ወደ ኋላ ሄድኩ። ነበሩን…….
ዘንድሮ የኛ ሀገር በብሄር ቁመና እየተለኩ የተኮለኮሉ ፖለቲከኞች እንኳን ባህር ተሻግረው አድማስ ሰንጥቀው ፣ ወደ ኋላ በታሪክ፣ ወደ ፊት እየሆነ ባለው ነገር መሰረት አድርገው ጂኦ-ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሊተነትኑ ይቅርና ስለገዛ ቢሯቸው የስራ ሀላፊነት እንኳ በአግባቡ ሊነግሩን የሚችሉ አይደሉም። ~~~ ከዝያ ክልል እዚህ ክልል ቃላት ሲወራወሩ፣ በየድግሱ መድረክ ላይ ተጽዕኖ ከመፍጠር ግጭት እየፈጠሩ ወር እየሞሉ ፔሮል ላይ መፈረም ቪ-8 ላይ መቆለል እንጂ ዜጎቻቸውን የሚያንጽ አንድ አረፍተ ነገር እንኳ መመስረት የማይችሉ ሆነው በችግር ላይ ችግር ሆነውብናል።
~ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዳይደናቀፍና ተደጋግፎና ተረዳድቶ እንዴት በጋራ መጓዝ እንደሚቻል ዛሬ እሳት ጭረው ለጠፉት የህወሀት አባላት ጭምር ምክር መለገሱንና ይህ መጥፎ ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል አስቀድሞ ማሳሰቡን እየነገረን እንዲሁም ዛሬ በቋንቋና በብሄር ተከፋፍለን የምናፈሰው ደም እሱ አስቀድሞ “ተው ይቅርባችሁ” ብሎ የመከራቸው ሰዎች ለዚህ  እንደዳረጉን ስምና ጊዜ እየጠቀሰ ይነግረናል። አሁንም በቀረው ጊዜ ኢትዮጵያና ኤርትራ ብቻ ሳይሆኑ፦ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን በቀጣናው ላይ እንዴት በጋራ መጫወትና የውጭ ጫናን መቋቋም እንደሚችሉ እንደ አንጋፋ የአካባቢው መሪነቱ በአጽንኦት ይመክራል።
~~ የሚበጀንን እንዲህ ያለውን ከሀገር አልፎ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብርና በመደጋገፍ ማደግና መለወጥ፣ ተጽእኖ ለማሳረፍ የሚበጀንን መንገድ ትተን እንደ ሽንኩርት እየላጠ ባዶ ለሚያስቀረን የዘር ፖለቲካ እየሰገድን እንድንተላለቅ የሚያደርጉን መሪዎቻችንና ፖለቲከኞቻችን ከኢሳያስ — ቁጭ ብለው የፖለቲካን ሀሁ ቢማሩልን በሚል ህልም አድምጬ ጨረስኩት። ~ አድምጡት!! https://bit.ly/3tGaiHT
Filed in: Amharic