>

ታማሚና ጠያቂ...!!! በ በዕውቀቱ ሥዩም 

ታማሚና ጠያቂ…!!!

በ በዕውቀቱ ሥዩም 

ትወለጃለሽ፤ትኖርያለሽ፤ትሞቻለሽ፤ በየጣልቃው ግን ትታመምያለሽ! ሳይንሳዊ ሀቅ ነው!!
በሽታ ድሮ ቀረ! ደሞ የዛሬ ልጅ ምን በሽታ ያውቃል?
የኔ ትውልድ መኩራት ሲያንሰው ፤ እነ ፈንጣጣን፤ እነ ፖሊዮን፤ እነ ትክትክን፤ እነ አባ ሰንጋን ሸውዶ ነው እዚህ የደረሰው፤ በሽታ ብቻ ሳይሆን በሽተኛ ራሱ ድሮ ቀረ ! ያብማይቱን! ድሮ አንድ ሰው ከታመመ ቤቱ ውስጥ አነጣጥፎ ይተኛል፤ ከዚያ ዘመድና ጎረቤት ብርቱካን ሙዝ እና ፓፓያ ይዞ በመምጣት ይጠይቀዋል፤ እናቶች ብርቱካንን ለበሽተኛ መጠየቂያ የመረጡት አለብልሃት አይደለም! አብዛኛው በሽታ የሚመነጨው ከቪታሚን ሲ እጥረት መሆኑን በልምድ ገብቷቸዋል!!
ጎረቤቶች ጅምር ስፌት፤ ጅምር ፈትል ይዘው በመምጣት ታማሚውን ከበው ይቀመጣሉ፤ ታሞ የመነሳት ልምድ ያላቸው አሮጊቶች ላዲሱ በሽተኛ ልምዳቸውን ያካፍላሉ፤” ትኩስ ማር በፌጦ ብትቀምስበት ነቅሎ ይጥልልሃል ” ይላሉ፤ ይህን የሰማች ድሃ ጎረቤትህ ከጉዋሮ ፌጦ ታበረክትልሃለች! ደጉ ባላገር ወገንህ ማር እየቆረጠ ይልክልሃል፤ ታመህ ስትነሳ፤ ከያቅጣጫው የመጣልህን ማር ሰብስበህ ፤ ጠጅ ቤት መክፈት ሁሉ ትችላለህ፤ ልዩልዩ ምግብ፤ደንበጃን ሙሉ አረቄ ተልባ እና የመሳሰለው ገፀበረከት ቤትህን ይሞላዋል፤ ባጭሩ፤ አንድ አመት ሰርተህ እማታገኘውን ሲሳይ ፤አንድ ወር ታመህ ታገኘዋለህ፤ ጠያቂዎች ዋና ጥቅም ስነልቦናዊ ነው፤ ከሰው ጋር መጫወትን የመሰለ ምን መዳኒት አለ?
“ያሳብና የጅብ ሌሊት ነው ጉልበቱ ቀንማ ምን ይላል፤ከሰው ሲጫወቱ “ ይል ነበር አዝማሪ ወርቄ፤
ስለበሽተኛና ስለጠያቂ ባሰብኩ ቁጥር ትዝ የሚለኝ የጡት አባቴ ነው፤ በታመመ ቁጥር ከህመሙ በላይ የሚያሳስበው ለጠያቂዎች የሚሰጠው ምላሽ ነበር፤ አስቀድሞ፤ ጠያቂዎቹን ወዳጅ ወይ ጠላት መሆናቸውን ያረጋግጣል፤ ለወዳጅ እና ለጠላት ጥያቄ የተለያየ ምላሽ ይሰጣል፤
ወዳጅ ዘመድ ፤ “እንዴት ነው ተሻለህ?” ካለው፤ህመሙን እያጋነነ ይቀዳል፤ “እረ ምን ይሻለኛል፤ ጭንቅላቴ እንዳረንዛ ይከብደኛል፤ጉበቴ ተኮማትሮ ሶስተኛ ኩላሊት መስሏል:: ሃኪሙ ሆዴን አምስት ጊዜ ከፍቶ ከድኖታል ፤ እንደኔ እንደኔ ዶህተሩ ሆዴ ውስጥ የሆነ የከበረ ማእድን ያገኘ ይመስለኛል:: የምተርፍ አይመስለኝም!! የስምንት ልጆቼን ነገር አደራ”፤ጠያቂው ዘመድ ይሄ ሰውየ ልጆቹን ጥሎብኝ እንዳይሞት ብሎ ሰግቶ ፤ ተንከባክቦ ያድነዋል፤ በሽተኛ እሚጠይቅ ሁሉ ወዳጅ አይደለም፤ ጠላትህ ራሱ መታመምህን ሲሰማ አገር አቆራርጦ፤ ወንዝ ተሻግሮ የልጁን ሰርግ መርሃግብ ሳይቀር ሰርዞ፤ ይመጣል፤ አላማው ጠላቱን ውድቀት አይቶ መደሰት ነው፤ ይህን እሚያውቀው ጡት አባቴ ለጠላቱ ይሄን አይነት የመደሰት እድል ላለመስጠት ይፍጨረጨራል፤ ከደመኛዎቹ አንዱ ሊጠይቀው መምጣቱን ሲሰማ ፤የሚውጠውን ክኒን ትራሱ ስር ደብቆ ፤ግልኮሱን እንደ አምባር አወላልቆ ፤በተቻለ መጠን ገፅታውን ገንብቶ ይጠብቀዋል፤ ‘ ምፅ! እንዴው ምናገኘህ?” ይላል ደመኛው፤ “ደሞ ምን ያገኝኛል፤ አገር ምድሩን በዙረት ሳካልል ውየ፤ ገብቼ ገና ጋደም ከማለቴ ነው የደረስህ” ይላል የጡት አባቴ! “ትናንት ባልጋ ተሸክመው ከውጭ ወደ ቤት ሲያስገቡህ ያየሁ መስሎኝ ” ይላል ደመኛው
የጡት አባቴ አይረታም፤ “ እና የመኳንንት ዘር ሆኘ በግሬ እንድሄድ ፈልገህ ኑሯል?!” ብሎ ይገግማል፤
አሁን በዘመናችን ሆስፒታል ሄዶ በሽተኛ የመጠየቅ አኩሪ ባህላችን እየተመናመነ መምጣቱ ያሳስበኛል::
እንዲያውም አሁን አሁን፤ ታማሚውም ጠያቂውም የሚገናኙበት ብቸኛ መድረክ ፌስቡክ ብቻ ሆኗል::
ባለፈው አንዱ በደምና በፋሻ የተሞላ ሰልፊው ስር “ወንድሞቼ ወደ መሪ ሲኤም ሲ መገንጠያ ላይ ሌቦች መንገድ ላይ አግኝተው ሞባይሌን እና ላፕቶፔን ዘረፉኝ፤ይሄ አልበቃ ብሏቸው በፌሮ ፈነከቱኝ፤አሁን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቁጥር 23 ተኝቼ እገኛለሁ ”ብሎ ፌስቡክ ላይ ለጠፈ:: የመጀመርያው ከመንት:
“ሞባይልህን ላፕቶፕህ ከተዘረፈ ይሄንን በምን ፖስተከው?”
Filed in: Amharic