>
5:13 pm - Monday April 18, 5289

ሜ/ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ ከ1981 ዓ.ም የመንግስት ግልበጣ የተረፉት ብቸኛው ጀነራል....!!!

ሜ/ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ ከ1981 ዓ.ም የመንግስት ግልበጣ የተረፉት ብቸኛው ጀነራል….!!!
·ታሪክን ወደኋላ 
“ እኔ ለሀገሬ ቁምላቸው ስሆን ፣ ለገንጣይና አስገንጣይ ደግሞ ቁምባቸው ነኝ” በሚለው ንግግራቸው የሚታወቁት ሜጀር ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ፣ ከመፈንቅለ መንግስት አድራጊ ጀነራሎች ውስጥ በህይወት የተረፉት ብቸኛ ጀነራል ናቸው፡፡
ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ላይ ርዕሰ ብሔሩ  ወደ ቀድሞው ምስራቅ ጀርመን ሲሄዱ የመፈንቅለ መንግስት እንቅስቃሴው በይፋ ተጀመረ፡፡ ሜጀር ጀነራል መርዕድ፣ አጠቃላይ ማስተባበሩን ያዙ፡፡ ሜጀር ጀነራል አበራ አበበ መንግስት ፈንቃዩን ጦር ማደራጀትና ማሰማራት ጀመሩ፡፡ ለዚህ ኦፕሬሽን የተዘጋጀው ጦር ልዩ ነበር፡፡
ከአስመራ 400 መቶ የ102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር ኮማንዶዎች በአንቶኖቭ አዲስ አበባ እንዲገቡ ፣ ከጦላይ ደግሞ አንድ ሻለቃ የስፓርታ ጦር በሄሌኮፕተር እየተመላለሰ አዲስ አበባ ባስቸኳይ እንዲከት፣ ከብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዋና መምሪያ ደግሞ አንድ ሻምበል ጦር እንዲንቀሳቀስና  ጀነራሎቹ የተሰበሰቡበትን የመከላከያ ሚኒስቴር ሕንጻ እንዲጠብቅ ታዘዘ፡፡ ይህንንም ጦር የሚመሩት ሜጀር ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ እንዲሆኑ ተወስኖ፣ ቁምላቸው ደጀኔ ከመፈንቅለ መንግስቱ አስተባባሪዎች በሚሰጣቸው ትዛዝ መሰረት እንዲዋጉ ተወስኖ ፍንቀላው ተጀመረ፡፡
አንድ ሻለቃ የስፓርታ ኮማንዶ ጦር፣ አንድ ሻምበል ያየር ወለድ ኮማንዶ ጦርና አንድ ሻምበል የብሔራዊ ጦር ለመፈንቅለ መንግስቱ ክንድ እንዲሆን ታዟል፡፡ የታዘዙት ወታደሮች ግን የተነገራቸው ሌላ ነው፡፡ ስለ ሚስጥሩ ምንም አያውቁም፡፡
ለቁምላቸው ደጀኔ ፣ ልዩ የአየር መንገድ በረራ ተጠይቆ ወደ አስመራ ባሰቸኳይ በረሩ፡፡ ለሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ የተላከውን ደብዳቤ ሰጥተው፣ አራት መቶ ያያር ወለድ ጦር ይዘው በአንድቶኖቭ ወደ አዲስ አበባ  ተመለሱ፡፡ ከቀኑ አስር ሰዓት ሆናል፡፡ ከሳቸው ጋር 200 ያየር ወለድ ጦር፣ ከሳቸው በኋላ ደግሞ ሌላኛው ሁለት መቶ ይደርሳል፡፡ እሳቸው ሁለት መቶ ያየር ወለድ ኮማንዶዎችን ይዘው ቦሌ ደረሱ፡፡ ከኋላቸው ለሚመጣው ጦር ቦሌ ላይ መልክት አስቀምጠው ፣ አብሯቸው የመጣውን ሰራዊታቸውን ይዘው ተጓዙ፡፡ መጀመርያ ጥይት ከመጋዘን ይወስዱና ለወታደሮቻቸው የሚገባቸውን ያህል ከሰጡ በኋላ ለግዳጅ ዝግጁ ሆነው ትዕዛዛ ይጠብቃሉ፡፡
በሄሌኮፕተር የሚመጣውም፣ የስፓርታው ጦር የታዘዘው ምድር ጦር እንዲሰበሰብ ነው፡፡ በሄሌኮፕተር ተጓጉዞ የመጣው የስፓርታ ጦር ቀድሞ ደርሷል፡፡ በዚህ መሀል ግን ችግር ተፈጠረ፡፡ የጥይት ዴፖ ሰራተኞች ከስራ ስለወጡ፣ እነሱ ተፈልገው መጥተው ጥይት እንሲያከፋፍሉ ግዜ ወሰደ፡፡ ቁምላቸው ይህን ሲያስተባብሩ ፣ ሌላ ከባድ ችግር ቀጠለ፡፡ ከሳቸው ኋላ የመጣው ያየር ወለድ ጦር፣ ቁምላቸው ቦሌ ላይ ያስቀመጡለትን መልክት ሳያገኝ፣ በቀጥታ ሪፖርት ለማድረግ ወደ መከላከያ መገስገስ ቀጠለ፡፡
200 ልዩ ያየር ወለድ ኮማንዶ ፣ ከቦሌ ወርዶ ወደ መከላከያ እየተመመ እንደሆነ የሰማውና ሌላም ተከታይ ጦር እየመጣ እንደሆነ ያወቀው የደህንነት ሃለፊው ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ክንድ ሻምበል መንግስቱ ገመቹ ፣ በቀጥታ ወደሚመጣው የአየር ወለድ ጦር በመቅረብ “ ለምን እንደመጡ “ የመስመር መኮንኖቹን ጠየቀ፡፡ ለስራ ታዘው እንደመጡና ጀነራል ቁምላቸው ጋር እንደሚሄዱ ነገሩት፡፡ የመፈንቅለ መንግስቱን እንቅስቃሴ ከጠዋት ጀምሮ ሲከታተል የነበርው መኮንን ነገሩ ወዲያው ገባውና፣ ጦሩን “ሲጠብቀው የነበረ ጦር” መሆኑንና የሚፈለጉትም ቤተ መንግስት እንደሆነ ነገራቸው፡፡ ምንም ፍንጩ የሌላቸው እነዚህ ኮማንዶዎች ቤተ መንግስት መሳርያቸውን እያወረዱ ወደ እራት እንዲገቡ ካደረገ በኋላ ሁሉንም በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ቁምላቸው፣ ዝግጅታቸውን ጨርሰው፣ ወታደሮቻቸውን ቦታ አስይዘው፣ በምድብ መድበው ትዛዝ እየተጠባበቁ ነው፡፡ግን ምንም የለም፡፡  ዝምታው ያስጨነቃቸው ቁምላቸው ፣ ወደ መከላከያ መጠጋት ጀመሩ፡፡ቀሪው የስፓርታና የአየር ወለድ ጦር፣ ምድር ጦር ግቢ ነው፡፡ ቁምላቸው ደጀኔ፣ በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውሉም ፣ከመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች መልስ ያጣሉ፡፡ ጀነራል መርዕድንም ሆነ ጀነራል አበራ አበበ ድምጻቸው ጠፍቷል፡፡ በተደጋጋሚ ፣ “ተዋጊው ኃይል የውጊያ መስመሩን ይዟል፣ ትዛዝ እየጠበቅን ነው” ብለው ሬድዮ ቢያደርጉም መልስ የለም፡፡
እሳቸው ያላወቁት ነገር ነበር፡፡ የቤተ መንግስት ልዩ ጥበቃ ኮማንዶ ጦር፣ መከላከያን ከቦ፣ ጥበቃ ላይ የነበሩትን የብሔራዊ ውትድርና ወታደሮች፣ ባጭር ግዜው ውስጥ ተቆጣጥሮ፣  ውስጥ ያሉ ጀነራሎችን በቁጥጥር ስራ ካደረጋቸው ከሁለት ሰዓት በላይ አልፏል፡፡ እሳቸው ግን አላወቁም፡፡
 ዝምታው ያላማራቸው ፣ ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ፣ ወደ ምድር ጦር ተመልሰው ጉዳዮችን ለማረጋገጥ ይሄዳሉ፡፡ በዚህ መሀል ፣ የኢትዮጵያ ሬድዮ ያስተላለፈውን ዜና ሰሙ፡፡ በጀነራሎች ተሞክሮ የነበረው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉንና ፣ በዚህ መሀል ሶስት ጀነራሎች ማለትም መከላከያ ሚኒስትሩ፣ ሜጀር ጀነራል አመሀ ደስታ፣ ሜጀር ጀነራል መርዕድ ንጉሴ መሞታቸውንና ሌሎቹ ከሁለቱ በስተቀረ መያዛቸውን ሰሙ፡፡
እሳቸው ይሄንን እየሰሙ እያለ ፣ አሁንም የደህንነቱ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ሌላ ሪፖርት ይደርሳቸዋል፡፡ በነጀራል ቁምላቸው የሚመራው ጦር ወደ መከላከያ እየተጠጋ እንደሆነና ፣ ሌሎችም ያየር ወለድና ስፓርታ ኮማንዶዎች ምድር ጦር እንደሚገኙ ሰሙ፡፡
ሁለቱ መኮንኖች ፣ ሁለት እጅግ የሰለጠኑ ኮማንዶዎችን ይዘው የመጭረሻ ፍልምያ  አዲስ አበባ ላይ ሊያደርጉ ነው፡፡ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴና ሻምበል መንግስቱ ገመቹ፣ እስራኤል የተማሩ የልዩ ጥበቃ ኮማንዶዎችን ፣ ታንክና ብረት ለበስ አስታጥቀው ተዘጋጅተዋል፡፡ ሜጀር ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ ደግሞ በኮርያኖች የሰለጠኑትን ስፓርታ ኮማንዶችናዝነኞቹን 102ኛው በራሪ ነብር ያየር ወለድ ኮማንዶ ፣ የሚበቃውን ያህል ጥይት አስታጥቀው ተዘጋጅተዋል፡፡ አየር ወለድ እንጅ የሰለጠነ የኮማንዶ ጦር ነው፡፡ በተደጋጋሚ ውጊያ ላይ እንደታየውም፣ በ እልህ የተሞላና በቀላሉ የማይበገር፣ በውጊያ የተፈተነ ከባድ ጦር ነው፡፡ስፓርታዎችም እጅግ ከባድ ኮማንዶዎች ናቸው፡፡
የቤተመንግስቱም ጦር፣ ከፍተኛ የኮማንዶ ስልጠና ስፔሻል ኮማንዶ ጦር ነው፡፡  ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ሥላሴ፣ ከአየር ወለድ ጋርና ከስፓርታ ኮማንዶዎች ጋ የሚደረገው ውጊያ እንዲህ በቀላሉ እንደማያልቅ አውቀዋል፡፡ በመሀል አዲስ አበባ ልትነድ ትችላለች፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ሜጀር ጀነራል ቁምላቸው ሃይለኛ አዋጊ በመሆናቸው ነገሩ በቀላሉ አያልቅም፡፡ ቁምላቸው ደጀኔም በበኩላቸው ሀሳብ ይዟቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሁለት ያገሪቱ ልዩ ኮማዶዎች ከፍተኛ ውጊያ ሊያደርጉ ነው፡፡ ያስጨነቃቸው እሱ ብቻ አይደለም፡፡ መፈንቅለ መንግስቱ ከሽፏል፡፡ ውጊያው ምን ለውጥ ያመጣል? የመንግስት ባለስልጣናት፣ እጅግ ብዙ ደጋፍ ጦር እያስገቡ እንደሚሆን መገመቱ አይከብድም፡፡ መፈንቅለ መንግስቱን የሚያስተባብሩት ጀነራሎችም ተይዘዋል፡፡ ከአየር ኃይል ደጋፍ ጠይቀው ፣ ያየር ድጋፍ ቢመጣላቸው እንኳን የሚከተልው ውድመት ቀላል አይሆንም፡፡
ጥቂት አሰቡና ፣ ወታደሮቻቸውን ሰብስበው፣ “ ግዳጁ ስለታጠፈ፣ ወደ ምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ ተመለሱ ፣ ምንም አይነት ጥይት እንዳትተኩሱ” የሚል መመርያ ሰጥተው ፣ ከሁለት ረዳቶቻቸው ጋር ተሰወሩ፡፡
ከዚያ ራሳቸውን ሰውረው በሚገርም ወታደራዊ ጥበብና ሚስጥራዊ እገዛ፣ አሜሪካ በመግባት ከመፈንቅለ መንግስቱ የተረፉት ብቸኛ ጀነራል ሆኑ፡፡
ሜ/ጀነራል ቁምላቸው ደጀኔ ከሀገራቸው ከወጡ ከ 14 ዓመታት በኃላ በሀገረ አሜሪካ በ 1995 ዓ.ም በተወለዱ በ 61 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል።
Filed in: Amharic