ስለ ዶክተር ዝናቡ እርገጤማ አለመናገር አይቻልም!
አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)
ወደን የማንስቅባቸው ብዙ አጋጣሚዎች መኖራቸውን “ወደው አይስቁ” የሚለው ፈሊጥ ያረጋግጥልናል፡፡ አዎ፣ አንዳንዴ ተገደንም ቢሆን እንስቃለን፡፡ አንገቱ የተቆረጠ ሰው – አሉ ነው – ከሰውነቱ የሚለዬው ጭንቅላት በሣቅ እየተንከተከተ ለተወሰነ ጊዜ ራሱን ችሎ ይንቀሳቀሳል ይባላል፡፡ ይህ ግን የውዴታ ሳቅ አይደለም፡፡ እናም ሆዳችን እያረረ የምንስቅባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ – ልክ እንደማሽላዋ፡፡
ዶ/ር ዝናቡ እርገጤ ሕዝበ አዳምን በሣቅ ጦሽ ማድረጉን እንደቀጠለ ነው፤ ግሩም ተዋናይ እኮ ነው! በዚህ የሣቅና ስላቅ ሂደት የሚያሳዝኑኝ አንዳች ድግምት የተዞረባቸው የሚመስሉት ጭፍንና ምናልባትም የዋህ ደጋፊዎቹና ተከፋይ አክቲቪስቶቹ በነሀብታሙ አገላለጽ ውታፍ ነቃዮቹ ናቸው፡፡ “አውቆ የተደበቀ ቢጠሩት አይሰማም” – ትክክል ነው፡፡ ውታፍ ነቃዮቹ መተዳደሪያቸው ኅሊናን ሸጦ በሚገኝ ሶልዲ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል እውነት ቢነገርና ቢለፈፍ ጆሮ የላቸውም፡፡ በቆረቡበት ውሸትን የማራገብ የሆድ አደርነት ተግባር እንደተሰለፉ እስከህቅታቸው ማብቂያ ይዘልቃሉ፡፡ በገንዘብ የተለወጠ ኅሊና ወደ ሆድ ወርዶ ስለሚሸጎጥ ሰውን መግደልና ማረድም ለነሱ ጽድቅ እንጂ ኩነኔ አይደለም፡፡
ዶ/ር እርገጤ ማነው ዝናቡ እርገጤ “በጎጃምና በሰሜን ሸዋ ዝናብ ያዘነብኩት እኔ ነኝ” እያለ ነው – ይህ ልጅ ጊዜ ካገኘ እንደ ሊቀ ሣጥናኤል እኛን ጭምር “አነ ፈጠርክክሙ በአምሳሊየ ወበአርአያየ” ሳይለን ይቀራል ብላችሁ ነው? እንዲያውም ይህን ዝናብ የማዝነብ ጥበቡን ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ መሆኑንም “አብሥሮናል” – አሃ! ግን ቴሌ ባለአራት ጂቢ ብሮባንድን በኦሮሚያ ሲያስጀምር “ዝናብ” በሚል ኮድ ባላጡት ሥፍራ በአማራ ክልል የተጀመረው ዝናብን የማዝነብ የመንዝ ደብተራ ድግምት “አልጋ እንዲረጋ ለሰይጣን ግብር የሰው ደም ማፍሰስ” ለማለት እንደሆነስ ቅኔው እንዴት ሊገባን ይችላል? ለማንኛውም ጆሯችን ጤንነቱን አይጣ እንጂ እርገጤ ገና ብዙ ጉድ ያሰማናል፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ ወደሥልጣን እንደመጣ ሰሞን በቲቪ መስኮት ብቅ ብሎ በሀገራችን የነዳጅ ድፍድፍ መገኘቱንና ወደምርት ልንገባ ጫፍ ላይ መድረሳችንን ነገረንና በነዳጅ አምሮት የተቃጠለውን ምላሳችንን ምራቅ በምራቅ አደረገው፡፡ እስካሁን ድረስ ግን ወፍ የለም፡፡ እንዲያውም ያን ጊዜ የነበረው የነዳጅ ዋጋ አሁን ዕጥፍ ድርብ አድጎ በነዳጅ ውድነትና እርሱን ተከትሎ መጣ በተባለው የኑሮ ውድነት ሀገር ምድሩ እየታመሰ ነው፡፡ ታሪክ ከታቢዎች የእርገጤን የየዕለት ውሸት ዘግቡና ለታሪክ አቆዩት እባካችሁን፡፡ ወደፊት በታሪካችን “እንዴ! እንዲህ ዓይነት መሪም ኢትዮጵያ ነበራት?” ተብሎ ትውልዱ እንዲማርና በነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ሳይሆን በስሜት ከሚነዳ ወፈፌ መሪ እንዲጠነቀቅ ሀገርን እንርዳ፡፡
ሰሞነኛውን የኦነግ/ኦህዲድ በአማራ ሕዝብ ላይ የተካሄደና አሁን ድረስ ያልቆመው ጦርነት መንስኤው የአማራ አልጠግብ ባይነትና በኦሮሞ ላይ ያለው ጥላቻ የወለደው እንደሆነ በብጥለው ገለበጠኝ ከኦነጋውያን እየሰማን ነው፡፡ አለማፈርን ከሸጡ አይቀር እንደዚህ ነው፡፡ የአጣዬና ማጀቴ ሕዝብ ነቅሎ ወጥቶ ሆሮ ጉድሩ ላይ የሚገኝን ኦሮሞ ሲጨፈጭፍ የተገኘ አስመሰሉት፡፡ ይሉኝታንና ሀፍረትን መሸጥ ከዚህ በላይ ማረጋገጫ የለም፡፡ ዶ/ር ኮሎኔል ሎሬት እርገጤም ተደርቦ “አማራና ኦሮሞ ድብድባችሁን አቁሙ” ዓይነት ንግግር በአሻንጉሊት ፓርላማው ፊት ሲናገር ተደምጧል አሉ፡፡ ማን ተንኳሽ ማን ጥፋተኛ እንደሆነ ልቦናው እያወቀ ጥፋትን ለንጹሓን ጭምር ማጋራት ወይም ማከፋፈል የተንኮለኞችና የሤረኞች ጠባይ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ አማራን በደለኛ ለማስባል የሚሄዱበት ርቀት እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኦነግ/ኦህዲድ በቀቀኖች ያጠኑትን ንግግር በፓርላማ ተብዬው የኦህዲድ ብልግና ፓርቲ የባለጌዎች ሠርግ ዳስ ውስጥ ሲዘላብዱ የሰማቸው ሁሉ ተደንቋል፡፡ ካበዱ አይቀር እንዲህ ነው፡፡
ዶ/ር እርገጤ ማነው ዝናቡ እርገጤ የዚህ ሁሉ ድራማ ደራሲ መሆኑን ለመረዳት በቅርቡ የተከበረውን 125ኛ የዐድዋ ዝክረ በዓል ማስታወስ በቂ ነው፡፡ መስቀል አደባባይ ላይ አክራሪ ኦሮሞዎች ያሳዩት ነውር የተሞላበትና የደጃች ባልቻ አባነፍሶ ቤተሰብ ማኅበርም አጥብቆ የተቃወመው የበዓል አከባበር ለዚህ ለሰሞኑ ዕልቂት የዋዜማ ዝግጅት ጠቋሚ ነበር፡፡ ያን አንዳችም ኢትዮጵያዊነት ያልተንጸባረቀበት በዓል የታዘበ ሰው እነዚህ ሰዎች የሽመልስ አብዲሣን ንግግር ተግባራዊ ለማድረግ ቀን ከሌት እየተራወጡ እንደሆነ መረዳት አይከብደውም፡፡ ሕዝበ አዳም ግን የተደገሰለትን ያወቀ አይመስልም፡፡ አብዛኛውን ሕዝብ ስታዘበው በአገር አማን ምንም ሳይመስለው ኑሮውን ይገፋል፡፡ ግርምቲ አዲ!
ካለፈው ተነስቼ መጪውን እያወቅሁት “እገሌ እንዲህ በል፤ እነገሌ እንዲህ አድርጉ” ማለት አልፈልግም፡፡ ለነገሩ ምን ጥልቅ አደረገኝ?