ለእውነት መቅረብዎ ያዋጣዎታል እንጂ አያከስርም፤ የጠቅላዩ የፓርላማ ውሎ
ያሬድ ሀይለማርያም
ወደ እውነት መቅረብዎን ይብል ብያለሁ። ትላንት በነበረው የፖርላማ ውሎ በርካታ ጉዳዮች የተነሱ ቢሆንም በጥቂት ጉዳዮች ላይ ጠቅላዮን ማበረታታት እና መደገፍ የግድ የሚል ይመስለኛል።
1ኛ/ በትግራይ ጉዳይ፤ መንግሥት ትግራይ ውስጥ ስለተፈጸመው ሰቆቃ፣ ስለ ኤርትራ ወታደሮች ጣልቃ ገብነት እና በመታደሮች ተፈጸሙ ስለተባሉት የመድፈር፣ ግድያና የዝርፊያ ወንጀሎች አይኔን ግንባር ያድርገው ከሚል ደካማ መከላከያ ወጥተው በከፊልም ቢሆን እውነታውን ማመናቸው እጅግ ጥሩ ውሳኔ ነው። ተደብቆ የማይዘለቅ እውነትን ለመሸፈን መፍጨርጨር አጉል መላላጥ እና እስካሁን ከደረሰው የዲፕሎማሲ ክሽፈትና ኪሳራ በላይ የከፋ ኪሳራ ከማስከተሉ በፊት በዚህ መልክ መታረሙ ይበል ያሰኛል። ቀሪው በምርመራ የሚጣራ ነው የሚሆነው።
2ኛ/ ኦነግ-ሽኔን በተመለከተ የተናገሩት ግማሽ እውነት እንዲሁ ሙሉ እንዲሆን ጠቅላዩን ማበረታታት ግድ ይላል። አዎ ይህ ቡድን የሽብር ሥራ እየሰራ ነው። በሚፈጽማቸው ወንጀሎች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እና የኦሮሞ ሕዝብን ጨምሮ ሁሉም እየተጓዳ ነው። የቀረዎት ነገር ይህ ቡድን የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢላማ አድርጎ እንቅስቃሴ ስለሚያደርግ በርካታ የአማራ ብሔር እና የኦርቶዶክስ አማኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት የሚፈጽም መሆኑን በግልጽ ማስቀመጥ እና ይህን ቡድን ከመጥፎ አድራጎቱ ለማስቆም የመንግስትዎ ቁርጠኝነት ምን ያህል እንደሆነ እና በቀጣይ ምን እርምጃ ለመውሰድ እንዳቀዱ መግለጽ ነው።
ከዚህ በግማሽ ከታመነው የጠቅላዩ እውነት በመነሳት በተለይም በትግራይ ጉዳይ የብልጽግና ካድሬዎች፣ የከሸፈ የዲፕሎማሲ ፍትጊያ ውስጥ የገቡ አምባሳደሮች እና በPublic ዲፕሎማሲ አገራቸውን ለመደገፍ እየጣሩ ያሉ በውጭ የሚገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጽያዊያን እራሳቸውን እንደሚቃኙ ተስፋ አደርጋለሁ። አለም ለሚያውቀው እና ጸሀይ በሞቀው እውነት ላይ ‘አይኔን ግንባር ያድርገው’ የሚል ሙግት ይዞ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር መግጠም ክሽፈታችንን እጅግ ያከፋዋል፣ እንደ ሀገርም ትዝብት ላይ ይጥለናል፣ ከእውነት ያርቀናል፣ በታሪክ ተወቃሽ ያደርገናል፣ ግፍን ለመሸፈን በመጣርም ከግፈኛች ጎን ያሰልፈናል።
ጠቅላዩ የእስካሁኑ ‘የአይኔን ግንባር ያድርገው’ ዲፕሎማሲ እንደማያዋጣ ዘግይተውም ቢሆን መረዳታቸው ይበል ያሰኛል። የተካዱ እውነቶች በሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ እና በተባበሩት መንግስታት ጥምር የማጣራት ስራ መጋለጡ ስለማይቀር፤ ቀድሞ በዚህ መልኩ መገለጹ በኋላ የሚመጣውን የመረረ እውነት በቀላሉ ለመቀበልና ለመዋጥ መደርደሪያ ይሆናል። የትላንቱ የፖርላማ በግማሽ የታመነ እውነት መራሩን እውነት ለመቀበል፤ ልክ የኮሶ መዳኒት ለመጠጣት ጉሮሮ እንደመጠራረግ ቆጥሬዋለሁ። ጠቅላዩ በዚሁ ይጽኑ።