>

"ያለፉት ሁለት ዓመታት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የጨለማ ዓመታት ነበሩ...!!!" (አቶ ኦባንግ ሜቶ)

“ያለፉት ሁለት ዓመታት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የጨለማ ዓመታት ነበሩ…!!!” 

 የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶ 

 
*….በጉሊሶ፣ በቄለም፣ በሆሮ ጉዱሩ ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በማይካድራ፣ በወሎ እና በሰሜን ሸዋ ንፁሃን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ መላው ኢትዮጵያዊያን በጥብቅ አውግዙት!!!
የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ ኦባንግ ሜቶ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ዛሬ መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባጋሩት መልዕክት በጉሊሶ፣ በቄለም፣ በሆሮ ጉዱሩ ፣ በወለጋ ፣በመተከል ፣በማይካድራ፣ከሰሞኑ ደግሞ በወሎ፣ በሰሜን ሸዋ እና በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ውድ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በጥብቅ እንደሚያወግዙት ገልፀዋል።
አቶ ኦባንግ በዚሁ የሰብአዊነት ጉዳይም ሰላም ወዳድ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋርም ለመወያየት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል።
“በዚህ የጎሳ ፖለቲካ ሽብር ለተጎዱ እና በዚህ የሀዘን ሰዓት ለቤተሰቦቻቸው የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን ለመግለጽ እፈልጋለሁ ፤ ከዚህ በተጨማሪም ከዚህ ለመውጣት እግዚአብሔር ለቤተሰባቸው ብርታት ፣ ፅናት እና ድፍረት እንዲሰጣቸው እፀልያለሁ ።” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል።
በአገሪቱ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል ያሉት አቶ ኦባንግ ይህ የሽብር ተግባር በመላው ኢትዮጵያ በተከታታይ እየተፈፀመ መሆኑን ገልፀዋል።
“ሁላችንም በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ  የሚፈፀም ይህን አረመኔያዊ የሽብር ተግባር ማውገዝ አለብን፤ ያለፉት ሁለት ዓመታት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የጨለማ ዓመታት ነበሩ” ያሉት አቶ ኦባንግ “በእነዚህ ወንጀሎች ጥፋተኛ የሆኑት ሰዎች ምን እንደሚሰማቸው መገመት ከባድ ነው ፡፡ እነዚህ የራሳቸው ልጆች ቢሆኑ ምን ይሰማቸዋል?” ሲሉም ጠይቀዋል።
“የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ባለመቻል እጅግ በጣም እጨነቃለሁ፤ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ካልተረጋጋ ዘላቂ ሰላም ማግኘት በጭራሽ አይቻልም “ሲሉም አክለዋል አቶ ኦባንግ በመልዕክታቸው፡፡
ለፖለቲከኞች ባስተላለፉት መልዕክትም ጤናማ ያልሆነ ፣ ሀላፊነት የጎደለው እና ለሀገር አደገኛ በመሆኑ ከዕለት ተዕለት እውነታ ራሳቸውን ማግለል የለባቸውም ብለዋል።
ብጥብጥን እና ቂም በቀልን በማስወገድ ረገድ እንደ ህዝብ ስኬታማ መሆን እንዳለብንና ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ህዝብ እንድተያይ መክረዋል፤ ሁላችንም የኢትዮጵያ ህዝብ  እና የሰው ልጅ ቤተሰብ አካል ነን ብለዋል።
ይህ የበቀል ወይም የጥፋት ጊዜ አይደለም ያሉት አቶ ኦባንግ ይልቁንስ ለመላ አገሪቱ ስንል እርስ በርሳችን እርቅ መፈጠር የምንጀምርበት ወቅት ነው ብለውታል፡፡
በመጨረሻም “እውነተኛ ውይይት እና ትርጉም ያለው ተሃድሶ ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው፤ በኢትዮጵያውያን መካከል ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ለሰው ልጆች ሁሉ በሚያደርጉት ትግል ይታወቃሉ፤ ሀገር ወዳድ ከሆኑት ኢትዮጵያውን መካከልም አንዱ ናቸው።
Filed in: Amharic