>
5:13 pm - Wednesday April 20, 9960

አደጋው ላልታያችሁ፤ ኢትዮጵያ በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አደጋው ላልታያችሁ፤ ኢትዮጵያ በአስፈሪ ሁኔታ ውስጥ….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ይህን ደብዳቤ መሰል ጽሑፍ የምጽፈው በታሪክ አጋጣሚ የኢትዮጽያ እጣፈንታ እጃቸው ላይ ለወደቀው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እና በነውጥ የታጀበውን ለውጥ ለሚመሩት ባልንጀሮቻቸው፣ አጋሮቻቸው፤ እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው ትኩረት ቢሰጡት በሚል እምነት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ለእዚች አገር ያለዎትን ራዕይ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እጅግ በሚስቡና ማንንም በሚያማልሉ ቃላቶች ሲገልጹ ቆይተዋል። የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት ያለዎትንም ጉጉት እና የቆየ የልጅነት ህልም ፈቺም በማያስፈልገው መንገድ ራስዎ ደጋግመው ከነፍችው ነግረውናል።
ይሁንና በዚህ ሦስት አመት ውስጥ ኢትዮጵያ በታሪኳ አስተናግዳ የማታውቀውን አደጋ ሁሉ በአንድ ጊዜ እያስተናገደች ትገኛለች። ዛሬ እጅዎት ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ክፉት እና ጭካኔ የተሞላባቸው የወንጀል አይነቶችን፣ የሚሊየኖችን መፈናቀል፣ የከፋ ዘረኝነት፣ ጦርነት፣ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያ፣ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ የከፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ የሴቶች ጥቃት፣ የጎረቤት አገር ጣልቃ ገብነትና የድንበር መወረርን፣ የከፋ የኑሮ ውድነት፣ አመጽን፣ አለም አቀፍ ወረርሽኝ በሽታን-ኮቪድ፣ የምእራባዊያንን ኩርፊያና ቁጣ፣ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ማባሪያ የሌለው ንቁሪያ፣ የውስጥ ታጣቂ ቡድኖች ወረራን፣ ማህበረሰቡን ጥልቅ ፍርሃትና ሽብር ወስጥ የሚከቱ የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን በአንድ ጊዜ እያስተናገደች ነው።
እርሶ በየመድረኩ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም’፣ ‘እኔ ከኢትዮጵያ ቀድሜ ልፍረስ’ እያሉ ሰላሳ ጊዜ ቢምሉና ቢገዘቱም አገሪቱ የመፍረስ አፋፍ ላይ የደረሰች ትመስላለች። የኢትዮጵያም ፖለቲካ እጅዎት ላይ እንደበረዶ እየቀለጠ ሲንጠባጠብ ለርሶና ለአፍቃሪዎችዎ ባይታይም አገሪቱ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ በቅጡ ላጤነ ቁልጭ ብሎ ይታያል።
ከላይ የጠቀስኳቸው አብዛኛዎቹ ችግሮች ለኢትዮጵያም ለአፍሪካም እንግዳ ባይሆኑም ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ችግር በአንድ ጊዜ ያስተናገደችበት ወቅት ግን ቢያንስ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን አይደለም። የችግሮቹንም ምንጭ ብንመለከት ቡዙዎቹ አደጋዎች የርሶ መስተዳድር የወረሳቸው (አውራሹም እራሱ ቢሆንም) ሲሆኑ የቀሩት ደግሞ የእርሶ መስተዳድ በግልጽ ከሚታይበት ቅራኔዎችን በጥንቃቄ እና በፍጥት የመፍታት ክህሎት ወይም የፖለቲካ አስተዳደር ጥበብ ማነስ የመነጩ መሆኑ ብዙም ከያከራክርም።
የሕግ የበላይነትን ለማስፈን፣ የአገሪቱን ጸጥታና ደህንነት ለማስከበር፣ የዜጎችን መብት ለማክበርና ለማስከበር፣ የአገሪቱን ዳርድንበር ለማስከበር እና ግጭቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቁመና ያጣው አስተዳደርዎ ኢትዮጵያን እጅግ አስፈሪ ወደሆነ ወጥመድ ውስጥ ከቷታል። ዛሬ ኢትዮጵያ፤
+ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወድቃ ሌሎች አዳዲስ ግጭቶችን ልታስተናግድ አፋፍ ላይ ነች፣
+ ከሻሸመኔ፣ ከመተከል፣ ከማይካድራና ከአክሱም የከፉ  በዘር ላይ ያነጣጠሩ ግጭቶችን ልታስተናግድ እንደምትችል በአለም አቀፊ ሚዲያዎች ሳይቀር መወያያ ሆናለች፣
+ የአባይ መዘዝ የቀሰቀሰው አካባቢያዊ ውጥረት ወደ ድንበር አቋራጭ ጦርነት ሊያመራ አንድ ሐሙስ የቀረው መሆኑን በርካታ ማመላከቻዎች እየታዩ ነው፣
+ በአገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለው አስከፊ የኑሮ ግሽፈት እና በላዩ ላይ የታከለው የኮቪድ ወረርሽኝ እጅግ አስከፊ የሆነ የኑሮ እና የኢኮኖሚ መቃወስን እያስከተለ ነው፣
+ ከመቼው ጊዜ በከፋ ሁኔታ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ መፈናቀል፣ ዝርፊያና የወንጀሎች መበራከት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም ውሎ በሰላም ማደርን እንደ ብርቅ ነገር እንዲታይ እያደረገ ነው፣
በአንጻሩ አገሪቷ ወሳኝ የተባለውን ምርጫ ለማካሄድ ሽር ጉድ እያለች ነው። ምርጫው በራሱ ይዟቸው የመጣው መዘዝ እንዲሁ የአገሪቷን መከራ የማያልፍ ቀን አስመስሎታል። አገሪቱ ይህን ወሳኝ ምርጫ ማካሄድ አለባት ብለው ከሚያምኑት አንዱ ብሆንም ተያይዘው የመጡት አደጋዎች እንቅልፍ ከነሷቸው ኢትዮጵያዊያንም ራሴን እመደባለሁ። የምርጫው መዘዞች በጥቂቱ፤
+ ወሳኝ የሆኑ የኦሮሞ ፖርቲዎች ከወዲሁ በሰበብ አስባብ እና በተፈጠሩ መሰናክሎች ከምርጫው ሂደት እራሳቸውን ማግለላቸው ሰፊ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ሕዝብ አማራጭ እንዳያገኝ ከማድረጉም ባሻገር የክልሉን ሰላም ወደ ከፋ አግጣጫ ሊያመራው ይችላል፣
+ የተወሰኑ ክልሎች ውስጥ የሚታየው የሰላም መታጣት፣ የርስ በርስ ግጭት፣ የውስጥ ድንበር ውዝግብ፣ የታጣቂ ሃይሎች መጠናከር እና እየጨመረ የመጣው የውስጥ መፈናቀል በአገሪቱ በርካታ ቦታዎች ምርጫ ለማካሄድ የማያስችሉ ሁኔታዎችን ከወዲሁ እየፈጠረ ይመጣል፣
+ ተቃዋሚዎች ተንቀሳቅሰው የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የሚችሉባቸው የአገሪቷ ክፍሎች እየጠበቡና የዜጎችም የመንቀሳቀስ ነጻነት በመሀል የአገሪቱ ክፍል እየተወሰነ መጥቷል፣
+ በክልሎች መካከል ያለው ውጥረት እየከረረ እና አልፎ አልፎም ወደ ግጭት ማምራቱ እራሱ ገዢው ፖርቲ የፖለቲካ ነውጥና የሥልጣን ትንቅንቅ ወስጥም የገባ አስመስሎታል፣
የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አስተዳደር ከላይ የተዘረዘሩትን አደጋዎች አንድም በተናጠል እያየ አለያም አደጋዎቹን  አኮስሶ እየገመተ ወይም በማን አለብኝነት ስሜት ተሰቅፍ ወይም በተስፋ መቁረጥ ሊሆን ይችላል አደጋዎችን የሚመጥን ምላሽ ሲሰጥ አይታይም። በአንዳንዱ ሁኔታዎች እንደውም በተቃራኒው አደጋዎቹን የሚያባብሱ ሥራዎች በመንግሥት አካላት ሲፈጸም ይስተዋላል። አደጋዎቹን አቅላችሁ ለማየታችሁ አንዱ ማሳያ የኦነግ ሽኔ ታጣቂ ቡድን ከወለጋ ተነስቶ የአገሪቷ እምብርት ላይ በደረሰበት እና ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ ቀውስ እና ውጥንቅጥ ውስጥ በወደቀችበት በዚህ ወቅት ካድሬዎችዎ የዕርሶን የሦስት አመት ሲመተ በዓል ለማክበር ሽር ጉዲ ሲሉ መታየታቸው ነው።
አዎ አገሪቷ የገባችበት አጣብቂኝ እና ያንጃበቡባት አደጋዎች ለእርሶ ለጠቅላዩም ሆነ ለተከታይ ካደሬዎችዎ እየታያችሁ አይመስልም። የእናንተን በሥልጣን መቆየት አገሪቱ ለተጋፈጠቻቸው ችግሮች ሁሉ እንደ ቁልፍ መፍትሔ አድርጎ ማየት የአደጋውን መጠን እና ጥልቀት ያለመረዳት ችግር ብቻ ሳይሆን የመጣንበትን የፖለቲካ አዙሪት ድግምግሞሽ ማሳያም ይመስለኛል። የኢትዮጵያ ችግር ከቁመታችሁ በላይ ከሆነ ውሎ አድሯል። አደጋዎቹም እናንተ ብቻችሁን የማትመልሱትበት ደረጃ ላይ ከደረሱ ከራርሟል። ሞልቶ እየፈሰሰ ያለውም ግፍ እናንተን ጠራርጎ የሚሄድ ብቻ ሳይሆን አገሪቷንም ወደ ለየለት የፖለቲካ ቀውስ የመክተት አቅሙ እና ፍጥነቱም እየጨመረ መሜጣቱን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
አገሪቱ በዚህ ሁሉ ውጥረት ውስጥ ሆና ጠቅላይ ሚንስትር  አብይም ሆኑ አስተዳደራቸው በያዛችሁት የማስመሰል ፖለቲካ የምትቀጥሉ ከሆነ ታሪክ የምትሆኑበት ጊዜ እሩቅ አይመስለኝም። ችግሩ እየመጣ ያለው አደጋ እናንተን ጠራርጎ የማያቆም መሆኑ ነው። አሁንም ለእናንተም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚበጀውን ከመናገር ወደ ኋላ አልልም።
መፍቴሔ
+ መንግስት አገሪቷ የገባችበትን ቀውስ እና ያንጃበበውን አደጋ ከግምት በማስገባት የብሔራዊ የቀውስ መፍትሔ አፈላላጊ አካል በአፋጣኝ ሊያዋቅርና አፋጣኝ የምክክር መድረኮችን ሊያካሂድ ይገባል። በዚህ ውስጥ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ማረጋገጥ ግድ ይላል።
+ ገዢው ፖርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፖርቲዎች ግጭት አባባሽ ከሆኑ ድርጊቶቻቸው ታቅበው ወደ ምክክር እና የጠረጴዛ ውይይቶች ለመምጣት የሚከፈለውን መስዋትነት ሁሉ መክፈል አለባቸው።
+ በገዢው ፖርቲ አባላት እና በክልሎች መካከል የሚታየው መፉጠጥ እና ጤናማ ያልሆነ ፉክክር ከወዲሁ እልባት ይሻል። በፖርቲው ውስጥ ያለን ሰላም ማምጣት የተሳነው በወ/ሮ ሞፈሪያት የሚመራው ‘የሰላም ሚንስትር’ የአገር ሰላም ለማምጣት አቅም ያለው ስለማይመስል ሊፈተሽና በአዲስ መልክ ሊዋቀር ይገባል።
+ ውዝግብ የተነሳባቸው የውስጥ የድንበር ጥያቄዎች ዘላቂ  የሆነ የሕግና የፖለቲካ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ ለሌሎች ግጭቶች መንስዔ ሳይሆኑ በፊት በአፋጣኝ ከተወዛጋቢዎቹ ክልሎች እጅ ወጥተው በፌደራሉ መንግስት እንዲተዳደሩ ሊደረግ ይደረግ።
+ የሽምቅ ተዋጊዎች፤ በዋነኝነት ኦነግ ሽኔ እያደረገ ያለውን መስፋፋት እና በንጹሀን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ሰቆቃ ባፋጣኝ መቆጣጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት።
ያንዥበቡት አደጋዎች ሊቀለበሱ የሚችሉ ናቸው። ሆኖም የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ርብርብ ይጠይቃሉ። ገዢው ፖርቲ አደጋዎቹን ብቻውን የመቋቋም አቅም እንደሌለው በብዙ መልኩ እየታየ ነው። የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ፣ ሁሉን አቀፍ፣ የአጣዳፊና የቀውስ መፍትሄ ስልት መቀየስ የግድ ይላል። በዚህ ዙሪያም የምክክር መድረኮች ሊከፈቱ ይገባል።
ቸር እንሰንብት!
Filed in: Amharic