>

አማራው የራሱን ጀግና በአፋጣኝ አምጦ መውለድ አለበት.. !!! (ዶክተር ደረጀ ከበደ)

አማራው የራሱን ጀግና በአፋጣኝ አምጦ መውለድ አለበት.. !!!

ዶክተር ደረጀ ከበደ

የአማራው እልቂት እንደቱትሲዎች እልቂት በአለም ህብረተሰብ ደንቆሮ ጆሮዎች ላይ አርፎአል።
ቱትሲዎች በጄኖሳይድ ጨረሰው እንዳይጠፉ የደረሱላቸው የአለም ሃያላን ሳይሆኑ አንድ ቁመተ ቀውላላ (6ft 2 in)፣ ነፋስ በቀላሉ የሚያወዛውዘው ቀጫጫ የቱትሲ ብሄር ሰው ነበር።
በሩዋንዳው ጄኖሳይድ ቱትሲዎችን ከሁቱዎች ሜንጫ ያዳነው ፖል ካጋሚ የቱትሲው ተወላጅ  ከ 2000 አ.ም ጀምሮ የሃገሪቱ ፕሬዜዳንት ሆኖ የቆየ ጀግና፣ የብሄሩ፣ በሁዋላም የጠቅላላ ሩዋንዳዎች ባለውለታ ነው። ፖል ካጋሚ ይህን ያህል በስልጣን የመቆየቱን ነገር በግሌ ባልወድለትም፣ ለሃገሪቱ ጥሩ ሰላምና መረጋጋትን አምጥቶላታልና ምስጋና ይገባዋል።  ለጊዜው ግን ትኩረቴ የሱን የአስተዳደር ዘመን ገድል ለማውራት ሳይሆን ፕሬዚዴንት ከመሆኑ በፊት ወገኖቹና ደሞቹ ቱትሲዎች በሁቱዎች በጅምላ ሲታረዱና አለም ፊቱን ባዞረባቸው ወቅት፣ እሱና አማፅያን ኮመሬዶቹ የሁቱን መንግስት ወግተው ጭፍጨፋውን የማስቆማቸውን ታሪክ ነው ማስታወስ የምፈልገው።
ፓል ካጋሚ ይመራው የነበረው ተዋጊ ሃይል Ruwanda Patriotoc Front (RPF) በ 1986 በዩጋንዳ በስደት ላይ በነበሩ ቱትሲዎች በፖል ከጋሚ መሪነት ተመሰረተ። አላማው የሩዋንዳውን ሁቱ መሪ ለማውረድና በሃገሪቱ የቱትሲዎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ በተጨማሪም በሃገሪቱ ውስጥ የበይ ተመልካች እንዳይሆኑ የዜግነት መብታቸውን ለማረጋገጥ የሁቱዎችን አስተዳደር ለመግፋት የተመሰረተ ነበር።  ፖል ካጋሚና ሰራዊቱ ከመራር ውጊያና ድል በሁዋላ  ሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ከተማን ሲቆጣጠሩ ቱትሲዎች ከሁቱዎች ጋር ስልጣን እንዲካፈሉ በጠየቁት መሰረት  ፊት አሻፈረኝ ብሎ የነበረው የሃቢአሪማና መንግስት በ 1993 አ.ም ሳይወድ ወደ ድርድር ጠረጴዛ መጥቶ ስልጣን ለማጋራት በፊርማ አረጋገጠ። በዛን ጊዜ የተገኘውን የሰላም ስምምነት ለማስጠበቅ የተባበሩት መንግስታት 5000 ወታደሮችን ወደ ሩዋንዳ ላከ።
ዳሩ ግን ይህንን ስልጣን የመካፈል ስምምነት ሁቱዎች በሁለት ምክንያቶች አምርረው ተቃወሙት። አንደኛ/ ቱትሲዎች መጤዎች ናቸው ተብሎ ስለሚታመን (ከኢትዮጵያ ግጦሽ ፍለጋ የሄዱ እንደነበር የታሪክ ምርምር ይጠቁማል)፣ ሁለተኛ/ ቱትሲዎች  ከሩዋንዳ ህዝብ ቁጥር 14% በጣም አናሳ ብሄር ሲሆኑ፣ ሁቱዎች ደግሞ 85% ቱን የያዙ በዛም ላይ ሃገር-በቀል (indiginous)ህዝብ ናቸው። ስለዚህ ሁቱዎች ስልጣን አናካፍልም በሚል ማጉረምረም ጀመሩ።
ሁለቱ ብሄሮች፣ ሁቶዎችና ቱትሲዎች፣ ከቅኝ ገዢዎች መከሰት በፊት በስምምነት ይኖሩ ነበር። ሩዋንዳ በጀርመንና በቤልጂየም መንግስታት ለብዙ አመታት በቅኝ አገዛዝ ስር ወድቃለች። ተንኮለኞቹ ቤልጂየሞች ታዲያ አናሳዎቹን ቱትሲዎችን በብዙሃኑ በሁቱዎች ላይ አለቃ አድርገው ሾመዋቸው ከፋፍለው ገዝተዋል። ያም የበላይነትና የበታችነት ጉዳይ በሁለቱ ብሄሮች መካከል ፊት ያልነበራቸውን ደመኝነትን ፈጠረ።
ከአመታት በሁዋላ በApril 6, 1994 የሁቱውን ፕሬዚደትን ይዞ የነበረ ፕሌን በአየር ላይ እንዳለ በሚሳይል ተመቶ ፕሬዜዳንቱ ተገደለ። በዛን ጊዜ ሁቱዎች ቱትሲዎችን የፕሬዜዳንቱ ገዳይ ናችሁ በሚል ከሰሱዋቸው። በሁዋላም በዛ ሳቢያ ቱትሲዎችን መጨፍጨፍ ጀመሩ።
በግድያው ወቅትና ከዛም ጥቂት ቀደም ብሎ ነገራት እያሰጉ ሲሄዱ፣ ቱትሲዎችና በወቅቱ በሩዋንዳ ሰፍሮ የነበረው የሰላም አስከባሪ ጀነራል ጭምር ለአለም መንግስታትና ሌሎችም ሃያላን አገሮች ካናዳም ጭምር  የድረሱልን ልመናም ጥሪም አቅርበው ነበር። ማንም አልሰማቸው። ጄኖሳይዱ በሙሉ ሃይል ከመካሄዱ በፊት የምእራብ አገሮችና የተባበሩት መንግስታት ደርሰው ቢሆን ኖሮ 800, 000 ቱትሲዎች ባልተገደሉ ነበር።
ዩናይትድ ኔሽን ለቱትሲዎች የድረሱልን ጥሪ ጀርባውን ሰጣቸው። በሩዋንዳ የነበሩት የኢንተርናሽናል ፀጥታ አከባሪ መለዮ ለባሾች በብጥብጡ ሰሞን 10 ወታደሮች እንደተገደሉባቸው UN 200 ወታደርቶች ብቻ አስቀርቶ ወታደሮቹን ሁሉ ከሩዋንዳ አስወጣ።
ፍራንስ ጀርባዋን ሰጠቻቸው ምክንያቱም በጊዜው ከነበረው ከጄኖሳይደሩ ከሁቱ መንግስት ጋር የጠበቀ ግንኑነት ነበራት
ቤልጂየም በጄኖሳይዱ ወቅት 450 ወታደሮች ስለተገደሉባት የተረፉትን ወታደሮችዋን ፈጥና ከሩዋንዳ አስወጣች። ከዛ የበለጠ ሪስክ እንዳይወስድ አዛዡኙን ጄነራል ዳላይርን አዘዘች።
አሜሪካም በወቅቱ ሶማሌ ውስጥ በሽንፈት ተዋርዳ ስለነበር ወደ ሩዋንዳ መዝመት አልፈለገችም።ከዛም በላይ በሰላም ማስከበር ተልእኮ ከመደበችው በጀት በላይ የሚያስወጣት እንደሚሆን ስለገመተች በሩዋንዳው ጉዳይ ጣቃ አልገባ አለች።
አሜሪካ፣እንግሊዝ፣ፍራንስ ቤልጂየም የሮማን ካቶልክስ ቤተክርስትያንና የተባበሩት መንግስታት የሩዋንዳን ጥሪ ላለመስማት ጆሮአቸውን የደፈኑ የታሪክ ተጠያቂዎች ናቸው ። እንዲያውም ፖፕ ፍራንሲስ ፖል ካጋሚን በካቶሎኮች ስም በቅርብ ይቅርታ ጠይቀው ነበር። ካቶሊኮች ቱትሲዎችን ሲያስገድሉና ሲገድሉ እንደነበር በመረጃ ስለታወቀ።
እነኝሕ ሁሉ መንግስታት ጀርባቸውን ስለሰጡዋቸው ቱትሲዎች እንደዛሬው አማራ ምንም ተስፋ የሚያደርጉት አልነበራቸውም ነገር ግን ከመካከላቸው ራሱን ለህዝቡ የሰዋ አንድ ሰው ተገኘ እሱም ከበለጠ እልቂት አተረፋቸው።
በ1994 በጄኖሳይዱ አመት ፓል ካጋሚና ጎሬላ ተዋጊ ሰራዊቱ የሁቱዎችን መንግስት ተዋግተው ኪጋሊን ተቆጣጠሩ። በዛን ጊዜ ወደ 2 ሚሊዮን ሁቱዎች ሸሽተው ወደ ኮንጎ ፈረጠጡ። ፓልና RPF የወገኖቻቸውን የቱቲስዎችን ጀኖሳይድ አስቆሙ።
አማራው የአለምን ነጮች ያዋረደና ያስቆጣ ጠንካራ ህዝብ ነው። እሱ እያለ ኢትዮጵያን ሊቆራርሱና ሊሰለቅጡ አይችሉም። ይህን የሚያውቁ ሃያላን መንግስታት የአማራው ማለቅ ለጆሮአቸው የወፎች የማለዳ ዜማ ነው። ስለዚህ መዳኛው ከሌላ አይደለም። ፋኖን የወለደ አማራ፣ ሌሎች ጎቤዎችን መውለድ አይሳነውም። የኛው ጎቤ ሆድ አደር ባይቀድመው ኖሮ እንደሩዋንዳው ፖል ካጋሚ በእግዚአብሄር እርዳታ ከአራጆች ባዳነን ነበር።
Filed in: Amharic