>
5:13 pm - Monday April 19, 6404

ገዳይን «ጀግናዬ!» የሚል ስንቅና ትጥቅ አቀባይ እስካለ ድረስ  ሞታችን ይቀጥላል...!!! (ክርስቲያን ታደለ)

ገዳይን «ጀግናዬ!» የሚል ስንቅና ትጥቅ አቀባይ እስካለ ድረስ   ሞታችን ይቀጥላል…!!!

ክርስቲያን ታደለ

እውነታ አንድ፦ ትሕነግ 27 ዓመታት ሙሉ በሕዝባችን ላይ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው በደልን አደረሰች። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ትግል ላይ የነበርን ብንሆንም ማሸነፍ አቅቶን የሆነብን ሁሉ ተፈፀመብን።
ምክንያት አንድ፦ ትሕነግን ማሸነፍ ያቃተን ትግላችን ከራሳችን ወንድሞች ጋር ስለነበረ ነው። ትሕነግ ያሳረፈቺብን ጠበሳ ሁሉ እንደአሻንጉሊት ጠፍጥፋ በሰራቻቸው በራሳችን ወንድሞች ክንድ በተሰነዘረብን በትር ነው።
እውነታ ሁለት፦ 27 ዓመታት ታግለን ማሸነፍ ያቃተቺንን ትሕነግ ከ2 ዓመታት ባነሰ ሕዝባዊ ተጋድሎ ከ4 ኪሎ ቤተመንግስት ማባረር ቻልን። ሃያ ሰባት ዓመታት ያቃተንን ተጋድሎም በ17 ቀናት ትግል የሕዝባችንን ደመኛ ግብኣተመሬት በመፈፀም አጠናቀቅን።
ምክንያት ሁለት፦ የትሕነግ እጅ ሆነው ሲደበድቡንና ሲገሉን የነበሩ ወንድሞቻችን ክንዳቸው ስለዛለ ጭምርና ውለው አድረውም ወደ ኅሊናቸው በመመለሳቸው፤ ቀጣዩ የትሕነግ የጭካኔ በትርም ማረፊያ በራሳቸው እና ቤተሰቦቻቸው ላይ መሆኑን ስለተረዱ፤ አልፎ አልፎም ቢሆን በትር ሆነው ማገልገልን በመቃወማቸው፤ ትሕነግን ከአራት ኪሎ መንቀል ቻልን።
ከአራት ኪሎ ወጥቶ መቀሌ በመሸገው ትሕነግ ላይ ያላንዳች ልዩነት በጠላትነቱ ላይ መግባባት በመድረስ የተናበቡና የተቀናጁ ሁሉንአቀፍ ሥራዎች በመስራታችን፤ «ፍጡር ቀርቶ እግዜሩ አያሸንፈኝም» እያለ ሲፎክር የነበረውን ትሕነግ በ17 ቀናት ብቻ ግብኣተመሬቱን መፈፀም ቻልን።
እውነታ 3፦ የፋሽት ጣሊያን መንትያ ውሉዶች ከሆኑት ውስጥ ትሕነግ የውኅድ ኃይል በመሆኑ ግፋ ቢል የተጽእኖ (Dominance) ብልጫ በመውሰድ ወሳኝ የሚባሉ የተጽእኖ ተቋማትን (ፖለቲካ፣ ሚዲያ፣ ደኅንነት፣ ኢኮኖሚና አቃቤ ሕግ) ከመቆጣጠር ያለፈ የዋጭ ሰልቃጭነት (Overwhelming) አድማስ እንደማይኖረው ታውቆ ያደረ ነው።
 በትሕነግ ዱካ የተተካው፤ ኢትዮጵያን እንደእንጀራ እናት ከሳሹ፤ ተረኛ ኃይል ግን ተጽእኖ በመፍጠር ሳይገደብ «እኔን ነህ ወይም ጠላት ነህ» በሚል የዋጭ ሰልቃጭነት ስምሪት፥ ውኅዳንን እየዋጠና እየሰለቀጠ፥ ብቸኛ አውራ የመሆን ኅልም መያዙን፤ ትሕነግ ከ4 ኪሎ ለመውጣት 6 ወራት ሲቀሯት ጀምሮ፤ በኣራት ተከታታይ ክፍሎች ባሉት የማንቂያ ጽሑፍ (የኦሕዴድ መንገድ በሚሉ ርእስ)፤ በአንክሮ አሳስበን ነበር።  ይህ እውነት የገባቸው ወንድሞችና እህቶችም የጉዳዩን አሳሳቢነት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ አስገንዘበው ነበር። ነበር ሆነ እንጂ! (በዚህ የተነሳ የተከፈለውን ምትክ የለሽ መስእዋትነት ልባም ትውልድ ሲመጣ ይዘክረዋል።)
ብቸኛ አውራ የመሆን የዋጭ ሰልቃጭ ፕሮጀክት ብርቱ በትር ያረፈው፤ የዚህ ኅልም ቀጥተኛ ተገዳዳሪ ይሆናል ተብሎ ብያኔ በተያዘበት፤ የአማራ ሕዝብ ላይ ነው። አማራው በስልቀጣ (assimilation) የማይበገር (resilient) መሆኑና የቀደመ መንግስታዊ ወግና ባሕል የነበረው ታላቅ ሕዝብ መሆኑ ተደምሮበት ፋሽስቱ ኃይል «መደመር» ሲል የዳቦ ስም ላወጣለት የመዋጥ መሰልቀጥ ዘመቻ ብርቱ እንቅፋት ሆኖ ተገኜ። እንቅፋት ብሎ ድምዳሜ ለደረሰበት ችግሩም ፋሽስት ኃይሉ ያለው አስቀያሚ አማራጭ ያለምኅረት ይህን ሕዝብ መጨፍጨፍ ሆኖ አገኜው።
ግብኣተመሬቱ እንደተፈፀመው መንትያ ወንድሙ ትሕነግም፥ ዋጭ ሰልቃጭ  ኃይሉ  ከአማራ የፀዳ አካባቢን የመፍጠር ፕሮጀክቱን በወለጋ ሀ ብሎ ጀመረ። (የፕሮጀክት መጀመሪያ ጊዜ ማጣቀሻው ፋሽስት ኃይሉ አራት ኪሎ ከገባ ጀምሮ ያለውን ነው!) በወለጋ የፈፀመውን አማራውን በጅምላ በመጨፍጨፍ ከአማራ የፀዳ አካባቢን መፍጠር ፕሮጀክት አድማስ ወደ መተከል በማስፋትም ያለሀይ ባይ የዘር ፍጅትና ጅምላ ማፈናቀል ተግባሩን አጠናክሮ ገፋበት። ጉራፈርዳ፣ ኮንሶ፣ አርሲ፣ ሐረርጌ፣ ድሬዳዋ፣ አጣዬ–ከሚሴ፣ ጂማ፣ ኢሉባቦር፣…እያለ ከአማራ ነፃ አካባቢን የመፍጠር ፕሮጀክቱን ያጧጡፍ ጀመር።
በዚህ ሁሉ ያልተቋረጠ የፍጅት እምቧለሌ አማሮች እንደጠል ረገፉ። ሞታችን ለዜና ፍጆታ እንኳን መሆን እስኪሳነው ድረስ ጨፈጨፉን። በሕይወት ላለነው ኃፍረትና ዘላለማዊ ውርደት እንዲሆን ታስቦም የጅምላ መቃብራችን ወግ የራቀው ሆነ። የትም ተገድለን እንዴትም እንደቆሻሻ ተጣልን።
ምክንያት 3፦ የሆነብን ሁሉ የሆነው እንደትሕነጉ 27 የመከራ ዓመታት ሁሉ ዛሬም በገዳዮቻችን ላይ አንድ ዓይነት አቋም መያዝ ስላልቻልን ነው። አንዱ በገዳይ ላይ የበረታ አቋም ይዞ ጠንካራ ተጋድሎ ሲያደርግ፤ ሌላው ገዳይን ካባ ይሸልማል። የፋሽስት ኃይሉ ብቸኛ አውራ የመሆን የዋጭ ሰልቃጭነት ፕሮጀክትን አንዱ አምርሮ ሲታገል፤ ሌላው ይኸንኑ ፋሽስት ኃይል የኢትዮጵያ ትንሳዔ ፊትአውራሪ አድርጎ ያቀርባል። ከዚህ ባስ ሲልም ዋጭ ሰልቃጭ ፋሽስቱን ኃይል የሚቃወሙትን፤ አስቀድመው የነቁና የበቁትን ወንድሞችና እህቶች፤ በጽንፈኝነት ሲከስ ይውላል።
በዚህ የተነሳም፥ የጅምላ እርድ ሲቃችን እንደመዝናኛ ተቆጠረ። ኃዘናችን መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆን አልፎ የዋጭ ሰልቃጩ ፋሽስት ኃይል የስኬት መለኪያ እስከመሆን ደረሰ። ሞታችንንም፥ አሟሟታችንም ተዳፍኖ እንዲቀር ብርቱ አፈናዎች ተደረጉ። ጉዳዩም «ለምን የጅምላ ግድያ ይፈፀማል» ከሚል ወጥቶ በሂደት «የተገደለው በጥይት ነው ወይስ በቆንጨራ»፤ ከዚያም «የሟቾች ቁጥር ተጋኗል» ወደሚል ክርክር፤ አሁን ደግሞ «የዘር ፍጅት ተፈፀመብን» ብለን ለማዘን እስከመሳቀቅ ደርሰናል።
እኮ ለምን? በገዳይ ላይ አንድ ዓይነት ብያኔ ይዘን ሕዝባችንን ለመታደግ መታገልን ስላልቻልን። እኮ ለምን?  የዘር ፍጅት ከሚፈፀምበት ሕዝባችን ይልቅ ገዳይ ጋር ያለን የፓርቲና ማኅበራዊ ዝምድና ስለበለጠብን። እኮ ለምን? የኅልውና ትግሉ በአማራነታቸው ላይ ብዥታ ባለባቸው ግለሰቦች ጭምር የሚመራ በመሆኑ። እኮ ለምን? በአማራነቱ ላይ ጥያቄ የማይቀርብበት  ኃይልም ለሕዝብ ኅልውና ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ባለመሆኑ። እኮ ለምን?  መስእዋትነቱ እንደቀደሙት ሁሉ የውሻ ደም ሆኖ እንዳይቀር ስጋት በመኖሩ።
መውጫ፦ መግቢያ ያጣን ሕዝብ መውጫ ማለት ከንቱነት ነው። ቢሆንም የሚመስለንን መናገራችን ከዝም–ዝምብሎ ይሻላል በሚል ግምት እንዲህ እንላለን። መላው አማራ በአማራና አማራነት ኅልውና ላይ የግድ መስማማትና መግባባት ይኖርበታል። ለሕዝባችን ኅልውና የወዲያው አጣዳፊ ዋነኛ ስጋት  ዋጭ ሰልቃጩ የፋሽዝም ኃይል በመሆኑ ጉዳይ ላይም የማያወላዳና አንድ ዓይነት አቋም መያዝ ይኖርበታል። በሁለቱ ላይ የጋራ አቋም መያዝ ከተቻለ፤ የኅልውና ትግላችን ከግማሽ በላይ ለድል ይቀርባል። ሌላውን መዘርዝር በውስጥ የምንመክርበት ይሆናል።
ፋሽዝም ሲከስም፥ የአማራ ኅልውና ስጋት ይቀረፋል፤ የኢትዮጵያ ትንሳዔ ይጀምራል!
Filed in: Amharic