መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በጽኑ እናወግዛለን !
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
*…. በዛሬው ዕለት እና በነገው ቀን እጅግ ደማቅ እና በአይነቱ ለየት ባለ መልኩ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ፤ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ፣ የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎችን በማስተባበር የምርጫ ቅስቀሳ ለማድርግ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ቢሆንም ፤ እንደ ሃገር በገጠመን ጥልቅ ሐዘን ምክንያት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊያካሂደው የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ ወደ ሌላ ቀን አሸጋግሮታል !!
ባለፉት ዓመታት በተለይ “ለውጥ” መጣ ከተባለበት ጊዜ አንስቶ በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል በአይነቱ እና በመጠኑ እየጨመረ መጥቷል ። ለዚህም ዋንኛው ምክንያት አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው መንግስት እንደሆነ ብዙ አስረጂ የሚሻ ጉዳይ አይደለም ።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ ቦኔ ቀበሌ የተፈጸመው የዘር ፍጅት ወንጀል ከዚህ ቀደም በክልሉ ሲፈጸም ከነበረው አረመኔያዊ ተግባር የተለያየ አይደለም ። በዚህ ሰይጣናዊ ተግባር ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች፣ ወዳጅች እና ዘመዶች ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጥልቅ ሐዘን ይሰማዋል።
ባለፉት ዓመታት በዜጎች ላይ የሚፈፀመውን የዘር ፍጅት ወንጀል ለማስቆም “መንግስት ነኝ” የሚለው አካል አንዳች ተጨባጭ ነገር ሲያደርግ አልታየም ። ለዚህ ሁሉ ዕኩይ ተግባር “መንግስት” ተጠያቂ እያደረገ ያለው ኦነግ ሸኔ የተባለውን ገዳይ ቡድን ነው። ሆኖም ግን ይህ የዳቦ ስም የተሰጠው ገዳይ ቡድን “መንግስት ነኝ” ከሚለው ኃይል በትጥቅ ሆነ በስንቅ በልጦ አይደለም ። ከምንም በላይ ደግሞ “መንግስት” ንፁሃንን መታደግ ዋንኛ ተግባር መሆን ነበረበት። ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ አይደለም በተደጋጋሚ እንዲህ አይነቱ ማንነትን መሰረት ያደረገ የዘር ፍጅት ወንጀል በአይነቱ እና በመጠኑ እየጨመረ ለመምጣቱ ዋናው ምክንያት መንግስታዊ ሽፋን ያለው ወንጀል እንደሆነ ባልደራስ አጥብቆ ያምናል።
ይህም በመሆኑ ዜጎች በማንነታቸው ተለይተው ለደረሰባቸው እና ለሚደርስባቸው የዘር ፍጅት ወንጀል፣ እንዲሁም ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል ዳተኝነት በማሳየት ብቻ ሳይሆን ለዚህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚ ቡድን ሽፋን በመስጠት ጭምር አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው። “መንግስት” ዋንኛ ተጠያቂ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በተመለከተ ሥር- ነቀል ለውጥ ለማምጣት ከሚያከናውናቸው የፖለቲካ ትግል ባሻገር ከሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተሟጋች ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመሆን ይህንን ጉዳይ ከአገር ውስጥ ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ የሕግ ተቋማት በመውሰድ ወንጀለኞች በፍትሕ አደባባይ እንዲዳኙ በማድረግ የንጽሃን ደም ደም ከልብ ሆኖ እንዳይቀር አጥብቆ ይሰራል።
ልናካሂደው የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ ሰርዘናል !!
ከሁሉ አስቀድመን በአገራችን በኦሮምያ ክፍለ-ሃገር በተለያየ ወቅት በተደጋጋሚ በተፈጸመ ጥቃት ፤ በንጹሃን ዜጎች በኦህዴድ/ብልጽግና ይሁንታ እና ኦነግ ሸኔ በተባለ የዳቦ ስም የተሰጠው ገዳይ ቡድን አድራጊነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባ ለሆኑ የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን ባልደራስ እውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገልጻል!
የሟቾችን ነፍስ ፈጣሪ በአጸደ ገነት ያኑርልን፡፡ ለውድ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡
በንጹሃን ዜጎች ላይ ሆነ ተብሎ ለሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሽፋን በመስጠት የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳድር ከማንም በላይ ተጠያቂ እንደሆነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል፡፡ ይህን መሰል በዜጎች ላይ የሚፈጸም ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ንብረት ማውደም እና ዘረፋ ከምንም በላይ መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው እንዲህ አይነቱ ዕኩይ ተግባር ሥር- ነቀል ለውጥ ለማምጣት ባልደራስ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉን አጠናክሮ ይቀጥላል ፡፡
ይህ በእንዲ እንዳል በዛሬው ዕለት እና በነገው ቀን እጅግ ደማቅ እና በአይነቱ ለየት ባለ መልኩ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ፤ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ፣ የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎችን በማስተባበር የምርጫ ቅስቀሳ ለማድርግ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ቢሆንም ፤ እንደ ሃገር በገጠመን ጥልቅ ሐዘን ምክንያት ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊያካሂደው የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ ወደ ሌላ ቀን አሸጋግሮታል !!
ሰላማዊ እረፍት ለግፍ ሰለባዎች !
ለውድ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን !
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ