>
5:33 pm - Friday December 5, 5264

የጭንጋፉ ብአዴን መወገድ ለአማራ ሕዝብ ህልውና ወሳኝ ነው (ከይኄይስ እውነቱ)

የጭንጋፉ ብአዴን መወገድ ለአማራ ሕዝብ ህልውና ወሳኝ ነው

 

ከይኄይስ እውነቱ


ኢሕአዴግ ከሚባል የሠላሳ ዘመን አዛባ፣ ‹ሰው› ያውም ኢትዮጵያን የሚታደግ ሰው ይወጣል ብለን ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት የፈጸምነው ታላቅ ስህተት አገራችንንና ሕዝቧን በውዱ እያስከፈለን ነው፡፡ ሥጋቱ አገር ወደ ማሳጣት ጥግ እየገፋንም ይገኛል፡፡ አንዳንዶቻችን ሳይዘገይ በማለዳው የባነን ቢሆንም ጅምላው ግን ተጠራርጎ በመወሰዱና አድርባይነቱም ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሥር በመስደዱ የማይመለስ የሰው ሕይወት፣ የማይጠገን ዘረፈ-ብዙ ጥፋት በሕዝባችን በተለይም በአማራው ማኅበረሰብ እና በአገራችን ላይ  ደርሷል፡፡ ከአዛባ የሚወጣው ትል እንደሆነ አጥተነው አልነበረም፡፡ መንፈሳዊነቱ ድርቅ ቢመታውም የሃይማኖት አገር ስለሆነች ለተአምር ዕድል እንስጠው ብለን እንጂ፡፡ የአዋልደ ኢሕአዴግ (ኦነግንና ሌሎች የጐሣ ድርጅቶችን ጨምሮ) አመለካከት (ጐሠኛነትና መንደርተኛነት እስከ ሕጋዊ መሠረቱና መዋቅሩ) – በገዢ አሳብነቱ – ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር ካልተወገደ ኢትዮጵያና ሕዝቧ ዕረፍት ያገኛሉ ማለት ዘበት ነው፡፡ 

ይህንን በመግቢያነት ካነሣሁ፣ በእኔ እምነት በሕይወት የመኖር ህልውና የተነፈገው እና ደኅንነቱ ዋስትና ያጣው የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ከብት ጋጣ የተከለለ ግዛት/ድንበር የለውም፡፡ ስማቸውን ሰይጣን ይጥራውና ወያኔና ወራሹ የኦሕዴድ አገዛዝ በበገሩት የአትድረሱብን አጥር ወገኖቼ! ‹‹የአማራ ክልል›› ብሎ መጥራቱ እንዴት ይቀፋል! እንዴት ያስቀይማል! አስጸያፊ ነው፡፡ ይህ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይሠራል፡፡ አገራችን በታሪክ ህልው ከሆነችበት ዘመን ጀምሮ የኖርነው መላው የኢትዮጵያ ግዛት የሕዝቧ ሁሉ ርስት÷ ምድር ብለን ነውና፡፡ ላንድ ነገድ/ጐሣ አጽመ ርስት ተደርጎ የተሰጠ ግዛት የለም፡፡ ኢትዮጵያዊ መንግሥት ሲኖረን የጋራ ጥቅምን መሠረት አድርጎ ለአስተዳደር አመቺ የሆኑ ግዛቶች ክፍፍል ይኖረናል፡፡

በቁሙ ስለሞተው ድርጅትና አባላቱ ከዚህ ቀደም የሚሰማኝን ደጋግሜ ጽፌአለሁ፡፡ (https://www.ethioreference.com/archives/21180)

የግፍ ጽዋው ሞልቶ ተትረፍርፎ የፈሰሰበትን የአማራ ሕዝብ እንኳን በድኑ ብአዴን የትኛውም ድርጅት ወክሎት፣ ጥብቅና ቆሞለት አያውቅም፡፡ ዛሬ የዘር ፍጅት እየተፈጸመበት ባለው ሕዝብ ስም በአገር ውስጥና በውጭ ‹የተደራጁ› ስብስቦች እንዳሉ እንሰማለን፡፡ ምን እየሠሩ እንደሆነ ግን አላውቅም፡፡ ባርነት የባሕርይው የሆነው ብአዴን ቀድሞም ለወያኔ አሁን ደግሞ ለኦሕዴድ አድሮ የጌቶቹን ተልእኮ እየፈጸመና እያስፈጸመ ይገኛል፡፡ ስለዚህ ጭንጋፍ ድርጅት በአባላቱ (የላይ፣ የታች አመራር፣ ተራ አባላት እያልን) መካከል ልዩነት ማበጀት በሕዝቡ መሳለቅ ነው፡፡ አገርንና ሕዝብን የሚበድል ድርጅት/ቡድን አባል መሆኑ በራሱ ይቅርታ የሌለው በደል ነው፡፡ የከርሣሞች ስብስብ በመሆኑ እንጂ የወንድነት ተግባር ለመፈጸመ ጥቂት ቆራጦች ብቻ ነበር የሚያስፈልጉት፡፡ ይህ አባባል ተመሳሳይ ዓላማ ላላቸው ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ይሠራል፡፡ 

የቅድሚያው ተግባር ጭንጋፉን ድርጅት ማስወገድና የሕዝቡን የመኖር ህልውና ማረጋገጥ ነው፡፡ በሕይወት ለመኖር የሚደረግ ትግል ደግሞ ሰላማዊና የትጥቅ የሚል ምርጫ የለውም፡፡ ቀጣዩ ትግላችን የኢትዮጵያን ህልውናና አንድነት በዘረኝነትና በሽብር አደጋ ላይ ከጣለውና በራስ ወዳዱ ዐቢይ (selfish beast) ከሚመራው የተረኞች አፓርታይዳዊ አገዛዝ ጋር ይሆናል፡፡

አገር የሚኖረን እኮ ሕዝብ በሕይወት የመኖር ዋስትና ሲኖረው ነው፡፡ ጎበዝ! ለአገር መሳሳት ለሕዝባችን መሳሳት ማለት አይደለም እንዴ?

የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመባቸው ስላሉ የአማራ ወገኖቻችን ምን እንበል? እኔ በግሌ ከየትኛውም ድርጅት መግለጫ መስማት አልፈልግም፡፡ የከረመውን እልቂት እየዘነጋን በአዲሱ እየተንጫጫን እስከ መቼ እንዘልቃለን? በተግባር ያልታገዘ ሐዘንና ከንፈር መጠጣም የት ያደርሰናል? ወገኖቻችንን እያስጨረስን በነፍስ ይማር ማለፍና መርሳትም እስከሚበቃን ተለማመድነው፡፡ እኔ በበኩሌ ሕያው ነኝ ብዬ በራሴ ከማፍር በስተቀር አንደበት የለኝም፡፡ የቀረውን ሕዝብ ህልውና ከታደግን፣ የተፈናቀሉትንም ካቋቋምን በኋላ ሐዘን እንቀመጣለን፤ እንደ አልባሌ በግሬደር ተዝቀው ባንድ ጉድጓድ የተጣሉትንና በየጫካው ተበትነው የቀሩትን ለሰው ልጅ አስከሬን በሚገባ ክብር እናሳርፋቸዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Filed in: Amharic