>
5:26 pm - Tuesday September 15, 3063

የግብጽ ትምክህትና ኢትዮጵያ! ደረጀ መላኩ (የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የግብጽ ትምክህትና ኢትዮጵያ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail,com

 


መንደርደሪያ

ከጥንት እስከ ዛሬው ዘመን ድረስ ግብጽ የሚሊተሪ ክንዷን( ሃይሏኝ ለኢትዮጵያ ማሳየቷ በታሪክ የተመሰከረ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለተደጋጋሚ ግዜ የዒትዮጵያን ክንድ መጋቷ ደግሞ ለግብጽ ጎምዛዛ የሆነ የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ ስለሆነም ግብጽ ያላትን የጦር ሀይል ዘመናዊነት ለኢትዮጵያ ማሳየቷ አዲስ ነገር የለውም፡፡ ግብጽ ዛሬ የምታደርገው ትንኮሳም ሆነ ሃኬተኝነት ችግርን ከመጋበዝ ውጪ መፍትሔ አያመጣም የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እጆቻቸውን ወደ ሰማይ ይዘረጋሉ፡፡ ( ያነሳሉ)

ቅድመ ፍረጃ ያለፈውን ለመገምገም ግራ ያጋባል፣ አሁን ያለውን ችግር ለማወቅ ያስቸግራል፣ወደፊት ለማየት አያሥችልም፡፡

እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( ነብስ ይማር)፣ ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ ወዘተ ወዘተ የተባበረችው አሜሪካ ኢትዮጵያን ስትራቴጂክ ወዳጅ ሀገር ማድረግ እንዳለባት የሚያሳዩ በርካታ የጥናት ወረቀቶችን ማቅረባቸውን አስታውሳለሁ፡፡ በተለይም በአለም ባንክ ከ30 አመታት በላይ በአማካሪነት ያገለገሉት ኢትዮጵያዊው የምጣኔ ሀብት ጠበብት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በቅርቡ ባስነበቡት የጥናት ጽሁፍ አዲሱ የባይደን አስተዳደር (Biden Administration) የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ወዳጅ እንዲሆን ምሁራዊ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

በነገራችን ላይ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ እና ከላይ. የተጠቀሱት ምሁራን እንደሚስማሙበት ከሆነ አለም አቀፉ ህብረተሰብ ኢትዮጵያን ስትራቴጂክ ወዳጅ ሀገር አድርጎ መውሰድ ያለበት በሚከተሉት ምክንያቶች ይመስለኛል፡፡

  1. ዋነኛውና የመጀመሪያው ምክንያት ኢትዮጵያ በአሜሪካ የፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ  ሰጪዎች ድምዳሜ መሰረት የመረጋጋት ምሰሶ (a pillar of stability. ) በመሆኗ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተባበሩት የሰላም አስከባሪ ሀይል እና በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጥላ ስር ሆና በዳርፉር ሱዳን፣ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ግዛት ውስጥ ሁነኛ የሰላም ማስከበር ስራ አከናውናለች፡፡ በኮሪያ የባህረ ሰላጤ ከተባበረችው አሜሪካ ጎንለጎን በመቆም ሰላም አስከብራለች፡፡ የዝነኛው የቃኘው ሻለቃ ተጋድሎ በወርቅ ቀለም ተጽፎ የተቀመጠ አንጸባራቂ ታሪክ ነው፡፡ የክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ሻለቃ ኦርኬስትራ ቡድን አባላት፣ የቃኘው ሻለቃ እና ሩቅ ምስራቅ ሳለሁ የሚባሉት ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎች የኢትዮጵያን ውለታና ተጋድሎ የሚስታውሱ ናቸው፡፡ በኮንጎ ካታንጋ ግዛት የተገንጣይ ቡድን መሪ የነበሩት አመጸኛው ሚስትር ቾምቤን ለመቅጣት ከተባበሩት መንግስታት ጦር ጋር በመጣመር የኢትዮጵያ ወታደሮች ሰላም ለማስከበር ዘምተው ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ በጸረአሻባሪ ጦርነት የተባበረችው አሜሪካ ስትራቴጂክ ወይም ጥብቅ አጋር ሀገር ናት፡፡ በተባበረችው አሜሪካ የሚኖሩ በብዙ መቶሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለአሜሪካ የምጣኔ ሀብት እድገት የራሳቸውን ድርሻ የሚወጡ ከመሆናቸው ባሻግር አፍሪካንና አሜሪካን እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገናኙ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያን ማግለል ወይም ገሸሽ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራቷን፣ ክብሯን፣ ሉአላዊነቷን፣ ብሔራዊ ጸጥታዋን አስከብራ የቆየች ሀገር በመሆኗ ነው፡፡ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ፣ ሉአላዊነት፣ ብሔራዊ ጸጥታዋ ቢጠበቅ ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ ጥቅም እንጅ ጉዳት የለውም፡፡ ጉዳት አለው ከተባለም ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ብቻ ነው፡፡

የተዳከመች፣ polarized,፣ የተበታተነች፣ ደሃ፣ በቴክኖሎጂ እጅግ ወደ ኋላ የቀረች ኢትዮጵያ የምእራባውያን ዴሞክራሲ ፍልስፍና ፍላጎት አይመስለኝም፡፡ በተቃራኒው አንድነቷ የጠበቀ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በነጻነት የሚኖርባት ኢትዮጵያ፣ ራሷን የቻለች ኢትዮጵያ፣ እና ሰላሟ እና ጸጥታዋ የተጠበቅ ኢትዮጵያ ለምእራባውያን ስትራቴጂክ ወዳጅነት በእጅጉ የምትመች ናት ብዬ አስባለሁ፡፡

በዚህ ምክንያት በሀገራት መሃከል ያለው የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መሰረቱ በጋራ መከባበር፣በእኩልነት አቀባበል ላይ የተመሰረተ፣ parity አንደኛው ሀገር በሌላኛው ሀገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የማይገባበት መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ቻርትር መሰረት መሆኑን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡

  1. ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የበርካታ አለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ ምክንያት በአለም አቀፉ ህብረተሰብ መደገፍ አለባት
  2. ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ በመለጠቅ በአፍሪካ አህጉር ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት ሀገር ናት፡፡ በስለ ህዝብ ተጠባቢዎች ጥናት ውጤት ከሆነ 98 ፐርሰንቱ የኢትዮጵያ ህዝብ እድሜው ከ65 አመት እድሜ በታች ሲሆን፣አብዛኛው ህዝቧ ወጣት ነው፡፡ 40 ፐርሰንቱ የኢትዮጵያ ህዝብ አድሜው ከ15 አመት በታች ነው፡፡ ስለሆነም ይህ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ለአሜሪካ ምዋለንዋይ አፍሳሾች እንደ ካፒታል አሴት የሚቆጠር ነው፡፡
  3. ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ከመሆኗ ባሻግር፣ የሶስቱ ዋናዋና ሃይማኖቶች ማለትም ክርስቲያን፣ኢስላም፣ እና ይሁዳ መገኛ ናት፡፡ Ethiopia is among the origins of humankind. It is home to the three major faiths of this planet–Christianity, Islam and Judaism.  

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ህዝብ የተደበላለቀ በመሆኑ ምክንያት የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማግኘት እድሉ አለ ( ከተጠቀምንበት ማለቴ ነው)፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናትተከባብሮ ይኖር የነበረበት ሚስጥርም ይሄው ነው፡፡ ስለሆነም አክራሪ ብሔርተኞችም ሆኑ በኢትዮጵያ ጥፋት ትርፍ ለማግኘት የሚያሰሉ የቅርብም ሆነ የሩው ሃይሎች የኢትዮጵያን ህዝብ ብህሃነት በመጠቀም፣ በመከፋፈል ወደ ጦርነት ለዶሉት አይገባም፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ ልዩነት እንደ ጌጥ መቁጠሩ አይከፋም፡፡

  1. ምንም እንኳን የኮቪዲ ቫይረስ በሽታ አደጋ ከፊቷ ቢጋረጥም፣ በትግራይ ክልል አንዳንድ አከባቢዎች ጦርነት እንዳለ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ቢነገርም፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና በወለጋ አካባቢ ብሔር ተኮር ግድያዎች ቢፈጸምም የኢትዮጵን ልማት በተለይም የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ለማሰናከል የቋመጡ ሀይሎች በተለይም ግብጽ የሚሳካላት አይመስለኝም፡፡

በነገራችን ላይ በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ የገበያ ማእከል ህዝባዊት ቻይና፣ቱርክ፣ፓኪስታን፣አውሮፓውያን፣ የተባበረችው አሜሪካ፣ እና ሌሎች የካምፓኒ እና አምራች ድርጅቶች በገበያ ፉክክር ላይ እንደሚገኙ መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ይህም ብቻ አይመስለኝም ከመቼውም ግዜ በላይ የሀገር ውስጥ የግል ባለወረቶች የፋብሪካ ግንባታ እየተስፋፋ ስለመሆኑ ከመገናኛ ብዙሃን ( በተለይም ከመንግስት የዜና አውታሮች ) ይሰማል፡፡

  1. ሰላም እና መረጋጋት በኢትዮጵያ የሚሰፍን ከሆነ፣ የግለሰብ ነጻነት  የሚከበር ከሆነ ለልማት እንደ ሁነኛ ግብአት ይቆጠራል፡፡

የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ የሀገሪቱን እርሻ ዘመናዊ ማድረግ፣ የተሻሉ መኖሪያ ቤቶች መገንባት፣ ለኢትዮጵያ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ቀንጦት ሳይሆን፣ የመኖር ያለመኖር ጥያቄ መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከሁለት አመት በፊት እንደተነበዩት ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማእከል ትሆናለች ብለው ነበር፡፡ ወይም በአፍሪካ የኢንዱስትሪ ማእከል ፊተአውራሪ ትሆናለች የሚል ትንበያ አቅርበው ነበር፡፡ በእኔ በኩል ይህ የተጋነነ ትንበያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሀገሪቱ  ወደ የላቀ የኢኮኖሚ እድገት ለመሸጋገር ከፍተኛ አቅም አላት፡፡

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ ያለው የንግድ እና የኢንቨስትመንት መስፋፋት እድል፣ ለምእራባውያንና ለተባበረችው አሜሪካ አሜሪካ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል፡፡ ምእራባውያን ባለወረቶች በኢትዮጵያ መዋእለንዋይ ማፍሰስ ከቻሉ፣ በሌሎች የአፍሪካ ክፍሎችም ካምፓኒዎች ሊከፍቱ ይችላሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ምእራባውያን ተወዳዳሪ የሚሆኑት  በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጥጠር መጋቢት 2021 የአፍሪካ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር ከ1.3 ቢሊዮን በላይ እንደ ደረሰ የስነህዝብ ጠበብት ካደረጉት ጥናት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ቁጥርን ብቻ አያሳይም፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ አምራችና ሸማቾችን ያሳያል ባይ ነኝ፡፡ አፍሪካ ትልቅ አቅም ያላት አህጉር ናት፡፡ እንደ ዶክተር አክሎግና ዶክተር በፍቃዱ በቀለን የመሰሉ ስመጥር የምጣኔ ሀብት ጠበብት በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ በአፍሪካ በመጪዎቹ አስር አመታት ከፍተኛ የንግድ ወድድር እንደሚኖር ይገመታል፡፡ ስለሆነም ምእራባውያንም ሆኑ የተባበረችው አሜሪካ ልክ ቻይና እንደምታደርገው  የአፍሪካ ሀገራትን በሚጠቅም መልኩ መዋእለ ንዋያቸውን ማስፋፋት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

ይህን ካሰፈርኩ ዘንድ፣ እስቲ አሁን አሳሳቢ ስለሆነው የአፍሪካው ቀንድ እና የሰሜን አፍረካ የጂኦፖለቲካል ችግር በተመለከተ አጭር የግል አስተያየቴን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በቅርቡ ሱዳንና ግብጽ የሚያደርጉትን የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብር የአስተያየቴ መነሻ ይሆናል፡፡

በታሪክ እንደተጠቀሰው ግብጽ ምንግዜም ቢሆን የሚሊተሪ ጡንቻዋን ለኢትዮጵያ ከማሳየት ተቆጥባ አታውቅም፡፡ ስለሆነም አሁን የሚታየው እውነታ አዲስ አይደለም፡፡ አሁን ግብጽ የምታሳየው ማስፈራሪያ በችግር እንደታጀለች የሚያሳይ ነው፡፡

ምን ተፈጠረ ?

ሀ. እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 6 2020 የኢትዮጵያን የሰሜን ድንበር ከሃያ አመታት በላይ ሲጠብቅ የነበረው የኢትዮጵያ ወታደር፣  የትግራይ ገበሬን እህል አጨዳ ሲያግዝ በነበረው የሰሜን እዝ ጦር ላይ የትግራይ ነጻ አውጪ ወታደሮችና ሚሊሻዎች ጥቃት በመሰንዘራቸው ጦርነት ሊቀሰቀስ ቻለ፡፡ ይህ በውጤቱ ለሱዳን መልካም አጋጣሚ ፈጠረላት፡፡ ይህን ተከትሎ ሱዳን በሰሜን ጎንደር በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር መሃከል የሚገኝን ሰፊ እና ለም መሬት በወረራ ያዘች፡፡ እንደ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ  ከሆነ የሱዳን ወታደሮች በቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚገመት ኢትዮጵያዊ የእርሻ ባለይዞታዎችን ንብረቶች ዘርፈዋል፡፡ ወይም አውድመዋል፡፡

ለ. እንደ አለም አቀፉ ጋዜጣ ፎሪያን ፖሊሲ ሜጋዚን( Foreign Policy Magazine )የምርመራ ዘገባ ከሆነ የሱዳን ወታደራዊ ሀይል በግብጽና በሌሎች በኢትዮጵያ ላይ ክፉ በሚያስቡ ሀገራት ይደገፋል፡፡  ሱዳን በተሳሳተ የቅኝ ገዢዎች መረጃ ተነሳስታ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ማንሳቷ ትክክል ነው፡፡ እንዲሁም ታሪካዊ መረጃ አላት በማለት ለሚደግፉት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ስርግና ምላሽ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የኢትዮጵያ ዜጎች በየጊዜው የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጠው እርሻ ያርሰሉ፣ የሱዳንን ሉአላዊ ግዛት ጥሰዋል በማለት በየጊዜው የሚያሰሙት የሀሰት ትርክት ፍጹም ስህተትና ክህደት ነው፡፡ የዝነኛው የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ የሙዚቃ አቀንቃኝ የነበረው አመለሸጋው ጋሼ ተፈራ ካሳ ( አፈሩን ገለባ ያድርግለት) በዛ ጥኡምና ለስላሳ ድምጹ፤-

የራሷን የማትሰጥ፣ የሰው የማትነካ፤

ኢትዮጵያ መሆኗን አልተረዱም ለካ፡፡

በማለት አዚሞ እንዳለፈው ኢትዮጵያ በታሪኳ የሰው ሀገር ድንበር ደፍራ ወይም ነጥቃ አታውቅም፡፡ የራሷን ድንበር ግን ለመድፈር የመጡ ታሪካዊ ጠላቶቿን አሳፍራ የመለሰች ባለታሪክ ሀገር ነበረች፡፡ ነበር ልበል ዛሬ የሱዳንና ግብጽ መዘባበቻ በመሆኗ፡፡ ( ለግዜውም ቢሆን የኢትዮጵያን መሬት ተቆጣጥረዋል፡፡)

ሐ. ከወያኔ አገዛዝ በቀር፣በተከታታይ ለዘመናት የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት ሱዳን ይገባኛል የምትለውን መሬት ( በአረብ መገናኛ ብዙሃን አጠራር አል-ፋሽካ ይሰኛል ) the Arab media call “Al-Fashqa (አልተቀበሉም ነበር፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም ያለው ይመስለኛል፡፡ አል-ፋሽካ ከ100 ስኩዌር ማይልስ ስፋት እንዳለው ይነገራል፡፡“Al-Fashqa  has  a land mass that is more than 100 square miles

ሆኖም ግን ይሁንና ይህ በአረብኛ ቋንቋ ስያሜ የተሰጠው ባለሶስት አንግል እጅግ ለም መሬት የታሪክን እውነት በምንም አይነት መልኩ ሊለውጠው አይቻለውም፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ የአካባቢው ነባር መጠሪያዎች፣ ማለትም በረከተ ለጉዲኢን፣ በትክክለኛው አጠራር ሁመራ (Bereket Legudi in Humera proper, )፣ሴናር( Senar )፣ ባህረሰላም (Bahire-Selam )፣ አቦተር Abotir ፣ እና ኮርደም ሆር በምእራብ ሁመራ and Koredem Hor in Western Humera …ሁሉም በኢትዮጵያ ጎንደር የሚገኙ ግዛቶች ነው፡፡ ሱዳን የቦታዎችን ስሞች በአረብኛ ቋንቋ ስያሜ የምትሰጠው፣ ለቦታዎቹ ህጋዊነት ለመስጠትና፣ ቦታውን አረባዊ ለማድረግ አስባ ነው፡፡ አውነታው ይሄው ነው፡፡ አሁን ሱዳን በወረራ የያዘችው መሬት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ገበሬዎች ለዘመናት የኖሩበትና ኑሮአቸውን የሚገፉበት ቦታ ነበር፡፡

እንደ ብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ስጋት እና ምርምር ከሆነ ሱዳን ሰፋ ያለ አላማ ይዛ ነው የተነሳቸው፡፡ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የማይታይና እውነት ላይመስል ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ሱዳን እጅግ ድብቅና ጥልቀት ባለው ሁኔታ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ነገ ተነገወዲያ የታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ በሚገነባበት የቤኒሻንጉል ግዛት በኩል በሚያዋስናት ድንበር ላይ የግዛት ጥያቄ ስለአለማንሳቷ ምንም መተማመኛ የለንም፡፡ የሱዳን ተጠቂ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት 100 አመታት በዲፕሎማቲክ ሰላማዊ ተጋድሎ በሁለቱ ሀገራት መሃከል ያለውን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት ከባድ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት የደረሰባትን ጥቃት አስመልክታ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይገባታል፡፡

መ.ለብዙ ወራቶች ግብጽና ሱዳን ለካርቱም ቅርብ በሆነ የጦር ሰፈር፣ የጦር ልምምድ ሲያደርጉ እንደነበር ከመገናኛ ብዙሃን የተሰማ መራር ሀቅ ነው፡፡ በቀይ ባህር አካባቢ የተባበረችው አሜሪካ እና ሩሲያ የጦር መርከባቸውን ማስጠጋታቸው ሌላው ስጋት ነበር፡፡

ያነጣጠሩት፣ በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ላይ ነው

አንዳንድ የአፍሪካው ቀንድ ፖለቲካ ተንታኞች በደረሱበት ጥናት እና ድምዳሜ መሰረት ሱዳን የተባበሩት ምግስታት እና የአፍሪካ ህብረትን ቻርተር በመጣስ የኢትዮጵያን ሉኣላዊ ድንበር በመድፈር የኢትዮጵያን መሬት የወረረችው በዋነኛነት ምክንያቱ ከታላቁ የአባይ ወንዝ ግንባታ እና ወደ ግድቡ በሚገባው የውሃ ሙሌት የግዜ ሰሌዳ ላይ የሚደረገው የሦስትዮሽ ውይይት ወይም ንግግር (በኢትዮጵያ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የውሃ ኤክስፐርቶች ) መሃከል አሁን ድረስ ሁነኛ ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ በአጭሩ ሱዳንና በተለይም ግብጽ በብዙ መልኩ እጅግ ብዙ ርቀት ተጉዘው በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማቲክ ጫና በማሳደር የታላቁን የአባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ባለመቻላቸው ይመስለኛል፡፡ ( ቢያንስ አሁን ድረስ አልሆነላቸውም፡፡) በነገራችን ላይ ሱዳን ከጀርባዋ ግብጽ እና የአረቡ ረቢጣ ማህበር እንዳሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡

ከዚህ ባሻግር ሱዳን ገቢራዊ እያደረገች ያለችው የግብጽን ፖሊሲ ነው፡፡ ይህም ማለት የግብጽ ፖሊሲ ኢትዮጵያ ወደ ታላቁ የአባይ ግድብ፣ ሁለተኛውን የውሃ ሙሊት በአሰበችው የግዜ ሰሌዳ ገቢራዊ እንዳታደርግ የሚያነጣጥር ነው፡፡ ( ወይም ሰትራቴጂካሊ ታቅዶና ታልሞ የወጣ የግብጽ ፖሊሲ ነው)

ሠ. የአረብ ሀገራት መገናኛ ብዙሃን በስህተትና በውሸት በታጀለ ዜናዎቻቸው ሱዳን በአማራ ክልል ልዩ የጦር ሀይል አባላት፣ በአካባቢ ሚሊሻዎችና በሌሎች ታጣቂዎች ተጠቃች፣ጉዳት ደረሰባት ብለው ወሬውን መናኘታቸው ስህተት ይመስለኛል፡፡ የመገጣጠም ሁኔታ ይሁን በሌላ ምክንያት አላውቅም የሌሎች አረብ ሀገራት ይህንኑ በአለም አቀፍ ሚዲያ ቀርበው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ አለም በሸፍጥ የተሞላች ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የኢትዮጵያን ምስል በአለም ላይ ለማጠልሸት ካደረገው የስም ማጥፋት ዘመቻ ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሱዳን በሃይል የያዘችውን የኢትዮጵያ መሬት ህጋዊነት ያስገኝልናል በሚል ምክንያት ተነሳስታ አንዳንድ የኢትዮጵያን ከፍተኛ ባለስልጣናት ስም በማንሳት አሁን የያዝነው መሬት የሱዳን ሉኣላዊ ግዛት እንደሆነ ተስማምተዋል የሚል አምደምታ ያለውን መረጃ በመገናኛ ብዙሃን አመሃኝነት አስተጋብታ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሱዳን በመገናኛ ብዙሃን አመኃኝነት ላቀረበችው የቃል መረጃ ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ምላሽ ስለመኖሩ የሰማሁት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ሱዳን ላቀረበችው ፕሮፓጋንዳ ስማቸው የተነሳው የቀድሞው ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለስልጣን ምላሽ መስጠት የነበረባቸው ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ በሱዳን የተወረረው የኢትዮጵያ የድንበር ግዛት ክልላዊ ወይም የአማራ ክልል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ሉአላዊ ግዛት የደፈረ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚጎዳ ጠብ ጫሪነት ነው፡፡ አፋጣኝ መፍትሄ ካተሰጠውም ውሎ አድሮ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍለን መሆኑን በተለይ ወጣቱ ትውልድ መገንዘብ ለበት ይመስለኛል፡፡

annexation of Ethiopian territory is not a regional or Amhara matter. It is a violation of Ethiopia’s sovereignty that affects all Ethiopians.

ረ. እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር መጋቢት 2 ቀን 2021 ግብጽና ሱዳን ወታደራ ስምምነት መፈራረማቸወን የሚያወሱ ዜናዎች በታወቁ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል፡፡ የሱዳን እና ግብጽም የዜና አውታሮችም ቢሆኑ ወሬውን ናኝተውት ነበር፡፡ ከሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ስምምነት ጀርባ የነበረው ስትራቴጂ ምን ነበር ? የትኛዋን ሀገር ለማጥቃት የተወጠነ ነበር ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ  መልሱ ግልጽ በመሆኑ በእኔ በኩል የምለው የለኝም፡፡ አንባቢው ግን በየአካባቢው እንዲወያይበት ስጋብዝ በአክብሮት ነው፡፡

በነገራችን ላይ እንደ አንዳንድ የፖለቲካ ጥናት አዋቂዎች የምርምር ጽሁፍ ውጤት ከሆነ፣ በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ግንባታ ዙሪያ የሚደረገው የዲፕሎማቲክ ውይይት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ከደረጉት መሃከል በርካታ ሀገራት እጃቸውን ሊዶሉበት የሚፈለግ ውይይት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ለአብነት ያህል ግብጽና ሱዳን የተለያዩ ስልቶችን በመከተል የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ለማሰናከል በጉዳዩ ብዙ ሀገራት ጣልቃ እንዲገቡ ( በአደራዳሪነት ወይም በሸምጋይነት ስም ማለቴ ነው) ለማድረግ የማይቆፍሩት ጉድጓድ፣ የማይምሱት ስር፣ የማይበጥሱት ቅጠል የለም፡፡

ለአብነት ያህል የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት the UN Security Council ፣ የተባበረችው አሜሪካ መንግስት the US Department of the Treasury ( በኢትዮጵያ ተቀባይነት አላገኘም ነበር)፣ የአለም ባንክ the World Bank እና የአፍሪካ ህብረት African Union በግልግሉ ውስጥ እንዲገቡ ግፊት አድርገው ነበር፡፡ በቅርቡ ደግሞ ግብጽ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበረችው አሜሪካ እና የአለም ባንክ በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ዙሪያ ሶስቱ ሀገራት የገቡበትን እሰጥ አግባ እንዲዳኙ የዲፕሎማቲክ ዘመቻ መጀመሯ የታወቀ ነው፡፡ ይህ የግብጽ አጉል የዲፕሎማቲክ ዘመቻ ግን የአፍሪካን ህብረት ሚነሳ የሚያኮስስ ነው፡፡ ይህ የግብጽ እብሪት አፍሪካውያን የአፍሪካን ችግር መፍታት አይችሉም የሚል አምድምታ ያለው ነው፡፡ ይህ የዘረኝነት አስተሳሰብ ስለሆነ ጥቁር አፍሪካውያን ሁሉ ሊሞግቱት ይገባዋል የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡

This call diminishes the status of the African Union. It says that Africans cannot resolve an African matter on their own. This is patently prejudicial and must be rejected by Black Africa

በነገራችን ላይ እንደ አለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ጠበብት የጥናት ውጤት ከሆነ በአለም ላይ ካሉት ድንበር ተሻጋረ ወንዞች ሁሉ በተፋሰሱ 11 ሀገራት ስምምነት አልተደረሰበትም፡፡ በአጭሩ የናይል( የጥቁር አባይ ወንዝና ነጭ አባይ ወንዝ ውህድ)  አጠቃቀሙን በተመለከተ ወይም በሌሎች ጉዳዮች ላይ 11ዱ የተፋሰሱ ሀገራት የደረሱበት ህጋዊ ስምምነት የለም፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው ግብጽ የሁለትዮሽ ወይም የሶስትዮሽ ስምምነት እንዲደረግ ስትገፋፋ ነው፡፡ ይህ የግብጽ የስምምነት ፍላጎት ደግሞ ከናይል ወንዝ የውሃ መጠን ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ለመቀራመት የታሰበና የተሰላ ነበር፡፡ ገቢራዊም አድረገውት አሁን ድረስ ዘልቀዋል፡፡ ማንም አለከለከላቸውም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ 86ቱን ፐርሰንት የናይል ወንዝ ውሃ መጠን የምታዋጣው ኢትዮጵያ በቂ የሃይል ምንጭ ለማመንጨት ሰትል የታላቁን የአባይ ወንዝ ግድብ ለመገንባት መነሷ ሉኣላዊ መብቷ ነው፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት የአባይ ገባር ወንዞችን በመገደብ የመስኖ እርሻ ማስፋፋት ተፈጥሮአዊ መብቷ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም ግብጽ የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ለማስተዳደር ይፈቀድልኝ በማለት በየግዜው የድርድር ሃሳብ ለማድረግ መነሳቷ አግባብነት የለውም፡፡ በሌላ በኩል ግብጽ የታላቁን የአባይ ግድብ ግንባታ አስተዳደር ለቆጣጠር ማለቷ ከባድ ድርቅ በሚከሰትበት መጥፎ ግዜ ኢትዮጵያ ከግድቡ ውሃ እንዲፈስ በማድረግ ለግብጽና ሱዳን ለማድረስ ግዴታ ውስጥ ሊያስገባት ይችላል የሚል የግል አስተያየት የሚሰነዝሩ ምሁራን አሉ፡፡ ይህ ለውጤታማ ድርድር በር የሚከፍት አይመስለኝም፡፡ ይህ የግብጽ ሃሳብና ፖሊሲ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጻረር፣116 ሚሊዮን ህዝቧን ጥቅም በእጅጉ የሚጎደሳ ኋላቀርና የስገብግብነት ባህሪ የተጠናወተው ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ ግብጽ እንደምታደርገው ሁሉ፡-

  • የውሃ ፍላጎቷን
  • የሃይል ፍጆታዋን እና
  • የምግብ ፍላጎቷን ለማሟላት መብት አላት፡፡

ከ65ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ገና የኤሌክትሪክ ሃይል ማግኘት አልቻለም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ 100 ፐርሰንት የሚጠጋው የግብጽ ህዝብ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ነው፡፡ሌላም አመክንዮም ማስፈር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ በመገንባቷ ምክንያት የናይል ወንዝ አጠቃላይ የውሃ መጠነ እንደማይቀንስ የውሃ መሃንዲሶች በጥናታቸው ደርሰውበታል፡፡ ዋናውና ተጨባጩ ምክንያት ግን የናይል ወንዝ ውሃን በእኩልነት ለመጠቀም መስማማቱ ላይ ነው፡፡ የላይኛው የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት፣ የታችኞቹን የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ጥቅም ሳይነኩ በግዛታቸው በሚገኝ ወንዝ ላይ ልማት አልምተው የህዝባቸውን ህይወት ማሻሻል ይችላሉ፡፡ ይህ እውነት ወይም መርህ በተባበሩት መንግስታት ስለድንበር አቋራጭ የአለም ወንዞች በተመለከተ ሀገራት የደረሱበት ስምምነት የሚደግፈው ነው፡፡

. This principle is a corner stone of UN transboundary water conventions, treaties, and practices that govern all other major rivers

በርካታ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ምሁራን በተለያዩ ጽፎቻቸው ላይ እንደጠቀሱት ከሆነ ባለፉት በርካታ ወራቶች ግብጽ የመረጃ ልውውጥ እና ወታደራዊ ትብብር በማድረግ ኢትዮጵያ ላይ የሁለትዮሽ የጦርነት ጨዋታ ከፍተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለማዳከምና አቅመቢስ ሀገር ለማድረግ ሴራቸው ውስብስብና ሰፊ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የግብጽ ወታደራዊ አዛዦች፣ የመረጃና ደህንነት ሰዎች፣ የዲፕሎማቲክ መሪዎች መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የሀሰት ወሬ በመንዛት እውነት በማስመሰል ወሬውን ለአለም ይናኙታል፣ የጦርነት ነጋሪትም ይጎስማሉ፡፡በእነኚህና በሌሎች ምክንያቶች ጉልበት ያገኘችው ሱዳን ጌዜው አሁን ነው በማለት ነበር የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቃ በመግባት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በእብሪት የደፈረችው፡፡ ሁለቱ ሀገራት ( ሱዳንና ግብጽ) ወታደራዊ ስምምነት በሚፈራረሙበት ግዜ ሱዳናዊው ጄኔራል ሞሃመድ ኦትማንአል-ሁሴን ለግብጽ አቻቸው በዚህ አስቸጋሪ ግዜ በደግነትና በጠንካራ የወንድማማችነት ስሜት ለረዱን የግብጽ ወንድሞቻችን እናመሰግናለን ሲሉ ነበር ወዳጅነታቸውን የገለጹት፡፡

At the signing ceremony of the defense pact, Sudanese General Mohamed Othman Al-Hussein, Chief of staff said, “We thank our brothers from the Egyptian armed forces for their good intentions, generous assistance and their strong support to overcome the present difficulties.

በነገራችን ላይ ግብጽና እንደ አንድ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ትራጄዲክ የሙዚቃ ቅንብር ፣ ተናባው፣ አብረው አጥንተው ነው የሚሰሩት፡፡

ከተለያዩ የአለም መገናኛ ብዙሃን እንደተሰማው የግብጹ ጄኔራል ሞሃመድ ፋሪድ ሄጋዚ , General Mohammed Farid Hegazy በሁለቱ ሀገራት መሃከል ለሚደረገው የሚሊተሪ እና ጸጥታ ኦፕሬሽን በተመለከተ ዘለግ ላሉ ሰአታት ከሱዳን የጦር አታሺዎች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ እንደተናገሩት ከሆነ ሁለቱም ሀገራት በወታደራዊ ስለላ፣ ወታደራዊ እርዳታ እና ስልጠና ላይ ለመተባበር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህም ማለት ግብጽና ሱዳን በታላቁ የአባይ ግድብ ግንባታ ላይ ያላቸው የጸጥታ አቋም ተመሳሳይ ነው፣ እንዲሁም፣ ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት  መውረሯ በግብጽ ስለመደገፉ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡

ከግብጹ ጄኔራል ንግግር በመነሳት ኢትዮጵያውያን መገንዘብና ማወቅ ያለባቸው ቁምነገር ቢኖር ኢትዮጵያን በቀጥታ ለማጥቃት ወይም ስጋት ላይ ለመጣል ሁለቱም ሀገራት አብረው መነሳታቸውን ነው፡፡ ሁለቱም ሀገራት ለሚገጥማቸው ማናቸውም ድንገተኛ ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች እንደደረሱበት ከሆነ ግብጽ ሱዳን ለምታቀርበው ማናቸውም የእርዳታ ጥያቄዎች ለመመለስ ቆርጣ ተነስታለች፡፡ ለአብነት ያህል፡-

  • ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ
  • የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ
  • የቴክኒክ እርዳታዎችን መስጠት
  • የጋራ ድንበር ሰላም ለመጠበቅና በመሳሰሉት ጉዳዮች ለመተባበር ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

ይህ መላምት ወይም ወፍዘራሽ መረጃ አይደለም፡፡ ይህ እውነትነት ያለው በመሬት ላይ የሚታይ መራርና ጎምዛዛ ሀቅ ነው፡፡ ግብጽና ሱዳን ያደረጉት ወታደራዊ ስምምነት ለኢትዮጵያ አደገኛ ሊጋብዝ የሚችል የማንቂያ ደውል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ምን ማድረግ ይጠበቅባታል ?

ሀ. ኢትዮጵያ አሁን ይዛ የተነሳችውን የውሃ አጠቃቀም ፖሊሲ አጥብቃ መቀጠል አለባት፡፡( በተለይም የናይልን ወንዝ ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት እኩል መጠቀም አለባቸው ከሚለው ፖሊሲ በፍጹም ወደኋላ ማፈግፈግ ያለባት አይመስለኝም)

ለ. ኢትዮጵያውያን ሁሉ በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ላይ ያላቸው ብሔራዊ አቋም አንድ አይነት መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ አለፉት አመታት ሁሉ ኢትዮጵያውያን የገንዘብና እውቀታቸውን እንዲያፈሱ ግዜው ግድ ይላል፡፡

ሐ. የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት የአካባቢውን የጂኦፖለቲካ ሁኔታ በተመለከተ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብና ለኢትዮጵያ ህዝብ  የሚሰጠው መረጃ ግልጽና በእውነት ላይ እንዲሁም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

መ. በመጨረሻም ግብጽ ተሸናፊ ትሆናለች፡፡ ለምን ? ምክንያቱም ግብጽ ኢትዮጵያን በወታደራዊ ሀይል በወረረች ማግስት ፣ኢትዮጵያ በመላው ሀገሪቱ የመስኖ እና የሃይል ማመንጫ ግድቦችን መገንባት አለባት፡፡ ይህ ለግብጾች አንድ ግልጽ መልእክትን የሚያስተላልፍ ይመስለኛል፡፡ ይህም ጠብ ጫሪነት ሲስፋፋ፣ የንግግር በሮች ሲዘጉ መልካም እድሎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ነው፡፡

ሠ. በእኔ የግል አስተያየት ቢያንስ አሁን ድረስ የፌዴራል መንግስቱ በዲፕሎማቲክ ተጋድሎና በህዝብ ግንኙነት ስራ ቢያንስ አሁን ድረስ የተሳካለት አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው የወያኔ ደጋፊዎች፣ ግብጽና ሱዳን በአለም አቀፉ መድረኮች ላይ ተሰሚነት ያገኙት ( የያዙት አቋም ምን እንደሆነ ይታወቃል፣ እውነት እነርሱ ጋር የለችም፡፡ ሆኖም ግን ሸፍጥ ተጠቅመው ሀሰትን እውነት አስመስለው አቅረበዋል፡፡ ውጤትም አግኝተውበታል፡፡) ይህን ተከትሎ አለም አቀፉን ህብረተሰብ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በማግኘቱ፣ ተበዳይ ኢትዮጵያን እንደበዳይ በማየት መግለጫ እስከማውጣት ደርሷል፡፡አለም ወረተኛ ስለሆነች ለግዜው ገንዘብ እና አጭበርባሪዎቿን መስማቷ ግድ ነው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያን ለሚወዱ የዲፕሎማቲክ እውቀት ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን ጥሪውን በማድረግ ኢትዮጵያን መታደግ ታሪካዊ ግዴታው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በእውነቱ ለመናገር ከተማ ይፍሩ፣ ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ብርሃኑ ድንቄ፣ ኮሎኔል ብርሃኑ ባዩ፣ ኮሎኔል ጎሱ ወልዴ፣ ዶክተር ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ፕሮፌሰር አሻግሬ ይግለጡ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ዶክተር ልጅ አስራተ ካሳ፣ ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ ወዘተ ወዘተ የመሳሰሉ ታላላቅ ዲፕሎማቶች እና የፖለቲካል ሳይንስ ሳይንቲስቶችን አምጣ ወልዳ፣ ኋላም ከአፈርገፊው አፍ ነጥቃ በማስተማር  ያፈራች ሀገር ዛሬ እንዘጭ እሞቦጭ ብላ መውደቋ ሲታሰብ በእውነቱ ልብን ያደማል፣ህሊናን ያቆስላል፣ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

ረ. ይህ የግል አስተያየቴ ነው ( ይህን ጽሁፍ ለማንበብ ጊዜ ያገኙ የፌዴራል መንግስቱ መሪዎች፣ ወይም በፕሬስ አታሺዎቻቸው አማኝነት መረጃውን ካገኙ ማለቴ ነው) መልእክቱ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ወይም ምክትል ሚንስትር ነው፡፡) በሁለቱ ታላላቅ ባለስልጣኖች የተመራ የዲፕሎማቲክ ልኡካን ቡድን አባላት በዋሽንግተን ዲሲ፣ ብራስልስና ሌሎች የታወቁ ከተሞች በመጓዝ የኢትዮጵያን አቋም በተመለከተ ከአቻ መሪዎች ጋር ቢወያዩ መልካም ነው፡፡

ሰ. በታላላቅ ከተሞች የተመደቡ የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ሰዎች የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ በታወቁ አለም መገናኛ ብዙሃን( ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ቢቢሲ፣ስፑትኒክ ወዘተ) በመቅረብ ወይም ግብዣ ሲደረግላቸው ለአለም  ህብረተሰብ ቢያስረዱ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ይመስለኛል፡፡

ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ምን ይጠበቃል ?አለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረግ ያለበት ምን ይሆን ?

ሀ. የብይነ መንግስታቱ ማህበርና የአፍሪካ ህብረት ወደለየለት ጦርነት ሊፈነዳ የተቃረበውን ግጭት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለስ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር ሱዳን ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣ መጠየቅ አለባቸው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡

ለ. ኢትዮጵያ እና ሱዳን ወደ 1000 ማይል  እርቀት ያለውን የጋራ ድንበራቸውን ጊዜ ገድበው በባለሙያዎች እንዲሰመር ማድረግ ለሰላም በር የሚከፍት ነው፡፡

 የብይነ መንግስታቱ ማህበር እና የአፍሪካው ህብረት ግብጽና ሱዳን የጦርነት ፉከራቸውን ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የውክልና ጦርነት ለመከፍት የሚየደርጉትን የፖለቲካ ሴራ እንዲያቆሙ ማሰጠንቀቅ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

መ.  የብይነ መንግስታቱ ማህበር፣የተባበረችው አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ባይገቡ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የእነርሱ ሚና መሆን ያለበት የአፍሪካው ህብረት የሚያደርገውን የሽምግልና ሂደት መርዳት ነው፡፡

የአፍሪካ ህብረት አመራር አስጣጡን በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ በታላቁ የአባይ ወንዝ ግድብ ዙሪያ የሚካሄደውን የሶስቱን ሀገራት ድረድር ደረጃ ከፍ በማድረግ ሁሉም የናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት የሚካፈሉበት አንድ ታላቅ አህጉር አቀፍ ኮንፍረንስ ቢዘጋጅ፣ የናይል ወንዘን እንዴት በእኩል ደረጃ መጠቀም ይቻላል ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ የጠበብት መልስ ሊገኝለት ይቻለዋል፡፡ 

   ረ.  የብይነ መንግስታቱ ማህበር፣የተባበረችው አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት፣ ግብጽ በኢትዮጵያ ሰላም እንዳይሰፍን የምትጎነጉነውን ሴራ እንድታቆም በብርቱ መጠየቅ አለባቸው፡፡

ሰ. የተባበረችው አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት፣የአፍሪካው ህብረት፣ በዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር በሆኑት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪ አመሃኝነት በታላቁን አባይ ወንዝ ግድብ ዙሪያ ሶስቱን ሀገራት ለመሸምገል የሚያደርጉትን ሙከራ መርዳት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አሜሪካም ሆነች የአውሮፓው ህብረት በቴክኒክ አኳያ እርዳታቸው እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡

ሸ. የተባበረችው አሜሪካ፣የአውሮፓው ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በሚዳፈር መልኩ ኢትዮጵያ ወደ ስምምነት እንድትገባ የሚያሳድሩትን ጫና ማንሳት አለባቸው፡፡ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ለህዝብ የተሻለ ኑሮ መሻሻል የሚለውን መርህ መከተል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡.

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከሁለት አቅጣጫዎች ጫና እየደረሰባት እንዳለ ይሰማኛል፡፡ (የምእራባውያን ዲሞክራሲ ጫና እና የሱዳን እና ግብጽ ወታደራዊ ትብብር) ስለሆነም ኢትዮጵያ ከመቼውም ግዜ በላይ እየተፈታተናት የሚገኘውን የውስጥ አንድነቷን በፍጥነት ማስጠበቅ አለባት ብዬ አስባለሁ፡፡ በሀገር ውስጥ የሚቀፈቀፉ አለመረጋጋቶች ነሰለጠነ መንገድ መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቋንቋና ብሔር መሰረት ላይ የተንጠለጠለውን የፌዴራል ስርአት በተመለከተ ቁጭ ብለው በሰከነ መንፈስ መነጋገር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ ለሚከሰቱ ግጭቶች ዋነኛው ምክንያት ጎሳ ተኮር ፖለቲካ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት መንፈስ የተሻለ ኑሮ እንዳይኖሩ ደንቃራም የሆነ ነው፡፡

አቤቱ አምላኬ ሆይ የኢትዮጵያን ክፉ አታሳየን!

 

Filed in: Amharic