>
5:26 pm - Thursday September 17, 0865

የኦሮሚያ ብልፅግና ናቡከደነጾሮች...!! (ሔቨን ዮሐንስ)

የኦሮሚያ ብልፅግና ናቡከደነጾሮች…!!

ሔቨን ዮሐንስ

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል የሆነውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ የብዙዎች ኢትዮጵያዊ ልብ የተሰበረበት እንዲሁም ዜጎች በመንግስት ተስፋ የቆረጡበት ነገር ተፈጥሮ ነበር። መንግስት ዋና ስራው በቅድሚያ የዜጎቹን ደህንነት ማስጠበቅ ቢሆንም ቅሉ ግን ንፁሃን በአሰቃቂ ግድያ ሲጨፈጨፋ ተመልክተናል አዝነናል። የሆነው ሆኖ ይህ ችግር የሚፈታው በፓለቲከኞች ድርድር ስለሆነ ፓለቲከኞች ቁጭ ብለው እየተነጋገሩ መሆኑን ሰምተናል። ይህ ጥሩ ጅምር ነው ነገር ግን ያወሩትን እያፈረሱ ህዝብ የሚጨርሱ ፓለቲከኞች አደብ የሚገዙበት ነገር መፈጠር አለበት። ዛሬ የኦሮሚያና የአማራ ክልል አመራሮች የጋራ ልማትና ሰላም ላይ በአዲስ አበባ ላይ እየመከሩ መሆናቸውን ስሰማ ይበል ብየ ለጠቅላላ ትውስታም ቢሆን የትናንት ታሪክ አስቼ የተሰማኝን እነሆ:-
አስራ ሰባት ዓመት ኢትዮጵያን አንቀጥቅጠው የገዙት ሌተና ኮሎኔል #መንግሥቱ ኃ/ማርያም አልፎ አልፎ በየምሽቱ የአንዳንድ ኢትዮጵያውያንን ቤት ይጎበኙ እንደነበር ይነገራል፡፡ የኮሎምቢያው ደራሲና በሥነ ፅሁፍ የኖቤል ተሸላሚ #ማርከስ_ጋርሺያ እንዲህ ይሉ ነበር “አምባገነኖች ከሞቱ በኃላ እንኳን #የፓለቲካ_ሞት ይሞታሉ” እንዳሉት እኛ አገር የስጋ ሞት ብቻ ሳይሆን የፓለቲካ ሞት የሞቱ እነ መለስን ስንጠቅስ፣ ሌ/ ኮ/ል መንግስቱም የፖለቲካ ሞት እንደ ሞቱ ይገመታል። የዛሬዎቹ ደግሞ ከትናንቶቹ አልማር ብለው ገና በጥንስሱ የፓለቲካ ሞት በቁመናቸው የሞቱ አንዳንድ #የኦሮሚያ_ብልፅግና ሀላፊዎችን እያየን ነው!
ጻዕረ መለኮታቸው እየተመላለሰ የሚያቃቸውን ሰው ሁሉ ይበጠብጣል፡፡ የደረቅ ሌሊት ጋኔን ተመስሎ ይመጣል፡፡ ይመላለሳል፡፡ <<እንደመሰሳለን- በጠላቶቻችን መቃብር ላይ ሕዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባለች- እናሸንፋለን>> የሚለው <<የጓድ>> መንግስቱ መፈክርና ማስፈራራት ሌሊት ሌሊት እየመጣ እነ እንቶኔን ሲያባንናቸው ከእንቅልፋቸው እየባነኑ ቀን ቀን እየቃዡ በእየ መድረኩ፣ በእየ ሚዲያው የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎች፣ የደርግ ርዝራዥ እያሉ ሲያወግዙ ይታዩ ነበር፡፡ እነ እንቶኔ እንደዛ የሚሉት ሌ/ኮ መንግስቱን በደንብ ስለሚያውቋቸው ነው። ጓድ መንግስቱ ደግሞ የሚሉትን የሚያደርጉ የተግባር ሰው ናቸው፡፡
<<መቃብራቸው ላይ…>> ሲሉ መቃብሩ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች አዘጋጅተው ነው፡፡ በነገራችን ላይ በእግራቸው የተተኩትም የተግባር ሰው በመሆናቸውና፣ በጥርስ አነካከስ ይልቁንም ከበድ ያለ እርምጃ በመውሰድ እረገድ አይተናነሱም፡፡ የቃልም የተግባርም ሰውነታቸው እዚያ ላይ ይመሳሰላል፡፡ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ እንደሚነግሩን #አጤ_ልብነ_ድንግል ግዛት ሰፍቶላቸው፣ ጠላት ጠፍቶላቸውና ሰላም ሰፍኖላቸው ሲኖሩ የማይበገሩ- የማይቀመሱ መስሎአቸው <<ጦር አውርድ>> እያሉ ይቁነጠነጡ ጀመር፡፡ የእብሪተኞች አዋራጅ የሆነው አምላክ ተቆጣና አህመድ ግራኝን አስነሳባቸው፡፡ ግራኝ አህመድም ገስግሶ እስከ ቤተ መንግስታቸው ሄዶ አንገታቸውን ቆርጦ መንግስታቸውን አፈረሰው ይባላል፡፡
ይህን ሳስብ የባቢሎኑ ንጉሥ #ናቡክድነጾር ሰባት ዓመት ሙሉ እንደከብት ሳር መብላቱንም አጤናለሁ! ናቡክድነጾር ይህ የሆነበት ትዕቢት፣ ክፋት እና ካለ እኔ ማን አለ የሚለው እብሪቱ ነው! እብሪት፣ ጉራ-፣ ይሉኝታ ማጣትና ድንፋታ ምንኛ አደገኛ እንደሆኑ አለመረዳት ራሱ ክፉ ደዌ ነው! አንድ እንግሊዛዊ ጸሐፊ #pride_Goes_Before_A_fall በሚል ርዕስ ጹሐፍ ጉራና እብሪት ሳይውል ሳያድር ትንሽ ሙቀት የሚገላምጠው ክምር በረዶ መሆኑን የሚገልጥ የዘላለም ማስታወሻ ትቶልናል፡፡ እናም እኛም በዚች አጭር ጊዜ የተመለከትነው ይህንን ነው! ሁሉ የእኛ የሚሉ እና ለሰው ልጆች ቅንጣት የማይራሩ፣ ለአገር የማያስቡ በእብሪት፣ በጉራ፣ በይሉኝታ ማጣትና በክፋት የተለከፉ አንዳንድ #የኦሮሞ_ብልፅግና #ናቡክደነጾሮችን ፓለቲከኞች እና ደጋፊዎች ነው!
እናም ይህ ክፉ ደዌ የመታቸው ፓለቲከኞችን የምመክረው የእንግሊዛዊ ጸሐፊ ሀሳብ በማንሳት ነው! “ጉራ እና እብሪት ሳይውል ሳያድር ትንሽ ሙቀት የሚገላምጠው ነው” እንዳለው ጉራና እብሪት ለማንም አይጠቅምም፤ የሚጠቅመው ጥበብ እና ብልሃት ማስተዋል ነው። ስለዚህ ጥበብ የራቀው ብልሃት የጎደለው እንዲሁም ህዝብ የጠላ መሪነት ከታሪክ ተወቃሽነት ባለፈም እድሜ የለውምና አንዳንድ #የኦሮሚያ_ብልፅግና_ናበክደነጾሮች ለራሳችሁ ስትሉ አስቡ፤ ስራችሁን ፈትሹ!
Filed in: Amharic