>
5:13 pm - Tuesday April 19, 8687

ከ’አቃፊ’ ወደ ጨፍጫፊ? (አሰፋ ታረቀኝ)

ከ’አቃፊ’ ወደ ጨፍጫፊ?

አሰፋ ታረቀኝ


ለፉት ሦሥት አመታት ውስጥ፣ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድና በተዋረድ ባሉ ባለሥልጣኞች፣ ስለ ኦሮሞ አቃፊነት ሳይነግሩን ያለፉበትን ጊዜ አላስታውስም። በስልሳና በሰባወቹ የዕድሜ ክልል ለምንገኝ ዜጎች፣ስለኦሮሞ ማንነት ህዋህት ኮትኩቶ ካሳደጋቸው ካድሬዎች ሊነገረን ባይገባም፣ ጊዜው ነውና ተቀብለናል፡፡ጥያቄው፣ አባመላ ሀብቴን፣ ባልቻ አባነፍሶን፣ራስ አበበ አረጋይን፣ በቅርቡም፣ ጀኔራል ረጋሳ ጂማን፣ ጀኔራል መርዕድ ንጉሤንና ጀኔራል ደምሴ ቡልቶን የመሳሰሉ ጀግኞችን ለኢትዮጵያ ያበረከተው የኦሮሞ ጎሳ በምን የተነሳ ነው እነሽመልስ አብዲሳን በመሳሰሉ ድኩማን እጅ የወደቀው?በወለጋ ከተፈጸመው ዕልቂት በህይወት ተርፈው ወሎ ከገቡት መካከል በአምባሰል ወረዳ፣ ጃሪ የጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የቀረበው ተጠያቂ የሰጠውን ቃለ ምልልስ፣ ላዳመጠ ሰው፣የኦሮሞ ሽማግሌዎች የት ገቡ? በባድማቸው ላይ የሚፈሰው የእናቶች፣ የህጻናትና አዛውንቶች ደም የሚያጠራቅመው መዘዝ አልታያቸውምን? ያሰኛል፡፡ ቃለ መጠይቁን በትክክል ላዳመጠ ሰው ወለጋ ውስጥ እየተሰራ ያለው የጭካኔ ጣራ ‘አማራ’ ተብሎ የተሰየመውን ብቻ ሳይሆን ሁሉን የህብረተሰብ ከፍል የሚያሰጋ ነው፡፡ተጠያቂው እንድህ ሲል ጀመረ ”ወላጆቸ ወደ ወለጋ የሄዱት በንጉሱ ጊዜ ነው፡፡ ተወልጄ ያደግሁት ወለጋ ነው፡፡ ኦሮሙኛንና አማርኛን አቀላጥፌ እናገራለሁ፡፡ ህዝቡን እየጨረሱ ያሉት በመንግሥት የታጠቁትና ልዩ ሀይል የሚባሉት ናቸው፤ የሚገርመ አባገዳወቹም የሚሉን ልቀቁና ውጡ ነው፤ በርኅራሄ ዐይኑ የሚያየን አጣን” ነበር ያለው፡፡ ይኸ እየሆነ ያለው፣ በጀግኞቿ መስዋዕትነት ነጻነቷን አስከብራ በኖረችው፣ ከዚሁ የነጻነት ክብር የትነሳ ከአህጉሩ የመጀመሪዋ የተመድ አባል በሆነችው፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራችና መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ሣያስገድድ በፍቅር፣ ሣያንገላታ በክብር ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ የቅኝ ገዥወችን ቅስም የሰበረን መሪ፣ በሉተራን ት/ቤት ተኮትኩተው ያደጉ የወለጋ “ምሁራን” አጼ ሚኒልክን ቅኝ ገዥ፣ አማራውን ወራሪ አድርገው ሲስሉ ፊት ለፊት የገጠማቸው አልነበረም፡፡ ከኢትዮጵያ መሬት በተገኙ “ምሁራን” አማካይነት አጼ ሚኒልክ ሲወነጀል መስማት ደግሞ ለነጮቹ ያልታሰበ ሲሳይ ነበር፡፡

የዚህ በቅጥፈት ላይ የተመሠረት ተረትና ወንጀለኛ ትርክት አመንጭወች አሁንም በህይወት አሉ፡፡ ኦነጎች ያረሱትን ህዋህት አለሰለሰና  ዘራበት፤ የኦሮሞ መሬትም፣ በቀለ ገርባን፣ ጁሀር ሙሃመድን የመሳሰሉ የአዶልፍ ሂትለር መንፈስ የተጸናወታቸው ሰወችን አፈራች፡፡ ሁሉቱ ወደ እሥር ቤት ቢጋዙም የሁሉንም ድርሻ የመሸፈን አቅም ያለው ሽመልስ አብድሳ ባስታጠቀው ጦር “ነፍጠኛን” እያስፈጀ “ኦነግ ሸኔ” ነው ይለናል፡፡

ከሂትለር አነሳስ ጀምሮ ጀርመን ውስጥ ለ Universal News Services እና ለ CBS የዜና አውታሮች ይሠራ የነበረው ጋዜጥኛ William L. Shirer ‘ The rise and fall of the Third Reich በተባለው መጽሐፉ ውስጥ የዘረኝነትን ጠንቅ አበጥሮ አስቀምጦታል፣ 1245 ገጽ ከሚሸፍነው መጽሐፍ ውስጥ ካለንበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰሉትን ሦሥት መስመሮች ብቻ ልጥቀስ “ – There was nothing hidden, of course, about the laws which Hitler decreed against the Jews or about government- sponsored persecution of these hapless people. The so-called Nuremburg Laws September 15, 1935, deprived the Jews of German citizenship, confining them to the status of ‘subjects.” P233.

ክላይ በተጠቀሰው ቀንና አመት፟ምህረት ሂትለር ያጸደቀውን ህገ፟-መንግሥት አንድም አይሁዳዊ የመቃወም ቀርቶ የመሳተፍ መብት አልነበረውም፡፡ ህዋህትም የጫካ ፕሮግራሙን አምጥቶ ህገ-መንግሥት አሰኝቶ ሲያጸድቅ፣ አንድም የአማራ ድርጅት አልተወከለም፤ አድራጊ ፈጣሪዎቹ ህዋህትና ኦነግ ነበሩ፣ በህዋት በጠላትነት፣ በኦነግ በወራሪነት የተፈረጀው አማርኛ ተናጋሪው ህብረተሰብ በፕሮፓጋንዳ የታገዘ የጥቃት ኢላማ የሆነ ወዳውኑ ነበር፡፡ ህዋህት ኦነግን ለማፍዘዝ አማራን ቁጥር አንድ ጠላት አድርጎ ቢያቀርብለትም፣ ከራሱ በስተቀር ማንም ወዳጅ አልነበረውምና ኦነግን የመረጋጊያ ጊዜ ሳይሰጥ ወደ አምስት ትንንሽ ክፍልፋይ ሸነሸነው፡፡ የተፍጥሮ እድገቱን ጨረሰና ህዋህትም ተሰናበተ፡፡ ተበታትኖም ቢሆን ኦነግ በህይወት አለ፡፡ አይሁዶች ከምዕተ አመታት በላይ በኖሩባት ጀርመን ሁሉንም የመብት አይነት እንደተነፈጉት ሁሉ፣ “ኦሮሚያ’ ተብሎ በተሰየመው ክልል ውስጥ የሚኖረው “አማራ” እንደ አውሬ እየታደነ ሲርቅ በጥይት ሲቀርብ በስለት መታረድ ዕጣው ሆኗል፡፡ ከሞት የተረፉት የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ነው ይሉናል፤ ሜዲያውና መንግሥት ኦንግ ሼኔ ነው ይለናል፡፡ የገዳዮቹ ስም መቀያየር ለሟቾቹ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ እየሞቱ ያሉት በገዛ ሀገራቸው፤ እየተገደሉ ያሉት በኦሮሙኛ ተናጋሪዎችና ‘ኦሮሚያ’ ተብሎ በተሰየመው የሀገሪቱ ክፍል ነው፡፡የሩቁን ትተን ባለፉት ሦሥት አመታት ለተደረጉት እጂግ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች፤ የ ‘ኦሮሚያው’ ፕሬዚዳንት የተነፈሰው ነገር የለም፡፡ ዝምታው ሁለት መልዕክት አለው፤ ወይ እሱ ፕሬዚዳንት ይደለም፣ ወይ ግድያው ተገቢና ትክክል ነው ብሎ ተቀብሎታል:፡ 

ኦነግ ሼኔ ሽፍታ ነው፣ ሰላም አደፍራሽ ነው እሚባለውን እንቀበል፤ ኦነግ ሼኔ በፒካፕ መኪና መሳሪያና የሰው ሐይል እያጓጓዘ ሲዋጋ/ሸዋሮቢትን፣ ርቄን፣ ከሚሴንና ኤፍራታን ያስታዉሷል/ የአቶ ሽመልስ አብዲሳ ልዩ ሐይል የት ነበር? በወለጋ በተለያዩ ወረዳዎች ከተፈጸመው ዕልቂት የተረፉት ምስክርነት የሚያሳየውና እየሆነ ያለው፣ እንደ ሂትለር አዋጅ  በአደባባይ አይነገር እንጂ፣ “አማራውን” ከ “ኦሮሚያ” መሬት ለማጽዳት በውስጥ መመሪያ የተደገፈ ተግባር አስመስሎታል፡፡ ምናልባትም ነገሩ እየበረታ ከሄዴ፣ “ነፍጠኛ እንጂ ሰው አልገደልንም” ሊሉንም ይችላሉ፤ “ቱቲሲ እንጅ ሰው አልገደልንም” አደል ሁቱዎች ያሉት፡፡ ተወልጀ ባደግሁበ ሀገር፤ የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርስ ሁኔታ ሲፈጠር፣ ታላላቅ የሀገር ሽማግሌዎች መልካ ላይ ወርደው ይቀመጣሉ፡፡ ሽማግሌዎች መልካ ላይ ተቀምጠዋል ከተባለ፣ በአጎራባች የሚኖረው ህዝብ ምክንያቱን ሳይረዳ ወደ በቱ አይገባም፡፡ ተወካዮች ልኮ ምክንያቱን ይጠይቃል፡፡ መልካ ላይ የተቀመጡት ሽማግሌዎች፣ አካባቢውን ሊያናጋ የሚችል የዘረፋ፣ የግዲያ ወይም የሰውን እጮኛ ጠልፎ የመውሰድ እቅድ እንዳለ መርጃ እንደደረሳቸው አሳውቀው ጉዳዩ መፍትሄ ሳያግኝ ከተቀመጡበት እንደማይነሱ ያሳውቃሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ እንዳይበርዳቸው ልብሱ እንዳይርባተው ጉርሱ ይቀርብላቸዋል፡፡ ጉዳዩ ተበጥሮ ለህብረተሰቡ ከተገልጠ በኋላ ጥፋቱን አቅዶ የነበረው ሽማግሌዎች የወሰኑበትን ቅጣት ይቀበላል፡፡ ሽማግሌዎችም ህዝቡን መርቀው ይነሳሉ፡፡ 

ሀገራቸው በንጹሀን ደም፣ ያውም በህጻናትና በእናቶች ስትጨቀይ፣ የኦሮሞ አባገዳዎች የት ነው ያሉት? እየሆነ ያለውን አልሰሙም? ወይስ አረመኔዎቹን መርቀው ልከዋቸዋል? አባገዳዎች ልጆቻቸውን “ በመሬታችን ላይ ግፍ አትሥሩ” ማለት አይችሉም? 

ሂትለር አይሁዶችን ሲጨፈጭፍ በዙሪያው ለነበሩት ህዝቦችና መንግሥታት በዚያው የሚያቆም መስሏቸው ነበር፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጅ ሁሉም ኢላማ ውስጥ ነበሩ፣ አልቀረም ሁሉም ተፈጁ፡፡ እንደጀመረ ቢያስቆሙት ኖሮ ያሁሉ የሰው ልጆች ሰቆቃ ይቀንስ ነበር፡፡ የ“አማራውን” እልቂት ዛሬ ጉራጌው፣ ከምባታው፣ ሀዲያው፣ ወላይታው፣ ሶማሌውና አፋሩ ተጯጩሆ ካላስቆመው፣በሚቀጥለው ተራው የሱ ነው፡፡ አቶ ሽመልስ አብዲሳ የ “አማራውን” በህዋህትና በሱዳን ጦር ፍልሚያ ተወጥሮ መያዙን እንደ ትልቅ ዕድል የቆጠረው ይምስላል፡፡ የ”አማራው” ልዩ ሀይል ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ሲታደግ፣ የአቶ ሽመልስ ልዩ ሐይል ሲያርስ የዋልን ገበሬ፣ ባሏን በማገዝ በጉልጓሎ ተጠምዳ የዋለች ደሀ እናት፣ከእናቱ ጡት ላይ በቂ ወተት ለማግኘት የሚታገልን ሕጻን ያለ ርኅራሄ መፍጀትን ተያይዞታል፡፡ ለአቶ ሽመልስ እየሞተ ያለው ሰው አይደለም፡፡ ነፍጠኛ ነው፡፡ አቶ ሽመልስ፣ “ኦሮሚያን” እየነዱ ባሉበት ጎዳና ላይ ከእርሰወ ችሎታ በእጅጉ የተራቀቀ ዕውቀት የነበራቸው “ሾፌሮች” ነድተውበት ሁሉም አቀዱት ሳይደርሱ ገደል ገብተው ቀርተዋል፡፡ አንዳንዶቹንም ራሰዎ ምስክር ነወት፡፡

ዛሬ በሥልጣኑ ጫፍ ላይ ያላችሁት ከመወለዳችሁ በፊት እንዳቅማችን የኦሮሞን ታሪክ ከምንጩ ያነበብን በህይወት አለን፡፡ ስለ ታላቅ ህዝብነቱ ሊነገረን አይገባም፤ ስለምናውቀው፡፡ አቃፊ ብላችሁ በአንደበታችሁ አውጃችሁ በእናንተ እኩይና አረመኔያዊ ድርጊት፣ ከአቃፊነት የጨፍጫፊነት ሥዕል እያላበሳችሁት ነው፡፡ ዕብሪት መጥፎናት፤ መጨረሻ ላይ የምታፈነዳው ያሳበጠችውን ነው፡

Filed in: Amharic