ሽልማቱ…!!!
በእውቀቱ ስዩም
በቀደም ሰይፉ ላይ የሰማሁት ዜና እንዲህ ይላል” የናይጀርያ ዜግነት ያላቸው ሌቦች አዲሳባ ገብተዋል” ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋራ ልምድ ልውውጥ ለማድረግ መሆን አለበት!
ሌብነት ሲነሳ የሚከተሉት አስተካዥ ገጠመኞች ትዝ ይሉኛል፤
ሰውየው የበግ ነጋዴ ናቸው፤ ወደ ገበያ ሲሄዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ እንደተለመደው አንድ ማለዳ ገንዘባቸውን ከፍየል የቆለጥ ማቀፍያ ቆዳ የተሰራች ትንሽየ ቦርሳ ውስጥ ጠቀጠቁት፤ ከዚያ ቦርሳውን እንደ ቡዳ መዳኒት አንገታቸው ላይ አንጠለጠሉት ፤ በላዩ ላይ ግድንግድ የድሮ ቢትልስ ለበሱበት፤ በዚያ ላይ ካሽሚር ጃኬት በጃኬቱ ላይ ጋቢ፥ በጋቢው ላይ ደግሞ መለስተኛ ቤተሰብ ማስጠለል እሚችል ካፖርት ደረቡበት፤ ከዚህ ሁሉ ጥንቃቄ በሁዋላ ገበያ ውለው ሲወጡ እጃቸውን ወደ አንገታቸው ሲሰዱ ቦርሳው አምልጡዋል ፤
ቤታቸው ገብተው የደንቡን ያክል አልቅሰው ሲያበቁ ወደ ሚስታቸው ዞረው
“ ጉድ እኮ ነው! ይሄን ሁሉ አለባብሼው፥ ሌባው እንዴት አርጎ ወሰደው?” አሉዋቸው’?’
ሚስትዮም እንዲህ መለሱ ፥
“ አንተ ደሞ! ላት ያላት በግ አትሰረርም ያለህ ማነው?”
2
ሸገር ውስጥ “የሌባ ሰፈር ” ነው እየተባለ የሚታማ ሰፈር አለ! እስከ ሰባ አመት ፥በዚህ አለም መቆየት ስለምፈልግ ስሙን አልጠቅሰውም! አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ በሬድዮ ፕሮግራሙ ላይ ስለዚህ ሰፈር ለየት ያለ ቆንጆ ፕሮግራም ሰራ፤ የሰፈሩ ልጆች ሰምተው ፈነጠዙ! “ በስርቆት ብቻ ሲነሳ የነበረ ሰፈራችንን ገፅታ ስለገነባህልን የምስጋና ድግስ አዘጋጅተንልሀል ፤ ሽልማትም ተሰናድቶልሀል” ብለው ጋበዙት፤ እሱም ልቡ በጣም ተነክቶ በዝግጅታቸው ላይ ታደመ፤ መኪናውን ዝግጅቱ ከሚዘጋጅበት አዳራሽ ጀርባ አቆመና ወደ ውስጥ ዘለቀ፤ ድብልቅልቅ ባለ ጭብጨባ ተቀበሉት::
የተለያየ የኪነጥበብ ድግስ ተከታትሎ መቅረብ ጀመረ፤ አንድ ወጣት “ ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ
ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ” የሚል ግጥም አነበበና በቅርቡ ከሚታተመው መድብሌ የተወሰደ ነው ብሎ ከመድረክ ወረደ::
የስነፅሁፍ ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ ምሳ አበሉት፤ ምን ምሳ ብቻ፤ በሹርቤ ብርሌ ጠጅ አቀረቡለት፤ ብርሌውን ሾፍ ሲያደርገው “ ብሄራዊ ሙዝየም “ የሚል ማህተም ተለጥፎበታል፤ በመጨረሻወደ መኪናው ሄደ፤ ባየው ነገር ክው ብሎ ቀረ፤ የመኪናው ሁለት ስፖኪዮ በቦታው የለም፤
የደረሰበትን የነገረኝ ቀን በምን ቃል እንዳፅናናሁት አልረሳም
” ጎማውን ስለማሩልህ እንደ ሽልማት ቁጠረው”