>

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ራዕይ እና ተልዕኮ !

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ራዕይ እና ተልዕኮ !


 

 ራዕይ !
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሃገራችን ኢትዮጵያ ወርድና ስፋት በእየሥልጣን እርከኑ የመንግሥት ስልጣን ምንጭ፣ ባለቤት፣ ተቆጣጣሪ እና ገሪ  እንዲሆን እንሻለን የኢትየጵያ ዜጎች ስብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ የተከበሩበት፣ ለመላ ሕዝቡ ፍላጎት መሟላት በኃላፊነትና በተጠያቂነት መንፈስ የሚሰራ መንግስታዊ አመራር እንዲኖር እናልማለን፡፡ ሕዝቡ በማንነቱ ሳይለያይ በአንድ ሃገር ልጅነት እና በዜግነት የእኩልነት መንፈስ፣ የሃገሩ አንድነት እና ሉዓላዊነት ተጠብቆ ለትውልድ የሚተላልፍበትን ሁኔታ እውን ሁኖ ማየት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገትና የልማት  እንቅስቃሴ ስኬት ቀጣይነት ባለው ጠንካራ እና ከገጠር እስከ ከተማ ድረስ በስፋት በተሳሰረ በውድድር ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት እውን ሆኖ ማየት ነው፡፡ የሃገሪቱ ኢኮኖሜ ሃብት  አምራችና የሥራ ፈጣሪ የሆኑትን ብቻ በማበልፀግ የሚወሰን ሳይሆን፣ የሃገሪቱ ሃብት ማህበራዊ ፍትህን ባረጋገጠ መልኩ የመላ ሃገሪቱን ሕዝብ  የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚውልበት፣ የሃገሪቱ ብልፅግና ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊ እና የባህላዊ ተሃድሶ የሚያካተትበት ሁኔታ እውን ሁኖ ማየት ነው፡፡
ተልዕኮ !
አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ተቀይሮ ሕዝቡ በስፉት ተወያይቶ በሚያፀድቀው ሕገ መንግስት እንዲተካ ማድረግ፣ የሃገሪቱ የመንግስት አወቃቀር ከቋንቋ ወደ ጂኦግራፊያዊ አወቃቀር እንዲለወጥ እንታገላለን፡፡ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገባነት፣ ለፍትህ እና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ ዜጎችን በእኩልነት የሚያይ፣ ለተሻለ ሕይወታቸው የሚተጋ፣ ለሕዝቡ ደህንነት እና ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር ሳይታክት የሚሰራ መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪ የፓለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ነፃ ትክክለኛ እና ግልፅ በሆነ መንገድ የሚወዳደሩበት የምርጫ ስርዓት እንዲገነባ እንታገላለን፡፡
የትምህርት ስርዓቱ ሕዝብን  የሚያራርቅ ሳይሆን የሚያቀራርብ እንዲሆን፣ ዜጎች ለሀገራቸው ታሪክ ፍቅር እንዲኖራቸው፣ የዜግነት ክብርና ኩራት እንዲሠማቸው፣ ሙያዊ ብቃትን እንዲላበሱ፣ በስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑ የሚያስችል እንዲሆን እናደርጋለን፡፡
ለብሄራዊ እንድነት፣ ለሃገር ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ለዘላቂ ልማት የሚያመች ጤናማ ሃገራዊ ምህዳር  እንዲኖር ብሔራዊ እርቅ እንዲደረግ ሁኔታዎችን እንዲመቻቹ እንጥራለን፡፡ በነፃነት የሚያስብና ለመብቱ የሚቆም ሕብረተሰብ መመሰረት፣ የሃገራችን ወጣት ትውልድ ከተስፋ መቁረጥ እና ከባከነ አኗኗር ተላቆ በራሱ እና በሃገሩ የሚኖረውን የኩራት መንፈስ እንዲያዳብር ባለማሳለስ እንሠራለን፡፡ ወጣቱ ትውልድ በሕይወቱ ጥሩ ተስፋ እንዲሰንቅ እና ለከፍተኛ ግብ ራሱን እንዲያነሳሳ መርዳትና እናደፋፍራለን፡፡
Filed in: Amharic