>
5:33 pm - Wednesday December 5, 2260

ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ለአማራ ሕዝብ ያለው አንድምታ...!!! (በለጠ ሞላ  የአብን ሊቀመንበር)

ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ለአማራ ሕዝብ ያለው አንድምታ…!!!

በለጠ ሞላ  የአብን ሊቀመንበር

* «ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ የሕዝባችንን ነገ የመወስን አቅም ያለው መሆኑን በመገንዘብ ካርድ በማውጣት በንቃት መሳተፍ አለበት!»
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ሊቀመንበር አቶ በለጠ ሞላ ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እኛም ለአንባቢያን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ!
1.  ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ለአማራ ሕዝብ ያለው አንድምታ፤
እንደሚታወቀው ከአሁን ቀደም በተደረጉ ምርጫዎች የአማራን ሕዝብ በዚህ ደረጃ ሰፊ ንቅናቄን ፈጥሮና በንቃት አደራጅቶ እንዲሳተፍ በማድረግ በርካታ እጩወችን አስመዝግቦ ለምርጫ ዝግጁ የሆነ ፓርቲ ባለማግኘቱ ለበርካት በደሎች ተዳርጎ ቆይቷል፡፡ አብን ይሄን ክፍተት በመድፈን በሕዝባችን ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ ለመቅረፍ በሃቀኛ የአማራ ልጆች ተመስርቶ ወደ ፖለቲካ መድረኩ ከመጣ ወዲህ የሕዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጠረጴዛ ላይ ቀርበው አጀንዳ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ሕዝባችን ነቅቶና ተደራጅቶ ለዘላቂ ጥቅሙና ፍላጎቶቹ መከበር እንዲታገል በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል፤ በመስራት ላይም እንገኛለን፡፡
ዘንድሮው በሚካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሕዝባችን የምርጫውን ወሳኝነት በመረዳት በንቃት እንዲሳተፍ እየሰራን እንገኛለን፡፡ በመጭው ግንቦት ወር መጨረሻ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ለአማራ ሕዝብ የተለየ ትርጉም ያለውና እጅግ ወሳኝ ነው ብሎ አብን ያምናል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቶች አሉን፡፡ የመጀመሪያው የአማራ ሕዝብ በአማራነቱ ተደራጅቶና ሰፊ ንቅናቄ ፈጥሮ በኃቀኛ ልጆቹ ለመወከል የሚሳተፍበት የመጀመሪያው አማራዊ ምርጫ ይሆናል፡፡ ሁለተኛ የአማራ ሕዝብ ሲፈፀምበት የቆየውንና በአሁኑ ወቅት ተባብሶ የቀጠለውን መዋቅርና ሕግ ሰራሽ ችግሮችን በማስቀጠልና ነፃነትን በመጎናጸፍ መካከል የሚደረግ የሕዝባችንን ነገ የመወስን አቅም ያለው ምርጫ ነው። ሶስተኛ በተለይም ከክልሉ ውጭ ያለው አማራ ለመጀመሪያ ጊዜ በአማራነቱ ተደራጅቶ ፖለቲካዊ ውክልና አግኝቶ ኁሉን አቀፍ መብቶቹንና ጥቅሞቹን ብሎም ዘላቂ ደህንነቱን ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥልበት ነው።
ስለሆነም ሕዝባችን የምርጫ ካርዱን አውጥቶ ነገውንና ዛሬውን በሚወስነው በዚህ ወሳኝ ምርጫ ኃቀኛ ወኪሉን አብንን እንዲመርጥ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ ፓርቲያቸን አብን አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ሕዝባችንን በስፋት በማንቀሳቀስ፣ በማደረጀትና በንቃት በማሳተፍ ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ ያለውና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተመዘገቡ አባላትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን ማፍራት የቻለ ሲሆን የአማራን ሕዝብ የሚወክሉ በርካታ እጩወችንም በማስመዝገብ በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከግንባር ቀደሞቹ መካከል ይገኛል።
2. አብን ከአማራ ሕዝብ ውጭ ስላለው ድጋፍ፤
ፓርቲያችን አብን እንደ አማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታም በሚገባ በመረዳት አጠቃላይ በአገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት እየተሳተፈና ጉልህ አበርክቶ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተለይም አገር ችግር ውስጥ በወደቀችበት ጊዜ ሁሉ ከፖለቲካና ከጥሬ የሥልጣን ፍላጎት በላይ ሕዝብንና አገርን ያስቀደመ እና ለአገራዊ አንድነትንና ብሔራዊ ጥቅማችን የወገነ ቆራጥ ውሳኔ በመወሰን በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሰፊ ድጋፍ እንድናገኝ አስችሎናል። በተጨማሪም የትኛውም ኢትዮጵያዊ ችግር ሲደርስበት ድምጽ በመሆንና የአቅማችንን ድጋፍ በማድረግ የሁሉም ሕዝብ ኃቀኛ ጠበቃ መሆናችንን በተግባር ማሳየት ችለናል፡፡ በዚህም ምክንያት ማኅበራዊ መሰረታችን ከሆነው ከአማራ ሕዝብ ውጭ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና ሰፊ ድጋፍ አለን፡፡ እነዚህን ስኬቶች በመጠቀም በምርጫው በንቃትና በኃላፊነት በመሳተፍ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፊውን የአማራ ሕዝብ በአማራነቱ ለመወከል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥርዓትና ለመገንባት አብን በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡
3. በምርጫው ሂደት ከመንግስት መዋቅር ያጋጠማችሁ ችግር በተመለከተ፤
አብን አገር አቀፍ ፓርቲ በመሆኑ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይም አማራ በብዛት በሚኖርበት እጩዎችን በማቅረብ እንወዳደራለን፡፡ የምንወዳደረው ለአጃቢነት ሳይሆን ለአሸናፊነት በመሆኑ መጠናቸው ቢለያይም የተለያዩ ችግሮች በተለያዩ አካባቢዎች እየገጠሙን ይገኛሉ፡፡ አማራ ክልልና አዲስ አበባ ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ላይ አልፎ አልፎ እንቅፋቶች የሚገጥሙን ቢሆንም እስካሁን ያለው በጎ የሚባል ነው። ችግሮች ሲገጥሙንም ወዲያውኑ ለሚመለከተው አካል እያሳወቅን ፈጣን ምላሽ ማግኘት የምንችልበትን ሁኔታ እየፈጠርን ለመሄድ እየሞከርን ነው። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበቂ ሁኔታ ተንቀሳቅሶ ለመሥራት ፓርቲያችን ተግዳሮት እያጋጠመው በመሆኑ በክልሉ ካለው የአማራ ሕዝብ ብዛት አኳያ በቂ የሚባል ባይሆንም በአንፃራዊነት ጥሩ ሊባል የሚችል የእጩወች ብዛት ማስመዝገብ ችለናል፡፡
በተለየ ሁኔታ ግን በኦሮሚያ ክልል በጣም ሰፊ የሆነ ተግዳሮት እያጋጠመን ይገኛል፡፡ እንደሚታወቀው በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ከ15 ሚሊዮን በላይ አማራ አገሬ ብሎ ይኖራል። ሆኖም ክልሉ ላይ ተንቀሳቅሰን ይሄን ሰፊ ሕዝባችንን ለማደራጀት እና የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት የማያስችል በጣም ሰፊ የሆነ ተግዳሮት ሲያጋጥመን ቆይቷል። በዚህም ሕዝባችን በሚኖርባቸው በአብዛኞቹ የኦሮሚያ አካባቢወች ላይ እጩወችን ማቅረብ አልቻልንም፤ በጣም ውስን በሆኑ አካባቢወች ላይ ብቻ ነው እጩወቻችን ማቅረብ የቻልነው።
የፖለቲካ ሥራወችን ለማከናወን በክልሉ አስቻይ ሁኔታ የለም ሊባል የሚችል ነው። አሁን ላይ እንኳንስ ለምርጫ ስራ ለመንቀሳቀስ ይቅርና አማሮች በማንነታቸው ብቻ እየተለዩ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የሚፈፀምበትና በጅምላ የሚገደሉበት አስከፊ ሁኔታ መኖሩ ዓለም የሚያውቀው እውነታ መሆኑን ወለጋን በማሳያነት ማንሳት ብቻ በቂ ነው፡፡ አብን በአገሪቱ ሕግ ታውቆና ተመዝግቦ በሕጋዊነት እየተንቀሳቀሰ የሚገኝና ከፖለቲካውም ባሻገር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኝ መሆኑ እየታወቀ በኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ በኩል የታየው ሕዝባችንን ከጥቃት ያለመታደግ እና አብንን በተሳሳተ መንገድ የማየትና በሐሰት ስሙን የማጠልሸት አካሄድ በክልሉ ተንቀሳቅሰን ብቁ እጩዎችን በማቅረብ ሕዝባችን ፖለቲካዊ ውክልና እንዳይኖረው ለማድረግ ታስቦ የሚደረግ የሴራ አካሄድ ነው።
አብንን በሐሰት የመወንጀልና ሕዝብን በማንነቱ ከሚጨፈጭፉ የጥፋት አካላት ጋር በአንድ ላይ ስሙን ፓርቲውን በሕዝብ እንዲጠላ የማድረግ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አካሄድ ለጠቅላይ ሚ/ሩ የድጋፍ ሰልፍ በወጡ ደጋፊወቹና በአንዳንድ ከፍተኛ አመራሮቹ ዘንድ ሳይቀር በአደባባይ የተገለፀ ኃቅ ነው። ይህም በምርጫው ሂደት ላይ የከፋ ተግዳሮት ሊፈጥር የሚችልና ተዓማኒነቱንም በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠለሽ፣ አገርና ሕዝብን የሚጎዳ የተሳሳተ የሴራ አካሄድ በመሆኑ ከአሁኑ ሊታረም እንደሚገባና በክልሉ የሚኖረውን አማራ ደኅንነት በመጠበቅ ለምርጫ ውድድር አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡
የአብን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ሰዓት ነው፤ #ሰዓትን_ይምረጡ!
Filed in: Amharic