>
5:26 pm - Monday September 17, 5240

የባንዲራው ጦርነት... !!  (ገነነ መኩሪያ)

የባንዲራው ጦርነት… !! 

ገነነ መኩሪያ

… ድርጊቱ የተከሠተው በጋና አክራ በተዘጋጀው በአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጫወታ ላይ ነው፡፡ 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ከጋና ጋር እየተጫወተች ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን ወደ ጋና ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ በደሎች ሲደርስባቸው ስለነበር በመጥፎ ስሜት ነበር ወደ ሜዳ የገቡት፡፡ በጨዋታው ላይ በጉዳት ምክንያት ያልተሳተፈው “ኢታሎ ቫሳሎ” ክራንቹን እንደያዘ ቤንች ወንበር ላይ ተቀምጧል፡፡ ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያ ባንዲራ ሆን ተብሎ ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል በመደረጉ ተናዶ አምባጓሮ ፈጥሮ እንዲስተካከል ያስደረገው ኢታሎ ነበር፡፡
… ኢታሎ የአስመራ ተወላጅ ሲሆን በወቅቱ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይጫወት ነበር፡፡ ጨዋታው ቀጥሏል፡፡ በዳኛው አድሏዊነት ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ አንድ ጎል ተቆጠረ፡፡ የኢታሎ ንዴት ይበልጥ ናረ! ጎሉ ሲቆጠር በጫወታው ላይ የክብር እንግዳ የነበሩት የጋናው መከላከያ ሚኒስተር ጄነራል በደስታ ስሜት ተውጠው ከመቀመጫቸው ተነስተው ወደ ሜዳው ሲንደረደሩ መጡ፡፡ ኢታሎ ግራ ገብቶት በአይኑ ይከታተላቸው ጀመር፡፡ ጄነራሉ ጎሉ አከባቢ ደርሰው የተሰቀለውን የኢትዮጵያ ባንዲራን ያወርዱት ጀመር! ኢታሎ አይኑን ማመን አቃተው፡፡ ሲንደረደር ተነስቶ በክራንቹ እየተጎተተ ደረሰባቸውና ጄነራሉን በክራንቹ ጀርባቸውን ብሎ አጋደማቸው፡፡ ይህን ያዩ የጋና ፖሊሶችም ኢታሎን ለመያዝ ሲሮጡ መጡ፡፡ ከነርሱም ውስጥ ሁለቱን በክራንቹ ብሎ ጣላቸው፡፡ ፖሊሶቹ በብዛት ሆነው ከበውት ይደበድቡት ጀመር፡፡ ይህን ያዩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችም ሜዳውን ለቀው በመውጣት ከፖሊሶቹ ጋር መደባደብ ጀመሩ!! በቴስታ፣ በእርግጫ፣ በቡጢ… ባገኙት ነገር ሁሉ በመደባደብ ቦታውን የጦር አውድማ አስመሰሉት። ባንዲራችን ነዋ የተነካው! በባንዲራቸው እንዴት ይደራደሩ?
… ከብዙ ጥረት በኋላ ግርግሩ ተረጋግቶ ጨዋታውን ሊቀጥሉ ወደ ሜዳ ገቡ፡፡ ሜዳ ሲገቡ ግን እነርሱ ድብድቡ ላይ እያሉ የጋና ተጫዋቾች ባዶ ሜዳ ላይ ጎል አስቆጥረው ስለነበር ዳኛው ሁለተኛ ጎል አድርጎ አፀደቀላቸው። በዚህ የተናደደው ኢታሎም በክራንቹ እየተጎተተ ወደ ዳኛው አመራ፡፡ አንደኛው ፖሊስ ሊያስቆመው ሲይዘው በክራንቹ ዘረረው፡፡ ፖሊሶች ሲከቡት አሁንም የሀገራችን ተጫዋቾች ሜዳውን ጥለው ወጥተው ከፖሊሶቹ ጋር 2ኛ ዙር ድብድብ ጀመሩ! በካልቾ… በቴስታ…!! ሜዳው ዳግም ወደ ጦር አውድማነት ተቀየረ፡፡…
ኢትዮጵያን በዚህ ጫወታ ላይ በአድልዎ 2 ለ 0 ተሸንፈው ቢወጡም፣ ጫወታው ግን ለባንዲራ ክብር ሲባል ጦርነት ቀረሽ ድብድብን በማስተናገዱ ታሪክ ሁሌም ያስታውሰዋል፡፡
——————-
ምንጭ:- ፍትሀዊ “የጠጅ ክፍፍል” ከተሰኘው  መጽሐፍ የተወሰደ ነው ።
Filed in: Amharic