>

ቀደምት መሪዎች አልሸለሙም ነበር? በተወልደ በየነ(ተቦርነ)

ቀደምት መሪዎች አልሸለሙም ነበር?

በተወልደ በየነ(ተቦርነ)

*… የዛሬን ለማወደስ የትናንትን ማሳነስ – አሳፋሪና አስተዛዛቢ ….?!?
 
የሠራን ማመስገን ፣ማክበር፣መሸለም በማንኛውም ዘርፍ አዲስ ጀግናን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለው ከሚያምኑት አንዱ ነኝ።
ሽልማት እና እውቅና ማግኘት ለኪነጥበብ ሙያተኛው ሲሆን ደግሞ የበለጠ አበረታች ነው ። በትላንትናው እለት በሁሉም ዘርፍ ለተሰማሩ የጥበብ ሰዎች የተደረገው የሽልማት ስነ ስርአትም  ከዚህ አንፃር ተገቢ ነው። በፕሮግራሙ ላይ እንዲህ አይነት የሽልማት ስነስርአት ከዚህ ቀደም እንዳልነበር መገለፁ ግን ክህደት የተሞላበት የተሳሳተ መረጃ ሆኖ አግኝቼዋለው።
 
ማስረጃ አንድ
    ቀዳማዊ ሀይለስላሴ በስማቸው በተቋቋመ የሽልማት ድርጅት የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ከመሸለም አልፈው ባለሙያዎቹ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ሙያቸውን በትምህርት እንዲያሳድጉ ልከው አስተምረዋል።
 
ማስረጃ ሁለት
መቶ አመት የሞላው የሀገራችን የቲያትር ሙያ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ ዝግጅቶቹን የሚያቀርበው ምንም አይነት አዲስ ቲያትር ቤት ሳይሰራ ቀዳሚው ሀይለስላሴ ባሰሯቸው ትያትር ቤቶች ነው።
 
ማስረጃ ሶስት
ብቸኞቹ የስእል እና የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በቀዳማዊ ሀይለስላሴ የተቋቋሙ ናቸው።
ባለሙያዎችን ከመሸለም አልፈው ባለሙያ ማፍርያ ተቋማት ገንብተዋል።
 
ማስረጃ አራት
የኮረኔል መንግስቱ ሀ/ማርያም መንግስት በበጎ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ ለኪነጥበብ እድገት ያደረገው አስተዋፅኦ ነው።ከዋነኞቹ አንዱ በሁሉም የኪነጥበብ ዘርፍ 90 ከመቶ የሚሆኑት የቀበሌና ከፍተኛ ኪነት ያፈራቸው የሙያ ውጤቶች መሆናቸው ነው።
 
ማስረጃ አምስት
የወሎ ራስ አምባ ላሊበላ ኪነት፣ የጎንደር የፋሲለደስ የኪነት ቡድን፣የጎጃም ግሽ አባይ የባህል ቡድንን፣ የሰራዊቱ የተለያዩ ክፍሎችን ጨምሮ ለውጤት ያበቋቸው በርካታ ባለሙያዎች አሉ።
 
ማስረጃ ስድስት
የህዝብ ለህዝብ አደይአበባ የባህል ቡድን የተሰጠውን ሀገራዊ ግዴታ በድል አጠናቆ ሲመለስ የደርግ መንግስት በወቅቱ ውድ የሆነውን የቴሌቪዥንና የቪዲዮ ዴክ ማጫወቻ በማበርከት ባለሙያዎችን አበረታቷል።
 
ማስረጃ ሰባት
በተለምዶ አዝማሪ የሚለው ስም ሙያውን ለማናናቅ ጥቅም ላይ ይውል ስለነበር ደርግ እንዲቀር አድርጎታል።
 
ማስረጃ ስምንት
ከሽልማት ጋር በተያያዘ በህወሓት/ኢህአዴግ ጊዜ ተቋቁሞ የነበረ የሽልማት ድርጅት ሁለት ተከታታይ የሽልማት ስነስርአቶችን አስተናግዶ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል።  በነገራችን ላይ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሀያ አንድ አመት የአገዛዝ ዘመናቸው የኪነጥበብ ባለሙያዎችን አንድ ግዜ ጠርተው አወያይተዋል።በወቅቱም ባለሙያዎቹ ለጠ/ሚሩ ጥያቄያቸውን ሳይሆን ጭብጨባቸውን አቅርበው የወርቅ ብእር ሸልመው ሸኝተዋቸዋል።
እነዚህና ሌሎችም የምስልና የድምፅ ማስረጃዎች ስላሉ አርቲስቶቻችን ሆይ በምትናገሩበት ወቅት ዛሬን ብቻ ሳይሆን ትላንትናችሁንም አስቡ።ካልሆነ እኛ ልናስታውሳችሁ እንገደዳለን!
  ለተሸላሚዎች እንኴን ደስ ያላችሁ! 
Filed in: Amharic