>

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ጉዳዮች አስገዳጅነት የተሰጠ መግለጫ!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ ጉዳዮች አስገዳጅነት የተሰጠ መግለጫ!

 
*…በግጭቶች የሚጠፋው የሰው ህይወት እንዲቆም ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪ አቀረበች ..!!!
 
“ወበየውሀትክሙ ወበፍርሐተ እግዚአብሔር አሠንዩ ግእዘክሙ- 
በቅንነታችሁ እግዚአብሔርን በመፍራት ሁናችሁ ግብራችሁን አሳምሩ፡፡” (1ኛ ጴጥ 3፡16)
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የሰው ልጆች ሰላምና አንድነት፣ የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን ሁለንተናዊ ደኅንነት እያስጠበቀች ማንኛውም የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ ሲፈጠር በጾምና በጸሎት በመትጋት ማኅበራዊ ችግሮች እንዲወገዱ ግንባር ቀደም ሆና ስትሰለፍ ኖራለች፤ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊና ሕዝባዊ ግዴታዋን በየዘመኑ በመወጣት ሐዋርያዊ ተልእኳን ስትፈጽም ቆይታለች፤ ዛሬም የሚጠበቅባትን ሐዋርያዊና ማኅበራዊ ተልእኮ ለመፈጸም የሚቻለውን ሁሉ እያደረገች ትገኛለች፡፡
እነዚህ ተግባራትም የሚመነጩት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ከተሰጣት ሐዋርያዊ ተልእኮ መንፈሳዊ አደራ ነው፡፡ ይኽ እንደተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የተከሰቱ የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ ሲሄዱም ቤተ ክርስቲያን የሚጠበቅባትን ከማድረግ አልተቆጠበችም ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የቤተ ክርስቲያናችንን አስተዋጽኦ ለመግለጽና ለወደፊቱም የሚጠበቅባትን እንደምትፈጽም ለመግለጽ ያህል በቅርቡ በመላው ሀገራችን በተለይም በሰሜኑ ክፍል የተፈጠረውን ችግር ለመቅረፍ ገና ከጅምሩ በርካታ ጥረቶችን ስታከናውን ቆይታለች ለመጥቀስ ያህል፡-
በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የሰላምና የአንድነት ዐቢይ ኮሚቴ በማቋቋም፣ ከራስዋ ቋት በጀት በመመደብ፣ የማስተማሪያ መመሪያ በማዘጋጀት፣ አባቶችን፣ ሊቃውንትንና ሰባክያንን በማደራጀት በመላው ሀገሪቱ ሁለት ጊዜ የሰላም ሥምሪት አድርጋለች፤
በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉበኤ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት፣ ስለመላው ሕዝብ ደኅንነት አጀንዳ ቀርጾ በመነጋገር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሕዝብ መሪዎች ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን በማቅረብ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለፍቅር፣ ለሕዝብ ዘላቂ ትሥሥር እና ለሀገራዊ መረጋጋት የሚጠቅሙ ውሳኔዎችን በመወሰን፣ መግለጫዎችን እና ጥሪዎችን በማስተላለፍ የበኩሏን ተወጥታለች፤
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተከሰቱ የሰላም ዕጦትና አለመረጋጋት በእግዚአብሔር ቸርነት እንዲፈቱ ሕዝቡ በጸሎትና በምሕላ በአንድነት ሆኖ ወደ እግዚአብሔር እንዲጮኽ መመሪያዎችን በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በማስተላለፍ በጥንታውያን አድባራት፣ ገዳማትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በአደባባይ ሳይቀር ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መነኰሳት፣ ምእመናንና ወጣቶች በአንድነት ያለማቋረጥ ጸሎትና ምሕላ ሲያደርሱ ቆይተዋል፤ አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ፤
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓበይት በዓላት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻና የመዝጊያ መግለጫዎቸ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች በተገኙባቸው መድረኮች ሳይቀር እስከ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ/ም በዓለ መስቀልና ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ/ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መዝጊያ ድረስ በቀጥታ በመላው ዓለም በሚዲያ ሥርጭቶች የሰላም፣ የአንድነት፣ የመግባባትና ችግርን በውይይት የመፍታት ጥረት እንዲደረግ መግለጫ ሲተላልፍ ቆይተዋል፤
ቤተ ክርስቲያናችን በቅዱስ ፓትርያርኩ መሪነት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በልዑክነት የተሳተፉባቸው በአካል ችግሮች በነበሩባቸው ቦታዎች በመጓዝና በሌሎችም አካባቢዎች በመዘዋወር ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መጠነ ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል፤
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ወደ ለምሳሌ ወደ መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ ኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ በመሰሉ የሀገራችን ክፍሎች በመጓዝ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ ላይ ተደጋጋሚ የሰላምና የዕርቅ መድረክ በማዘጋጀት ችግሮችን በተከበረው የሀገራችን የሽምግልና ባህል ለመፍታት ያልተቋረጠ ሥራ ተሠርቷል፤
የቤተ ክርስቲያናችን ታሪካውያን ገዳማት አበው መነኰሳት፣ የአብነት መምህራን የሆኑ ሊቃውንት በአንድነት ሁነው ካለባቸው መንፈሳዊ ግዴታ አንፃር በፈቃደ እግዚአብሔር ተነሣስተው መቀሌና ሌሎች አካባቢዎች ድረስ በመሄድ ችግሮችን በሽምግልና ለመፍታት ያለመሰልቸት ጥረት አድርገዋል፤
ከብዙ ድካም በኋላም ቢሆን ችግሮቹ ወደ ጦር ሜዳ ሲያመራ በጊዜው የቤተ ክርስቲያናችን መግለጫ በቂ የሚዲያ ሽፋን ባያገኝም ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ድምጽ አሰምታለች፤
ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የዘለዓለማዊ ሕይወት መማጸኛ ቤት ናትና ለመላው ሕዝብ መልካም አኗኗር ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት፣ በጸሎት፣ በምኅላ፣ በትምህርትና በማኅበራዊ ተልእኮ የድርሻዋን ያልተወጣችበት ጊዜ በታሪክ የለም፡፡
ችግር ተፈጥሮ በርካታ ጉዳት ከደረሰም በኋላ ቢሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ መመሪያ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ኃላፊዎችን እና መላውን የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በማንቀሳቀስ ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ሰብዓዊ እርዳታ፣ ትምህርትና መንፈሳዊ ማጽናኛ እንዲደረግ ዓቢይ ኮሚቴ አቋቁማ በመላው ዓለም እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፤
ዛሬም ቢሆን ይኽች ጥንታዊት ታሪካዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን በማንኛውም የሰው ልጅ ችግር ውስጥ የሚጠበቅባትን ታደርጋለች እያደረገችም ትገኛለች፤
ስለሆነም በድጋሜ ማስተላለፍ የምንፈልገው ዓቢይ ጉዳይ ቢኖር መንግሥትና የሀገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ አካላት በሙሉ ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት፣ ለሕዝብ አንድነትና መተሳሰብ፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነትና የሕይወት ዋስትና ቅድሚያ በመስጠት ችግሮችን በሰላማዊ እና በሠለጠነ መንገድ እንድትፈቱ ዛሬም ወደፊትም ለሚሆነው በአጽንዖት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
በሀገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች በአሰቃቂና ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ንፁሐን ዜጎች ሁኔታ አሳሰቢ ስለሆነ መንግሥት ከእስከዛሬው የበለጠ የዜጎች ሕይወት ይጠበቅ ዘንድ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
በተለይም መጭው ጊዜ የምርጫ ወቅት በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግሥት ከቅስቀሳው እስከ ፍጻሜው ያለው ሂደት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈጸም ታደርጉ ዘንድ  በድጋሜ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፤
አገራችንን ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ዕድገት እንደሚያደርስና ሕዝባችንንም ከዘመናት ድህነት እንደሚያላቅቅ የታመነበት የሕዳሴ ግድብ ፍጻሜ ሊያገኝ እየተቃረበ መሆኑ ይበልጥ ለፍጻሜው ግንባታ እንድንነሳሳ ተስፋ ሰጭ በመሆኑ መላው ዜጎች አሁንም ካለፈው በበለጠ የሚጠበቅብንን ድጋፍ እንድናደርግ የሁላችንንም ርብርቦሽ እንደሚያስፈልግ ቤተ ክርስቲያናችን አሁንም አጥብቃ ታሳስባለች፤
ውድና ክቡር ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ነፍሶቻቸውን እንዲምርልን ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲሰጥልን እየተማጸንን በሁሉም አካባቢዎች ንብረት ለወደመባቸው፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉና ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በሙሉ አቅም የፈቀደውን ሃይማኖታዊና ወገናዊ ድጋፍ እንዲደረግ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፤
እንደሚታወቀው በመላው ዓለም እየተዛመተ የብዙዎችን ሕይወት እየነጠቀ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ ሥርጭት በሀገራችንም ከፍተኛ ሥጋት ስለፈጠረ ካህናትና ምእመናን በቤተ ክርስቲያን አገልገሎትም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረጋችሁ ሥርዓተ አምልኮንና ማኅበራዊ ተግባራችሁን እንድትፈጽሙ በጥብቅ እናሳስባለን፡፡
የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርኣያና ምሳሌ የተፈጠረ፣ ሕይወቱና ማንነቱ እጅግ የከበረ ስለሆነ ክቡር በሆነ በሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ መከራን ማድረስ ውጤቱ ከድርጊቱ የባሰ መሆኑን በመገንዘብ፤ የሰው ሕይወት ተከፍሎ የሚሳካ ማንኛውም ምድራዊ ፍላጎትና ዐላማ ጠባሳው ለትውልድ ነውና በአስተዋይ አእምሮ ለሀገራችን እና ለሕዝባችን በማሰብ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሰላም ጥሪያችንን እናሳተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ/ም 
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
Filed in: Amharic