>
5:13 pm - Wednesday April 19, 5544

ተስፋየ ገብረአብ፡  የወያኔው ኦቶ ዲትሪኽ [መስፍን አረጋ]

ተስፋየ  ገብረአብ፡  የወያኔው ኦቶ ዲትሪኽ 

(በነ ሽመልስ አብዲሳ ክስ ዝርዝር ያልተካተተው ትልቁ የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ)

 

መስፍን አረጋ


በዐብይ አህመድ ተሹሞ በተመስገን ጡሩነህ የተሸለመውን ሽመልስ አብዲሳንና እሱን የመሰሉትን የአማራ ቀበኞች በዘር ማጥፋት ወንጀል ለመክሰስ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህን እንቅስቃሴ ደግሞ አማራ ብቻ ሳይሆን የጦቢያን በጦቢያነት መቀጠል የሚሻ ማናቸውም አገር ወዳድ በተቻለው አቅሙ ሊያግዘውና ሊያበረታታው ይገባል፡፡  የተከሳሾቹን ዝርዝር በተመለከተ ግን፣ በዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተተና ወደፊት በሚወጣ ዝርዝር ላይ ባንደኝነት ደረጃ ሊጠቀስ የሚገባው፣ በፀራማራ ትርክት የተካነ፣ ሰይጣናዊነት የተጠናወተው፣ አንድ እኩይ ግለሰብ አለ፡፡  እሱም አቶ ተስፋየ ገብረአብ ነው፡፡ 

አቶ ተስፋየ ገብረአብ፣ የወያኔን የዝቅተኝነት ስሜት ለመካብ ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፣ ምንትሴን የገረሰሰ ምንትሴ እያለ በተባ ብእሩ ያሻውን እንዳሻው መጻፍ መብቱ ነው፡፡ የቡርቃ ዝምታን በመጻፍ አማራን ጡት የሚሸልት፣ ፣ ማሕፀን የሚዘረክት፣ አጥንት የሚከተክት፣ በደም የሚፈትት የጭራቆች ጭራቅ አስመስሎ መሳል ግን የለየለት የጥላቻ ወንጀል (hate crime) ነው፡፡  በዚህ ሐሰተኛ የጥላቻ ጽሑፍ የተመረዙ የኦነግ መንጋወች የዘር ማጥፋት (ethnic cleansing) ወንጀል ከፈጸሙ ደግሞ፣ የጸሐፊው ወንጀል ከጥላቻ ወንጀል ወደ ፀረሰብ ወንጀል (crime against humanity) ከፍ ይላል፡፡   

የናዚ ፕሬስ መምርያ ኃላፊ የነበረው ያቆብ ዲትሪኽ (Jacob Otto Dietrich)በኒዩርምቤርግ ችሎት (Nuermberg trials) ቁሞ (tried)፣ በፀረሰብ ወንጀል (crime against humanity) ተወንጅሎ፣ ሰባት ዓመት ተፈርዶበት ዘብጥያ የወረደው፣ በዚህ አመክንዮ (reasoning) መሠረት ነበር፡፡  የዚህ ጦማር ዓላማ ደግሞ የወያኔው የፕሬስ መምርያ ኃላፊ የነበረው አቶ ተስፋየ ገብረአብ፣ እንደ ናዚ አቻው እንደ ያቆብ ዲትሪኽ በፀረሰብ ወንጀል ተወንጅሎ ተገቢውን ቅጣት ማገኝት እንዳለበት ለማሳሰብ ነው፡፡     

በፀራማራነት ላይ የተመሠረተው ዘረኛው ወያኔ፣ በፀረ ይሁዳነት ላይ ከተመሠረተው ዘረኛው ናዚ ጋር በብዙ ረገዶች ይመሳሰላል፡፡  

  • ወያኔ አፍሪቃዊ ናዚ ነው፡፡  ናዚ ፀረይሁዳ፣ ወያኔ ፀራማራ፡፡ 
  • መለስ ዜናዊ አፍሪቃዊ ሂትለር ነው፡፡
  • ስብሐት ነጋ አፍሪቃዊ ዲትሪኽ ኤካርት ነው፡፡  የሂትለርን ዘረኛ (በተለይም ደግሞ ፀረይሁዳ) አስተሳሰብ የቀረጸው፣ የናዚ ርዕዮተ ዓለም የመንፈስ አባት የነበረው፣ የሞርፊን ሱሰኛው፣ ሰካራሙና፣ ሴሰኛው ዮሐንስ ኤካርት (Johann Dietrich Eckart)
  • በረከት ስምዖን አፍሪቃዊ ዮሴፍ ጌቤልስ ነው፡፡  የናዚ ማስታወቂያ ሚንስቴር የነበረው ዮሴፍ ጎቤልስ (Joseph Goebbels)
  • ተስፋየ ገብረአብ ደግሞ አፍሪቃዊ ኦቶ ዲትሪኽ ነው፡፡  የናዚ ፕሬስ መምርያ ኃላፊ የነበረው ያቆብ ዲትሪኽ (Jacob Otto Dietrich)፡፡

መለስ ሙቶ ተቀብሯል፣ ስብሐት ነጋ አንድ እግሩ መቃብር ገብቷል፣ በረከት ስምዖን ታስሯል፣ ተስፋየ ገብረአብ ግን በየዕለቱ በሚያያቸውና በሚሰማቸው በቡርቃ ዝምታ አመርቂ ውጤቶች እየመረቀነ፣ ባስመራ ጎዳናወች እየተጀነነ፣ በነጻነት ይንፈላሰሳል፡፡  

ብአዴን በድን ሁኖ ነው እንጅ፣ በረከት ስምዖንን መከሰስ የነበረበት በትንሿ ወንጀሉ በገንዘብ ማጥፋት ሳይሆን፣ በትልቁ ወንጀሉ በዘር ማጥፋት ነበር፡፡  ብአዴን በድን ባይሆን ኖሮ፣ አቶ ተስፋየ ገብረአብን በዚያው ባማራ ክልል ውስጥ በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሶ፣ በኢንተርፖል (interpol) ታድኖ ተይዞ እንዲቀርብለት ቢጠይቅ፣ መጠየቁ ብቻ በግለሰቡ፣ በመሰሎቹና፣ ሊመስሉት በሚያስቡ ፀራማሮች ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ይኖረው ነበር፡፡  አማራን ለሚበሉትና ለሚያስበሉት የኦሮሙማ በላኤሰቦች ደግሞ ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ይሆን ነበር፡፡  

በነገራችን ላይ ሽመልስ አብዲሳ ጊዜው ደርሶ ለፍርድ ሲቀርብ፣ /መጠየቅ/ ካለበት ጥያቄወች ውስጥ አንዱና ዋናው ከብአዴን አመራሮች ውስጥ የትኞቹን እንዳታለላቸው (confused) እና የትኞቹን እንደደለላቸው (convinced) እንዲዘረዝር ነው፣ የተደለሉት ልክ እንደሱ የዘር ማጥፋት ወንጀለኞች ናቸውና፡፡  በዚህ ረገድ፣ አቶ ተመስገን ጡሩነህ፣ የሻሸመኔውን ከንቲባ አርፈህ ተኛ ያለውን ሽመልስ አብዲሳን፣ በሻሸመኔ የታረዱት ሰወች ደም ሳይደርቅ ተሸቀዳድሞ ካባ የሸለመው ወዶ ነው ተሸውዶ (convinced or confused)?  ተገዶ ሊሆን አይችልም፣ ሽመልስ አብዲሳ ተገደው አላለምና፡፡ ተሸውዶ ለማለት ደግሞ ያስቸግራል፣ በቀላሉ የሚሸወድን ተሸዋጅ ዐብይ አህመድ ሲፈልገው የክልል ፕሬዘዳንት፣ ሲፈልገው የደህንነት ኃላፊ እያደረገ ላገዛዙ ወሳኝ በሆኑ ቦታወች ላይ አያስቀምጠውምና፡፡  ለማንኛውም ወደ ርዕሳችን እንመለስ፡፡      

የተስፋየ ገብረአብ ጀርመናዊ አቻ ኦቶ ዲትሪኽ (Jacob Otto Dietrich) በመጀመርያ ደረጃ የወንጀለኛው ናዚ ድርጅት አባል በመሆኑ ብቻ፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በወንጀለኛው ድርጅት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች (በተለይም ደግሞ በፕሬስ መምርያ ኃላፊነት) ላይ በነበረበት ወቅት በተረከታቸው (narrate) መሠረተቢስ ፀረይሁዳ ትርክቶች (narration) ሳቢያ፣ ሰባት ዓመት ተፈርዶበት ወህኒ ከተወረወረ፣ ከዲትሪኸ እጅግ የከፋ የማጠልሸት ወንጀል (vilification) ባማራ ላይ የፈጸመው፣ የወንጀለኛው የወያኔ ከፍተኛ ባለስልጣን የነበረው አቶ ተስፋየ ገብረአብ ደግሞ ዓለምበቃኝ የማይጣልበት ምንም ምክኒያት የለም፡፡  

ልክ እንደ ናዚው የፕሬስ መምርያ ኃላፊ እንደ ኦቶ ዲትሪኽ፣ የወያኔው የፕሬስ መምርያ ኃላፊ የወዲ ገብረአብ ዋና ተልዕኮ ወያኔያዊ ሕትመቶችን (ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ መጽሐፎችን፣ ወዘተ.) በበላይነት በመቆጣጠር፣ ጦቢያዊነትን አመንምኖ ጎጠኝነትን በማግነን በካፍለህ ግዛው ዘዴ የወያኔን አገዛዝ በማይናወጽ መሠረት ላይ ማቆም ነበር፡፡  በተለይም ደግሞ የወያኔን ጥንካሬ እጅግ አግንኖ የማይጋፉት ባላጋራ ማስመሰል ይጠበቅበታል፡፡  ወያኔ በተቃዋሚወቹ ውስጥ ለሚያሰማራቸው አፈ ጮሌ ሠርጎ ገቦች ደግሞ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ተቃዋሚወችን የማተራመስ ተልዕኳቸውን እንዲያሳኩ ከፍተኛውን እገዛ ይደርጋል፡፡  በተለይም ደግሞ የጦቢያውያንን ጥቃቅን ልዩነቶች አግዝፎ ርስበርስ በማናቆር፣ ሙሉ ትኩረታቸውን ርስበራሳቸው ላይ አድርገው ርስበራሳቸው እንዲጠባበቁ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡  

ልክ እንደ ዲትሪኽ፣ ተስፋየም ለዚህ ከፍተኛ ኃላፊነት የበቃው፣ የወያኔን ፀራማራ አጀንዳ እንዲያራምድ አስቀድመው የተሰጡትን ኃላፊነቶች ሁሉንም በሚገባ ተወጥቶ፣ ከወያኔው መሪ ከመለስ ዜናዊ ከፍተኛ አድናቆት፣ ከበሬታና፣ መታመን በማግኘቱ ነበር፡፡  ልክ እንደ ዲትሪኽ፣ ተስፋየም አዲሱን ኃላፊነቱን ከተጠበቀው በላይ አሳክቶ የወያኔውን መሪ ይበልጥ በማስደሰቱ፣ ቅናት ቢጤ የለመጠጣቸው ባልደረባወቹ ከመሪው ጋር ሊያቃቅሩት ጥርሳቸውን ነክሰውበት ነበር፡፡

የወያኔን ጥንካሬ አንሮ ሰማይ እንዲያደርስ በተሰጠው ልዩ ተልዕኮ መሠረት፣ ወያኔ ሰውን ይቅርና ተራሮችን የሚያንቀጠቅጥ የማይጋፉት ባላጋራ ነው ለማለት “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” የተሰኘውን ልብወለድ ጽፏል፣ አስጽፏል፡፡  አማራንና ኦሮሞን እያፋጀ የወያኔን ዘመን በከፋፍለህ ግዛው ለማራዘም ደግሞ “የቡርቃ ዝምታ” የተሰኘውን አደገኛ መርዝ (ምናልባትም ከበረከት ስምዖን ጋር በመተጋገዝ) ቀምሟል፡፡ 

ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፣ ትልቁን የሰሃራ በታች ጦር የደመሰሰ ምንትሴ እያሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ (በተለይም ደግሞ አማራው) ገዝግዞ በጣለው የደርግ ግንድ ላይ ቁሞ መታበይ አጸያፊ ቢሆንም፣ ዋና ዓላማው ግን የዝቅተኝነት ስሜት ከፉኛ የሚያጠቃውን የወያኔን በራስ መተማመን መገንባት ስለሆነ፣ የተስፋየና የበረከት ሙሉ መብት ነው፡፡  በዚህ የቱልቱላ የሚተለተለው ግን በራስ መተማመኑን በውሸት ትርክት ላይ በመገንባት ማንነቱን በድቡሽት ላይ ያነጸው ራሱ ወያኔ ነው፡፡  ይህ በድቡሽት ላይ የተገነባ ማንነት በትንሽ ጩኸት እንደሚፈራርስ ማስረጃ ለማቅረብ ደግሞ የቅራቅሩን ውጊያ መጥቀስ ብቻ በቂ ነው፡፡  

ተስፋየ ገብረአብ ተራራ አንቀጥቃጭ ናችሁ ስላላቸው ብቻ፣ እውነትም ተራራ አንቀጥቃጭ ነን ብለው ከልባቸው የሚያምኑ፣ ጦርነት ባህላችን ነው እስከማለት የደረሱ፣ ቁጥራቸው የማይናቅ፣ ወርቅ ዘር ነን ባይ የትግራይ ተወላጆች፣ እስካፍንጫው የታጠቀው ተራራ አንቀጥቃጩ የወያኔ ጦራቸው፣ አንድ ጎራሽ ባነገቡ “ፎጣ ለባሽ” ፋኖወች ድባቅ ሲመታ ማመን አቅቷቸው የገቡበትን ከፍተኛ ስነልቦናዊ ቀውስ ለመታዘብ ወደ ዩቲዮብ (Youtube) ጎራ ማለት በቂ ነው፡፡  ያማራን አከርካሪ ሰብረነዋል ያለው፣ የተራራ አንቀጥቃጩ ትውልድ የመንፈስ አባት ስብሐት ነጋ፣ ባማራ ልዩ ኃይል አከርካሪው ተሰበረ፡፡  ያሁኑ ነፍጠኛ ሰባሪ ነኝ ባይ ሽመልስ አብዲሳ ደግሞ ትልቁ ፍራቱ፣ ልክ እንደ ስብሐት ነጋ በዚሁ ልዩ ኃይል እንዳይሰበር ነው፡፡ ይህን ልዩ ኃይል በዘር ማጥፋት ወንጀል አስከስሶ፣ በምዕራባውያን ቦምብ ለማስቀጥቀጥ የተነሳሳውም በዚሁ ፍራቻው ሳቢያ ነው፡፡        

አቶ ተስፋየ ገብረአብ ወያኔን ተራራ አንቀጥቃጭ ብቻ ሳይሆን ተራራ ፈልቃጭ ማለት መብቱ ቢሆንም፣ የቡርቃ ዝምታን መጻፍ ግን ፣ የመጻፍ ነጸነትን ገደብ በከፍተኛ ደረጃ የጣሰ፣ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስቀጣ ፀረሰብ ወንጀል (crime against humanity) ነው፡፡  ፀረሰብ ወንጀል ማለት ሰላማዊ ሰወችን ለመፍጀት ወይም ለማፋጀት ሲባል ሥራየ ብሎ የተፈጸመ ማናቸውም ዓይነት እኩይ ድርጊት ነው፡፡  ፀረሰብ ወንጀል እንደ ጦርነት ወንጀል (war crime) በጦርነት ወቅት ብቻ የሚፈጸም ወንጀል ሳይሆን፣ በጦርነትም፣ በሰላምም፣ በማናቸውም ጊዜ ሊፈጸም ይችላል፡፡  ፀረሰብ ወንጀልን ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ወንጀሉ በፈጻሚው ቡድን (ወይም ድርጅት) መመርያ ውስጥ በይፋ ወይም በሕቡዕ የተካከተ በመሆኑ፣ ቡድኑ ወንጀሉን በይፋ ወይም በሕቡዕ የሚደግፈው ወይም ደግሞ የሚቸልለው (condone)  (ማለትም ቸል የሚለው ወይም አይቶ እንዳላየ የሚያልፈው) መሆኑ ነው፡፡

ወያኔ ከጽንሰቱ ጀምሮ አማራን በጥቅሉ በጠላትነት በይፋ ፈርጇል፡፡  ይህ በራሱ ፀረሰብ ወንጀል ነው፡፡  ስለሆነም፣ የናዚ አባል ሁሉ በአባልነቱ ብቻ ፀረሰብ ወንጀለኛ እንደሆነ ሁሉ፣ የወያኔ አባል ሁሉ በአባልነቱ ብቻ ፀረሰብ ወንጀለኛ ነው፡፡  የወያኔው ወዲ ገብረአብ ደግሞ በወያኔ ፖሊሲ መሠረት ጠላት ተብሎ የተፈረጀውን አማራን፣ በኦነጋውያን ለማስፈጀት ሥራየ ብሎ እኩይ ትርክት ተርክቷል፡፡  ስለሆነም፣ አቶ ተስፋየ ገብረአብ፣ በወያኔ አባልነቱና በእኩይ ፀራማራ ትርክቱ ድርብ ፀረሰብ ወንጀለኛ ነው፡፡  የወዲ ገብረአብ እኩይ ትርክት ደግሞ ቀድሞውኑ ባማራ ጥላቻ የቀወሱትን የኦሮሞ ጽንፈኞች ይበልጥ አቀውሶ በማሳበድ አእላፍ አማሮችን እንዲያርዱ አድርጓቸዋል፡፡  ይህ ደግሞ አቶ ተስፋየ ገብረአብን ባማራ ጥላቻ ባበዱት ኦነጋውያን ለታረዱት አማሮች ቀጥተኛ ተጠያቂ በማድረግ ድርብርብ ፀረሰብ ወንጀለኛ ያደርገዋል፡፡

ስለዚህም አቶ ተስፋየ ገብረአብ ከፀረሰብ ወንጀለኛ አልፎ፣ ከድርብ ፀረሰብ ወንጀለኛ አልፎ፣ ድርብርብ ፀረሰብ ወንጀለኛ ነው፡፡  የወዲ ገብረአብን ድርብርብ ፀረሰብ ወንጀለኛነት ለማረጋገጥ፣ አንገቶች የተመተሩበት፣ ጡቶች የተቆረጡበት፣ ማሕፀኖች የተዘረከቱበት፣ ሆድ እቃወች የተዘረገፉበት የቡራዩ ጭፍጨፋ የቡርቃ ዝምታ መስታዋታዊ ነጸብራቅ (mirror image) መሆኑን መጥቀስ ብቻ ይበቃል፡፡      

አገራችን ጦቢያ የሮማን ፕሮቻዝካን (Roman Prochazka) ፀራማራ አጀንዳ በሕቡእ በሚያራምዱ ምዕራባውያን መንግስታት የሚደገፉ ጎጠኞች እንደ አሸን የፈሉባት አገር ናት፡፡  በዚች ጎጠኞች በነገሱባት አገር ይቅርና፣ ጎጠኞች ከሞላ ጎደል በከሰሙባቸው በምዕራባውያን አገሮች እንኳን  ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት የሚሄደው እስከተወሰነ ደረጃ ብቻ ነው፡፡  ለምሳሌ ያህል ታዳሚ በታደመበት ቲያትር ቤት ውስጥ፣ በውሸት እሳት ተነሳ ብሎ ኡኡ በማለት ትርምስ ፈጥሮ ታዳሚውን ለጉዳት ይልቁንም ደግሞ ለሞት መዳረግ፣ በሞት የሚያስቀጣ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡  የወዲ ገበረአብ የቡርቃ ዝምታ ደግሞ እልፍ አእላፍ አማሮችን በትርምስ ለመረጋገጥ ሳይሆን በሜንጫ ለመቆረጥ፣ በገደል ለመፈጥፈጥ የዳረገ ሐሰተኛ ትርክት ነው፡፡   

የፀረሰብ ወንጀል ሕግ የሚያገለግለው በነጮች ላይ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ብቻ ካልሆነ በስተቀር፣  የናዚ ፕሬስ መምርያ ሃላፊ ኦቶ ዲትሪኽ በናዚ አባልነቱና በእኩይ ሕትመቶቹ ብቻ ተወንጅሎ ሰባት ዓመት ከተፈረደበት፣ ከዲትሪኽ ወንጀል ሰባት ጊዜ ሰባ በላይ የከፋ ወንጀል የፈጸመው፣ የወያኔው ፕሬስ መምሪያ ሃላፊ የነበረው ወዲ ገብረአብ ደግሞ የጁን የማያገኝበት ምንም ምክኒያት አይኖርም፡፡  

የወዲ ገብረአብ ፀረሰብ ወንጀል ግልጽ ስለሆነ፣ የክስ ዶሴው ይከፈት እንጅ ለመዝጋት ጊዜ አይፈጅም፡፡  ወንጀለኛው ደብቁኝ፣ ደብቁኝ ሳይል፣ (በጻፈው የጥላቻ ትርክትና በትርክቱ አመርቂ ውጤት በመመርቀን) እዩኝ፣ እዩኝ እያለ ዶሴውን መክፈት ደግሞ የጁን የሚያገኝበትን ጊዜ ይበልጥ ያፋጥነዋል፡፡  

 

ኢሜል:-  መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic