>

በቸልታ የማይታለፉ ጉዳዮች  እናት ሀገር ኢትዮጵያ ጭንቅሺን ያበዙት እነማን ናቸው?! (ታየ ቦጋለ አረጋ - ኢልመ ደሱ ኦዳ)

በቸልታ የማይታለፉ ጉዳዮች 

እናት ሀገር ኢትዮጵያ ጭንቅሺን ያበዙት እነማን ናቸው?!

ታየ ቦጋለ አረጋ (ኢልመ ደሱ ኦዳ)

አብሮ የመኖር ወርቃማ ዘዴዎች አያሌ ናቸው። “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንደዚሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ዘላለማዊ የህይወት መርህ ብንከተል እጅግ አዋጪ ነው።
* መገደል አትፈልግም አትግደል!
* መሰረቅ አትፈልግም አትስረቅ!
* ‘አንተ የመሬት እንጂ መሬት የአንተ እንዳልሆነች ለማወቅ ወደ መቃብር ስፍራዎች ሂድ፤ እውነታውን አፍ አውጥተው ይነግሩሀል’ _ ዘላለም የአንተ ላልሆነች መሬት አምሳያህን አትግፋ! ብንፋቀር እንኳን እኛን ስደተኞችን ጨምራ የምታኖር ምድር አለቺን። ከሁሉም የሚቀድመው ሀብት ሰው/ ወገን ነው። ጃፓንና እስራኤል የበለፀጉት የበለፀገ መሬት ስላላቸው ሳይሆን የበለፀገ አእምሮ መፍጠር በመቻላቸው ነው። ኮንጎ ከአፍሪካ ቀዳሚውን የሚታይ ሀብት ይዛ፤ በጦርነት የምትታመሰውና እልቂት የምታጭደው፤ ምልዓተ ህዝቡን አፍ ከልብ አሰናኝተው ተፈጥሯዊ ሀብታቸውን መጠቀም የሚያስችል አእምሯዊ ሀብት የተላበሱ ምሁራን በማጣታቸው ነው። ምሁራዊ ትምክህት እና አድርባይነት ያጠፉናል።
ወደ እምነትም ብንሸጋገር፦
* ፈጣሪ ከኃጢአቶች ሁሉ የሚጸየፈው በወንድማማቾች መሀከል ጠብን የሚዘራ ስለመሆኑ መፅሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች አበክሮ ያስገነዝባል።
* በተመሳሳይ ታላቁ የእስልምና ነቢይ ነቢዩ መሀመድ ሰ.ዐ.ወ፦ “ዘረኝነት ጥምብ ናትና ተዋት!” ሲሉ ለሙስሊሞች በአፅንዖት አስተምረዋል።
* በአኳያው ዋቄፈና፦ እንኳን ሰው መግደል ይቅርና እርጥብ እንጨት መቁረጥ እርግማን መሆኑን ለዋቄፈታዎች ያስተምራል።
* ታዲያ ‘እንኳን ጥላቻ ጨምረንባት ለፍቅር እንኳ በቅጡ ለማትበቃ እድሜ’ ለምን ግፍ እንሠራለን?!
ፈረንጆቹ ባይሆኑም ብሪቶኖች እንዲህ ይላሉ፦
[Empathy is normally voiced as ‘putting yourself in my shoes’ or ‘see it from my point of view’]
ራሳችሁን በሌላው ጫማ ውስጥ አስገብታችሁ ነገሮችን ማየትና መመዘን ስትጀምሩ ችግሮችን ለማቅለል ይረዳል።
በአይጥ ያልተሞከረ ሰዎች አልፈው የመጡበትና የደረሱበት በአንፃራዊ መንገድ የተሻለ ኮረኮንች አልባ መንገድ አለ። የዓለም አያቶች የተናቆሩትን ሩብ የእኛ አያቶች አልተናቆሩም። የሁላችንም አያቶች ተጠያቂ ከሚሆኑበት ያነሰ ግጭት ይልቅ፤ በፍቅር ያሳለፉት ዘመን የትየለሌ ነው። እንደ ሰው መመዘን ብንችል አብዝተን እናተርፋለን። በ21ኛው ክፍለዘመን እየኖርን ጥንት በሰብአ ትካት ዘመን ያልተፈፀመ ግፍ ስናይና ስንሰማ፤ እንደ ሰው ተፈጥረን እንደ እንስሳ እንኳ መኖር ሲያቅተን ማየት ያሳቅቃል።
ችግራችን የእኛ ያልነውን ወገን የጠቀምን መስሎን ፀብን ወደሌላው ለመግፋት መሞከራችን ውሎ አድሮ ዋጋ ያስከፍላል። በግጭትም ሆነ በስሜት በምንሰግርበት አውድ፦ Both parties look their dispute from the other person’s view point. አዎ የሌሎችን ሀሳብ መዝኖ ለመቀበል መትጋት (Compromise) ፍቱን መፍትሔ መሆኑን የሰለጠነው ዓለም አሳምሮ ተረድቷል። የእውነት እራሳችንን የምንመዝንበት Deceptively simple question እናንሳ፦ It is so easy to do when one asks oneself: ‘Why did he say that?’ ለምን ይህንን ወይም ያንን አለ? በማለት መነሻውን በቀናነት ከመረዳት ይልቅ ለምን ቁጣ ይቀናናል? ስለምንስ መታበይ ያኮራናል?
‘ከዓመፃ ብዛት የተነሳ በሰዎች መሀከል ፍቅር መቀዝቀዟ’ የተፃፈ ነውና ጥላቻ ተከታይ ያበዛልናል። ብሶት በጅምላ እና በችርቻሮ ማከፋፈል ገዢዎችን ያበራክታል። እሳት እያዋጡ ገሀነም መፍጠር ቀላል ነው። ገሞራ ህፅሙ እንደማያቃጥለን በመጠኑ እርግጠኛ የምንሆነው ውጭ ሀገር ቁጭ ብለን የምናናክስ ከሆነ (ሀገር ቤት የሚከስል ዘመድ ከሌለን)፤ አሊያም በዘቀጠ ስብዕና የሚደልብ ኪሳችን ከወገንና ሀገር የበለጠብን እንደሆነ ብቻ ነው።
እንደ ውሻ መናከስ፤ እንደ ኮብራ መናደፍ፤ እንደበግ መጋጨት፤ እንደአህያ መራገጥ፤ እንደ እንስሳ የአሁን ሆዳችንን በማየት የሩቅ አብሮነታችንን ማሻከር ከሰውነት ተራ ከወረድን ይመቸናል። እንደ ነጭና ጥቁር ዝንጀሮ ጎራ መለየትና መቆራቆስ፤ በመንጋው ተከቦ መፎግላት የአሸናፊነት ጥግ ይመስለናል። እንደ ሩሲያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፦
“Our friends will respect us in so long as we are strong.
There is no respect for the weak ones as they get beaten” ብለን የ’Melancov’ን መርህ ብናነግብ፤  በአፀፋው እንደ አሜሪካኖቹ፦
“Soviets do understand only one language, how many division have you?” እየተባባልን፤
አሊያም ለጥፋት ‘Get more maxim gun’ በማለት ወገናችንን ጥበብ ሳይሆን ጠብመንጃ ስናስታጥቅ ዓለም አለቅጥ ራቀቺን። በእርስበርስ ጥርጣሬ (Mutual suspicion) ለሁላችንም የማይመለስ፤ ግቡ ኢትዮጵያን ማዳከም የሆነ ዓለማቀፋዊ ኃይል ዙሪያችንን የከፋ ጠላት ከቦን ሳለ፤ የጋራ ሀገራዊ ኃይል ከመገንባት ይልቅ ወገኖቻችንን ለመፈታተን (አጥፍተን የምንኖር መስሎን) ክልላዊ ጡንቻን ማፈርጠምን መረጥን። በአደባባይ እየተሳሳምን በማጀት ለመጠፋፋት ማድባት ፍርቱናችን ሆነ። ቁማር ለጊዜው ያበለፀገ ቢመስልም መጨረሻው ተያይዞ መክሰርና ትርፉ ለአጫዋቹ ሲሳይ መሆን ነውና እንመዝን!
የስነልቡና ጠበብት “When persons lowers their voice, they want something. When they raise it, it is a sign they didn’t get it.” ይላሉ። እርጋታ ጠፍቶ ፉከራ ከበረታ የመሸነፍ ምልክት ነው። ከወያኔ በላይ 46 ዓመት የፎከረ፤ የእብሪት የቀለም የሰልፍ ትርዒት ያሳየ አልነበረም። ውጤቱ ግን በ17 ቀናት ሰርጥ ለሰርጥ ተሯሩጣ፤ ስትሮጥ ገደል ገብታ ሞታ፣ ከመንግሥትነት ወደ ሽፍትነት የቀየራት እብሪቷ ነው። የጦር ሠራዊት ከማብዛት ህዝብን ልማታዊና ሀገራዊ አርበኛ ማድረግ ይቀላል። ‘ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኃ ኃይሉ” _ ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንምና። ደርግና ወያኔ In our mind ህዝብን አሰናኝቶ ማደራጀት አሸናፊ ያደርጋል። ህዝብ መቼም አይሸነፍምና! ፋሺስቶችንና ዚያድባሬን ያንበረከክነው ዘግይቶም ቢሆን ህዝብን ማደራጀት ስለተቻለ፤ ለሀገሩ የሚሰዋ ህዝብ መፍጠር ስለተቻለ ነው። በኢትዮጵያ ቀልድ የለም።
እንግዲህ ቢያንስ እንደ ባለ አእምሮ እናስብና የኖርንበት _ ጠበንም ሰፍተንም እናስብ _ የሁላችንንም ወገን በየተራ ያሳጣን _ ወደፊትም የሚያጠፋን የጠብ ዘመን ይብቃን።  ‘እዚያም ቤት እሳት አለና’ ፤ ፍቅር እንጂ ፀብ ዘለቄታዊ ድል አይሆንምና የጥል ግድግዳ ይደርመስ። ቁጭ ብለን እንምከር። በጥላቻ መጓተትና መሳከር ይብቃን።
ለዚህ ሁነኛ መፍትሔው፦ ኬኩ በአንድ በኩል አይወፍር። በየተራ የራሳችን ወገን ላልነው አናስፋ! አንዱ ድፎ ሌላው ጥቢኛ፤ አንዱ እንጀራ ሌላው እንጎቻ አይድረሰው። የጉርሻው መጠን ባስመዘገበው ስኬት እንጂ በነጠቀበት ጡንቻ አይመዘን።
ነፃ እኩል የተመቻቸ የውድድር ስፍራ ይኑር።
በነፃ የውድድር ሜዳ ውጤት፦
የቀደመ _ ዳይመንድ
የተከተለ _  ወርቅ
የሠለሰ _ ብር
በረቡዕ የደረሰ _ ነሐስ
የሐሙሱ _ ዲፕሎማ
የዓርቡ _  የምስክር ወረቀት ይሰጠው (ምስክርነቱ የታመነ ነው።)
 እንጂ!
ሁለተኛም ለቅጥረኞች ሰለባ አንሁን! የእኛን እያሳረሩ የእነሱን እንዲጋግሩ አንፍቀድላቸው! ዐስተውል፦ ካላከበርህ አለመከበርህን ተገንዘብ።
አዎ የምንግባባው በሌሎች ጫማ ውስጥ ቆመን ማየት ስንችል ነው።
ጠንካራ አቋማችን ሊሆን ይገባል!
ለጥቂቶች እኩይ መሻት ኢትዮጵያ እናት ሀገራችን እንዲህ ስትናጥ፣ ደም እንደጎርፍ ያለማቋረጥ ሲፈስና ለባእዳን ሀገራት ጥቃት ስትጋለጥ በዝምታና በቸልታ ያለፋችሁ፦ ምሁራን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የየማህበረሰቡ ሽማግሌዎች፣ ማህበራዊ አንቂዎችና በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት ኃላፊዎች (ልሂቃን) አንድ ቀን በታሪክ ፊት ትጠየቃላችሁ።
ኢትዮጵያ ወደ ከፋ ምስቅልቅል ከገባች በኋላ – የፈሰሰ ውሀ ላይታፈስ ትፀፀታላችሁ።
የጎደለንን ሳይሆን ፀጋችንን እንቁጠር
በማስተዋል ስንመዝነው ከተደረገብን ይልቅ የተደረገልን በእጅጉ ይተልቃል።
በህይወታችን በርካታ መሰናክሎች አጋጥመውናል። አልጋ በአልጋ የሆነ ኑባሬ የለም። በጉዟችን የትየለሌ ውጣውረዶችን ጋሬጣና አሜከላዎችን አልፈን ይቺን እለት ደግሞ ፈጣሪ ተጨማሪ አድርጎ ሰጥቶናልና በሸለቆ ውስጥም ቢሆን እናመስግን። ላለው ይጨመርለታልና!
ፀጋችንን ዘንግተን የጎደለንን ከቆጠርን (ለብዙዎቻችን በቁሳዊ ህይወት ሞልታ ባልሞላችው ዓለም) ‘ላይኞቻችንን’ ዕያስተዋልን _ በገንዘብ ለማይተመን እምነት ህሊናችን እና ሰውነት ዋጋ ካልሰጠን ያላግባብ መከፋታችን አይቀርም። ጫማ የለኝም ብለህ አትዘን እግር የሌለው አለና በሚል አጓጉል ይትበሀል ተሸብበን፤ ጫማ ከሌላቸው መወዳደር ከጀመርን እድገት አይታሰብም። እግር ለሌላቸው ፓራሊምፒክ፤ እግር ላላቸው ኦሊምፒክ የሆነውም በየዘርፋችን እንድንወዳደር ነው። የጥበብ መፅሐፍ ሊሠራ የማይወድ አይብላ ይላልና በቃሉ መሠረት በወዛችን ጥረን ግረን እንብላ።
በሥልጣንህ አሊያም በማጭበርበር ያግበሰበስከው ህንፃ ቀን ሲወጣ (ባለቤት አልባ) ተብሎ ይወረሳል። ደም ካፈሰስህ አሟሟትህ በክብር አይሆንም። ዐስተውሎ ላለው ደደቢቶችን ማየት ይበቃል።
አብዝተህ እንቅልፍ አትውደድ። ፀጋዎችህ ብዙ ናቸው። ፈጣሪ ሆይ፦  ከእንስሳት ወይም እጽዋት፤ ከነፍሳት አሊያም ከግዑዛን ፍጥረታት ሳትመድብ ሰው አድርገህ ፈጥረኸኛልና ተመስገን በይ።
ተመስገን ከልብ ካመንኩህ ውጊያዎቼን አንተ ቀድመህ በድል ትወጣልኛለህና! የሌለሺን ለማግኘት እየተፍጨረጨርሽ ለተሰጠሽ በረከት እግዚአብሔርን አመስግኚ።
ተመስገን አውቶሞቢል ባይኖረኝ ሁለት እግሮቼን አፅንተሀልና ብለሽ ዛሬ የሌለሽ የማያስፈልግሽ ነውና (ራስሺን፦ ሊሠራ የማይወድ አይብላ ነውና) ለተሻለ ህይወት አዘጋጅተሽ፤ መሻትሺን ለፈጣሪሽ በንፁህ ልቦና ንገሪው። ነገሮች ሲወሳሰቡ በርከክ ማለቱ አዋጪ ነው። When things go down look up!
*
ሀብት ባታትረፈርፍልኝ ጤናውን አብዝተህልኛልና ተመስገን በዪው። በታላላቅ ህንፃዎች ውስጥ የተደበቁ ብዙ ስቃዮች አሉና፤ ትንሿ ጎጆዬ ትልቅ ስነስርአት ትፈልጋለች በማለት በአጭሯ በርሽ ጎንበስ ብለሽ ግቢና የሳር ፍራሽሽ ላይ በሀሴት አንቀላፊ። አዎ ነገ ሌላ ቀን ነው። በፍፁም ተስፋ አትቁረጪ፦ ባህርን ከፍሎ ማሻገር ያውቅበታል። በነደደ እሳት መሀከል የልብስ ዘርፍ ሳይቃጠል መዘመር ያስችላል። የአናብስትን (የአንበሶችን) አፍ መዝጋት ይችላል። ገዳዮችን በቁም ገድሎ ለሰማዕታት ዘላለማዊ ህይወትን የሚያቀዳጅ አምላክ አለን።
ጥቂት እኩያን ቢያጋጥሙንም በበርካታ ደጋግ ሰዎች መሀከል በፍቅር ያኖረናልና! ለአንተ ምን ይሳንሀል? እንበለው።
ነገሮችን አቅልለን ዕንድናይ አድርጎናል። ከድቅድቅ ጨለማ በኋላ የሚደነቅ አንፀባራቂ ብርሃን እንደሚከተል እንመን። እንመን እንጂ አንፍራ። ክምር አፈር ቢቆለል ወርቅ ፈላጊዎች በውስጡ አንድ ግራም ወርቅ እንዳለ ዐስተውለው ጭቃውን ይዝቃሉ። መከራ ሲበዛ በእሳት ተፈትነን መውጣትን እንለማመድ። አዎ ሊነጋጋ ሲል መጨለሙን ህይወት ደጋግማ አስተምራናለች።
ወገኖቼ ያሬድ ግዕዝ እዝልና አራራይ ዜማዎችን ያበረከተልን ስድስት ጊዜ ወድቆ በሰባተኛው ተነስቶ ነው። ቶማስ አልቫ ኢድሰን በ65 ዓመቱ ፋብሪካው ሲጋይ፦
“ተመስገን ያለፉ ስህተቶቻችን በሙሉ ተቃጥለዋል። አዳዲስ ነገሮችን እንጀምራለን”
በማለት በመፍጨርጨሩ በርካታ ፈጠራዎችን ለዓለም አበርክቶ አልፏል።
*
መኖር በራሱ ትግል ነው። ያለመስዋዕትነት ድል የለም። ፅጌረዳን ለመቅጠፍ እሾኾቿን ጨብጦ ማለፍ ያስፈልጋል። መርህ አልባ ህይወት ካለን በመካከም እንሰቃያለን። ሰው ሆነን የተፈጠርነው ራዕይ ሰንቀን፣ ተልእኮ አንግበን፣ ዓላማ አስቀምጠን፣ ግቦችን ጥለን፣ ሁኔታዎችን ተንትነን (SWOT/ SLOT Analysis)፣ የአፈፃፀም አቅጣጫዎችን ተልመን፣ የጊዜ ሰሌዳ ዘርግተን፣ ግምገማ እና ግብረ መልስ ተቀብለን፣ በሂደት የጎበጠውን አቅንተን፣ ፈተናው እንደእናቶች እርግዝናና ምጥ በወጀቦች ቢታጀብ _ የሚወለደውን ህፃን እያሰብን ህመሙን ለመቋቋም እንጀግን።
*
ድርጊት ይሉሀል ህይወትን ወደ ፍቅር ጣዕም መለወጥ ነው እንዳለው ፈላስፋ መራራን ወደ ጣፋጭ በመቀየር ልንካንበት ይገባል። የፈፀመው እየከነከነው መፈጸም ካማረው ሊለምድ ሳይሆን ልማደኛ ነውና እንደ ፈንጅ አምካኝ ከስህተቱ ለማይማርና ለቀጠለበት _  ውድቀቱን ዕያየን ሰው ከሆንን ከውድቀታቸው ትምህርት እንቅሰም። ከራስህ ይልቅ ከሌሎች ውድቀት ትምህርት ልትቀስም ይገባልና። እውነተኛ ፍቅር በወንዝ ዳር የበቀለ ፅጌረዳን ይመስል ይለመልማልና በመከራ ውስጥ እንኳ ብናልፍ ፈጣሪ ከኛ ጋር ነውና አንፈራም።
በእኔኛ እንደምሞት ሳስብ እንኳ አስቀድሜ የምሰጋው ለሞቴ ሳይሆን ለአሟሟቴ ነው። በቁም ሞቶ በውርደት ከማለፍ፤ ሰው ሆኖ መኖርና መሰዋት በገዳዮች ፊት የሚያስጀግን ህያውነት ነው። እንደሚገድሉን እያወቅን የማንፈራው ከቁም ሞት ስለማይብስ ነው። ህይወት እዚህ ምድር ላይ የምታበቃ መስሏቸው ደም ለሚያፈስሱና ለሚያስፈስሱ ወዮላቸው።
*
በመጨረሻም በየመክሊታችን ዘወትር ዛሬ ምን ሠራሁ? ብለን በመጠየቅ ቀኑን ማጠናቀቅ ነገን ያለእርባና እንዳናሳልፍ ይረዳናል።
ለአዕምሯችን እንቶ ፈንቶ (አሰስ ገሰስ) አንጋብዘው። ለሰውነታችም ትርኪ ምርኪ አናግበሰብስ። ጥጋብ ቁንጣንን ፥ ቁንጣን እድሜን አሳጥሮ አንጎልን ደፍኖ ያጠፋልና።
(በተለያዩ ወቅቶች አንብቤያቸው በአእምሮዬ ሰሌዳ የተሰደሩትን አሳክቼ፤ የትላንትና 01/08/ 2013 ውሎዬን ገመገምሁ፦
ኮልፌ ለቅሶ ደርሼ ቤተሰብ አፅናንቼ፣ የእድሜ ዘመን ጓደኛዬን “አንድነት ፓርክ” ወስጄ ጋብዤ፣ ከባለቤቴና ልጄ ጋር ለጥቂት ሰአታት አብሬ ወጣ ብዬ፣ ከሰፈር ሰዎች ጋር በፀጥታ ዙሪያ ተወያይቼ፣ ስድስት የሠፈር ህፃናትን ሰብስቤ ለአጭር ጊዜ አስተምሬና “ቹቹዋ – ቹቹዋ” _ “ሮዛ ሮዚና” አጫውቼ፣ ባይስክል አስነድቼ፣ እንደተለመደው ከመፅሐፍ ቅዱስ ክፍል አንብቤ፣ የሀሩን ያህያን “The Evolution Deceit” አንብቤና የፌስቡክ አስተያየቶችን ቃኝቼ፣ በእለቱ አስቀይሜ እንደሁ ብዬ ፈጣሪዬን ይቅር በለኝ፤ ህሊናዬን እባክህ መቼ እንደምታልፍ አታውቅምና ክፉ ሀሳብ አታመንጭ ብዬ ተሟገትሁትና ከሌሊቱ 10:00 ሰአት ለመተኛት ወስኜ እነሆ ሩብ ደቂቃ ያህል ቀረኝ።
የትኛውንም  ሀሳብ የምፅፈው ወይም የምሰነዝረው እናት ሀገሬን ኢትዮጵያ እና ህዝቧን እጠቅማለሁ ብዬ ነው። በዚህ ንፁህ መሻቴ ላስቀይማችሁ የማይገባ ወገኖቼን ሳላውቅ ካስቀየምኩ ይቅር በሉኝ። መቀየም ያለባቸው (ገዳዮችና አስገዳዮች፤ አሊያም በጥላቻ የተሞሉ ህዳጣን) ቢቀየሙ ምንም ማድረግ አልችልም ፈጣሪ ልቦናቸውን ይፈውስ።
መልካም ጊዜን ተመኘሁላችሁ።
ታየ ቦጋለ አረጋ (ኢልመ ደሱ ኦዳ)
ዘነጌሌ ቦረና ቦረና_ወጉጂ
ሚያዝያ 2013
ከሁላችንም ከተማ አዲስ አበባ
Filed in: Amharic