>

«ሰዶ መሳደድ ካላማረህ፣ ሠላምህን በጄኖሳይድ አትለውጥም...,!!!» (አሰፋ ሀይሉ)

«ሰዶ መሳደድ ካላማረህ፣ ሠላምህን በጄኖሳይድ አትለውጥም…,!!!»

አሰፋ ሀይሉ

— የማይሞት ትምህርት፣ ከሩዋንዳው ሠላም አስከባሪ አዛዥ፣ ከጄ/ል ሮሚዮ ደሌር
በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት አዛዥ የነበረው ካናዳዊው ጄነራል ሮሚዮ ደሌር በመካከሉ ቆሞ ያየውን ያን ዘግናኝ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ያሳተማቸውን ሁለት መጽሐፍት ከዚህ በፊት በፌስቡክ ገጼ ለአንባብያን አስተዋውቄያለሁ፡፡ አንደኛው «Shake Hands with the Devil» የሚለውና የሩዋንዳው ጭፍጨፋ ከመጀመሩ በፊት ስለነበረው ሁኔታ በአካል ተዘዋውሮ የታዘበውን እውነት፣ ጭፍጨፋው ተጀምሮ እስኪጨረስ የነበረውን አሰቃቂ ሂደት፣ እና ጭፍጨፋው ያበቃበትን መንገድ የዘገበበት የዓይን እማኝ ማስታወሻው ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ እጅግ እጅግ ጠቃሚ የአይን እማኝ ማስታወሻ ነው፡፡ እንደ እኛ የዘር ጭፍጨፋ የተደቀነበት ሕዝብ ሁሉ ሊያነበው የሚገባ እጅግ አስተማሪና አስጠንቃቂ መጽሐፍ ነው፡፡
ሁለተኛው የጄኔራል ሮሚዮ ደሌር መጽሐፍ «They Fight Like Soldiers They Die Like Children» የሚለው ሲሆን፣ በተለይ የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ሩዋንዳውያኑን በጊዜ ከጭፍጨፋው ሊታደጋቸው ሲችል ያሳየውን ታሪክ ይቅር የማይለው ሰብዓዊ ኃላፊነትን የመሸሽና የምንተዳዬ አቋም አጠናክሮ ያሳየበትና፣ በተለይ ደግሞ በሩዋንዳው ጭፍጨፋ ወቅት ገጀራና ክላሽ አነግበው የተሰማሩት አብዛኞቹ ለአካለ መጠን ያላደረሱ ህጻናት መሆናቸውን በዝርዝር ያሳየበት መጽሐፉ ነው፡፡
በዚህ ሁለተኛው መጽሐፉ የራሱን የልጅነት የቦይ ስካውት አስተዳደግ በሩዋንዳው ተሞክሮው ካገኛቸው የህጻን ወታደሮች ተሞክሮ ጋር በማወዳደር የሩዋንዳውያኑን ህጻናት ሰቆቃ፣ ጭካኔ፣ አሳዛኝ የእልቂት መጠቀሚያነት፣ እና ልብ ሰባሪ ሞትና የግጭት ሰለባነት ያወሳበትን ልብ የሚነካ ታሪክ እናገኛለን፡፡ ጄ/ል ሮሚዮ ደሌር በሁለተኛው መጽሐፉ ወቅት እንቅልፍ እንደሌለው፣ ከባድ ብስጭትና ፀፀት ተሸክሞ እንደሚኖርና ከዚያም አልፎ ወደ ሀገሩ ካናዳ ከተመለሰ በኋላ በማያውቀው በል-በል በሚል ውስጣዊ ግፊት ተመርቶ መኪናውን ከድልድይ ላይ ወደ ገደል ከስክሶ ራሱን ለማጥፋት ያደረበገው ሙከራ እንደከሸፈና በደረሰበት ጉዳት ማገገሚያ መግባቱን በጥቂቱ ጠቅሶልን ነበር፡፡
በዓለም እየዞረ ስለ ጄኖሳይድና መዘዙ፣ በሩዋንዳ ስላጋጠመው ሆረር፣ እንዲሁም በብቃት ግዳጁን የሚወጣ ሠላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ሲያስተምርና ተሞክሮውን ሲያካፍል የቆየው ጄ/ል ሮሚዮ ደሌር አሁን ደግሞ ሶስተኛ መጽሐፉን አሳትሟል፡፡ በዚህ «Waiting for First Light – My Ongoing Battle with PTSD» በሚል መጽሐፉ ሮሚዮ ደሌር ቀደም ብሎ የጀመረውን ከሩዋንዳው ጭፍጨፋ ማግስት ጀምሮ የደረሰበትን የአዕምሮ ስቃይ፣ እረፍት ማጣት፣ ከቤተሰቡና ከወዳጆች መገለል፣ የማያቋርጥ በደም የተጨማለቀ አሰቃቂ ህልም፣ በሰው ልጅ የተቆራረጡ አካሎች ስለተሞላው የቀንና የሌሊት ቅዠቶቹ፣ እና ሊያገግም እንዳይችል ሆኖ ስለተቀየረው ማንነቱ፣ በጦርነት አካሉን አጥቶ ወደሀገሩ እንደተመለሰ ወታደር እርሱም ጤነኛ አዕምሮውን አጥቶ ጎዶሎ ከሆነው ከአዲስ ህይወቱ ጋር እንደ አዲስ ለመለማመድ የፈጀበትን ትግልና የገጠመውን ፈተና ይተርክልናል፡፡
በዚህ ሶስተኛ መጽሐፉ ሌተና ጄኔራል ሮሚዮ ደሌር በዚህ መጽሐፉ የሚነግረን ከሩዋንዳው ጭፍጨፋ በኋላ ያጋጠመውንና እስካሁንም እያሰቃየው የሚገኘውን ከብዙ አሰቃቂ አደጋና ትዕይንቶች ተርፈው የወጡ ሰዎች የሚደርስባቸውን የአካልና የስነልቦና ቀውስ «ፒ.ቲ.ኤስ.ዲ.»- PTSD (Post-Traumatic Stress Disorder) ነው፡፡ ብዙዎች ከአሰቃቂ ጦርነት ተርፈው የመጡ ወታደሮች ለዚህ ዓይነቱ ሰቆቃ-ወለድ የአዕምሮ ጭንቀት ይዳረጋሉ፡፡ ከኢራቅ፣ አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ወዘተ የተመለሱ የአሜሪካ ወታደሮች ብዙዎቹ በዚህ ህመም ይሰቃያሉ፣ ብዙዎቹም ህይወታውን በገዛ እጃቸው እያጠፉ ስለተገኙ ለረዥም ወራት የሚቆይ የስነልቦና ምክር አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡
ይህ ከሰቆቃ ሥፍራ የተረፉ ሰዎች የሚያጋጥማቸው የሳይኪያትሪ ችግር ክፋቱ በተጠቂዎቹ ላይ ብቻ የሚገታ አለመሆኑንም ይነግረናል ጄ/ል ሮሚዮ ደሌር፡፡ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውም የህመሙ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ፒቲኤስዲ ያለበት ሰው በሚያሳየው የባህርይ ለውጥና ብስጭት፣ በአልኮል መጠጥ ስካር የመደበቅና የመዘፈቅ ጦስ፣ አስፈሪ ቅዠትና ራስንና አካባቢን መርሳት፣ ፍርሃትና ከማህበራዊ ህይወት መገለል፣ ወዘተ. በሰለባዎቹ የቅርብ ቤተሰቦች ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከባድ ነው፡፡ የሩዋንዳው ጭፍጨፋ ቢያበቃም በሰቆቃው ውስጥ ላለፉት ግን ግብግቡ ገና አላበቃም፡፡ ሮሚዮ ደሌርን ውቅያኖስን ተሻግሮ በሄደበት እንደ ጥላ እየተከተለ ሰላሙን ይነሳዋል፡፡
ከሩዋንዳው ጭፍጨፋ መልስ በሀገርቤቱ በሠላም እየኖረ በድንገት ከድልድይ ራሱን ሊከሰክስ ሞክሯል፡፡ የወላጅ አባቱን 50 ዓመት የቆየ የዛገ የፂም መላጫ አውጥቶ እጁንና እግሩን እየገዘገዘ ባኞ ቤቱን በደም አጥለቅልቆት ተደርሶበት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል፡፡ አዕምሮውን ለማሳረፍ በሄደበት መናፈሻ ፓርክ ውስጥ ጠርሙስ ሙሉ ውስኪ ጠጥቶ ራሱን ስቶ በወደቀበት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ደርሰው በአምቡላንስ አፋፍሰው ህይወቱን አትርፈውታል፡፡
ሮሚዮ ከዚህ ድርጊት በላይ በድንጋጤ የደረቀው በወቅቱ ለህክምና እርዳታ የተጠጉትን ሃኪሞች «ግደሉኝ! እባካችሁ ግደሉኝ! ስለፈጠራችሁ አምላክ ግደሉኝ!» እያለ እንባውን እያዘራ በተኮላተፈ አንደበት እስከመለመን መድረሱ ሲነገረው ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ድርጊቶች ሲፈጽም አይታወቀውም፡፡ በል-በል የሚል ውስጣዊ ሰይጣናዊ ሃሳብ ነው የሚገፋፋው፡፡ የእርሱ ዕድል እንደ ግዑዝ መታዘዝ ብቻ ነው፡፡ ስንት ሠራዊት በስንት ጦርሜዳ የመራ የጦር ጄነራል፣ በጄኖሳይድ ጭፍጨፋ ማግስት የማያውቀው የገዛ ቅዠቱ ታዛዥ ብቻ ሆኖ ሲገኝ ያሳዝናል፡፡ ደሌር በሚገርም ግልጽነትና ቀናነት የገጠመውን ፈተናና፣ ባለፉት 20 ምናምን ዓመታት ወደ ሰላማዊ አዕምሮውና መደበኛ ሕይወቱ ለመመለስ የገጠመውን የማያቋርጥ ትግል ይመሰክራል፡፡
ሌ/ጄኔራል ሮሚዮ ደሌር በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ በሚሆኑ ሀገራት የአገልግሎት አድማሱን ለማዳረስ የቻለ የህጻናት ወታደሮችን ወደ ሰላማዊ ህይወት የሚመለሱበትን መንገድ የሚያመቻች ግብረሰናይ ድርጅትና ፋውንዴሽን በስሙ መሥርቶ በጥላቻ ምድር በቅለው ገና በጮርቃ ዕድሜያቸው ወደ ደም ማፋሰስ ተግባራት እንዲገቡ የተደረጉ ያልታደሉ የምድሪቱን ጎስቋላ ህጻናት ህይወት ለመታደግ እየማሰነ ይገኛል፡፡ ለማስቆም ላልቻለው የዘር ጭፍጨፋ የአዕምሮ ዕረፍት የሚሰጠውን ማካካሻ በጎ ተግባር እያከናወነ ይመስለኛል፡፡ ከልብ ሳላደንቀውና ሳላመሰግነው ማለፍ ይከብደኛል፡፡
ይህን መጽሐፍ ማግኘት የሚችል ሰው ቢያነበው እጅግ ብዙ ቁምነገሮች ይማርበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት አማራውን ለይተው የዘር ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) እያከናወኑ የሚገኙት የኦሮሙማው አጥፍቶ-ጠፊ ጨፍጫፊዎች – ይህ የጭፍጨፋ ጅማሯቸውና ጥሪያቸው – በእነሱ መቃብር ላይ እንደሚደመደም ማወቅ ብቻ አይደለም፣ የሰውን ልጅ ጨፍጭፈው የትም ማምለጥ እንደማይችሉ፣ ከህግና ከኢትዮጵያውያን ፍርድ እናመልጣለን የሚል ህልም ካላቸው፣ ከህግና ፍርድ መዳፍ የማምለጥ ዕድል እንኳ ቢኖራቸው፣ ዕድሜያቸውን ሙሉ ከሚከተላቸው የአዕምሮ ስቃይና የህሊና ፍርድ ማምለጥ ግን ከቶውኑ እንደማይችሉ – ይህ የሌተና ጄኔራል ሮሚዮ ደሌር መጽሐፍ ትልቅ ምስክር ነው፡፡ የኦሮሞ የዘር ጨፍጫፊዎች ሆይ፦ የክፋት እጃችሁን ከአማራው ሕዝብ ላይ አንሱ!
ተቀድቶ የማያልቅ ፍቅር ለዓለሙ ሁሉ እንዲበዛ የዘወትር ምኞቴ ነው፡፡ ሠላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን፡፡ ፈጣሪ የአማራን ህዝብ ይጠብቅ!
ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም!
Filed in: Amharic