‹‹ኢህአዴግ በጭቆና ውስጥ ጸጥ ብሎ የተቀመጠን ሕዝብ እየቆሰቆሰ ነው››
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ከቃሊቲ እስር ቤት
( በኤሊያስ ገብሩ – ጋዜጠኛ)
ሁለቱም ፍጹም ሰላማዊነት፣ እርጋታ፣ ትህትናና ፈገግታ አብሯቸው ነበር፡፡ ያው ሁለቱንም በአንድ ጊዜ ማናገር ስለማይቻል ተነጣጥለን ማውጋት ግዴታ ነበርና ጥቂት ከአንዷለም ጋር ከተጨዋወትን በኋላ ከእሴው ጋር አወጋን፡፡
እስክንድር የፊታችን ማክሰኞ፣ ሕዳር 2 ቀን 2007 ዓ.ም ፍርደ ቤት ስለምቀርብበት የክስ ጉዳይ አንስቶ የሚሰማውን ነገረኝ፤ ጠንካራ ምክርም ለገሰኝ፡፡ የክሱ እንደምታንም ባላሰብኩት መንገድ አስረዳኝ፡፡ (ይህ ግላዊ ምክር ስለሆነ ልለፈው)
እስክንድርን ከታሰረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ ጠይቄዋለሁ፡፡ ስለራሱ መናገር አይፈልግም፡፡ ግን ትናንት ባተለመደ መልኩ ስለራሱ ልቡን ከፍቶ አወጋኝ፡፡ በተለይ ስለፈጠሪው! ሃሳቡን እንዲህ አስቀመጥኩት፡፡
‹‹ኤልያስ፣ እስር ለእንደእኔ አይነት፣ ቤተሰብ ለመሰረተ እና ልጅ ለወለደ ሰው ትንሽ ሊከብድ ይችላል፡፡ ስለባለቤትህ እና ልጅህ ሁሌ ታስባለህ፤ ኃላፊነት አለብህና! ነገር ግን፣ በሌላ መልኩ፣ በመታሰሬ ሎተሪ እንደወጣልኝ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ እስሬ፣ ጥሩ ክርስቲያን፣ ሰውና ታጋይ አድርጎኛል፡፡ አሁን በጣም ሰላም ይሰማኛል፡፡ ክርስቶስን በጣም እንዳውቀው አድርጎኛል፡፡ ፍቅሩ ምን ያህል እንደሆነም ገብቶኛል፡፡ ይህን በመረዳቴ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ መታሰሬ መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ እንዳነብ አስችሎኛል፡፡ ባልታሰር ኖሮ እንዲህ የምሆን አይመስለኝም፡፡ ለሌሎች ነገሮች ቅድሚያ እሰጥ ነበር፡፡ ግን ቀዳሚው መሆን ያለበት አምላክህን ማወቅ ነው፡፡ ነገ፣ ይበልጥ የተሻልኩ ሰው እሆናለሁ፡፡ …››
እስክንድር ከላይ ከጠቀስኩላችሁ ሀሳብ አስከትሎ በአሁን ወቅት በሀገሪቷ ላይ ስላለው ጭቆና በጠባቂ ፖሊሶች ፊት ሲናገር ያ ፍጹም የተለመደ ድፍረቱ እና ትህትናው አብሮት ነበር፡፡ እንዲህም አለ፡-
‹‹የስደት፣ የእስርና የክስ መብዛት ሥርዓቱ ያለበትን ከባድ ችግር በግልጽ ያሳያል፡፡ ኢህአዴግ በጭቆና ውስጥ ጸጥ ብሎ የተቀመጠን ሕዝብ እየቆሰቆሰ ነው፡፡ (ከዚህ ጋር በተያያዘ አፈታሪክ ነው ብሎ አንድ ሀገራዊ ምሳሌ ነገረኝ) ይህ ነገ በራሱ ላይ መዘዝ ያመጣበታል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ ሥርዓቱ እንዲህ በማድረጉ (የስደት፣ የእስርና የክስ መብዛት) ነገ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ሳይፈልግ እና ባለማወቅ አበርክቶት እያደረገ ነው፡፡ አለመረጋጋት ይህን ይፈጥራል፡፡ …››
እስክንድር ውስጠ ወይራ ንግግር ተናግሯል፤ ልብ ያለው ልብ ይበል!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!