>

አቢይ ለቅጣት መምጣቱን ራሱስ ያውቅ ይሆን? (አምባቸው ደጀኔ-ከወልዲያ)

አቢይ ለቅጣት መምጣቱን ራሱስ ያውቅ ይሆን?

አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)


ያለንበት ዘመን መቼም የግረባ ዘመን ነው፡፡ መገረብ ምን ማለት እንደሆነ ለማያውቅ ማስታወሱ ለመግባባት ይረዳልና አይከፋም፡፡ ግረባ ከጫት ጋር ይያያዛል፡፡ ጫቱ ሲያልቅ የተቃመውን ማለትም እንጨቱ ላይ ተንቆ የቀረውን ከእንደገና መከለስ ማለት ነው፡፡ በዝርክርክ የወጣትነት ዘመን ያለፈ ይቺን ይቺን ያውቃታል፡፡ እናም ዘመናችን የሁሉም ነገር መገረቢያ መሆኑን ለማስታወስ የደርግን ጭካኔ፣ የወያኔን ዐረመኔነትና ከነዚያ በፊትም ሆነ በኋላ በሀገራችንና በዓለም ዙሪያ የተፈጸሙ የመከራና የግፍ ተግባራትን መቃኘት በቂ ነው፡፡

ግረባ ከተነሣ አይቀር ታዲያ አንድ ታሪክ ባጭሩ ልገርብላችሁ፡፡ አንድ ወቅት በእስራኤል አንድ ጨካኝ ንጉሥ ይነግሣል አሉ፡፡ ሀገሪቱና ሕዝቡ ልክ እንደኛ እንዳሁኑ እሳት ይነድባቸው ገባ፡፡ ድንበር ዘለል ጦርነቱ፣ የርስ በርስ ግጭቱ፣ አስተዳደራዊ በደሉ፣ ርሀቡ፣ ድርቁ፣ ወዘተ. ሕዝቡን በወያኔ አማርንኛ ጠርንፈው ያዙት፡፡ ያኔ አገር ምድሩ ተጨነቀ፤ ክፉኛ ታመሰ፡፡ ለም አፈርና ሣር ቅጠል ሳይቀሩ ለምግብነት ይውሉ ገቡ፡፡  ፈጣሪ ያንን ንጉሥ እንዲያነሳላቸው ሕዝቡ አምርሮ ያለቅስና ይጸልይ ገባ፡፡ “አንሳልን!” ብሎ እሪ አለ፡፡

የተላከበትን ዓላማ ጠንቅቆ የተረዳው ንጉሥ  “እስኪ የኔን ስም በጥሩ የሚያነሳ ካገኛችሁ ፈልጉና አምጡልኝ” በማለት ባለሟሎቹን አዘዛቸውና በየሥፍው አሰማራ፡፡ ሁሉም ሕዝብ ንጉሡን እንዲያነሳላቸው ለፈጣሪ እዬዬ ሲል አንዲት ባልቴት ግን አንድ ጥጋት ይዛ ለንጉሡ ዕድሜና ጤና ስትለምን በዚያ አካባቢ የተላኩ ቃፊሮች አገኟት፡፡ ያቺንም አሮጊት እያዋከቡ ወደንጉሡ አመጡ፡፡ የሆነውም ለንጉሡ ነገሩት፡፡

ንጉሡም “አንቺ ሴት! እኔ ደግ ንጉሥ እንዳልሆንኩና ሕዝብም እንደማይወደኝ – ይልቁንም እግዚአብሔር እንዲያነሳኝ እንደሚጸልይብኝና እግዚዖ እንደሚልብኝ አውቃለሁ፡፡ አንቺ ታዲያ በየትኛው ደግ ሥራየ ነው እንዲህ ለኔ ዕድሜና ጤና የምትጸልይልኝ?” በማለት ይጠይቃታል፡፡ ባልቴቷም እንዲህ ትመልስታለች፡- “ንጉሥ ሆይ እውነትህን ነው፤ የለዬለህ ጨካኝና ዐረመኔ ነህ፡፡ በአንተም ክፉ ሥራ ሀገርና ሕዝብ በድኝ እሳት እየነደዱ ነው፡፡ ግን አንተ የተካኸው አባትህም እንዳንተው ክፉ ነበር፡፡ የርሱ ክፋት ግን ካንተ ይሻል ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ታዲያ ሕዝቡ አባትህን ለፈጣሪ “ያንሳልን” ብሎ ጸለየ፤ አነሳለትም፡፡ ነግር ግን ከእርሱ የባስክ አንተን ተካ፡፡ ስለዚህ ላንተ የምጸልየው አንተን ወስዶ ካንተ የከፋ እንዳያመጣና ሕዝቡ አሁን ካለበት ስቃይ የባሰ ስቃይ እንዳይደርስበት በመስጋት እንጂ ለአንተ አስቤ እንዳይመስልህ፡፡” (እነዳንኤል ክብረት፣ ሠርጸ ፍሬስብሃት፣ ንዋይ ደበበ፣ አለማየሁ ገ/ማርያም፣ ዮናስ ዘውዴ፣  ወዘተ. ለዚህ ይሆን አቢይን የወደዱልን? ኢትዮጵያውያን በሚገርም የአስተሳሰብ ማዶዎች ላይ የመገኘታችን ምሥጢር ሁል ጊዜ ይገርመኛል – በነገራችን ላይ፡፡)

ግሩም ታሪክ ነው አይደል? ከኛው ታሪክ ጋር አልተመሳሰለባችሁም?

ለኔ ግጥም አድርጎ ነው የተመሳሰለብኝ፡፡ ደርግን አማረርን፤ እውነት ነው በብዙ ነገር ማማረር ነበረብንና አምርረን አማረንዋል፡፡ በዘመኑ የዘመኑ ወደር-የለሽ ክፉ ነበር፡፡ ይህ ቀረህ የማይባል የተዋጣለት ጨካኝ፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ጥፋቱም ሆነ ልማቱ ለሁሉም መሆኑ ደግሞ አሁንም ድረስ አንድ የሚያጽናና ነገር ነው፡፡ ጊዜውን ጠብቆና በአብዛኞቻችን ጸሎትና ልመና ደርግ ተወገደ፤ ወያኔም ተተካ፡፡

ወያኔ ከደርግ የባሰ የእፉኝት መንግሥት ነበር፡፡ ጭካኔው ወደር አይገኝለትም ብለን በወቅቱና ከወቅቱም በፊት ብዙ ተናግረናል፤ ጽፈናል፡፡ ወያኔ ዘረኛ ነበር፡፡ እልል የተባለለት ሽል መንጣሪ፡፡ አንዱን ዘውግ እላይ አውጥቶ ሌላውን እታች አውርዶ የሚፈጠፍጥ የአድልዖና የሙስና አውራ ነበር፡፡ በዜጎችና በሀገር ላይ የሠራቸው በቃላት ሊገለጹ የሚከብዱ ግፍና በደሎች ወያኔን መቅ ከተቱት፡፡ ስለዚህም ወያኔ በጸሎትም በምህላም በመስዋዕትነትም ዕድሜው ተቀጨና ወደ ታሪክ ማኅደር ተከተተ፡፡ የሥራውን አገኘ፤ እያገኘም ነው – ጦስ ጥምቡሱ በተለይ ለተጋሩና በአጠቃላይ ደግሞ ለሁላችንም መትረፉ ከፋ እንጂ፡፡ የዘሩትን ማጨድ መኖሩን የሚረሱ የየትኛውም ጎራ ጅላጅሎች ለራሳቸውና ለሀገርም አይበጁ፡፡ ቆምንለት ለሚሉት ወገንም አይጠቅሙም፡፡ ከታጥቦ ጭቃ የማያወጣ የኋሊዮሽ ጉዞ!!

ያ ሁሉ አለፈና ከወያኔ ማኅጸን የወጣው ኦነግ/ኦህዲድ ወያኔን በሚያስከነዳ ጭካኔና የሤራ ፖለቲካ ሀገርንና ሕዝብን አሁንና በዚህች ቅጽበት ሳይቀር መቅኖ በማሳጣት ላይ ይገኛል፡፡ “የዱባ ጥጋብ ካለስንቅ ያዘምታል” እንዲሉ አንዳች የታሪክ አጋጣሚ ያገኘ የጎደሎ አስተሳሰብ ድውይ ሁሉ አራት ኪሎን እየተቆጣጠረ ሀገርንና ሕዝብን ጉድ መሥራቱን ቀጥሏል፡፡ እናም እየባሰ እንጂ እየተሻለ የሄደ ነገር በሀገራችን አልታየም – የከዚህ በላዩ ሃሳብ ማሳረጊያ፡፡

አቢይ አህመድ በተፈጥሮው ጨካኝ ላይሆን እንደሚችል በበኩሌ መገመት አይከብደኝም፡፡ ይህ ብላቴና እንዲህ አስመሳይና ብልጥ ሊሆን የቻለው አንዴ ወዶና ፈቅዶ የገባበት የአጋንንት ዓለም አስገድዶት እንጂ ጥሩ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት ለሥልጣን ከመብቃቱ በፊት ያሳያቸው ከነበሩ አንዳንድ መልካም ምግባራት መረዳት ይቻላል፡፡ ዋናው የሀገሪቱን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን ፈርሞ ለገባበት የጨለማው መንግሥት መቶ በመቶ ሊባል በሚችል ደረጃ ማደሩን “አውቆ የተደበቀ…” እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሊረዳው የተገባ ነው፡፡ ግዴላችሁም – አቢይን እንረዳው፤ የሰይጣን ባርያ መሆኑን እንወቅለትና ቢቻል እንጸልይለት፡፡ ከዚያ ባለፈ “አላሠራው ብለው ነው እንጂ እሱ እንዲህ እንዲያ ነበር…” የሚለው ጉንጭ አልፋ ንግግር በተለይ አሁን ሁሉም ነገር ፍንትው ብሎ በሚታይበት ወቅት አያዋጣም፡፡

አቢይ ከአክራሪ ኦሮሞ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት ጋር እየተናበበ የሚሠራቸውን ሀገር አፍራሽ ተልእኮዎች ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ እነዚህን ተንኮሎችና ሤራዎች መካድ ማለት ደግሞ አንድም የኅሊና ዕውርነት ነው አሊያም ሆዳምነትና የዓላማ አንድነት ነው፡፡ ወያኔ በ27 ዓመታት ከጨረሳቸው አማሮች ይልቅ በአቢይና ሽመልስ ጥምር የፌዴራል አመራር ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ያለቁት በቁጥር እጅጉን ይበዛሉ፡፡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለአንድ ጥቁር በነጭ ፖሊስ መገደል ተጸጽቶ በይፋ አስፋልት ላይ በመንበርከክ ሴት ኮረዳ ልጁን ይቅርታ ሲጠይቅና 27 ሚሊዮን ዶላር ካሣ ሲከፍል አቢይ ግን ትናንት ማታ አጣዬ ላይ “የአማራ ሕጻን ማደግ የለበትም” በሚል ግልጽ ፉከራ ሊገድሏቸው ከአውቶቡስ ካወጧቸው ተሣፋሪዎች መካከል ያገኙትን አንድ ሕጻን በሜንጫ ለሁለት ከፍለው የገደሉትን እምቦቃቅላ ጨምሮ አማራ በመሆናቸው ብቻ ስንትና ስንት ዜጎች ሲጨፈጨፉ በቤተ መንግሥት ከቢጤዎቹ ጋር በደስታ ይምነሸነሻል፡፡ 

ለማንኛውም ትግራይ፣ አማራ፣ ሸዋ፣ ኦሮሚያ …. እነዚህ ሁሉ ፈርሰው ይሠራሉ፡፡ ግራኝ አቢይ አህመድ ግራዋ ነው፤ ግራዋ ለዕቃ ማጠቢያነት የሚያገለግል ተክል ነው፡፡ ግራዋው አቢይ በቅርቡ ሙልጭ አድርጎ ያጥበናል – እስካሁን አብዛኞቻችንን ኪሣችንንና የአእምሮ ሰላማችንን እያጠበ ለትልቁ ጽዳት ሲያዘጋጀን ባጅቷል፡፡ ዕንቅልፍ የሚባል የለውም፤ ተልእኮው ታላቅ በመሆኑ ብዙ እየሠራ ነው – በዚህ ሊደነቅ ይገባዋል – ሰው ለዓላማው ቁርጠኛ ሲሆን ያስመሰግነዋል፡፡ የተላከው ኢትዮጵያ እንድትታጠብና እንድትጸዳ ነው፡፡ ቤት ሲጸዳ ደግሞ ብዙ መዘዝ አለው፡፡ አቢይ ይምረኛል ብለህ ደግሞ እንዳትጃጃል፡፡ እርሱ በሥውርም ይሁን በግልጽ የማስገደል ዲያቢሎሣዊ ኃላፊነቱን ይወጣል እንጂ የመማር ድርሻ የአምላክ ብቻ ነውና አቢይን ተስፋ ማድረግ ጉም ከመጨበጥ አንድ ነው፡፡ አቢይ በአላጋጭነትና በመስሎ አዳሪነት እንዲሁም እንደየሁኔታዎች አስገዳጅነት አቋምን በመለዋወጥ ረገድ የሚስተካከለው የለም፡፡ ደግሞም ለማንም አዘኔታ ያለው ፍጡር አይደለም፡፡ ለማስመሰል ከሚያለቅስ ጋር ሊያለቅስ ወይም ያለቀሰ መስሎ ሊታይ ይችላል (ዕንባ ግን ሊወጣው አይችልም፤ አይቼበታለሁ የምትል ካለህ በመረጃ አሳየኝ!)፡፡ ሃይማኖትም የለውም፤ ሃይማኖት ያለው ሰው ሃይማኖትን በማጥፋት ሥራ አይሰማራምና፡፡ 

እንግዲህ ሜዳውም ፈረሱም ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ዐውድማው ተለቅልቆ ኮርማዎቹን እየጠበቀ ነው፡፡ የአንድ ወገን ልበ ድፍን ኮርማ በግልጽ ተከስቶ እያነጠነጠ ነው፡፡ የሚገጥመው ቢያጣ ንጹሓን ገበሬዎችንና ሴቶችን፣ ሕጻናትንና አእሩግን በሰላ ሣንጃ እያረደ፣ የዘመናት ጥሪታቸውንም በእሳት እያነደደ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ለአጨዳ የተሠማራው የአጋንንት መንጋ ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ደግነቱ ይህም ሁሉ ያልፋል፡፡ አቢይ ግን ተልእኮውን እየፈጸመ ስለሆነ ከርሱ የሚጠበቅ ደግ ነገር የለም፡፡ የተላከበትንም ሳይፈጽም ከአራት ኪሎ ንቅንቅ አይልም፡፡ የምርጫውን ነገር ደግሞ እርሱት … በርትተን እንጸልይ ይልቁንስ፡፡ መዳኛችን ከላይ ከሰማዩ ጌታ ከፈጣሪ እንጂ ከታች ከምድር ከሰው አይደለም፡፡ የሃይማኖት አባትም ሆነ ብቁ የሃይማኖት እረኛ ስለሌለን ከነሱም ምንም አንጠብቅ፡፡ የአምልኮት ቤቶች ራሳቸው በደንብ ከሚጸዱ ሥፍራዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡ ሀገራችንን የገደላት ዋናው እንዲያውም መስቀል-ከሰላጤነት ነው፡፡ ይህ ሁሉ መከራ የሚደርስብን አንድም እንኳን ለፈጣሪ ታዛዥ የሆነ ቀዳማዊው ኖኅንና ደኃራዊው ሎጥን የሚተኩ ብፁኣን አገናኝ መኮንኖች መጥፋት ነው፡፡ 

በነገይቷ ኢትዮጵያ አንዳች አወንታዊ ሚና በመጫወት በአንድ ወይ በሌላ አቅጣጫ ትውልድን መታደግ የምትችሉ በመንፈሣዊም (ትምህርትን ጨምሮ) ሆነ በቁሣዊ ሕይወት ጥሩ ደረጃ ላይ ያላችሁ ሰዎች በቀትር እባቦችና በተራቡ ዘንዶዎች እንዳታልቁ በተቻላችሁ መጠን ጥንቃቄ አድርጉ፡፡ ራሳችሁን ጠብቁ፡፡ ዘንዶው ኢትዮጵያን ሰው ለማሳጣት እየተወራጨ በመሆኑ አንዳንድ ስማችሁን መጥራት የሚቸግረኝ ግለሰቦች እባካችሁን ከፈጣሪ ዕርዳታ ጋር የናንተንም ጥንቃቄ አብዙ፡፡ ጊዜው ከባድ መሆኑን እኔ አልነግርህም፤ ታውቀዋለህና፡፡

ለማንኛውም የኦሮሚያን ልዩ ኃይል የሪፓፕሊካን ጦር የሚይዘውን መሣሪያና የሚለብሰውን ልብስ አልብሶና በዘመናዊ ወታደራዊ ተሸከርካሪ ጭኖ ወደ ገበሬዎች መንደር ልኮ በዘር ሐረጋቸው ምክንያት ንፁሓንን የሚያስጨርስን የዲያብሎስ ልዑክ “የሀገሬ ኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ነው” ብሎ ከሚያምን ውታፍ ነቃይ ይሠውራችሁ፡፡ (ይቺ የነሀብትሽ ቃል ስትጥም …. ‹ውታፍ ነቃይ›)፡፡ ሰላም በያላችሁበት፡፡ 

Filed in: Amharic