>

"የሚያንጫጫ ነገር ምን መጣ..?" (አሰፋ ሀይሉ)

“የሚያንጫጫ ነገር ምን መጣ..?”

አሰፋ ሀይሉ

 

የእኛን ጫጫታ እያዩ የብልፅግና ድልቦች በሆዳቸው የሚያስቡትና እርስበርሳቸው የሚነጋገሩት እንዲህ እያሉ ይመስለኛል፦
 
“… አሁን ቆይ ምን እንዲህ የሚያንጫጫ ነገር መጣ? ቤት መቃጠል አዲስ ነገር ነው? መሞትና መግደል ለዚህ ሕዝብ ብርቁ ነው? ተዋቸው ይንጫጩ፣ ተልባ ቢንጫጫ ባንድ ሙቀጫ ነው! ግፋ ቢል ፌስቡክ ላይ ወጥቶ ቢንጫጫ ነው ወሬ አድማቂው፣ እሱም ይዘጋል፣ ምን እንደሚያመጣ እናየዋለን! 
“ይሄ የዕለት ሽሮ ያረረበት ሕዝብ ምን እንዳያመጣ ነው? ይበጥብጥ ተወው፣ መንገድ ይዝጋ፣ ከፈለገ ሱቁ ጥርቅም ብሎ፣ ገበያው እስከ ዝንታለም ጭርርር ብሎለት ይቅር፣ በቅሎ ገመዷን በጠሰች በራሷ አሳጠረች ነው፣ ማን እንደሚጎዳ ያያታል!
“ተሰለፉ፣ ጮሁ፣ ወሬ አቀጣጠሉ፣ የትኛውን ሚሣኤል እንዳይተኩሱብን ነው? ምን እንዳያመጡብን ነው? ጀግና ነኝ ያለ እስቲ ይግጠመንና ይሞክረን፣ ጰርጳራ ሕዝብ! አናውቀውም እንዴ?
“የኤፈርት፣ የጥረት፣ የዲንሾ ቢሊየን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሱ የኢህአዴግ ብልፅግና የንግድ ድርጅቶች ውለው ይግቡ፣ ካድሬው መቼም የሚቃመሰው ፍርፋሪ አያጣም! 24 ሰዓት ጥሮግሮ ጠግቦ ለመብላት መፍጨርጨሩን ትቶ ያላቅሙ እኛ ላይ ልንጠራራ ያለው ይሄ ሕዝብ ግን እንዲህ እንደቀበጠ የጁን ያገኛታል! ተዉት ይቀጥል አመፁን፣ እስቲ ማን እንደሚጉዳ እናየዋለን!
“ተጨማለቀ አሁንስ ይሄ ሕዝብ፣ ድሮም ላበሻ ፊት መስጠት አይገባም! ቆይ ይሄ አሁን የሚያላዝነው ህዝብ እስከዛሬ ወያኔ ቀጥቅጦ ሲገዛው የት ነበር? አሁን እኛ ነፃነት ስለሰጠነው ነው? የታሠረውን ስለለቀቅነው ነው? በስደት ከሚነፋረቅበት ና ብለን በክብር ሀገሩ ስለመለስነው ነው? ጥፍር መነቀል፣ በአጋዚ መቀጥቀጥ፣ ማዕከላዊ መገረፍ ስላስቀረንለት ነው? የትኛው ነገር ነው እንዲህ የሚያንጫጫው ሕዝቡን?
“ድሮም ክብር አይወድለትም ይሄ ሕዝብ! የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን አጣች ሲሆን ከጎኑ ያገኘዋል፣ ይሄ ምስጋና ቢስ ህዝብ! ዋጋውን መስጠት ነው፣ መቀጥቀጥ የለመደ ክብር አይወድለትም፣ ሰው እንዴት የከፈልንለትን ያን ሁሉ መሥዋዕትነት ይረሳል? አሁን ከጁንታው ጋር የምንጋደለው ለማን ብለን ነው? በግላችን የጎደለብን ነገር ነበር? ይሄ ሾርት ሚሞሪያም ህዝብ!
“ኤጭ አሁንስ በዛ፣ ሙቅ አኝኩልኝ አለኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ! ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከመፈጠርስ እዚያው የሩዋንዳ ሠላም አስከባሪ ሆኖ መቅረት ይሻላል! ላይቤሪያ በስንት ጣዕሙ! ለካ መንጌ ወዶ አይደለም ይሄ ሕዝብ ወርቅ ቢያነጥፉለት ፋንዲያ የሚል ነው ያለው!
“ሆሆ፣ ከዚህ በላይ ምን እናርግለት ለሕዝቡ? ደሀ አገር ነች፣ የቻልነውን እያረግን ነው፣ ሕዝቡ ይሄ ካልገባው ገደል ሊገባ ይችላል፣ ይንጫጫ ወደለመደው ፌስቡክ ሄዶ፣ ፌስቡክ ደሞዙን ይክፈለው፣ ፌስቡክ ይጋደልለት፣ ፌስቡክ ሊጡን ያቡካለት እንጀራውን ይጋግርለት፣ ፌስቡክ የቤትኪራዩን ይክፈልለት፣ ፌስቡክ ልጆቹን ያሳድግለት! እስቲ እናየዋለን ምን እንደሚያመጣ!”
እንዲህ ይመስለኛል የሚያስቡት ገዢዎቻችን! ይሄን ፅሑፍ ራሱ ቢያነቡት መልሰው… እንዲህ የሚሉኝ ይመስለኛል፦
“እና ምን ይጠበስ? እንኳን እንደዚህ አሰብን! ተንጫጫ፣ ተንጨርጨር፣ ምን እንደምታመጣ እናይሀለን እስቲ፣ የፌስቡኩ ፍሮይድ? !  ሀሀሀሀ…! ሳይኮሎጂስቱ እስቲ ና ቀረብ ብለህ የምናስበውን በደንብ ንገረን፣ ይሄን ፌስቡክ የምትጠቀጥቅበትን ጥፍር ነበር መንቀል፣ አስኮናኝ! ቆይ እኛን አሳጣሁ ብለህ ስትፈራገጥ ሳታውቀውም ይሁን አውቀኸው የጁንታው ርዝራዥ፣ የግብፅ ተላላኪ ሆነህ እያገለገልክ እንደሆነ አውቀኸዋል ግን? “
ግን ግን አንድ ቀን እንዲሁ እየተሳሳቅንና እየተሳቀቅን፣ እየተናነቅንና እየተናናቅን… በአንዱ ቀን ላይ ሁላችንም ሀባ ሀባችንን የምናገኝ ይመስለኛል! ዕድሜ ይስጠንና ለማየት ያብቃን! እስከዚያ ተስፋ ሳንቆርጥ በአቅማችን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ! Do what you can! Wait and see! Never ever give up! God has a way! God bless Ethiopia!
Filed in: Amharic