>

በቃን-!!! የአማራዊያን ሕዝባዊ እምቢተኝነት አመጽ ትግል አላማ ከመነሻ እስከመድረሻ የሚጓዝበት የትግል መስመርና ይዘት፦ (ወንድወሰን ተክሉ)

በቃን-!!! 
የአማራዊያን ሕዝባዊ እምቢተኝነት አመጽ ትግል አላማ ከመነሻ እስከመድረሻ የሚጓዝበት የትግል መስመርና  ይዘት፦ 
ወንድወሰን ተክሉ

በቃኝ፣ በቃን የመላ አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት የአመጽ ትግል በሚሊዮን የተቆጠሩ አማራዊያን በባህርዳር ፣በደብረማርቆስ ፣በወልዲያ፣በደሴ ኮምቦልቻና በመሰል  አማራዊያን ከተሞች ውስጥ በመውጣት በይፋ ያወጁት የትግላቸው መጠሪያ ስም ነው፡፡ አማራዊያን ስንጨፈጨፍ ዝም ማለታችን በቃን፣በገዛ ሀገራችንና እርስታችን መጤ ሰፋሪ እየተባሉ ተዘርፎና ተገድሎ መባረር መፈናቀሉ በቃን፣ገዳይና አስገዳዮቻችንን ሀገር መሪ መንግስት ናቸው ብሎ ማመን፣ማገልገል፣ታዛዥ ሆኖ መከተልና ብሎም ወደ ተሻለ ስፍራ ያሸጋግሩናል ማለቱ በቃን፣እንደ አማራነታችን የብኩርናችንን መክሊት እረስተንና ትተን የራሳችንን እጣፈንታን ከመወሰን ይልቅ ላሌው እንዲወስንልን ተስማምተን መከተሉና አብሮም በሎሌነት መጓዙ በቃን፣የአማራዊያንን መጨፍጨፍ እያዩ እየሰሙ ማየትና እንዳላዩና እንዳልሰሙ ሆኖ ዝም ብሎ መተኛቱ በቃን፣በውስጥችን ሆኖ አማራዊ ማንነትን ሳይጎናጸፍ የአማራ ተወካይ ነኝ በሚለን የውስጥ ጠላት ብአዴን መወከሉና ብሎም ተገዢ ሆኖ አብሮ ማዝገሙ በቃን እና እንዲሁም በህልውናችን ጉዳይ መፍትሄን ከመንግስት ነኝ ባዩ ጸረ አማራዊ ከሆነው አቢይ መራሹ ኦነጋዊው የኦህዴድ ብልጽግና መንግስት ስር  በባርነት መኖር በቃኝ ሲል ማእበላዊ በሆነ ህዝባዊ ትእይንት በግልጽ አደባባይ በይፋ አውጇል፡፡
የመላ አማራዊያኑ በቃን ህዝባዊ እምቢተኝነት የአመጽ ትግል በሁለት መሰረታዊ የመታገያ መድረክና ስፍራ ተከፍሎ የተቀጣጠለ ሲሆን አንደኛውና ዋነኛው በቃኝ በሚል መሪ የመታገያ ቃል ስር በሚሊዮን የተቆጠሩ አማራዊያን በአማራ ግዛት ውስጥ ያቀጣጠሉት  ትግል ሲሆን ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ከዚህ ከሀገር ቤቱ ይፋ ትግላዊ እወጃ ቀደም ብሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ታውጆ ትግሉን እያጧጧፈ ያለው አለም አቀፉ የአማራዊያን ንቅናቄ ሲሆን የዚህ ጽሁፍ ዋና ትኩረትና አስኳል በሚሊዮን አማራዊያን በአማራ ከተሞች በይፋ ስለተበሰረው በቃን የአማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት የአመጽ ትግል ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን በቅድሚያ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
በቃን -!!! የመላ አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት የአመጽ ትግል ዋና አላማና ንቅናቄው የተፈጠረበት መንስኤን በአጭር ወፍ በረር አገላለጽ ስናስቀምጥ
በቃን-!!! የአማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት የአመጽ ትግልን የወለዱት እናትና አባቱ ፋሺስታዊው የኦሮሙማ አይዲኦሎጂ በነገደ አማራ ህዝብ ላይ ያወጀው የዘር ማጥፋት የጭፍጨፋ ዘመቻና እያካሄደ ያለው ወረራ ነው በማለት በአጭሩ ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ይህንን ሂደትና ሁኔታን ጀስቲፋይ ለማድረግ በአማራ ህዝብ ላይ የተፈጸመውን እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ የሆነውን ጭፍጨፋን በመዘርዘር ጊዜያችንን ማባከን ይገባናል ብለን አናስብም፡፡  ሆኖም በአጭር አገላለጽ በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ውስጥ በገፍ እየተፈጸመ ስንሰማው የነበረው በመቶ የሚቆጠሩ አማራ ተወላጆች ተጨፈጨፉ የሚለው ዜና በፍጥነት አድጎና ተመንድጎ አንድ ከተማ ሙሉ ህዝብና ንብረታዊ ተቋም እንዳለ ወደመ -ያውም በአማራ ክልላዊ መንግስት ግዛት ውስጥ ወደሚለው እጅግ ግዙፍና መጠነ ሰፊ የጭፍጨፋ ዘመቻ ደረጃ በመድረሳችን የተነሳ አማራው እጅግ ዘግይቶና ሲበዛም እጅግ ትእግስተኛ በመሆኑ ዘግይቶ የነበረን ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ማእበላዊ በሆነ ይዘትና ቁርጠኝነት የተጀመረ መሆኑን በስሱ መግለጽ ይገባል፡፡
በቃን-!!! የአማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት አመጽ ትግል በዚህ መልኩ የተወለደ በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ሁለገብ ህዝባዊ ትግል መሆኑን ከተገነዘብን በኃላ የዚህ ትግል መሰረታዊ የሚባሉትን የመታገያ ጥያቄዎችንና መልሶቻቸውን በግልጽ አስፍሮ በማስቀመጡ አስፈላጊነት ላይ አስማሚ ስሜትና መግባባት ስላለ እንደሚከተለው ተመላክቷል፡፡
1ኛ- የበቃን-!!! አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል ጥያቄዎች
– ከሚያዚያ 24 ቀን 2018 የኦህዴዱ አቢይ አህመድ አሊ ወደ ስልጣን በመምጣት ቃለ መሃላ ከያዘበት እለት አንስቶ እስከ አሁን ድረስ – በተለያየ ዘዴ ስልትና ምክንያት ፦
-በግፍ ለተጨፈጨፋ አማራዊያን ህይወት ተጠያቂ የሆነውን መንግስታዊና መንግስታዊም ያልሆነውን ማንኛውንም ኃይል ባለስልጣናትን (ከአቢይና ከሽመልስ ጀምሮ) ለፍትህ ማቅረብ
-በግፍ ቤት ንብረታቸውን ተነጥቀውና ተዘርፈው ለተፈናቀሉ አማራዊያን በሙሉ -ከየተፈናቀሉበት ክልላዊ መስተዳድሮችና ብሎም ከፌዴራሉ መንግስት በዓለም አቀፍ የካሳ ተመን መሰረት የህይወት የሞራልና የንብረት ካሳ በአስቸኳይ እንዲከፈላቸው ማድረግ
– ከኦሮሚያ ከቤኒሻንጉልና ጉምዝ ክልል በግፍ ተፈናቅለው ዛሬ በተለያዩ የመጠለያ ካምፖች ውስጥ እየተሰቃዩ ያሉትን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አማራዊያን ተፈናቃዮችን ተገቢውን የካሳ ክፍያ እየሰጡ ከበቂ የደህንነትና ዋስትና እና ጥበቃ ጋር በተፈናቀሉበት እርስተ ቀዬአቸው መልሶ ማስፈር
– በቅርቡ እንደየመንና ሶሪያ የወደሙትን አማራዊ ከተሞቻችንን
  -አጣዬን
  -ሸዋ ሮቢትን
  -ካሬ ቆሬንና መሰል የአካባቢ መንደርና ከተሞችን  በኦሮሚያና ፌዴራሉ መንግስት ወጪ በአስቸኳይ የመልሶ ግንባታ እንዲፈጸምና ዛሬ በአካባቢው ሰፍሮ ያለውን ኮማንድ ፖስት በፍጥነት ከአካባቢው ለቆ እንዲወጣ ማድረግ
2ኛ- የበቃን-!!! አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት የፖለቲካ ጥያቄን በተመለከተ
-መላው የአማራ ህዝብ ከፋሺስታዊው የኦሮሙማ ብልጽግና ድርጅት ጋር በጥምረትም ይሁን በትብብራዊ የጋሪዮሽ ግንባር አማራን ወክሎና በአማራው ስም አማራውን እወክለዋለሁ በማለት መንግስት የሆነ ድርጅትም ይሁን ግለሰብን ፈጽሞ እንደማያውቅና ይህንንም መሰረት አድርጎ የፌዴራሉ መንግስት በአማራ ስም አቅፎ የያዛቸውን አማራ ነን ባይ ምኒስትሮችን ባለስልጣናትንና ብሎም አዴፓ የሚባለው ፓርቲ የአማራን ህዝብ የማይወክሉ መሆናቸውን አውቆ የአማራን ፖለቲካዊ ድርሻን ለራሱ ለአማራ እንዲለቅ ማድረግ
– በመላ ኢትዮጲያ የሚኖሩ አማራዊያን ለመኖር በመረጡበት የትኛውም የሀገሪቱ ስፍራ ሙሉ የዜግነት መብታቸው ተክብሮና ተጥብቆላቸው እንደፈለጉ የመምረጥ የመመረጥ ሀብት የማፍራትና በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ተጥብቆ የሚኖሩበትን ሁኔታ መንግስታዊና መዋቅራዊ አድርጎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ
-በአዲስ አበባ ላይ ያለውን የአማራዊያንን እና ብሎም የሌሎች ኢትዮጲያዊያንን እኩል የባለቤትነት መብትን መንግስታዊ ህግ ማድረግና ብሎም ዛሬ የተስፋፋውን የኦሮሚያ ክልልን ልዩ ጥቅምና የመሬት ወረራና ምዝበራን ሙሉ በሙሉ የሚያጥፍ
– የሀገሪቱ መተዳደሪያ ህገ መንግስት በጸረ አማራ ተኮር ቅኝት ላይ ተመስርቶ የተቀረጸ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ጥሎና አፍርሶ ሁሉንም የሀገር ዜጋን ባሳተፈና መጨረሻም ላይ በህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም ) ቀርቦ በአብላጫ ድምጽ ያለፈን ህገመንግስት ለሀገር መተዳደሪያነት ለማብቃት
– ከአርባ አምስት ቀናት በታች ብቻ በቀረው በ6ኛ ሀገር አቀፍ ምርጫ በኦሮሚያ ሱማሌ ድሬደዋ ሀረሪ ትግራይ በማይካሄዱበትና የይስሙላ ምርጫን በአዲስ አበባና በአማራ ክልል ብቻ አካሂዶ የፋሺስታዊውን አቢይ መራሹን የኦህዴድ ብልጽግና ስብስብን በአዲስ አበቤና በአማራዊያን ላይ ለመጫን የታቀደውን ሴራ በማውገዝ በአጠቃላይ ምርጫው በአዲስ አበባና በአማራ እንዳይካሄድ ማድረግና በማሸጋገር
–  የአማራ ክልላዊ መስተዳድር ምክር ቤት ፈርሶና አዴፓም በአማራ ተወካይ ነኝ ባይነቱ በብልጽግና ውስጥ ያለውን ስፍራ አጥፎ በእኛ በአማራዊያን ብቻ በሚካሄድ የአስቸኳይ ጊዜ ምርጫ የአማራ ክልልን የሚመራና የሚያስተዳድር ኃይል መምረጥና ይህ ከሆነ ከ6-12  ወራት ባሉት ጊዜ ውስጥ እውነተኛ የሆነ ነጻ ዴሞክራሲያዊ ሀገር አቀፍ ምርጫ በማካሄድ አማራው ከማንም ጋር አጋርም ሆነ ተለጣፊ ሳይሆን ብቻውን ተሰልፎ በሀገሪቱ ላይ ያለውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ድርሻውን ማስጠበቅ የሚችልበትን ስርዓት ዘርግቶ እውን ለማድረግ የበቃን-!!!አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመታገል ቆርጦና ወስኖ ማእበላዊ በሆነ ሁኔታ በይፍ ጀምራል፡፡
3ኛ- የበቃን-!!! አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል የተነሳበትን አላማ ግብ ለማድረስ የሚጓዝበት የትግል ባቡርን በተመለከተ
ሚሊዮን አማራዊያን በበርካታ የአማራ ከተሞች አደባበይ ወጥተው ያሰሙት ሰላማዊው ትእይንተ ህዝብ ሰልፍ የአማራው ህዝብ በቃኝ ያለውንና ከላይ በመግቢያው ላይ የተዘረዘረውን ዘርፈ ብዙ ግፍ ጭቆና እና ዘረኝነትን ፈጽሞም ቢሆን ከስር መሰረቱ ፈንቅሎ የሚያስቀሩለት የትግል መስክ እንዳልሆነ መላው አማራዊ ይረዳል፡፡ በሰላማዊ ሰልፍ ብቻ እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራትና እንደ አቢይ አይነቱ ፋሺስታዊ ገዢ ኃይል ስልጣን ላይ ባለበት ሁኔታ ለውጥ ያመጣሉ ወይም ተሰሚነት ኖራቸው ቢያንስ የአማራን መጨፍጨፍ ማስቆም ይቻላቸዋል ብሎ የሚያምንና የሚያስብ አንድም አማራዊ እንደሌለ ይታወቃል፡፡
ሆኖም ሰልፎቹ የመላው አማራዊያን የጋሪዮሽ ስሜትና አቋም መግለጫ  ሆነው የሚያገለግሉ የመሆናቸው ጉዳይ የጋራ መግባባት ላይ በመደረሱ የሰልፎቹን በተከታታይ መካሄድ አስፈላጊነት ላይ ብዥታ ውስጥ ሳይገባ ዋናው የህዝባዊ እምቢተኝነቱ ትግል ውስጥ ተይዘውና ተፈጻሚ ከሚደረጉት የመታገያ መንገዶች ውስጥ ጥቂት ያህሉን ብቻ ለማስቀመጥ ያህል፦
– መንግስታዊ ግብር ታክስ ቀረጥና መሰል ክፍያዎችን ሙሉ በሙሉ ማቆም
-መንግስታዊ ስራን የንግድና መሰል የትራንስፖርት ስርጭትን ሙሉ በሙሉ አቁሞ መላ የአማራ ክልልን እንቅስቃሴ አልባ ባዶ በማድረግ
-አሁን ህይወቱና ህልውናው በከፍተኛ አደጋ ላይ የወደቀውን ህዝባችንን ከፋሺስታዊው የአቢይ አህመድ መራሹ የኦህዴድ ኦነግ ብልጽግና ወረራና ታጣቂ ሚሊሺያ ለመከላከል መላውን የአማራ ህዝብ ያሳተፈና በተለይም  የገዢውን ኃይልና ተወካይ ነኝ ባዩን አዴፓን ባላካተተና ባላሳተፈ መልኩ በእያንዳንዱ መንደርና ቀበሌ  በቁጥር ከ80-120 የሚቆጠሩ ህዝብ ጠባቂ ቡድኖችን እያስታጠቁ ህዝባችንን እንዲከላከሉ በማድረግ ጎን ለጎን ሰፊ አማራዊ የሆነ እና በህዝብ ብቻ ተደራጅቶና ሰልጥኖ የሚዘጋጅ የአማራ ጠባቂ ፋኖን መገንባት፡፡
አሁን ግን ያሉንን ፋኖዎች የአማራ ሚሊሺያና ማንኛውንም አማራዊ ታጣቂን አሰባስቦ በየአካባቢው የጎበዝ አለቃ መሪነት ህዝቡን የመጠበቅ ተግባር መስራት
-በአለም አቀፉ የአማራዊያን ንቅናቄ ክንፍ በኩል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረትባቸው ከተወሰነባቸው 18ቱ ባለስልጥናት ዝርዝር ውስጥ አቢይ አህመድ አሊን ጨምሮ የደህንነትና መረጃ ኃላፊውን ተመስገን ጥሩነህን ደመቀ መኮንንና መሰሎችንም በማካታተ ክሱን ማጧጧፍና አለም አቀፍ ዘመቻውን የማፋፋምን ትግል ማካሄድ
-የዳያስፖራው አማራዊ ኃይል በአለም አቀፉ አማራዊያን ንቅናቄ በኩል ለሀገር ቤቱ ተፋላሚ ወገን በገንዘብ በሎጀስቲክስ በቁሳቁስ በመድሃኒት በመረጃ በዲፕሎማሲና በማንቂያ ቅስቀሳ ደጅናዊ ኃይል አድርጎ በማታገል
-የወጣቶችን የሴቶችና የመላ አማራዊያን የመንግስት ሰራተኞችን የሚያንቀሳቅስ የትግል ኃላፊነት በመተለም
እና አሁን ልንዘረዘራቸው እማያስፈልጉን ዘርፈ ብዙ የሆኑ የህዝባዊ እምቢተኛነት መታገያ መንገዶችን ይዞ በቃን!!! የአማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ይታገላል፡፡
4ኛ- በቃን-!!!የአማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል መልስ የሚያገኘው ከማን ነው???
በቃን-!!! የአማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ዛሬ ስልጣን ላይ ያለው ፋሺስታዊው አቢይ መራሹ የኦህዴድ ኦነግ ብልጽግና መንግስት ለሚታገልለት አላማና ላነሳው ጥያቄዎች መልስ አገኛለሁ ብሎ አያምንም አይጠብቅምም፡፡የህዝባዊ እምቢተኝነቱ ንቅናቄ ከአቢይ ብልጽግናም ሆነ ከባህርዳሩ አዴፓ አንዳችም መፍትሄና መልስ አላገኝም ብሎ ሲያምን መልሶቹንና መፍትሄዎቹን በሙሉ በእጁ ያሉ መሆናቸውን በማወቅና በማመን ነው፡፡
የምንታገልለት አላማና ጥያቄ መልስ ያለው በእኛው በአማራዊያን እጅና እጅ ብቻ ያለ ሲሆን ይህም ተግባራዊ ሆኖ ለውጥ መፍጠር የሚችለው የያዝናቸውን መፍትሄዎችና መልሶችን ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያበቃ ስልጣንን በመጨበጥ ብቻ ነው፡፡
ይህ ማለት የአማራ ህዝብ ህልውናዊ አደጋን ማስቆምም ሆነ አክሽፎ ወራሪ ጨፍጫፊዎቹን ሰብሮ ለፍርድ ለማቅረብ ከእኛ ከአማራዊያን በስተቀር ማንም ኃይል ሊፈጽምልን እንደማይችልና እንደማይፈልግም አውቀን ተረድተናል፡፡
ስለዚህ የምንታገለው መንግስት የሚባለውን ቡድን ለጥያቄዎቻችን መልስ እንዲሰጥ ሳይሆን በእኛ በአማራዊያን እጅ ላይ ያለውን መፍትሄ ለመተግበር የምንችልበትን መንግስታዊ ስልጣንን ለመያዝ ብቻ ነው፡፡
ይህ ደግሞ ተፈጥሮአዊ መብታችን የሆነ የማንንም ይሁንታንና ፈቃድ እማንጠይቅበት ብቸኛው የእኛነታችን ህልውና ማስጠበቂያው ቁልፍ መልስ ያለው በእኛው በአማራዊያን እጅ ላይ ብቻ ነው፡፡
እናም የበቃን-!!! አማራዊያን ህዝባዊ እምቢተኝነት ግብ አማራውን የራሱን እጣፈንታን በራሱና በራሱ እጅ ብቻ እንዲሰስን ለማስቻል እንጂ ከከሀዲ ፋሺስታዊ ጨፍጫፊዎቻችን ብልጽግና ኦህዴድ አዴፓ እጅ እንዲሰጠን ለማድረግ አይደለም፡፡
መደምደሚያዊ ማስጠንቀቂያ 
የበቃን-!!!አማራዊያንን ህዝባዊ እምቢተኝነትን ትግል አቅጣጫ ለማስቀየስና አስቶም ለመጥለፍ በፋሺስቱ አቢይና ፓርቲው በኩል ጥቃቅን የስም ማጥፋት ክስ እየመዘዙ ብቅ ይላሉ – ለምሳሌ አብን የግብጽ ተላላኪ ነው ኦሮሙማን መንካት ማለት የኦሮሞን ህዝብ   መንካት ነው ወዘተ መሰል ያቀርባሉ፡፡ አንድም ሰው ለእነዚህ መልስ በመስጠት እንዳይተባበር፡፡
ይህ ትግል የመላ ኢትዮጲያዊያን ትግል ሳይሆን የመላ አማራዊያን ብቻ የህልውና ትግል ነው፡፡ እናም አብን የግብጽ ተላላኪ ሆነ አልሆነ እኛ አማራዊያን ነን የምናውቀው እንጂ ሌላ አውቃለሁ ባይ ስለእኛ እንዲነግረን መፍቀድ አይገባንም፡፡
የፈለጉትን ፕሮፖጋንዳ ይልቀቁ እኛ መላሽ ሳንሆን የራሳችንን የትግል ፕሮግራምና እቅድ መሰረት አድርገን መታገል ብቻ ይገባናል – የአማራ ህልውና ተጠብቆ በሀገሩ በሰላም መኖር የሚችለው በማንም በጎፈቃድ ሳይሆን በእኛ አማራዊያን የተባበረ ክንድና ትግል ብቻና ብቻ ነው-!!!
እናም የጀመርነውን የህልውናችንን ህዝባዊ እምቢተኝነት ትግልን መላው አማራ በአማራዊ አንድነትና ግንባር ታግሎ ለድል ያበቃዋል- አማራዊ አንድነት ይለምልም!!!
ድል ለታላቁ የአማራ ህዝብ-!!!!
Filed in: Amharic