>

እንኳን ለሰሞነ ሕማማት አደረሰን፤ አደረሳችሁ...!!! ( ክርሰቲያን ታደለ)

እንኳን ለሰሞነ ሕማማት አደረሰን፤ አደረሳችሁ…!!!

  ክርሰቲያን ታደለ

የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖች ሆይ፥ ከግማሽ ምዕተዓመት በላይ ሕማማት ላይ ስላለች ስለአገራችን ተግተን እንጸልይ፤ መከራ ስቅለት ላይ ስላለው ሕዝባችንም አልቅሰን ወደ ፈጣሪ እንማጸን!
እንደሄሮድስ ዘመን ሕፃናት የእናታቸው ማኅፀን ጭምር ተተርትሮ ወጥተው ይታረዳሉ። እንደነቅዱስ እስጢፋኖስ ዘመን ምእመናን ሰውነታቸው በገጀራ ይሰነጣጠቃል፤ ይከታተፋል። እንደነቅዱስ ጊዮርጊስ ዘመንም ንጹኃን በእሳት ተቃጠልው አመድ ይሆናሉ። እንደነራሔል ዘመን እናት በልጆቿ  መታረድ ደም ታነባለች። እንደብሉይ ክፋት መጨረሻ ዘመንም በበርባን ፈንታ ንፁኃን እንዲሰቀሉ በፍርድ ወንበር ላይ ጲላጦስን ሆነው የተቀመጡ አሉ።
እንደፈሪሳውያን ነገር እያጠቀሱ ከሳሾች ተነስተዋል። የእቡይነት እርሿቸውን በየቦታው ከንጹኃን ደም ጋር እያፈሰሱ   ምድርን አከረሰሷት። ደሊላዎች ሶምሶናዊ ምስጢራችን አጋልጠው ለጥቃትና ፍጅት ከዳረጉን እነሆ ዘመናት አለፉ።
እንዲህም ሆኖ ከሕማማት በኋላ ስቅለት…ከስቅለቱም በኋላ ፋሲካው እንደሚመጣ አምነን እንናፍቃለን። አምላካችን ሕማማቱን የመጨረሻ ያደርግልን ዘንድ ተንበርክከን…አልቅሰን እንለምነው። ፈጣሪያችን በሕዝባችን ላይ የታወጀውን ስቅለት የመጨረሻ አድርጎልን የፋሲካ ሰዎች ያደርገን ዘንድ በፆለት ደጅ እንጥናው።
በመጽሐፍ የምናውቃቸውን ፈርዖን፣ ሄሮድስና ጲላጦስ በዓይኖቻችን አየን!  በመጽሐፍ በክፋታቸው የምናውቃቸውን ፈሪሳውያንም በእኛ ዘመን ዶክመንተሪ አቀናብረው፤ የሀሰት ክስ ሰነድም ደርሰው ለምክር አቅርበውት አይተን ስለኢትዮጵያና ሕዝቧ ከልባችን አዘንን። ፋሲካው ሲቃረብ ክስ፣ ክህደት፣ እቡይነት፣…ወግ ናቸውና ሕማማቱን ታግሰን በስቅለቱ ወደ ትንሳዔው ለመሻገር እንናፍቃለን።
ለክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ በድጋሚ እንኳን ለሰሞነ ሕማማት አደረሰን፤ አደረሳችሁ። (ደካማውን እኔንም ወልደገብርኤል ብላችሁ አስቡኝ! )
ለቀጣዩ ትውልድ ፋሲካውን እንጂ ሕማማቱንና ስቅለቱን አናወርስም!
Filed in: Amharic