>

አብይ አህመድ ሀገሪቱን ለጨረታ አቅርቧታል! (በፋይናንሺያል ታይምስ ይፋ የወጣ ጥብቅ መረጃ) አሰፋ ሀይሉ

አብይ አህመድ ሀገሪቱን ለጨረታ አቅርቧታል!

(በፋይናንሺያል ታይምስ ይፋ የወጣ ጥብቅ መረጃ)

አሰፋ ሀይሉ

 

*…. በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ቴሌኮም በጥድፊያ ለእነ ቮዳፎን በዝግ ጨረታ ሲቸበቸብ አብይ ለዎርልድ ባንክ ብድር ቀብድ ያስያዘው የኢትዮ ቴሌኮምን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና፣ የኢትዮ ንግድ ባንክን፣ ኤልፓንና የመሣሠሉትን ሀገር አቀፍ መንግሥታዊ የንግድ ተቋማት አቅሙ ላላቸው ዓለማቀፋዊ ቱጃር የውጪ ካምፓኒዎች ፕራይቬታይዝ ለማድረግ (ለመቸብቸብ) በመስማማት መሆኑ ታውቋል።
 
ኢትዮጵያ በኦሮሙማው መደበኛና ኢመደበኛ ሠራዊቶች ከዳር ዳር እየተናጠች ባለችበት፣ እና የዜጎች ደህንነትና ነፃነት ባልተረጋገጠበት በዚህ ወቅት፣ የጨረባ ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ የተነሳው አብይ አህመድ – በሥልጣን ለመቆየት የምዕራቡን ዓለም ድጋፉን እንዲሰጠው ለማድረግ ባለመ ግልፅ ተግባር፣ በዛሬው ዕለት ኢትዮ ቴሌኮምን ለውጭ ሀገራት ተጫራቾች በቢሊዮን ዶላሮች ለመሸቀጥ ጨረታ ሲያካሂድ መዋሉን የዓለማቀፉ የፋይናንስ አውታር ይፋ አድርጓል።
አብይ አህመድ ያጫረታቸው ግዙፍ የውጭ ሀገራት ካምፓኒዎች የደቡብ አፍሪካና ኬንያን ቴሌኮም (እና የሞባይል ባንኪንግ) አገልግሎቶችን የተቆጣጠሩትን መልታይናሽናል ሞኖፖሊዎች፦ ኤምቲኤንን፣ ሳፋሪኮምን፣ ቮዳፎንንና፣ ቮዳኮምን መሆኑን የፌይናንሺያል ታይምስ ዘገባ ገልጿል።
በዚህ የምርጫ ዋዜማ ላይ እና ባልተረጋጋና ለኢንቬስትመንት አመቺ ባልሆነ ሀገራዊ ቀውስ ወቅት አብይ አህመድ ኢትዮ ቴሌኮምን ማጫረቱ ጅልነት መሆኑን ጠቁሟል። በምክንያትም ያቀረበው ለምሳሌ ትላልቅ የአሜሪካና አውሮፓ ካምፓኒዎች በሀገሪቱ በነገሰው ቀውስ አፈግፍገው ጥሩና ተወዳዳሪ የግዢ ዋጋ ለሀገሪቱ ሊያቀርቡ የሚችሉበት ዕድል በሌለበት የሀገሪቱን ከፍተኛ የቴሌኮም ሞኖፖሊ ለመሸጥ መሯሯጥ ግራ አጋቢ መሆኑን ገልጿል።
ከጥቂት ቀናት በፊት በአሜሪካ የሚዘወረው የዓለም ባንክ ለአብይ አህመድ የ907 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ግራንት ሲፈቅድ ብዙዎች አብይ አህመድ በለውጡ ምን ለመፈፀም ቅድመ ሁኔታ እንደተፈራረመ በድብቅ የተያዘ ቢሆንም፣ በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ቴሌኮም በጥድፊያ ለእነ ቮዳፎን በዝግ ጨረታ ሲቸበቸብ አብይ ለዎርልድ ባንክ ብድር ቀብድ ያስያዘው የኢትዮ ቴሌኮምን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና፣ የኢትዮ ንግድ ባንክን፣ ኤልፓንና የመሣሠሉትን ሀገር አቀፍ መንግሥታዊ የንግድ ተቋማት አቅሙ ላላቸው ዓለማቀፋዊ ቱጃር የውጪ ካምፓኒዎች ፕራይቬታይዝ ለማድረግ (ለመቸብቸብ) በመስማማት መሆኑ ታውቋል።
ለመሆኑ የአብይ አህመድ ኦሮሙማ መንግሥት ገና የህዝብ ይሁንታና ህጋዊ ቅቡልነትን ባላገኘበት በዚህ የምርጫ ዋዜማ ወቅት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብቶች በጨረታ የመቸብቸብ መብት ማን ሰጠው?
ነገ በምርጫው ቢሸነፍ ውድቅ በሚሆን ጨረታ አገሪቱን እየሸጣት እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ስለዚህ የኦሮሙማው (የአብይ አህመድ) ዓላማ በምዕራቡ ዓለም ሀያላን ሀገሮች ፊት ቃሉን የጠበቀ አዘማኝ መሪና ታላቅ ፕራይቬታይዜሽንን ያካሄደ መንግሥት ለመባልና ሥልጣኑን ይዞ ለመቀጠል ሀገሪቱን ለሽያጭ ማቅረቡን መረዳት አያዳግትም።
አብይ አህመድና የኦሮሙማው ሀይል በሥልጣን ሙጭጭ ብሎ ለመቅረት በሥልጣን ለውጥ ሀገሪቱን እየቸረቸሩ እየሸቀጡ ነው ማለት ነው። ከዚህ በላይ “የጉድ ሀገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” የሚያሰኝ ሸፍጥ ከወደየት ይገኝ ይሆን?
የሰዎቻችን የሥልጣን ተጋድሎ አስገራሚም፣ አስደንጋጭም፣ አሳሳቢም ነው በእውነት። ኢትዮጵያ ለሽያጭ ቀርባለች። ይህ ሁሉ በሥልጣን ለመቆየት የሚደረግ አሳፋሪ ነጋዴያዊ ክህደት? ወይስ ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ጎዳና ለማሻገር የተደረገ ታላቅ ጀግንነት?
አሁን – አብይ አህመድ ኮስተር ብሎ ሀገሪቱን ለግዙፍ የውጭ ካምፓኒዎች እየቸበቸበ ነው። የጥያቄውን ቁርጥ መልስ፣ የሀገሪቱን ሽያጭ ትርፍና ኪሣራ፣ አሊያም በረከትና መርገምት፣ አሊያም ህጋዊነትና ህገወጥነት ፍርድ ግን – ታሪክ እና ሕዝብ ወደፊት የሚበይነው ይሆናል።
ከአብይ አህመድ ተረኛ የኦሮሙማ ሀይል ጋር በሥልጣን የተጣመዱትም ሀይሎች “የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” የሚል መመሪያን አንግበው አብረው በሀገር ሽያጩ ላይ ተፍ ተፍ እያሉ በሚገኙበት በዚህ አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ፣ ፈጣሪ ህዝባችንን ከክፉዎች እጅ ይጠብቅ ዘንድ ከመፀለይ በስተቀር ኦሮሙማውን ለማስቆም ልናደርግ የምንችለው ነገር ያለ አይመስለኝም። ።
ሀገር በላያችን እየተቸበቸበች ነው። ለበጎ ያድርግልን። የፈጣሪ ብርቱ ጥበቃ አይለየን።
ኢትዮጰያ ለዘለዓለም ትኑር።
Filed in: Amharic