የአማራ ሕዝብ በአገዛዙ ላይ የቀረውን ተስፋና በጎ ግምት ሁሉ አስተባብሎ መጨረሱን እና በየቦታው በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ጭፍጨፋና ፖለቲካዊ አሻጥር በማያሻማ ሁኔታ በአገር ቤትና በውጭ አገር ባካሄዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች አውግዟል፤ አጋልጧል።
ሰልፎቹ እጅግ ሰላማዊና በሰለጠነ መልኩ የተካሄዱ ከመሆናቸው ባሻገር የአማራን ሕዝብ ጠንካራ ውስጣዊ አንድነት ለወዳጅም ለጠላትም በግልፅ ያሳዩ ነበሩ።
የአማራን ሕዝብ ጅምላ ሞትና መፈናቀል «የተለመደና ነባራዊ» ለማድረግ ከየአቅጣጫው የተከፈተውን ሴራ መመከት የሕዝባዊ ንቅናቄው አንድ ዘርፍ ሆኖ መቀጠል አንዳለበት አብን በጽኑ ያምናል።
አማራ በማንነቱ ተለይቶ ተከታታይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ሲከፈትበት ለባሕል፣ ለሞራልና ለሕግ ተቃራኒ መሆኑን ገልፀው ያላወገዙ አካላት ሁሉ የለመዱትን «ማኅበራዊ ሳንሱር» ለማድረግ የያዙት አካሄድ ዘመኑን ያልዋጀና ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ማስገንዘብ ያስፈልጋል።
አሁንም የአገራችንን ምኅዳር ለአንድ ወገን ዘረኛና ያልተገራ ሽምጥ ግልቢያ የሚያመቻቹ ኃይሎች ከወዲሁ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ስንል ማሳሰብ እንወዳለን።
በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈቱት ጥቃቶች አድማስ ከእለት ወደ እለት እየሰፉና ቅርፃቸውን እየቀያየሩ መምጣታቸውን ሁሉም የሚረዳው ኃቅ ከሆነ ውሎ አድሯል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ «በአማራ ክልል» በተለያዩ አካባቢዎች፣ በመሐል ቀጠናዎች ጭምር የተቀናጁ በርካታ ጥቃቶች ተከፍተዋል። ጽንፈኛው የኦነግ ሸኔ ኃይል በሰሜን ሸዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሠብ ዞን፤ ራሱን «የቅማንት ኮሚቴ» ብሎ የሚጠራው ኃይል በጎንደር ጭልጋ አካባቢ፤ የትሕነግ ናፋቂና ትራፊ ኃይል ደግሞ በዋግ ኽምራ ዞን በህዝባችን ላይ በርካታ ጥቃቶችን መክፈታቸው ተረጋግጧል።
በመሰረቱ እነዚህ በአንድ ላይ በቅንጅት የተከፈቱ ጥቃቶችን በማየት በአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠው «የኅልውና አደጋ» መሆኑን ማንም አገር ወዳድ ዜጋ የሚገነዘበው ነው።
ስለሆነም፦
1/ በሕዝባችን ላይ ለረጅም ዘመን ሲፈፀምበት የቆየው ስልታዊ የዘር ማጥፋት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምልክቶችና መመሪያዎች እንዲሁም የሚዲያ ግልፅ ቅስቀሳዎችን ተከትለው ሲፈፀሙ ተስተውሏል። የጥቃቶቹን ዘግናኝነት የሚያሳዩ ምስሎችም በግልፅ ይሰራጫሉ።
2/ ጭፍጨፋዎቹን መከላከልና ፍትኅ ማስፈን ይቅርና የሚፈጸመውን ወንጀል በስሙ የመጥራት ኃላፊነት በሚመለከታቸው አካላት አልተተገበረም።
3/ ሰሞኑን የአማራ ሕዝብ ያደረጋቸውን ሰላማዊ ሰልፎች ለማጉደፍ ከተንቀሳቀሱት ግንባር ቀደም ጽንፈኞችና ዘረኞች በተጨማሪ የሕዝቡን ጥያቄዎች በአግባቡ አድምጠው መልስ መስጠት የሚጠበቅባቸው የመንግስት አካላት ጉዳዩን ከስልጣናቸው ጋር በቀጥታ በማቆራኘት ብቻ በጥርጣሬና በስጋት መመልከት የጀመሩት ሰልፉ መካሄድ ከጀመረበት ቀን አንስቶ እንደነበር አይተናል። በዚህ መልኩ ኃሳቡን በሠላማዊ መንገድ የገለፀው ሕዝብ በቀጣይ ንቃቱንና አደረጃጀቱን እያጎለበተ ሄዶ የሚገባውን የመብት፣ የውክልና እና የጥቅም ጉዳዮችን ሊያነሳ ይችላል የሚል ከባድ ስጋት አድሮባቸዋል።
በዚህም መንግስት በሰልፎቹ ኺደት ለተጨፈጨፈው ወገናቸው ድምፃቸውን በጉልህ ያሰሙ፣ ያስተባበሩና ሲመሩ የነበሩ የአማራ ወጣቶችን፣ ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት መሪዎችን የማዋከብና በእስር የማዋል ተግባራት እየፈፀመ ይገኛል። ድብደባ የተፈፀመባቸው ወጣቶችና የአብን አባላት ያሉ ሲሆን በደረሰባቸው ከፍተኛ አካላዊ ጥቃት ምክንያት ሆስፒታል የገቡ መኖራቸውንም እንዲሁ አረጋግጠናል።
ንቅናቄያችን እነዚህን የአፈናና የጥቃት ተግባራት በጽኑ የሚያወግዛቸውና የሚቃወማቸው መሆኑን እየገለጸ መንግስት ያላግባብ የታሰሩ የሕዝብ ልጆች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱና በሕዝቡ የተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችንም እንዲመልስ ያሳስባል።
በተጨማሪ ሕገ-ወጥ እስራትና ድብደባ የፈፀሙ እና ያስፈጸሙ በየደረጃው የሚገኙ የገዥው ፖርቲ አመራሮችና የጸጥታ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ አበክረን እያሳሰብን አጠቃላይ ችግሩ ከመወባባሱ በፊት በጊዜው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ግልፅ የሆነ ጥያቄ ለማቅረብ እንወዳለን።
በሕዝባችን ላይ የሚፈፀመውን ጭፍጨፋ የምንታገለውን ያክል ተጠቂና ተጎጅ የሆነውን ሕዝብ ለመውቀስና ለመክሰስ የሚደረገውን የሸፍጥ ፖለቲካም እስከመጨረሻው በቁርጠኝነት የምንታገለው መሆኑን ለመላው ሕዝባችን ለማረጋገጥ እንፈልጋለን።
እጣፈንታችንን በራሳችን እጆች እንጽፋለን!
#የምርጫ ካርድዎን ያውጡ፤ በምርጫ ካርድዎ የመዋቅርና ሕግ ሰራሽ ችግሮችን ሰንኮፍ ነቅሎ ዲሞክራሲን ማስፈኛ ጊዜው አሁን ነው!
የአብን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ሰዓት ነው፤ #ሰዓትን_ይምረጡ!
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!