>
5:26 pm - Monday September 15, 5738

የካይሮ  ወርቅ  ማውጫ በቤኒሻንጉል...!!! (እስሌይማን ዓባይ )

የካይሮ  ወርቅ  ማውጫ በቤኒሻንጉል…!!!

 እስሌይማን ዓባይ

ኢትዮጵያ በታሪኳ ካገኘችው የወርቅ ክምችት ድምር የላቀ ወርቅ የግብፁ ኩባንያ ቤኒሻንጉል ውስጥ የማግኘቱ ዜና 6 ዓመት ሆኖታል። አስኮም ማይንኒግ የኩባንያው መጠሪያ ነው።
ቤንሻንጉል ጉምዝ የሱዳን ነው በማለት ግብፃዊ ልሂቃን በይፋ ዘመቻ ጀምረዋል። የቤንሻንጉል ነፃ አውጪ በአረብ አገራት ድጋፍና ዕውቅና እንዲሰጠውም ካይሮ ስራ ጀምራለች። ታዲያ ይህ የግብፅ ኩባንያ በቤንሻንጉል ከግድቡ ከቅራቢያ መከተሙ በቀላሉ መታየት ነበረበት?
ከደህንነት ምንጮች የወጡ መረጃዎች ደጋግመው እንደዘገቡት ግብፅ ከደቡብ ሱዳን እስከ ጉሙዝ ዜጎች በተለያዩ ቢዝነሶች እንዲሰማሩ ምቹ የብድር ስርዓት አመቻችታለች። ነጋዴዎቹ ብድሩን መረጃ በማቀበል ነው የሚመልሱት። ታዲያ የግብፁ አስኮም በቤንሻንጉል የወርቅ ማዕድኑ ሳያንስ ግድቡንም ክልሉንም ለመገንጠል እየሰራ አይደለም ማለት ይቻላልን?
የዛሬ ስድስት አመት የማዕድን ሚኒስትር የነበሩት አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር ጋዜጣ  “አስኮም ያገኘው የወርቅ ክምችት እስከዛሬ ከተገኙ ክምችቶች ድምር ሁሉ የላቀ ነው” ብለው ነበር። ኩባንያው በቤኒሻንጉል ያገኘው ወርቅ አለማቀፍ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ይሁንና ምኒስትሩ የግብፁ ኩባንያ ያገኘው የወርቅ ክምችት መጠን ምን ያህል እንደሆነ በአኃዝ ከመግለጽ ተቆጥበው እንደነበር ይታወሳል፡፡
‹‹እስከዛሬ ስናወራ የነበረው ስለ 30 እና 40 ቶን የወርቅ ግኝት ነበር፡፡ አስኮም ያገኘው ከዚያ በእጅጉ የሚበልጥ ነው፤›› ብቻ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ኳርትዝ ኢንተርፕራይዝ ዶት ኮም እና ኒውስዊክ በወቅቱ እንዳስነበቡት አስኮም በመጀመሪያ ግኝቱ ብቻ 48 ቶን ክምችት አግኝቷል። በቀጣይም የላቀ ክምችት ይጠብቀዋል ነበር ያሉት።
የግብፁ ኩባንያ ወርቁን ባገኘ ከሁለት አመት በኋላ ደግሞ የህወሃት ወታደራዊ አመራሮች ለወርቅ ልማት በቤኒሻንጉል መስፈራቸው ተዘግቦ ነበር።
ኢሳት በመስከረም 9፥ 2009 ዘገባው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጊዛን ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ የህወሃት ወታደራዊ አመራሮችና አባላት በአካባቢው ለወርቅ ልማት በሚል መስፍራቸው በነዋሪዎች ዘንድ ተቃውሞ በመቀስቀሱ 300 የሚጠጉ ሰዎች ወደ አሶሳ እስር ቤት ተወስደዋል ብሎ ነበር። ድርጊቱን ከተቃወሙት ውስጥም ከ10-20 የሚሆኑት መሞታቸውንና የህወሃት ባለስልጣናት አንድ ኮሎኔል ጦር ይህንኑ ድርጊት ለመቆጣጠር በስፍራው እንዲሰማራ ማድረጉን ኢሳት ዘግቦት ነበር።
ከቤኒሻንጉል እስከ መተከል የተስፋፋው ወንጀለኛ ሃይል በአብዛኛው በብሔር አንዳንድ ጊዜም መቱን የፈፀመው ዘግናኝ ግድያ አልተገታም። አካባቢው የህዳሴ ግድቡ መገኛ ነው። ሲቀጥልም ወርቅ ያውም በከፍተኛ መጠን የተገኘበት አካባቢ ነው። በእንቅርት ላይ ደግሞ የካይሮው አስኮም ኩባንያ ወርቃማው መሬት ላይ ተተክሏል። ግብፅም ቤኒሻንጉል የሱዳን መሬት ነው በማለት እየወተወተች ትገኛለች።
የወርቅ ማዕድን ሰርቬይ ማድረጊያና መቆፈሪያ ማሽኖች ባብዛኛው በግድቡ ስራ ላይ በተመሳሳይ አገልግሎት የሚውሉ በመሆናቸው ለተንኮል ተግባር የማጋለጥ ስጋት እንዴት ታይቶ ይሆን?
የግብፁ አስኮም ማይኒንግ ኩባንያ አሁንም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይም በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ ውስጥ እየሰራ ይገኛል። የሚገርመው ነገር ባካባቢው የወርቅ ማዕድን የሚፈጠሩ ግጭቶች የግብፁን ኩባንያ በተለየ ሁኔታ የማይተናኮሉት የመሆናቸው ጉዳይ ነው። ከስድስት አመት በፊት ባካባቢው በተፈገረ ማዕድን ወለድ ግጭት 24 ሰራተኞች ሲገደሉ ገዳዮቹ የአስኮምን ኩባንያና ሰራተኞችን ሳይነኩ እሱን አልፈው የሌላ አገር በቀል ማህበር ሰዎች ለይተው ነበር የገደሉት።
 እንደ አገር አፋጣኝ ስራ ያሻናል
Filed in: Amharic