>
5:29 pm - Thursday October 10, 0672

ኢትዮጵያና መጪዎቹ የማይነጉ ሌሊቶች !!  ( አሥራደው ከፈረንሳይ )

ኢትዮጵያና መጪዎቹ የማይነጉ ሌሊቶች !! 

( አሥራደው ከፈረንሳይ )

ማስታወሻ

ለጊዜ ጊዜ እንስጠው ብለን ዝም ብንል፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ እነሱን አሜን ብለን የተቀበልን ከመሰላቸው በእጅጉ ተሳስተዋል :: 

የህወሃትን ዘረኛና: የዘራፊዎች ቡድን ለ27 ዓመታት የታገለችው ብዕሬ፤ ከስህተታቸው የማይማሩና፤ የነጠፈ አይምሮ ያላቸው፤ የኦህዴድ፤ ኦነግና ብአዴን (ኢህአዴግ ቁጥር 2) የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞችንም ፍትህ ከተጓደለባቸው፤ ዕኩልነት ከተነፈጉ፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተፈጸመባቸውና: ሰብአዊ መብታቸውን፤ ከተገፈፉት ወገኖቼ ጎን ተሰልፋ ትፋለማለች::    

መንደርደሪያ 

«On a demandait à Socrate d’où il était. Il ne répondit pas d’Athènes, mais du monde.» « ሶቅራጥስን አገርህ የት ነው ብለን ጠይቀነው ነበር፤ መልሱ ይቺ ዓለም ! እንጂ የአቴንስ ከተማ ብሎ አልነበረም » የ 21ኛው ክ/ዘመን፤ የመንደርና የክልል ነፃ አውጪዎች ነን ባዮች፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞችን ዝቅጠት በዚህ ብቻ ተረዱልኝ::

« L’amitié est le dernier degré de perfection de la société » « አብሮነት (ጓደኝነት፤ ወንድማማችነት ወይም ፍቅር) የአንድ ማህረሰብ የመጨረሻው ፍጹማዊ ደረጃ ነው » የጎሣ ፖለቲከኞች ስንት ምዕተ ዓመታት ወደኋላ እንደሚጎቱትን ተመልከቱ፤ ለኛ ለኢትዮጵያውያን ትልቁ እሴታችን አብሮነታችን መሆኑ ታሪካችን ምስክር ነው !

መግቢያ

ያልተረጋጋው የአገር ውስጥ ፖለቲካ፤ 

አፈናቃይና ተፈናቃይ፤ ዘራፊና ተዘራፊ፤ አፋኝና ታፋኝ፤ ገዳይና ሟች፤ ረሃብተኛና ጥጋበኛ፤ ህመምተኛና ጤነኛ፤ የአብይ አህመድ የድጋፍ ሰልፍና: የመተከል የዘር ማጥፋት ወንጀል፤ የኑሮ ውድነት ያጎበጠውና: ተረኝነት አሳብጦ ያቀበጠው፤ የአብይ አህመድ: የሦስተኛ ዓመት የንግሥ በዓል በሽራተን ሆቴል ግብዣና ፤ የድሆች ወገናኖቻችን በኑሮ ውድነት መሰቃየት፤ እልፍም ብሎ: ትግራይ የመሸጉትን የህወሃት አልጠግብ ባይ ሹማምንት ጎሸም አድርጎ፤ (ዕድሜ ለአገር ወዳድ ጀግኖች):  የወዶ ገብ ቅልብ ፖለቲከኞችን ጀርባ እያከከና ትከሻቸውን መታ መታ እያደረገ፤ የተስፈኛ ጋዜጠኞችን ብዕር: ውስኪ አጠጥቶ እያንዠባረረ፤ የምርጫ ቦርድ ተብዬው በተለይ ወይዘሪት ብርቱካ ሚደግሳ፤ « ቃሌ » ያለችውን: በቃሏ አጥፋ፤ ኢትዮጵያን ለጎሣና ለዘር ፖለቲከኞች አሳልፋ ለመስጠ፤ ዶሮ ሳይጮህ ለ3ኛ ጊዜ ያስተማራትንና ያመናትን ህዝብ ክዳ፤ ከባለተረኞች ጎራ ስልጣን ለመቀላወጥ ስትል ብቻ፤ ልጇን ኢትዮጵያን ሳይሆን፤ ትንሽ የዘረኞችና የጎሠኞች መንደር ልታወርሳት ወስናለች :: 

በሽመልስ አብዲሳ ቆማሪነት፤ አገር በቁማር እየተበላችና እየከሰረች፤ አገር በዘረኞችና በጎሠኞች የጦር አበጋዞች እየታመሰች፤ ህፃናት ሲቀጠፉ፤ የእናቶች ማህፀን በስለት ሲበለት፤ ደካማ አዛውንት ሲታረዱ፤ ቤታቸው በላያቸው ላይ ሲቃጠል እያየ፤ በአብይ አህመድ ፓስተራዊ ስብከት፤ ህዝብ የማደንዘዣ መርፌ እየተወጋ በመደንዘዝ፤ በመቃብሩ አፋፍ ላይ ሆኖ ያንቀላፋል ::

 አገር ስትሞት የመቃብር ቦታ እንኳን እንደማይኖረው ገና አልተረዳም :: 

ምርጫ አይሉት እርግጫ  ውሉ ባለየለት ሁኔታ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ባለው ውጥንቅጥ፤ በግልጽ የሚታዩ አደጋዎች ተደቅነዋል ::

ከብዙዎቹ በጥቂቱ  

የዘርና የጎሣ ፖለቲከኛች፤ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ፤ የአብይ አስተዳደርን ድክመትና፤ እራሱም የሚከተለውን የጎሣ ተኮር ፖለቲካ በመጠቀም፤ በአቋራጭ የሥልጣን ወንበር ላይ ቂጢጥ ለማለት ቋምጠዋ፤ በእጅጉም ተቻኩለዋል :: በወገኖቻችን መቃብር ላይ ተራምደው ስልጣን ለመያዝ የሚሽቀዳደሙትን፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ ህዝብ ተባብሮ በቃ ! ሊላቸው ይገባል ::

የትላንቶቹና የዛሬዎቹ ሌቦቻችን፤ የሠረቁት ሃብታችንን ብቻ ሳይሆን፤ ፍቅራችንን፤ አብሮነታችንን፤ ምኞታችንን፤ ጤናችንና ህልማችንንም ጭምር ሆኖ ሳለ፤ ያ አልበቃ ብሏቸው አሁን ደግሞ አገራችንን ለመሥረቅ አቆብቁበዋል ::

ህወሃትን ለ27 ዓመታት በአሽከርነት በማገልገል፤ በሙስና የተጨማለቁት፤ ዓሣ ዓሣ የሚሸቱት ቱባ ቱባ የኦህዴድ፤ ኦነግና ብአዴን  (ኢህአዴግ ቁጥር 2) ባለስልጣናትን ይዞ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ጉም እንደመዝገን ይቆጠራል ::

ከህወሃት ባርነት ነፃ የወጡት በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል እንጂ፤ በነሱ ድፍረትና ቆራጥነት አለመሆኑን በደንብ እያወቁ፤ ዛሬ በህዝባችን አናት ላይ፤ ቂጢጥ ብለው ሲፈነጩ ማየት በእጅጉ ያሳፍራል፤ ያሳዝናልም :: የዘረፉት አልበቃ ብሏቸው፤ እንደመቃብር የማይሞላ ሆዳቸውን ለመሙላት፤ ባደኸዩት  ህዝባችን ላይ፤ ዳግም በልጻጊዎች ለመሆን « ብልጽግና » የሚል የክርስትና ስም አውጥተው፤ ዳግም በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ፊጢጥ ለማለት፤ ይዳዳቸዋል :: ህዝብ ተባብሮ ከእንግዲህ አይቻልም !! በቃ ሊላቸው ይገባል :: የዓብይ አህመድ « ብልጽግና » በሚባለው: የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የተሰባሰቡት የፖለቲካ ዝሙተኞች፤ ህወሃት ጠፍጥፎ የፈጠራቸው፤ (የኦህዴድ፤ኦነግ፤ ብአዴን፤ደህዴን) ድምሮች በመሆናቸው፤ ከነዚህ የአገር ዘራፊዎች፤ ዘረኞችና ጎሠኞች ፤ ለአገርና ለህዝብ የሚጠቅም አዲስ ሃሳብ ይመነጫል ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው::

የነጠፈ አይምሮ ባላቸው ሰዎች አገራችን ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ መመራት የለባትም !!

ዛሬ አብይ አህመድን፤ እንደ መለስ ዜናዊ አምላካቸውና ፈጣሪያቸው፤ አድርገው በመመልከት፤ ከኋላው እንደመንጋ የሚከተሉት፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ ከድሃው ወገናችን አፍ ነጥቀው በሚበሉት አካላቸው ቢወፍርም ፤ ከአይምሯቸው የሚመነጭ ምንም የረባ ሃሳብ የሌለ ከመሆኑም በላይ፤ የአይምሮ ድርቅ የመታቸውና፤ የነጠፈ አይምሮ ይዘው በህዝባችን ላይ የሚኮፈሱ፤ የአስተሳሰብ ድሃዎች ናቸው ::

እነዚህ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች፤ ስልጣን መያዝ ካልቻሉ፤ እኩይና አገር አፍራሽ የሆነውን፤ የፈጣሪያቸውን የህወሃት ህገ መንግሥት አንቀጽ 39 በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተዘጋጅተዋል ::

ዘር፤ ጎሣንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ የአካባቢ ሠፈራ በመንደፍና በመተግበር ላይ ተሰማርተው፤  ሌሎች ነዋሪዎችን ከአካባቢው የማጽዳት ሥራ እየሠሩ ከመሆኑም በላይ፤ የአብይ አስተዳደር ይሁንታን በማግኘታቸው፤ በአገሪቱ በአራቱም ማዕዘናት የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸሙ ይገኛል::

የህወሃት አድፋጭ፤  ፈርጣጭና ተቀናጭ  ቡድኖች ፤

አድፋጩ ቡድን : በመንግሥት መዋቅሮችና በየከተሞች አስተዳደር ውስጥ፤ በአብይ የብልጽግና ተብዬ ፓሪቲ ውስጥ ሳይቀር ተሰግስገው ፤ የአብይን አስተዳደር ይቦረቡራሉ፤ ሲዘርፉት፤ ሲያስሩትና ሲገሉት የነበረውን ህዝብ ሠላምና ደህንነት ያደፈርሳሉ :: 

ፈርጣጩ ቡድን: አብዛኛው በየክልሎቹ ገጠራማ ቦታዎች መሽጎ፤ ቀሪው በጎረቤት አገራት ተጠልሎ፤ ሲያመቸው ሰርጎ በመግባት፤ የግብጽና የአረብ አገራትን አጀንዳ አንግቦ፤ ቦንብ ያፈነዳል፤ ከቻለም ጦርነት ከፍቶ እንደ ልማዱ ይዘርፋል ::

ተቀናጪው ( ቅንጡው)  ቡድን ፤ በድሃው ህዝባችን ስም፤ በብድርና በዕርዳታ የተገኘውን ገንዘብ ዘርፎ ከባህር ማዶ ባሉ ባንኮች ያጠራቀመው ሲሆን፤ በተዘረፈው ገንዘብ ልጆቹን እያስተማረ፤ የቅንጡ ኑሮው እንዳይጓደልበት፤ ከዘረፈው ገንዘብ ለምዕራባውያን አገራት፤ ሎቢስቶች በመክፈል፤ የትግራይ ህዝብ ተበደለ በሚል ሰበብ እያላዘነ፤ የምዕራባውያን አገራት፤ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጠዋት ከማታ ይጮሃል :: ዓላማው ያው የህወሃት ዘረኛና የዘረፋ ስርዓትን መልሶ ለማምጣት ነው ::

ወዶ ገብ ቅልብ ፖለቲከኞች፤ 

ወዶ ገብ ቅልብ ፖለቲከኞች፤ አብዛኞቹ እድሜያቸው የገፋ ከመሆኑም በላይ፤ የስደት ኑሮ አንገጫግጮ በእጅጉ ያጎበጣቸው በመሆኑ፤ ከአሁን በኋላ እጅ ነስተው « እጅ ሰጥተው » ያስገባቸውን የአብይ አስተዳደር ደፍረው ለመቃወም ወኔው ስለሌላቸው፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ መብት ከመቆም ይልቅ፤ እስከ ምርጫ ተብዬው ድረስ የሆቴል ቀለባቸውን፤ ከምርጫው በኋላ የጡረታ አበላቸውን ላለማጣት፤ « አፌን በዳቦ » ካሉ ቆይተዋል ::  አብይም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚለው ይልቅ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚል የክርስትና ስም ስላወጣላቸው፤ ተጠምቀው መዳናቸውን አሜን ! ብለው አረጋግጠዋል ::

አንዳንዶቹ፤ ከዘርና ከጎሣ ፖለቲከኖች ጋር ዓይን እየተጣቀሱ የሚሠሩ መሆናቸውን፤ ብልሁ የአገሬ ሰው በወፍኛ ቋንቋ ቢነግራቸውም፤ እነሱ የሚያውቁት የእንግሊዝኛ  ቋንቋ በመሆኑ አልገባቸውም :: 

ሌላው ወዶ ገብ ፖለቲከኞች ያልገባቸው፤ ወይም እያወቁ ላለማወቅ የፈለጉት ጉዳይ፤ የዘርና የጎሣ ፖለቲከኞች « ሁንዱማ ኬኛ » ሁሉም ነገር የእኛ ነው ማለታቸውን እያወቁ፤ ሊመረጡ ቀርቶ ፤ ለምርጫ ቅስቀሳ እንኳን ሊያደርጉ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እያሉ፤ በምርጫው ሳይሆን፤ በእርግጫው መሃል ገብተው ለመረገጥ ወስነዋል ::

ተስፈኛ ጋዜጠኞች : 

ተስፈኛ ጋዜጠኞች፤ አብዛኞቹ ወዶ ገብ ፖለቲከኞችን አጅበው የገቡ ሲሆን፤ አብይ አህመድ የወዶ ገብ ፖለቲከኞችን አፍ በቂጣ ሲዘጋ፤ ለተስፈኛ ጋዜጠኞችም፤ ልፋጭ ብጤ ለማደል ቃል ሳይገባ አልቀረም:: በመሆኑም፤ ግማሾቹን የቴሌቪዥን ጣቢያ ትከፍታላችሁ፤ ሌሎቹን የራዲዮ ጣቢያ ትከፍታላችሁ የሚል መሸንገያ ቢጤ ቃል ስለተገባላቸው፤ ብዕራቸውን ለህዝባቸው ፍትህ፤ ዕኩልነት፤ ዕድገትና አብሮነት ትግል ከማዋል ይልቅ፤ የአብይን ሰብዕና ለመካብ፤ ቅንድቡን ለመኳልና የሦስተኛ ዓመት ንግሠ በዓሉን በማወደስ፤ ብዕራቸውን በማዶልደም፤ ከጎሣና ከዘር ፖለቲካው ድል ማግስት ስለሚከፍቱት የቴሌቪዥንና የራዲዮ ጣቢያ ማንጋጠጡን መርጠዋል ::

ማሳረጊያ

ህሊናቸው የተራቆተ ምሁራን ተብዬዎች ሁሉ፤ አይምሯቸውን በሽንፍላቸው ውስጥ ቀብረው በሚያንኳርፉበት በዚህ የከፋ ዘመን፤ ፀሐይ ጠልቃ፤ ጨረቃ በጥቁር ደመና ተጋርዳ፤ በኢትዮጵያ የማይነጉ ድቅድቅ የጨለማ ሌሊቶች፤ የሚመጡበት ጊዜ የተቃረበ መሆኑን መረዳት አልቻሉም :: 

ህይወት: የተንጠለጠለች የውሃ ጠብታ መሆኗን ለመረዳት፤ በየዕለቱ በዘርና በጎሣ ፖለቲካ፤ እንደቅጠል የሚረግፉ ወገኖቻችንን ማየት በቂ ሆኖ ሳለ፤ ከምቾት ክልላቸው አንዲት ስንዝር እንኳን ፈቀቅ ለማለት አልደፈሩም:: በሚቀጥሉት የዘርና የጎሣ ጦርነቶች፤ አሸናፊና ተሸናፊ አይኖርም፤ በርግጠኝነት መናገር የምንችለው ቢኖር፤ ሁላችንም ተሸናፊዎች እንደምንሆን ነው::

ባለው የዘርና የጎሣ ጥላቻ ላይ፤ ስግብግብነት፤ ልግመኝነት፤ አጎንብሶ አዳሪነትና እበላ ባይነት፤ ብሎም ወኔ ቢስነት ተደማምረውበት፤ አገር የምትታመስበት አፋፍ ላይ ደርሳለች :: 

ወጣቱም ተስፋ በመቁረጥ፤ በነፃ ተወልዶ ያደገባትን አገር ትቶ፤ ከባህር ማዶ ያለ ባርነትን በመናፈቅ፤ በገዛ አገሩ ሰው ሆኖ ከመኖር ይልቅ፤ በሰው አገር ውሻ ሆኖ መሞትን ይናፍቃል ::

በውጭ አገራት በስደት የምንገኝ ዲያስፖራ ተብዬዎች እራሴን ጨምሮ፤ በዕውቀታችን፤ በጉልበታችንና በገንዘባችን፤ በአገር ቤት ያለውን ህዝባዊ ትግል በመደገፍና በመቀላቀል፤ አገራችንን ለወደፊት የምንኖርባት እንጂ የምንሸሻት እንዳትሆን፤ ለልጆቻችንም የምናወርሳት አገር እንዲኖረን በህብረት መንቀሳቀስ ይኖርብናል ::

ከብሩህ አይምሮ በሚፈልቁ፤ ብርሃናማ ሃሳቦች፤ የማይነጉ ሌሊቶችን እናንጋቸው !

አምባ ገነኖች ህዝብን መናቅ የጀመሩ እለት መሞት ይጀምራሉ !!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ !!

 

Filed in: Amharic