>
9:32 pm - Tuesday March 21, 2023

የይሁዳ ውለታ ...!! (ሄኖክ ካሳዬ)

የይሁዳ ውለታ …!!

ሄኖክ ካሳዬ

 

ከሙት ባህር እየተነሳ የሚነፍሰው ንፋስ ፤ ሙቀት ያዘለ ነው። አንድ ጊዜ ኃይሉን አሰባስቦ ሲመጣ ጨርቅ ያስጥላል። ልጃገረዶች ቀሚሳቸውን ወደታች እየጎተቱ ከነፋሱ ጋር እየታገሉ ወደ አንዱ ጥግ እፍረት በወለደው ሳቅ እያሽካኩ ይፈተለካሉ።
ገርበብ ተደርጎ በተከፈተው መስኮት በኩል የሚገባው ንፋስ መጋረጃውን እንደ ሰንደቅ እያነሳ ሲያርገበግበው ነበር የቆየው። ኃይል ጨምሮ ሲመጣ ግን መስኮቱን እንደ ልጃገረዶቹ ቀሚስ ጎትቶ የሚያስጥለው አላገኘም። ወስዶ ከግርጊዳው ጋር አላተመው። ጓ !! ተመስጠው በነበሩ ሰዎች መሃል ይሄ ድምፁ ከፍተኛ ነው። ዘኪዮስ ለንግግሩ ጆሮውን ጣል እንዳደረገ ተነስቶ መስኮቱን ሸጎረው።
“መንገድም ፤ ህይወትም እኔ ነኝ” ይላል ድምፁ
የቤቱ ማዕዘናት ላይ ፋኖሶች ተንጠልጥለዋል። ቤቱ የኖራ ድንጋይ ከሚባለው ነው የተሰራው። መሬቱ ሰሌን ለብሶ ጥግጥጉ ላይ የሀር አልጋ ልብስ የለበሱ ፍራሾች ተዘርግተዋል። በዚህ ፍራሽ ላይ ዛሬ ብዙ እንግዶች ተቀምጠዋል። ከገሊላ ወገን የሆኑ ፤ የሳምራዊያን ዘሮች ፤ አይሁዶች ፤ የተለያየን ነን የሚሉ በአንድ ላይ ተቀምጠዋል። አንድ ላይ ስለመሆናቸው ምክንያት የሆነው ደግሞ ዛሬ በመካከላቸው ቁጭ ያለው። ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ የማሪያም ልጅ!!
ማነው የውቅያኖስን ውሃ ጭልጥ አድርጎ ጠጥቶ ‘እፎይ’ ብሎ ጥሙን የቆረጠ ? ማነው ሀሳብን ሁሉ ጥሎ ራሱን ባዶ አድርጎ ከደመና በላይ ወቶ የተደላደለ ? ማነው ? ማንም !! ኢየሱስን ለቅስፈት መመልከት ግን ከዚህ ሁሉ በላይ ፍፁም እርካታ ፤ ፍፁም ሰላም ነው። ለዚህም ነው ሀገር ምድሩ ሁሉ “ጌታ ሆይ ” እያለ የሚከተለው። ከሚከተሉት ውስጥ የተመረጡት ዛሬ በዘኪዮስ ቤት አብረውት አሉ። ከእነሱ ውስጥ  የአስቆረጦሱ ይሁዳ አንዱ ነው።
ይሁዳ ወደዚህች ከተማ ከሶስት  አመት በኃላ መመለሱ ነው። አሁን በቤቴ እረፉ ብሎ ካስተናገዳቸው ሰውዬ በቅርብ ርቀት ባለች መንደር ነበር የሚኖረው። በዛ መንደር ውስጥ ሰንበት ሲሆን ‘የጥቅምት አበባ’ መስላ መታ ወደ ከተማው ዳርቻ ወዳለ ኮረብታማ ቦታ ይዛው ሄዳ ‘በሚፍነከነክ ሳቋ ፤ በሚደንሰው ሰውነቷ ፤ በሚንዛለፈው ፀጉሯ ፤ ‘ዘራፍ’ በሚለው ደረቷ ” አለሙን አሳይታ ፤ ፍሳውን አስዳስሳ የምትመልሰው ‘ሴፔራ’ አለች። ይሁዳ ወደዚህ ቤት ከገባ ጀምሮ የሚያስበው ስለ እርሷ ነው። “በህይውት ትኖር ይሁን ? አግብታስ ቢሆን ? ያን ፀጉሯን ተቆርጣው እንዳይሆን ብቻ ” ይሁዳ ከዚህ ውጪ ሌላ ነገር ሊያስብ አልቻለም።
ይሁዳ በሀሳብ እንደተዋጠ ኢየሱስ “እንካቹሁ ተቃመሱ” ብሎ ለደቀመዛሙርቱ የሳጣቸው ቂጣ እርሱ ጋር ደረሰ ከላዩ ላይ ቆንጠር አርጎ አሳልፎ ለጴጥሮስ ሰጠው። ተከትሎ በዋንጫ የሆነ ነገር መጣ። ተቀብሎ አየው። ወይን ነው። ከሶስት አመት በፊት የተውው ነገር። ወይን ስትቀምስ ሙዚቃ የሚመስል ሳቅ የምትስቀው ሴፔራ መጣችበትና አፉ በሳቅ ተሞላ። ወንጫውን ከፍ አድርጎ ከንፈሩን አስነክቶ ሽራፊ ሳቁን ዋጫው ውስጥ ሳቀ።
በቤቱ ፀሎት ሆነ። ሁሉም በአንድ ላይ ተጉ። ይሁዳ ግን ሆዴን አመመኝ ብሎ ጥጉን ይዞ ቁጭ አለ። ትንሽ ቆይቶ በሩን ከፍቶ ወጣ። ከቤቱ ልክ እንደወጣ ጉልበቱ አገጩን እስኪነካ ድረስ እያነሳ ሮጦ ወደነ ሴፔራ መንደር ገባ። የተቀየረ ነገር የለም። መንደሩ ያው በፊት እንደሚያውቀው ነው። በቀጥታ ወደ ሴፔራ ቤት ሄዶ በቀስታ ቆረቆረ። ሴፔራ ነበር የከፈተችው። “ማን ልበል” አለችው ፤ ሳይነግራት በድንገት የጠፋባት ይሁዳ መሆኑን አለየችውም። ይሁዳ ግን አዘነ!
በቀጥታ ወደ ሴፔራ ቤት ሄዶ በቀስታ ቆረቆረ። ሴፔራ ነበር የከፈተችው። “ማን ልበል” አለችው ፤ ሳይነግራት በድንገት የጠፋባት ይሁዳ መሆኑን አለየችውም። ይሁዳ ግን አዘነ ! ሴፔራ ተጎሳቁላለች። ግንባሯ ላይ ያለችው ፀሀይ ጠልቃለች። እንደፈራው ፀጉሯንም ተቆርጠዋለች። የጎደጎደው አይኗ ከህይወት አርቋታል። ሴፔራ በጎረምሳ እጅ ላይ እንዳለች ሎሚ ሟምታለች። በይሁዳ ጉንጭ ላይ የሚፋጅ እንባ ወረደ ! ፈጥኖ አቅፉ ወደ ጉያው ሸጎጣትና ስቅስቅ ብሎ ማልቀስ ጀመረ። ጥሎት በመሄዱ ራሱን እየወቀሰ ይሁዳ አለቀሰ !!
ይሁዳ ከሴፔራ ተለይቶ ሲመለስ መንገድ ላይ የተባባሉትን መልሶ እያሰበ ነበር። ከንፈሩን ስማ ” ድጋሚ ጥለህኝ አትሂድ” ስትለው ‘እሺ’ ብሏታል። “ትንሽ ሳንቲም ብናገኝ ፤ የመኮመሪያ ቤት ከፍተን ኑሯችን ይደላደላል” ስትለውም አምኗት “ልክ ነሽ” ብሏታል። ነገር ግን ሳንቲሙን ከየት እንደሚያመጣው ሊገባው አልቻለም፤ ብቻ “መላ አላጣም” እያለ ነው ወደ ዘኪዮስ ቤት የተመለሰው።
በአንድ ማለዳ በጌቴሰማኔ እያሉ ሴፔራ በስትክክል ያለበሰችውን ሻርፕ ወደ ግራ ወደ ቀኝ እያማታች መጣች። የተጣደፈች ትመስላለች። እንደ ደረሰች ከህዝብ ማሃል እጇን ከፍ አድርጋ ለይሁዳ አውለብልባ ምልክት ሰጠችው። ይሁዳ እንዳያት ሰዎችን ይቅርታ እየጠየቀ አቆራርጦ መጣ። ሴፔራ የይሁዳን ክንድ ለቀም አድርጋ ወደ ጥግ ወሰደችውና
“እንኳን ደስ አለህ ” አለችው
“ለምኑ” አላት
” ብዙ ብር ሊኖርህ ነው “
“እንዴት ሆኖ “
“ቄሳሮች ሲፈልጉህ ነበር “
“እኔን? ለምን? “
“ኢየሱስ ወንጀለኛ ነው’ ነው የሚሉት ፤ ሊቀጡት ፈልገዋል መሰለኝ”
“እና”
“ሊይዙት ብለው የትኛው እንደሆነ አለዩትም”
“ልክ ነው ” አለ ይሁዳ ” አይለዩትም ፤ ኢየሱስና ዮሀንስ አንድ ነው መልካቸው። ከአፉ ላይ ቀበል አርጋ “እኮ” አለች ሴፔራ “እነሱም የፈለጉኹ ለዚህ ነው። አንዳቸውን በምልክት አሳልፈህ እንድትሰጣቸው ይፈልጋሉ። ለዚህም ’30 የወርቅ ዲናር አለህ” አለችው። ድምፆ ውስጥ የኔ ጌታ ፤ የሚል ማባበል ነበረው።
በመሸም ጊዜ ትምህርቱ አብቅቶ ስለነበር ደቀመዛሙርቱ ሰውን ሁሉ በአቅራቢያው ወዳለ መንደር ሸኝተው እነርሱ ኢየሱስን ይዘው ወደ ተራራው ወጡ።
ይሁዳ ቀን ላይ ወደ ቄሳሮቹ ጋር ሄዶ ተስማምቶ 30 ዲናሩን ተቀብሎ ነው የመጣው። “ስንመጣ ኢየሱስ የሆነውን ስመህ ምልክት ስትሰጠን እንይዘዋለን” ሲሉት እሺ ብሏል።
አሁን ከተራራው ላይ ፈንጠር ብሎ ለብቻው ተቀምጦ በሀሳብ ተጠምዶል።ዕቅዱ ዮሀንስን “ኢየሱስ ነው ” ብሎ ስሞ አሳልፎ መስጠት ነው። ያበላኝ ያጠጣኝ ኢየሱስ ላይ ከምጨክን ምንም የማልግባባው ዝምተኛው ዩሀንስ ቢሆን ይሻላል ብሎ ደምድሟል። ሚጠብቀው መምጣታቸውን ነው። ብዙም ሳይቆዩ ቄሳሮች መጡ። ይሁዳ ፈንጠር ብሎ ተነሳ። ከፊት ላለው ቄሳር ሰላምታ ሰቶ እየመራ ወደ ተሰበሰብበት ቦታ ይዞቸው ሄደ። አጋጣሚ ሆኖ ኢየሱስና ዩሃንስ ጎን ለጎን ቆመው ነበር። ይሁዳ ፈንጠር ብሎ ተራምዶ ኢየሱስና ዩሀንስ ፊት ቆመ። ዩሀንስን ተመለከተው ፤ ደሞም በተራ ኢየሱስን አየው። ወደ ዩሃንስ ተጠጋና እጁን ትከሻው ላይ አድርጎ መታ መታ አድርጎ ተወውና ኢየሱስን አቅፎ ስሞት ፊቱን አዙሮ ሄደ!
Filed in: Amharic