>
5:28 pm - Monday October 9, 7843

የአማራ መከፋፈል ራስን በራስ ማጥፋትና ለጠላት ምቹ መሆን ነው! (ይነጋል በላቸው)

የአማራ መከፋፈል ራስን በራስ ማጥፋትና ለጠላት ምቹ መሆን ነው! 

(A real societal suicide!)

ይነጋል በላቸው


“እርስ በርሷ የተከፋፈለች መንግሥት አትጸናም” ይላል መጽሐፉ፡፡ ከጎንደር ንፋስ መውጫና ላይ ጋይንት አካባቢ የሚሰማው ዜና አሣፋሪ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ በአካባቢው የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች በአፋጣኝ ገብተውበት ነገሩ ካልተስተካከለ ይህ የብአዴን ሤራ በአማራ ታሪክ ላይ የሚፈጥረው ጠባሳ ቀላል አይደለም፡፡ የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ነጻ መውጣት ውርርድ ውስጥ የሚገባ እንዳልሆነ በቅድሚያ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በመሆኑም ማንም ማንንም በማስገደድ ኢትዮጵያዊ ሁን ወይም አትሁን ማለት ባንችልም በግፍና በደል ተሸካሚው አማራ ስም እየተጠሩ የገዳይና አስገዳይን አጀንዳ ማራመድ አያቀባብርምና ይህ ችግር በአፋጣኝ መፈታት ይኖርበታል፡፡ አማራ ነኝ ከሚል ዜጋ እንዲህ ያለ ቅሌት መሰማት መታየቱ በውነቱ አሸማቃቂ ነው፡፡

በዚህ ሰልፍ የተሳተፉ ጋይንቶች አማራ ነን የሚሉ ከሆነ ከአማራ የማይጠበቅ ነገር ማድረግ የለባቸውም፡፡ አማራን በሀፍረት አንገት የሚያስደፋ ነገር አማራ ነኝ ከሚል አይጠበቅም፡፡ ጡጦ የሚጠባ ልጅ በሰልፉ አልታየም፤ ሁሉም ሰልፈኛ ዐዋቂ(ትልቅ) ይመስላል፤ በአእምሮ ካልሆነ በሰውነት ሁሉም ጤነኛ ለመሆኑ በእይታ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በዚህ የመረጃና የዕውቀት ዘመን ደግሞ ይህ ጨለማ ሲነጋ “ሳላውቅ ነው አታልለው እንድሰለፍ ያደረጉኝ” ቢባል የሚያስኬድ አይደለም፡፡ አገኘሁ ተሻገር ስለተወለደበት ወይም አካባቢው ብዙ የብአዴን ቱልቱላ ስለወጣበት ብቻ ጋይንቴ ለነዚህ ጎደሎ ሰዎች ብሎ ታሪኩን ማበላሸት የለበትም፡፡ የብአዴንም ሆነ የማንም ወገን ባለሥልጣናት መዳኘት ያለባቸው በሥራቸው እንጂ በትውልድ ቀያቸው ወይም በዘመድ አዝማድና በአጫፋሪዎቻቸው ብዛት መሆን የለበትም፤ እንደዚህ በጎሣ መርመጥመጥ ለወያኔና ለኦህዲድም አልበጃቸውም፤ ትግላችን ሰው ለመሆን እንጂ በዘርና በነገድ አዘቅት ገብቶ ለመምቦጫረቅ አይደለም፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን እንደማየት ዘግናኝ ነገር ደግሞ የለም፡፡ ንስሃ የሚያሻው ትልቅ ኃጢኣት ነው፡፡ ለምን የእናታችን ልጅ አይሆንም? ለምን አባትና እናት አይሆኑም? አማራ በዚህ ዓይነቱ ወገንተኝነት አይታማም ነበር፡፡ በስቅሎ ስቅሎ የመንጋ ፍርድ የገዛ ልጃቸውን ክርስቶስን ሰቅለው እንደገደሉት ቀደምት አይሁዳውያን መሆን ካላማረን በስተቀር አማሮችን በያሉበት የሚጨፈጭፈውን የአቢይ መንግሥትና የርሱን ተባባሪ አገኘሁ ተሻገርን ደግፎ ሰልፍ መውጣት እንደአማራም እንደኢትዮጵያዊም እንደሰውም በቁም ነፍስ ይማር የሚያሰኝ የሞት ሞት ነው፡፡ 

ስለሆነም ከሃምሣ አጋንንት የምንሻልበትን መልካም ነገር ሠርተን ለወገኖቻችን መቆርቆራችንን እንግለጽ እንጂ በተቃራኒው ተጉዘን ወንዝ በማያሻገር ጎጠኝነት በመለከፍ ትዝብት ውስጥ አንግባ፡፡ በዚህ ሰልፍ የተገኛችሁ ጋይንቶች ሁሉ የአማራን ሕዝብ በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ ከምድረ-ገጽ ላለመጥፋት የጀመረውን ትግል ተቀላቀሉ፡፡ ሌላውን ተውት አቢይ ራሱና መላው አክራሪ ኦሮሞ ሁሉ ይስቅባችኋል፤ ለኢትዮጵያም የሀፍረት ማቅ ትሆናላችሁ፡፡ አቢይና ተሻገር ይህን ጦርነት አያሸንፉም እንጂ ቢያሸንፉ በድላቸው ማግሥት ቀድመው የሚያጠፏችሁ እናንተን ጋይንቶችን ነው፤ ለምን ቢባል “እናንተ እንኳን ለኛ ለነገዳችሁ ለአማራም አትሆኑም” በሚል መሠረታዊና እውነተኛ ምክንያት፡፡ በቃ፡፡

 

Filed in: Amharic