>

በኮቪድና በድህነት የምትነግዱ ኮቪድና ድህነት ይፍጃችሁ!! (ፍርዱ ዘገዬ)

በኮቪድና በድህነት የምትነግዱ ኮቪድና ድህነት ይፍጃችሁ!!

ፍርዱ ዘገዬ


በውነት በውነት እጅግ ተበሳጭቼ ነው ይህችን ጦማር የምጽፍላችሁ፡፡ መቼም አንድ ሁለት አንባቢ አላጣም፡፡ ዘመኑ የማነብነብና የመቀወስ እንጅ የማንበብ እንዳልሆነ አውቃለሁና ከኔ ይውጣ በሚል ነው የምጫጭረው፡፡ ግን ግን ጊዜ ሲያረጅ እንዴት እንደሚያስጠላ የገባኝ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡

ከደቂቃዎች በፊት ሦስት ጓደኛሞች ስለወቅቱ ትኩሳት እያወራን ነበር፡፡ አንደኛችን አንድ ዜና አነሳን፡፡ “ትግሬዎች በባሌም ይምጡ በቦሌ በማንነታቸው ምክንያት እየተያዙ ወደ እሥር ቤት ይጋዛሉ” የሚል ነው ዜናው፡፡ እኔ በዚህ ዜና መከፋቴን ልገልጽ አልኩና ምን እንደነካኝ ሳላውቅ “እሰይ! እንኳን ታሰሩ! እንኳንም አማራና ትግሬ በየተራ የቁም ስቅላቸውን አዩ! የመለያየት ዋጋው፣ የመከፋፈል ዕዳው እንደዚህ በየተራ መበላት መሆኑን ማወቅ ነበረባቸው፡፡ ይሄኔ አንድ ቢሆኑ ኖሮ ማንም በየተራ እየተነሣ አይጫወትባቸውም ነበር፡፡ የሥራቸውን ነው ያገኙት፡፡ በተለይ ትግሬዎቹ አማራ እንደዚያ ፍዳውን ሲበላ ዝም ማለታቸው ትክክል እንዳልነበር አሁን ይረዳሉ፡፡ በቀጣፊዎች ስብከት እየተታለሉና በትናንሽ ጥቅሞች እየተደለሉ ለዚህ መጨረሻ ተዳረጉ፤ አንድ ቢሆኑ ኖሮ ግን… እሰይ!…” በማለት ብሶቴን ዘረገፍኩ፡፡ እውነቴን ነው፡፡

ሌላ ሌላውን የሀገር ጉዳይ አገባደን ወደኮቪድ ገባን፡፡ በኮቪድ ሀገራችን እየታወቀች መጥታለች፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃዋ ከመቶ ምናምነኛ አሁን ወደ 61ኛ ወርዳለች ወይንም ወጥታለች፡፡ ጠላታችን ግብጽ ከላይ ወርዳ 68ኛ ስትደርስ እኛ በሟች ባይሆንም በተጠቂ ብዛት በተለይ ወደነአሜሪካና ህንድ ለመድረስ ሽቅብ እየተወነጨፍን ነው፡፡ ጣጣችን በዝቷል፡፡ እነሽመልስና አቢይ በሸኔያቸው በዚያ በኩል ያርዱናል፤ በዚህኛው በኩል ደግሞ ኮሮናና ከኮሮና የከፉ የግል ሆስፒታሎች ባልተወለደ አንጀታቸው ይከታትፉናል፡፡ በዚህም ብቻ በበቃን፡፡ ስግብግብ ነጋዴዎች የፈጠሩት የኑሮ ውድነት አንድ ኪሎ ቅቤ ብር 600፣ አንድ መደብ ቅርጫ ብር 6000፣ አንድ ሊትር ዘይት ብር 120፣ አንድ ኩንታል ነጭ ጤፍ ብር 5500፣ አንድ ኪሎ ብርቱካን ብር 150፣ አንድ ኪሎ አምፖል ማነው አፕል ብር 250 … ገብቶብን “ደህና ደመወዝ አላቸው” የምንባለው የአሥርና የአሥራ አምስት ሽህ ብር ደሞዝተኞች ሳንቀር ምኑን እምን እንደምናደርገው ጠፍቶን ግራ ተጋብተናል፡፡ አስፈሪው ድርቅና ርሀብ፣ የኦህዲድ ሾኔ ገጀራ፣ የመንግሥት-የለሽነት ስሜት የሚፈጥረው ድቅድቅ ጨለማ፣ የነገሠው ሥርዓተ አልበኝነትና ሙስና… ከተነሣማ መነሻየን ያስተኛልና ይቅር፡፡

ድሃውን እንተወው፡፡ ኮቪድ ይቅርና ርሀቡ ራሱ ከቤቱ ወይም ከበረንዳው እልፍ ሳያደርገውና በምን እንደሞተ እንኳን ሳይታወቅ ይገላገላል – እሰዬው! ገንዘብ ያለው አንድ ሰው በኮቪድ ሲያዝ ግን በተለይ ለግል ሀኪሞችና ለህክምና ማዕከላት ሠርግና ምላሽ ነው – እነሱ እኮ ኮቪድ ቀርቶ ጉንፋንም የሚይይዛቸው አይመስላቸውም እናንተው! ስንቱ የህክምና ዶክተር በዚህ በሽታ መሞቱን ይረሳሉ፤ ታካሚዎቹን ከ50 ሜትር ርቀት ወዲህ የማያናግረው የቆዳ ስፔሻሊስቱ ሎሬት ጥበበ በዚህ ልክፍት መሰናበቱን እንኳ ዘንግተዋል፡፡ ግዴላችሁም የነዚህና የፖለቲከኞች ሆድ ይመርመርልን! በህክምናም በሉት በፖለቲካ በሁሉም መስክ የሙያ ሥነ ምግባርና የሞራል ዕሤቶች ሙልጭ ብለው ታጥበው ገደል በመግባታቸው ለሰው ማዘንና ለመጻፍ የማትመቸው በመጀመሪያ ዕርዳታነት የምትታወቀዋ የከንፈር ድምጽ ራሷ እየጠፉ ነው፡፡ 

ተመልከት – ሲሆን በነፃ ያ ባይቻል ደግሞ በጥቂት ብሮች (10 ወይ 20 ወይ 50) መደረግ የነበረበት የኮቪድ ምርመራ በግሎቹ በትንሹ 1500 ብር ነው፡፡ በመንግሥት ሀኪም ቤት በሃምሣ ብር ገደማ የምትወጋት አንዲት በስም የነገሩኝ በመርፌ የምትወሰድ ብልቃጥ መድሓኒት በግሎቹ ብር 5000 ናት፡፡ በአፍንጫህ ለሚለኮስልህ ኦክስጂንና ቬንቲሌተር የሚከፈለው ደግሞ ሊሰሙት ይሰቀጥጣል – አየሩን እነሱ ቢፈጥሩትማ ሥጋህን ካናካቴው ይበሉታል ማለት ነው፡፡ አንድ አዳር ለመቆየት የምትከፍለው ሒሣብ ሸራተን አዲስ ከሚያስከፍለው ዕጥፍ ድርብ ነው፡፡ ዳንክም አልዳንክም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር ምናልባትም ከዚያም የበለጠ ይገሸልጡህና ለማገገም ወደቤትህ ትመለሳለህ ወይም ዕድልህ ካላማረ “ሒሣብ ዘግታችሁ ሬሣችሁን ውሰዱ” ሊባልልህም ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያን በቁም ሞተናል፡፡ ፖለቲካው ላይ ፊጥ እያልን እነአቢይን እንወቅሳለን እንጂ በየደረጃው ከሞትንና ከሃይማኖትም ከሞራልም ከባህልም ካፈነገጥን ቆየን፡፡ “ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ…” በሚለው ነባር ቃል መጽናናታችን በጄን እንጂ በርግጥም አልቆልናል፡፡

ለመሆኑ አንድ የግል ሆስፒታል ይህን ያህል ለገንዘብ የሚዋደቀው የራሱ ሰዎችና ቤተሰቦች በሽታ አይነካቸውም ማለት ይሆን? የሚያጠራቅመው ገንዘብ ከሞትና ከበሽታ እንዲሁም ከእርጅናና ከአእምሯዊ ሰላም ማጣት ያድነው ይሆን? ሰው በሰው እንዲህ መጨከንን፣ የሙያ ቃል ኪዳንን በልቶ እስከዚህ ዐውሬ መሆንን ምን አመጣብን? ሰው እንዴት በበሽታ ያተርፋል? ተማረ ተመራመረ የተባለ ዘመናዊ ሰው እንዴት በድሆች ደም ይነግዳል? በርግጥም ወዴት እየሄድን ነው? በዚህ በሽታ ባይያዝና ባይሞት በሌላ አደጋና በሌላ አጋጣሚ መሞትም እኮ አለ፡፡ እባካችሁ እንደሰው እናስብ፡፡ ሰው ሰው እንሽተት እንጂ!

የመንግሥትን በድህነት የመነገድ ወያኔያዊ ቅርስ በስፋት ላነሳ ፈልጌ ነበር፡፡ ግን ላሳድረው፡፡ መንግሥት ድሆችን በምግብ ዘይትና በማትረባ የውሎ አበል እያታለለ ለምርጫና ተቃዋሚዎቹን ለሚያብጠለጥሉ ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚያዘጋጃቸው ይታወቃል (አደራችሁን “ተንኮለኛ ነህ/ነበርከ” እንዳትሉኝ፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ አንዱን ሰካራም የነበረ የት/ቤቱን ዘበኛ በስሙኒ ሁለት ብርሌ ጠጅ ከጓደኞቼ ጋር እንገዛለትና እንዲሳደብልን የምንፈልገውን ሰው አሳይተነው እየተከተለ በስድብ ያጥረገርግልን ነበር …)፡፡ ይህ አሁን የምናየው የአቢይ መንግሥት “እባብ የወጣበትን ጉድጓድ አይረሳም” እንዲሉ ነውና እንዲያውም ከትህነግም ብሶ ድሆችንና እነአገኘሁ ተሻገርን የመሳሰሉ የአእምሮ ዘገምተኞችን በዳቦና በስኳር እያታለለ የሚጠላቸውን እንዲሳደቡለትና እንዲገድሉለትም በማድረግ የሥልጣን ማራዘሚያ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ አእምሮ ወደ ሆድ ወርዶ ሲደበቅ ሆድ አናት ላይ ወጥቶ ያናፍላል፡፡ ያኔ አያ አገኘሁ ተሻገር ያን ማስጠሎ ፊቱን ከፍ ዝቅ እያደረገ ከትከሻውም እየተውረገረገና ወገቡን እየሰበቀ ለመለስ ጀግንነትና ምሁርነት በአደባባይ እንደሰበከው ሁሉ ዛሬም ለአቢይ አህመድ “ብስለትና የአመራር ብቃት” በአደባባይ ሳይውረገረግለት አይቀርም፡፡ ይህን ዘመን ማየት ሳይኖርባችሁ እንድታዩት ግን የተፈረደባችሁ የኔ ቢጤዎች እግዜር ይሁናችሁ፡፡ እንጂ ይህ ዘመን ብዙ ዝግንትል ነገር እያሳየን ነው፤ በየእምነታችን አጥብቀን ካልጸለይን ደግሞ የነገው ባይበልጥ፡፡ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና መዓቱን ያብርድልን፡፡

እንደውነቱ ከሆነ በገንዘብም ይሁን በአእምሮ ድሃ የሆነ ሰው ለኑሮው ይሸነፋል – በአብዛኛው፡፡ ከዚህ አንጻር በሚያገኟት ድርጎ ተደልለው ለመንግሥት የሚያጎበድዱ ድሆች ሀገራቸውን መበደላቸው ግልጽ ቢሆንም ዋናውን ጥፋት የሚወስደው ግን መንግሥት ተብዬው መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የግል ሀኪም ቤቶችም ሃይ ባይ ስለሌላቸው የድሆችንም የሀብታሞችንም ገንዘብ አላግባብ እየዘረፉ ነገ ትተውት ለሚሄዱት የድንጋይና የስሚንቶ ቁልል ለሕንጻ እያዋሉት ይገኛሉ – በአንድ የስድስትና የሰባት ሬክተር ስኬል የመሬት ርዕደት የዶግ ዐመድ ሊሆን የሚችል የሕንጻ ግንባታ ውድድሩና ፉክክሩ ጦፏል፡፡ አእምሮ እየጫጫ ሆድ በሚፋፋባት ሀገር እንዲህ ያለ አሳዛኝ ክስተት ማየት እጅግ ያማል፡፡ የመንግሥትም የግል ሀኪም ቤቶችም ኩነኔ እየገቡ ነው፡፡ ይህም ትልቅ ነውር ነው፤ ወንጀልም ነው፡፡ ኃጢኣትና ኢሰብኣዊነትም ነው፡፡ በስማም … በስንቱ ነው ግን የተገረምነው ማለቴ የተረገምነው!!

Filed in: Amharic