115 የማይሞሉ መርዞች፤ ከ115 ሚሊየን በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ እንዲያተራምሱት አንፍቀድላቸው!
ታዬ ቦጋለ አረጋ
NB. ‘አንዱም አንተ ነህ¡’ የምትሉኝ፤ እኔም እንዳተራምስ አትፍቀዱልኝ።
–
ለሁላችንም የምትሆን ሀገር መሥራት ስንችል፤ ለሁላችንም የማትበጅ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መውተርተራችን ያሳቅቃል!
–
ዕናስተውል! በጥሞና የሚነበብ!
እኛ ግን ምንድን ነን?!
–
የኢትዮጵያን የገፅታ ቅብ አጠልሽተናል። እኛ ግን ምንድነን?
98% አማኝ እና ለዘመናት በጋብቻና በመንፈስ ተሳስሮ _ ተፋቅሮ የኖረ ህዝብ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ምሁራን እና የማህበረሰብ መሪዎች እያሉን እንዴት የዓለም መሳቂያ መሳለቂያ ሆንን?
* ለምን ባላነሰን ረሀብ ላይ ጠኔ ለመጨመር እንበላላለን?
* ልሂቃን ቆምንለት ያሉት ወገን በየፊናው እንደጤዛ እየረገፈ፤ እንዴት ቆም ብለው ማሰብና መቀራረብ ተሳናቸው?
* ከዚህ ሁሉ በኋላ አዙረን ማየት ብንችል የቱ ህዝብ አተረፈ? በቀጣይስ የትኛው ወገን አትርፎ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል?
* እንዴት ከ፦ ኢራቅ ሶርያ ሊቢያ ሶማሊያ ደቡብ – ሱዳን የመን እና የሚታመሱ የዓለም ሀገሮች ዕጣ – ፈንታ ትምህርት ወስደን ቆም ብለን ማሰብ ይሳነናል?
* በርካታ መልስ እያላቸው _ ምላሽ ያጡ ጥያቄዎች
–
በዚህ ሂደት ግን አሰፍስፈው ሊቀራመቱን ለቋመጡ ዓለማቀፍ ጅቦች በራችንን በርግደን፤ ለሁላችንም መአት እያመጣን እንደሆነ ማስተዋል ተስኖናል።
–
ጥቂት ማሳያዎች፦
#የአማራ ዓለማቀፍ ማሕበራት እና የዳያስፖራው ልዩ ልዩ ክንፎች ‘የአማራን ሰቆቃ’ ለሚመለከታቸው ሁሉ ለማሳወቅ ሉላዊ ዘመቻውን እያጧጧፉ ነው። ማህበራዊ ሚዲያውም በተጨባጭ ምስሎች እና ቪዲዮዎች አስደግፎ በአማራ ላይ የሚደርሰውን ግፍ በየቀኑ ዕያሳየን ነው። በተጨባጭም አማራው ያለበደሉ በማንነቱ ብቻ በየቦታው አሳሩን ዕያየ ነው። በብዙ ሺዎች ከማይካድራ እስከ ወለጋ ህይወቱ ተቀጥፎ፤ በመቶ ሺዎች ተፈናቅሏል።
* የመንግሥትን ጭላንጭል እውነተኛ ቁርጠኝነት ባላየበት ሁኔታ ምንን ተስፋ አድርጎ በዝምታ ይመልከት?!
–
በተመሳሳይ #የትግራይ ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች ትህነግ (TPLF) የለኮሰቺውን እሳት ተከትሎ በትግራይ የተፈጠረውን ሰብአዊ ቀውስ ከሚፈለገው በላይ በማጓጓን የዓለማቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ፤ ትህነግ ዳግም ወደ ሥልጣን እንዲመለስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ይዋደቃታል እንጂ ዳግም ደማችንን አይመጡትም፦ የእናታቸው ጡት ቢሆንም የማይቧጥጡት ተራራ የለም። ትህነግ በለኮሰቺው እሳት የትግራይ ህዝብ ዛሬም አላስፈላጊ መስዋዕትነት እየከፈለ ለ46 ዓመታት በርካታ ልጆቹን አላግባብ አጥቷል፤ እያጣም ነው። ምንም እንኳ ሴራው ፈርጀ ብዙ ቢሆንም፤ በዚህ መሀከል በወያኔዎች የዳፋቸው ጦስ _ ጭዳ የሚሆነው ንፁህ የትግራይ ህዝብ ያሳዝናል። አውሬዎቹ ለህዝባቸው ፈፅሞ ደንታ የላቸውምና የጦርነት ሰለባ የሚሆነው ወገን ጉዳይ እንደ እግር ውስጥ እሳት ያንገበግባል። ለመሆኑ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያላለቀሰች የትግራይ እናት የትኛዋ ትሆን? ሀዘን በእያንዳንዱ ቤት ገብቷል። ተከስተ በወጣትነቱ ተሰውቶ፤ ስብሓት ነጋ እጅ ሰጥቶ ተጎልቶ ይበላል። (Paradox!)
–
#የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ሚዲያዎችም ከሁለቱም ባልተለየ አኳኋን ለዘመናት ዕንዳየነው _ ለግማሽ ክፍለዘመን ራሳቸው በለኮሱት እሳት፤ የኦሮሞን ህዝብ ለስቃይ ዳርገው፤ ጅራፍ ራሱ ገርፎ _ ራሱ እንዲጮኽ በእናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ ዘምተዋል። የኦሮሞ ህዝብ ልክ እንደ አማራ አቻው በዘመነ ወያኔዎች ላለፉት 27 ዓመታት የደረሰበት አሰቃቂ ግፍ ሳያንሰው፤ ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ከ40 በላይ አመራሮቹን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ አባላቱን፣ ከሺህ ያላነሱ ንፁሃን ነዋሪዎችን ህይወት ሰለባ አድርጓል።
–
#ሶማሊ #አፋር #ጋሞ #ኮንሶ #ኮሬ #ጉራጌ #ጉሙዝ #ቅማንት … ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ደረጃው ይለያይ እንጂ ሁላችንም ባዋጣነው እሳት እየተለበለበ ነው።
የያዝነው የመጠፋፋት መንገድ በቡሀ ላይ ቆረቆር ሆኖ፦ የኑሮ ውድነት ቀይዶ ይዞናል፣ የመኖሪያ ቤት ችግር ሰቅዞ ይዞናል፣ ሥራ አጥነት ጠፍንጎ አስሮናል፣ ስደት ገፍትሮ አባሮናል፣ ከቤት ወደ ጎዳና እየወጣን ነው፣ እህቶቻችን የማይወዱትን ገላ ለመብላት ሲሉ አቅፈዋል፣ ለማኞች ወደነጠፉ እጆች የሎተሪ ያህል እየተዘረጉ ነው፣ ከተሞች ይጋያሉ፣ የሰው ገላ ይጠበሳል፣ የፀጥታ ኃይሉ ይሰዋል… ህዝቡ ከዛሬ ነገ ምን ይመጣ ይሆን በማለት _ በችጋር ላይ ስጋት ተደርቦበታል።
–
* ካድሬዎች፦ ፌስቡክ ላይ ተጥደው መንግሥትን አትናገሩብን በማለት ከትናንት በዞረ የአምባገነንነት ‘ሀንግኦቨር’ እየፎገሉ፤ ማስፈራራት ማስፈራራት ይጫወታሉ።
* ተከፋይ ‘አክቲቭቢስቶች፦ እየተናበቡ _ የንፁሃንን ስም በማጠልሸትና ውገሩ የተባሉት ላይ የጭቃ ጅራፋቸውን በማንሳት ይረባረባሉ።
* ፖለቲከኞች፦ በቀቢፀ _ ተስፋ የማይመሯትን የመረረች ሀገር ለመምራት፤ ከአፍ እስካፍንጫ በሆነ እሳቤ፤ ነገን ሳያስተውሉ በዛሬ ባዶ የቃላት ጋጋታ ይንኳኳሉ። መሳደብና መራገም፤ ማንኳሰስና ማጠልሸት፤ ስሜታቸውን መከተል ተጣብቷቸዋል።
* የመንግሥት ብልፅግና አመራሮች፦ እርስበርስ በጓዳዊ ስሜት ተቀራርቦ የተዳለቡ ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፤ የየክልሉን የጎጥ አጥር ፅንፈኛ በመታከክ _ አጉል ልፊያ ይዘው ሀገርን ዋጋ እያስከፈሉ ነው። በዶለዶመ ብዕራቸው፤ ለከት ባጣው ያልተገራ አንደበታቸው፣ በሴራ ፖለቲካ ተተብትበው፤ ታሪክ እንዲመሩ የሰጣቸውን ጊዜ እየመረሩበት ነው።
* የፖለቲካ ፓርቲዎች፦ ወይ እንደ ‘ሚንስ ቤት’ ተስፈኛ፤ አሊያም እንደ ገመሬ ዝንጀሮ ከመንጎማለል የዘለለ አቅም ፈጥረው ጎልብተው አልወጡም። ዝንጀሮ ጎፈሩ ሲረዝም አንበሳ የሆነ ይመስለዋል።
NB. ከላይ የተቀመጡት ፍረጃዎች የማይመለከቷቸው፤ ቀን ከሌት ለለውጥ የሚማስኑ፣ በራሳቸው ህይወት ፈርደው _ ለእውነት የሚኖሩ… አያሌ ንፁሃን መኖራቸውን ግን ፈፅሞ አልክድም።
–
ችግሮቹ ፈርጀ _ ብዙ በመሆናቸው ዘርዝሮ መዝለቅ አይቻልም። ደግሞስ ማን ሊያነበው?
–
የመፍትሔ ሀሳቦች፦
፩ 98% ፺፰ እጅ የኢትዮጵያ ህዝብ፦ አማኝ ነውና በፈጣሪያችን ፊት እንንበርከክ፣ እንቃትት፣ እንውደቅ!
በየቤተእምነቱ ህዝብ ጎርፎ ሀገርን ለማዳን ይማር። በየእድሩ ይምከር!
የሀይማኖት አባቶች ከልባቸው አስፀያፊ ድርጊቶችን ያውግዙ! እጅለእጅ ተያይዘው አርአያ ይሁኑ።
፪ የሀገር ሽማግሌዎች፦ ከወገንተኝነት ፀድተው፤ ሌላው ላይ ጣታቸውን ከሚቀስሩ፤ የየራሳቸውን ወገን ይውቀሱ፣ ይገስፁ፣ ተዉ እንደዚህ አልኖርንም ነበር ብለው ፍቅርን ያስተምሩ።
፫ ምሁራን፦ ከስሜት ፀድተው በተማሩት ልክ _ የኃላፊነት ስሜት ተሰምቷቸው ተቀራርበው ይምከሩ።
፬ ፖለቲከኞች፦ ከሥልጣን ጥም ይልቅ፤ ሀገርን ያስቀድሙ፤ በስሜት ፈረስ አይስገሩ፤ ከምርጫ በላይ ከ115 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያን ህዝብ እያሰቡ ይሥሩ። ተቀራርበው ይመካከሩ።
፭ የብልፅግና አመራሮች፦ ትከሻ ለትከሻ መለካካትን አስወግደው፤ እንደአንድ ቤተሰብ አፍ_ከልብ ሆነው ህዝብ ያረጋጉ። በየሠፈራቸው የሚሰጡትን ተፃራሪ ማላገጫ ያቁሙ። የምናደንቃችሁ በአንድነታችሁ እንጂ እድሜ ባላስተማረው የጎረምሳ አይነት ፉክክራችሁ አይደለም።
፮ አክቲቪስት ተብዬዎች፦ ነገር ማቀጣጠል ይብቃን፦ ዕናስተውል!
፯ ህዝቡ፦ ጥላቻን ከመግዛት ይቆጠብ። ከተረገሙ ሚዲያዎች ይሽሽ። የሀገሬን መጥፎ፦ ዐላይም አልሰማም አልናገርም ይበል።
–
በስድብ ሳይሆን በአስተያየት መፍትሔ አክሉ። የፀያፍ ቃላት ችግር የለብንም። አጉል መካሪዎች ይሰናበታሉ፦ ኑሮህን ምከር!
“ዛሬ ስቅለት ነው” ይለኛል፤ ወገንህን ዘቅዝቀህ እየሰቀልህ ስለስቅለት ስታወራ ያቅለሸልሸኛል። የኢትዮጵያ ህዝብ በየቀኑ በዓለም አደባባይም እየተሰቀለ ነው። ስቅለትንም ለማክበር መጀመሪያ ተረጋግተን የምናከብርበት ሀገር ይኑረን።
–
እንደ ሙስሊም ክርስቲያን የዘመናት ልዩ ፍቅር ሁሉ፦ የስቅለት በዓል ስግደት እና የረመዳን ጁምዓ ሰላት (ዛሬም) ተሰናኝተዋል። ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም እንጸልይ።
NB. ስቅለት እና የረመዳን ጁምዓ የሚገናኙት ከዓመት በራቀ ጊዜ፤ ስቅለት በረመዳን ውስጥ በሚውልበት ጊዜ ብቻ ነው። ፈጣሪ ከክፋት አርቆ በጎ በጎውን ያስመልክተን።
ታየ ቦጋለ አረጋ (ኢልመ ደሱ ኦዳ)
ዘነጌሌ ቦረና ቦረና_ወጉጂ
ዓርብ ሚያዝያ 22 ቀን 2013
ከሁላችንም ከተማ _ አዲስ አበባ