>

‹‹ሸኔ›› የሚባል ድርጅት የለም፤ የኦነግ/ኦሕዴድ ጥምረት እንጂ! (ከይኄይስ እውነቱ)

‹‹ሸኔ›› የሚባል ድርጅት የለም፤ የኦነግ/ኦሕዴድ ጥምረት እንጂ!

ከይኄይስ እውነቱ


በዕለተ ትንሣኤ የአረመኔው ዐቢይ የውሸት ካቢኔ ሕወሓት እና ‹‹ሸኔ›› የሚባል ኃይል (እንዲህ የሚባል ድርጅት መኖሩን አላውቅም) ሽብርተኛ ተብለው እንዲፈረጁ ውሳኔ ማስተላለፉን ሰማሁ፡፡ አጭበርባሪው ዐቢይ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ራሱ ያውቀዋል፡፡ ገምት ብባል ግን አንድም እንደፎከረው ሳይሆን የሕወሓት ኃይል ባለመጥፋቱ ለሥልጣኑ ሥጋት ገብቶት፣ አንድም በመላ አምሐራ ኢትዮጵያውያን የተቀሰቀሰበትን ሕዝባዊ እምቢተኝነት የማለዘቢያ ወይም ሃሳብ ማስቀየሪያ ስልት ይሆነኛል ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ባንፃሩም ‹‹ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ›› ፍጆታ አገሪቱ ውስጥ ሕግና ሥርዓትን፣ ሰላምና ጸጥታን ማስከበር ያልቻልኩት ከቊጥጥሬ ውጪ በሆኑ የሽብር ኃይላት ነው ለማሰኘት ይመስላል፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም ምክንያቶች ለአገዛዙ የተፈለገውን ውጤት አያስገኙም፡፡ እገዛዋለሁ የሚለውን አገርና ሕዝብ ሕግና ሥርዓትን በማስፈን ሰላምና የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ ያቃተው አገዛዝ ቦታውን በክብር መልቀቅ ብቻ ነው ያለው አማራጭ፡፡ በተለይም የጸጥታና የደኅንነት መዋቅሩ፣ ‹የአገር መከላከያ› ኃይሉ ጭምር ለአገዛዙ የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሲውል፣ አገዛዙ በተግባር ኢትዮጵያዊነቱን ትቷልና ከሥልጣኑ መሰናበት ይገባዋል፡፡

ትናንት ከቡሬ ወደ ነቀምት በመጓዝ ላይ በነበር የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ውስጥ በሚገኙ አምሐራ ወገኖቻችንን በአሰቃቂ ሁናቴ ጨፍጭፎ ሽብርተኝነት ፈጽሞ ሲያበቀ በጎን ይህን እላይ የጠቀስነውን የሽብርተኛነት ፍረጃ ውሳኔ ማስተላለፉ ታላቅ ስላቅ ነው፡፡ በተጨፈጨፉት ወገኖቻችንም መዘበት ነው፡፡ ‹ውታፍ ነቃዮቹ› እየተቀባበሉ ያወድሱት ይሆናል፡፡ ለእኔ ግን ሽብርተኛው እና በአምሐራውና በትግራይ ንጹሐን እንዲሁም በኮንሶ፣ በአማሮ፣ በጅማ ወዘተ. በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ካለው የሽብር ተግባሮች ሁሉ በስተጀርባ ያለው አረመኔው ዐቢይና ድርጅቱ ኦሕዴድ/ኦነግ ነው፡፡ 

በእኔ ዕውቀት በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ድርጅትነት የተመዘገበ ወይም በነፃ አውጪ ዓማጺነት በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀስ ‹ሸኔ› የሚባል ድርጅት የለም፡፡ በጨነገፈው የዐቢይ አገዛዝ ሙሉ የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ንጹሐንና ሰላማዊ ሕዝብ በተለይም አማራውንና የርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ካህናት እና ምእመናን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመ ያለ፣ ከተማን፣ ቤትና ንብረትን በማውደምና በመቶ ሺሆችን በማፈናቀል የተጠመደ ሽብርተኛ ኃይል እንዳለ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ኃይል እኔም ሆንኩ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ ግልጽ እንደሆነለት የኦሕዴድ/ኦነግ ጥምረት የሆነ መደበኛ (የዐቢይ መከላከያ ኃይል) እና ኢመደበኛ (ሕገ ወጡ የአረመኔው ሽመልስ ‹ልዩ ኃይል› እና ጫካ ያለ ምናልባትም ከጃልመሮም ውጭ የሆነ የኦነግ ኃይል) ኃይሎችን አቀናጅቶ የያዘ ‹ኦሮሙማ› የሚባለውንና በኢትዮጵያ ባድማ ላይ ‹ኦሮሚያ› የሚባል የቅዠት አገር ለመገንበት የሚደረግ የጥፋት ፕሮጀክት ለማስፈጸም በእነ ዐቢይ የተደራጅ ሽብርተኛ ኃይል ነው፡፡ 

ስለሆነም ኦነጉ ዐቢይ ጭንቅላት/ራስ የሆነለት የውሸት ካቢኔውም ሆነ በድኑና የሕዝብ ያልሆነው ‹ምክር ቤት/ፓርላማ› የሽብርተኛነት ውሳኔ ለማስተላለፍም ሆነ ውሳኔውን በሕግ ለማጽደቅ ፍላጎት ካላቸው ደጋግመን እንደጠየቅነው ከሕወሓት ሌላ በሽብርተኛነት ሊፈረጅ የሚገባው በምርጫ ቦርድ ተብዬው የተመዘገበው ኦነግ እና ኦሕዴድ-ኢሕአዴግን በአዲስ ስም የተካው የኦሮሞ‹ብል(ጽ)ግና› የሚባለው ድርጅት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹ሸኔ› የሚለው ቃል በአፋን ኦሮምኛ ትርጕሙ ‹ሸን› አምስተኛው ማለት በመሆኑና ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ስም የሚታወቅ ሕጋዊም ሆነ ሕገወጥ ድርጅት ባለመኖሩ፣በእውነት አገዛዛዊ ሽብርን ለማቆምና ድርጊቱን ፈጻሚዎቹን በሽብርተኛነት ለመፈረጅና ተጠያቂነትን ለማምጣት ከተፈለገ ‹ሸኔ› የሚባል ሳይሆን ኦነግ/ኦሕዴድ (የኦሮሞ ብል/ጽ/ግና) የሚባሉ ሽብርተኛ ድርጅቶችን በስማቸው ጠርቶ መፈረጅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ አረመኔው ዐቢይ ፍላጎት ያለው አይመስለኝም፡፡ ራስን መወንጀል ይሆናልና፡፡ 

በዚህ አጋጣሚ በውጭ ሆናችሁ በኢትዮጵያ አምሐራው ማኅበረሰብ እና በርትዕት ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጉዳይ እየተከታተላችሁ ያላችሁ ወገኖቼ በተለይም ይህንን ጉዳይ የምታስተባብረው እውነተኛው የኢትዮጵያ ልጅ ጋሼ ዳዊት ካንተ የተሸሸገ አይደለምና ከግለሰቦች ውጭ በድርጅት መልክ በዚህ የዘር ማጥፋት ውስጥ ዋነኞቹ ተዋናዮች ሕወሓት፣ ኦነግ/ኦሕዴድ መሆናቸውን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡

‹በቃን› በሚል መሪ ቃል በመላው አምሐራ ሕዝብ የተጀመረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የንጹሐን ወንድሞቻችን እስር ከዓላማችን ጋት ያህል አያናጥበንም፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከማይወክሉት፣ የሕዝብን መገፋትና ምሬት ተጠቅመው  በውጭ ሆነው ከሚጮኹት በጥቂት የሕወሓት ርዝራዦች የጥፋት ንግግርና ድርጊት ሳንዘናጋ ከኢትዮጵያዊው የትግራይ ሕዝብ ጋር ባንድነት እንቁም፡፡ በትግራይ ሕዝባችን ላይ በአረመኔው ዐቢይ እና በሻእቢያ አረመኔ ኃይል የሚፈጸመው ጭፍጨፋ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ ባስቸኳይ ይቁም፡፡ ደጋግሜ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደምለው (እንዳንድ ፖለቲከኞች ለፖለቲካ ትክክለኛነት ሳይሆን)  የትግራይና የአማራ ሕዝብ ኅብረትህን አጥብቀህ አጠንከር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ራሱን ችሎ የሚቆም አንድም ክፍለ ሀገር የለም፡፡ የጋራ ህልውናችን የተሳሰረ መሆኑን አትዘንጋ፡፡  ከሕወሓትና አሁን ደግሞ ከዐቢይ ጭፍጨፋ የተረፉ የትግራይ ሽማግሎች ካሉ ጠይቋቸው፡፡

Filed in: Amharic