ሳኦል ሆይ ስለምን ታሳድደኛለህ…?
ዘሌ ተስፍሽ
በዶ/ር አብይ እና በአቶ ልደቱ አያሌው መካከል ያለው የአሳዳጅና ተሳዳጅ ውጥረት ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ መጽሐፍን ያውቃል፣ መንፈሳዊ ነው ተብሎ የሚነገርለት የብልጽግናው መሪ የዳዊትና የሳኦል ግልባጭ ሆኖ የታየኝ ለእኔ ብቻ አይመስለኝም፡፡
የአባቱን አህያ ፍለጋ ዱካውን እየተከተለ ወደ ከተማ የገባውንና በሰዎች ዘንድ አስታዋሽ የሌለውን ገበሬውን ሳኦል፤ የእስራኤል ንጉስ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር መረጠው፡፡ አህያ ፍለጋ የወጣውን ዙፋን ላይ አስቀመጠው፡፡ የተናቀውን አከበረው፣ በናቁት እስራኤላውያን ላይም ሾመው፡፡ በታላቁ ህዝብ ላይ አነገሰው፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ አቅምና ተጽዕኖ ፈጣሪውን ከነበረው ህወሐት ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል ፖለቲካል አቅም ያልነበራቸው የተናቁት “ኦህዴዳውያን” እያሳመጹም ቢሆን ድንጋይ አስወርውረው ሚኒሊክ ቤተመንግስት ገቡ፡፡ አስፈሪው ህወሃት በኦዲፒ እግር ስር ወደቀ፤ ተራሮችን ያንቀጠቀጡ ባለብዙ ገድል ጀግኖች የህወሃት የፖለቲካ ኃይሎች እግዚአብሔር በናቋቸው ላይ ሾማቸው፡፡ በሰው ዘንድ እዚህ ግቡ በማይባሉት የገበሬ ልጆች በታላቁ ህዝብና በታላቁ ሀገር ላይ አነገሳቸው፡፡ አከበራቸው፡፡
ሳኦል ከነገሰ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በተደጋጋሚ እየጣሰ ስህተት መፈጸም ጀመረ፡፡ በዚህ ምክንት በነብዩ ሳሙኤል አማካይነት በተደጋጋሚ እንዲገሰጽ ተደረገ፡፡ በተገሰጸ ቁጥር ከስህተት ለመታቀብ ቢሞክርም ባህሪ መጥፎ ነውና ከገባበት የስህተት መንገድ መውጣት አቃተው፡፡ ከዛሬ ነገ ይለዋጣል በሚል ተስፋ እግዚአብሔር በትዕግስቱን ሲያበዛለትም ታጥቦ ጭቃ በሆነ “እሪያዊ” መንገዱን ቀጠለበት፡፡ እግዚአብሔር ከየት እንዳነሳው ረሳ፣ ቸርነቱን ናቀ፣ ትእግስቱን አቃለለ፡፡
አብይ ስልጣን በተቆጣጠረ ማግስት ጌደኦን ከማፈናቀል ጀምሮ በርካታ ስህተቶችን ሰራ፡፡ ታላቋን ሀገር አንድነትና በፍቅር እንዲመራ የተቀባው መሪ በብሔርና በጎሳ ከፋፍሎ ማስተዳደሩን ቀጠለ፡፡ ከሚፈጽማቸው ተደጋጋሚ ጥፋትና ስህተቶች እንዲታረም ቢመከርና ቢገሰጽ አልሰማም አለ፡፡ ለብሔራዊ እርቅ አሻፈረኝ አለ፣ የተነሳበትንና ያለፈበትን መንገድ ረሳ፡፡ ከዛሬ ነገ ይለወጣል ቢባል፤ ባህሪ መጥፎ ነውና ከጠባብ አመለካከቱ መውጣ አቃተው፡፡ ከእውነተኛ ይቅርታ ይልቅ የታበየ ይቅርታ፣ ከትዕግስት ቁጣን፣ ከትህትና ትዕቢት፣ ከህብረት ይልቅ እኛ ብቻ ማለት፣ በውሸት እና በአጉል ብላጣብልጥነት ኢትዮጵን እስክትፈርስ ድረስ ከንቱነትህ ታይቷል፡፡
የአኪጦልፌን የተንኮል ምክር ያፈረሰ ጌታ የአብይን የብልጠትና የቂም ምክር ይንደዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ለመልካም እያለ የሚሰራው ሁሉ መጥፎ እስኪሆን ድረስ የእግዚአብሔር ክንድ በተግሳጽ ቢደቁሰውም ከጥፋት መንገዱ አልመለስ አለ፡፡
መጽሐፉ “ብዙ ጊዜ ተመክሮ አንገቱን ያደነደነ ልብ አንገቱ ድንገት ይሰበራል፤ ፈውስም የለውም” እንደሚል በተደጋጋሚ የተገሰጸው ሳኦል ከጥፋቱ ሊመለስ ባለመቻሉ እግዚአብሔር ቆረጠበት፡፡ “ሳኦልን በማንገሴ ተጸጸትኩ” አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ከተለየው ከፉ መንፈስ ያሰቃየውና ያብሰከስከው ነበር፡፡ ከወትሮ በተለየ መልኩ ቁጡና ንዴተኛ ሆነ፤ ወሬው ሁሉ የተምታታና ዝብርቅርቅ፣ ድርጊቱ ሁሉ ግራ የሚያጋባ ሆነ፡፡ ጸጋው ተገፈፈ፡፡
ከፉ መንፈስ በሚያሰቃየው ጊዜ ትንሽ የሚረጋጋው ዳዊትን በቤተ መንግስቱ ተጠርቶ በገና ሲደረድርለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሳኦል ለእሱ ሲል በጎቹን ጥሎ እየመጣ በገና እየደረደረ የሚያጽናናውን ታዳጊ ወጣት በቅናትና ተንኮል ዓይን ይመለከተው ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የሳኦል ቁጣና ንዴት በዳዊት ያየለው ዳዊት ጎሊያድን ድል አድርጎ በመጣ ጊዜ የእስራኤል ቆነጃጂት ከበሮ እየመቱ “ሳኦል ሺ ገደለ፤ ዳዊት እልፍ ገደለ ” በማለት ሲዘምሩ በመስማቱ ነው፡፡ “ለእኔ ሺህ ብቻ ሰጥተው ለዳዊት እንዴት እልፍ ይሰጡታል?” በማለት ንዴቱን የገለጸው ሳኦል ከዚያች እለት ጀመሮ ዳዊትን ማሳደድ ጀመረ፡፡
ምንም እንኳ ታሪኩ ብዙ ቢሆንም ሳኦል ሆይ እባክህን የደነደነ አንገት እንዳይሰበር ዳዊትን አታሳድደው ! እግዚአብሔር ሳኦልን በእንቅልፍ አድክሞት በዳዊት ዋሻ በር ላይ በእንቅልፍ እንደጣለውና አሳልፎ በእጁ እንደሰጠው አንተም በምታሳድዳቸው እጅ ተላልፈህ እንዳትሰጥ እወቅ፡፡