>

ኢትዮጵያ ታተርፋለች...!!! (ጌታቸው ሺፈራሁ)

ኢትዮጵያ ታተርፋለች…!!! 

በጌታቸው ሺፈራሁ

*… ለረዥም ጊዜ ትህነግና “ኦነግ ሸኔ” በሽብርተኝነት ይፈረጁ የሚል ውትወታ ነበር። በሰበር ዜናቸው ነግረውናል። አብን ከሁለት አመት በፊት ትህነግ በሽብርተኝነት ይፈረጅ ብሎ ነበር። ሌላውም በየፊናው አቅርቧል።  ብዙ ውድመት  ሳይደርስ ተፈርጀው ቢሆን መልካም ነበር። አሁንም ግን ኢትዮጵያ ታተርፋለች።
1) ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ሲባል መንግስት ከትህነግ ጋር እንዲደራደር አድርገው የዚህ ክፉ ቡድን ነፍስ ለማትረፍ ለሚፈልጉ የውጭ ሀይሎች ጥሩ ዜና አይደለም። ከአሁን በኋላ አሸባሪ ተብሎ ተፈርጇል። እስካሁን እንደነበረው ቀላል አይሆንም። ኢትዮጵያ ለመከራከሪያ ጥሩ እድል አላት። መንግስትም ውስጥ ሆነው ከትህነግ ጋር ለመደራደር ወለም ዘለም ሲሉ የነበሩ ካሉ በራቸው ለጊዜው ተዘግቷል።
2) በተለያየ መልኩ ድጋፍ የሚያደርጉ እንደ ግብፅና ሱዳን ያሉ ሀገራትም ቢያንስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገጥማቸው መከራከሪያና አቤቱታ እንደ ድሮው አይቀላቸውም። አንድ ሀገር አሸባሪ ብሎ የፈረጀውን ቡድን ማስታጠቅ፣ ማሰልጠንና መርዳት ሳይፈረጅ እንዳለው አይደለም።
3) ትህነግ አሸባሪ ነው ተብሏል። ኤርትራም ያሰጋኛል ብላለች። ሀገራት በመሰል ጉዳዮች ላይ ከተስማሙ የጋራ ዘመቻ የማድረግ መብት አላቸው። እንደ ቀጥታ ጦርነት ብቻ የሚታይ አይደለም። ከድሮው አንፃር አሁን የኤርትራ  ይውጣ ብሎ መነዝነዙ አዋጭ አይደለም። ኢትዮጵያና ኤርትራ ግልፅ የሆነ በሽብርተኝነት ላይ ስምምነት ማድረግ፣ በጋራ ዘመቻቸው ላይ መግባባት ነው የሚጠበቅባቸው። እነ አሜሪካ የትም ሄደው አሸባሪ ላይ ዘመቻ እንደሚያደርጉት ሁሉ ኤርትራም በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና እና ስምምነት ትህነግ የተሰኘ አሸባሪ ቡድንን ማደን መብቷ  ይሆናል። እንደ ሀገር ትህነግን በአሸባሪነት ብትፈርጀው ደግሞ የበለጠ አዋጭ ነው።
4) በተለያየ መልኩ ትህነግን የሚያግዙ ኀይሎች አሉ። አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ፕሮፖጋንዳውን የሚሰሩለት አሉ። የመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆኖ ትህነግን የሚያግዝ አለ። ለእነዚህ አካላት ግልፅ መልዕክት ነው። ይህኛው ለኦነግ “ሸኔ”ም ይሰራል። እስካሁን ካየነው ቁርጠኝነት ይኖራል ብሎ ድፍሮ ለመናገር ቢቸግርም በመዋቅር ለሚያግዙት መልዕክት ነበረው።
5) የትህነግን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ለመቆጠጠር፣ ሀብቱን ለማገድ፣ የሚያግዙትን ለመቆጣጠርም ሌላ ፋይዳ አለው።
6) ለውጭ ተፅዕኖ በትንሹም ለማሰሪያነት ያገለግላል። ምዕራባዊያኑ ሶማሊያ ውስጥ እንድንገባ አድርገዋል። ሰራዊቱ ሊወጣ ሲል ይቆይልን ብለው ሲወተውቱ ኖረዋል። ራሳቸውም ዘምተው የሰው ሀገር ላይ ኖረዋል። እንደ ቀላል ጦርነት በዚህኛው ላይ አዛዥ ናዛዥ እንዳይሆኑ ያደርጋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢትዮጵያ ለሚያግዙ ሀገራትም ጥሩ መነሻ ነው። የእኛውን ምክር ቤት ብናውቀውም እነሱ ግን “በምክር ቤታቸው የወሰኑት ጉዳይ ነው። ጣልቃ አንገባም” ብለው ለመከራከር በር አግኝተዋል።
7) ፍረጃ ዝም ብሎ አይደለም። ሕዝብ ከአሁን በኋላ የሚገረው በዚሁ ስም ነው። አብዛኛው የሚጠራው፣ መረጃ የሚደርሰው በዚሁ ስም ነው። እንደ ነፃአውጭ አይተው ሲከተሉት የነበሩ፣ ሲያግዙት ለነበሩ፣ ሊደግፉት ለሚፈልጉ ያርቃቸዋል። “አሸባሪዎች ነን” ብለው የቆረጡ ብቻ አብረውት ይዘልቃሉ። ሌላው ባይጠቁምም፣ ባይታገለውም ሊያርቀው ይችላል።
ይሁንና ጉዳትም ይኖረዋል!
1) እዚህ ሀገር የሚፈለገው ሰበብ ነው። ግብሩ ያልሆነውን ከትህነግና ኦነግ  ሸኔ ጋር ተገናኝተሃል ተብሎ የሚደረግ አፈና ይኖራል። ይህን መንግስት በደንብ ሊጠቀምበት ይችላል። ይህኛው መንገድ ይህን ፍረጃ የሚያረክሰው፣  ያስገኘዋል የተባለውን ጥቅም የሚያሳንሰው ይሆናል።
2) ኢትዮጵያ ውስጥ አንዲት ክፉ አባዜ አለች። አንድ ኃይል ከተመታ ሌላውን ሰበብ ፈልጎ መምታት። የኦነግ “ሸኔ” እና ትህነግ ኃይልን በዚህ ከፈረጃችሁ ሌላውንስ? ይባላል። ምንም ያላደረገውን ኃይልም አንድ ነገር ፈልጉና እናመቻምች ይባላል።
 ከእነ ሰበብነቱ ግን ለኢትዮጵያ ጥቅሙ ያመዝናል። ከኪሳራው ትርፉ ይበልጣል። የተለየ የስህተት መንገድ ሄደው ካላበላሹት በስተቀር። ትህነግና ኦነግ “ሸኔ” በሽብር ይፈረጁ ብለው ለተወተወቱ፣ ለምን በሽብር አይፈረጁም ብለው ለተቹ ቢዘገይም በመልካም ጎኑ ሊታይ የሚገባው ነው።
ሰበብ ፈልገው ሌላውን ማጥቂያ ካላደረጉበት ኢትዮጵያ ትህነግና ኦነግ “ሸኔ”ን በመፈረጃቸው ታተርፋለች።
Filed in: Amharic