>

እረኛስ የለንም፤ አሁን ያሉት ምንደኛ እረኞች ናቸው፤  ለበጎቹ አይጨነቁም፤ በጎቹም አያውቋቸውም...!!! (ታደለ ጥበቡ)

እረኛስ የለንም፤ አሁን ያሉት ምንደኛ እረኞች ናቸው፤  ለበጎቹ አይጨነቁም፤ በጎቹም አያውቋቸውም…!!!
ታደለ ጥበቡ

መልካም እረኛ አባት የለንም። እንደ ሙሴ ለበጎቹ ሲል  ከቤተ መንግሥት ልዑልነት ይልቅ ወደ ሎሌነት ወርዶ፣ ሥጋዊ ሓላፊነትን ንቆ፣ የቤተ መንግሥት ዝናሩን አውልቆ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጠው የእረኝነት ሥልጣን የኃያልነት ዝናርን የሚታጠቅ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከጥፋት ለመታደግ ከተኩላዎች ጋር የሚታገል አባት ጠፋ። ራሱን ስለ በጎቹ አሳልፎ የሚሰጥ መልካም እረኛ  ጠፋ።
ስለ በጎቹ ሲል እንደ ዳዊ ከአንበሳ ጋር የሚተናነቅ አባት የለንም። ስለ በጎቹ ሲል  እንደ ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ  ሕዝቡ ሃይማኖቱን እንዳይለውጥ፣ ቤተ ክርስቲያንን እንዲጠብቅ በዐደባባይ የሚመስክር አባት የለንም።
አሁን ላይ ያሉት ምንደኛ (ቅጥረኛ) እረኛች ናቸው። ለበጎቹ አይጨነቁም፤ በጎቹም አያውቋቸውም።
 በእናት ቤተ ክርስቲያናችን የተሾሙ አባቶች እንደነሙሴ፣ እንደነዳዊት፣ እንደነብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለበጎቹም የሚጨነቁ አይደሉም። ፓትርያርኩን አሳልፈው ለተኩላዎች ሰጥተዋቸዋል። ወቅሰዋቸዋል። ቤተ ክርስቲያን ሳታጠፋ ወንጀለኛ አድርገው፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም “ይቅርታ” ጠይቀዋል። በተቀደሰው ስፍራ የእነ ጥልምያኮሶ ጣኦት እንዲቆም ፈቅደዋል።
የቤት ቀጋ የውጭ አልጋዎች
አካለ ወልድና (በፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ለአአ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነት የተሾመ) አባ ሕፃን በአዲስ ቲቪ ቀርበው ይቅርታ እንዲጠይቁ ቀጭን ትእዛዝ ከቤተ መንግሥቱ ውታፍ ነቃዮች ተሰጥቷቸው ይህን ለማድረግ ጠብ እርግፍ እያሉ መኾናቸውን በጽዋዕ ቱብ የዕለቱ መርሐ ግብር ጥቆማ ሰጥተን ነበር። ይኸው ተረጋገጠ።
እነ አህመዲን ጀበል ያሉት ከእኛ ቤት ከእልፍኙ ውስጥ ነው። አባ “ሕፃን” – በአማን ሕፃን “በቤተ ክርስቲያናችን ስም ይቅርታ እንጠይቃለን” በማለት ተናግረዋል። በተቀደሰው ስፍራ የእነ ጥልምያኮስ ጣኦት እንዲቆም የሚተጉ ጀግኖች በማን አለብኝነትና በይሉኝታ ቢስነት ቤተ ክርስቲያንን በዐደባባይ ከስሰዋታል፣ በከረፋው ዕብደታቸው ፈርደውባታል። ወንጀለኛ አድርገዋታል።
ሕፃኑ አክለፍልፏቸዋል። ፓትርያርኩን አንጓጥጠው መግለጫ ለመስጠት ምንም ዓይነት ሥልጣን የላቸውም። እንዲሁም መስቀል ዐደባባይን ኢድ ዐደባባይ ለማድረግ የተከፈተውን ዘመቻ የተቃወሙትን የአቡነ ያሬድን ደብዳቤ የማሳበል ምንም ዓይነት ሥልጣን የላቸውም። መስቀል ዐደባባይን ለ፴ ዲናር ሸጠውታል።
እኒህ የሕፃን ሥራ በመሥራት የታወቁ ግለሰብ ከቤተ ክርስቲያን የልዕልና ጠባይ ቀርቶ በዓለም ሥርዓት የሌለ የነውር ሥራ ፈጽመዋል። መታለፍ የሌለበት አደገኛ እና ታሪካዊ ጥፋት።
እናቴ እንጀራሽን የሚበላ እንዲህ ተረከዙን ያነሣብሽ ዘንድ አይገባሽም። ዕንባሽን እንጠርግልሽ ዘንድ ቃል አለብን። ኦርቶዶክሳዊ ወጣት ይሁዳን እና ውሉደ ይሁዳን ጠራርጎ ለማስወጣት አንድ እንሁን። የተረኝነት መናጆዎችን እናርቅ። በውጭ ካሉት በፊት የውስጡን እናጥራ።
Filed in: Amharic