መስቀል — ሁሉንም ያገኘንበት፣ ሁሉንም የምንሰጥለት፣ የነፍሳችን መድኃኒት!
አሰፋ ሀይሉ
«† መስቀሉ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ዕድሜ፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት፣ ድንበር፣ ጊዜ፣.. የማይገድበው – ለሰው ልጆች ሁሉ በፍቅር የተገለጠ – የትንሣዔያችን ቃልኪዳን ነው!»
መስቀሉ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን የተከፈለ የታላቅ መስዋዕትነት ምልክት ነው፡፡ መስቀሉ ለሰው ልጆች ሁሉ ህይወት ይበዛልን ዘንድ፣ ጌታችን የሞትን ጽዋ የተቀበለበት ራስን ለሰው ልጆች ደህንነት አሳልፎ የመስጠት ምልክት ነው፡፡ መስቀሉ በእምነት የቱንም ያህል ምድራዊ መከራን መቀበል እንደሚቻል እንደ ሰው ሆኖ በመካከላችን በተመላለሰው ጌታችንና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በኩል ያየንበት የእምነት፣ የፅናት፣ እስከ ሞት የመታመን ህያው ምልክታችን ነው፡፡
መስቀሉ የአምላክን ያህል ሥልጣን ቢኖረን እንኳ በሚጠሉንና በሚንቁን ፊት ዝቅ የማለትን፣ የማይቻለውን ትህትናን ተላብሶ የመገኘትን ታላቅ ጸጋችንን በጌታችን ምሣሌነት ያየንበት ፍጹም ከመታበይ የራቀ የትህትና ዝቅታችን ምልክት ነው፡፡ መስቀሉ በሞት ስቃይ ውስጥ እንኳ ሆነን የሚወዱንን ብቻ ሳይሆን የሚጠሉንን፣ ሊያጠፉንም፣ ሊሰቅሉንም፣ ሊዘባበቱብንም የተነሱ ጠላቶቻችንን ጭምር እንደ ባልንጀሮቻችን መውደድ እንደምንችል ያየንበት የታላቅ የፍቅር ምልክታችን ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ጥቁር ነው ቀይ ነው ሳይል፣ ነጭ ነው ቡኒ ነው ሳይል፣ አረማዊ ነው ሳምራዊ ነው ሳይል፣ ትንሽ ነው ትልቅ ነው ሳይል፣ ክርስትያን ነው አይሁድ ነው ሳይል፣ ከቀለም በላይ፣ ከመልክ በላይ፣ ከእምነት ልዩነቶች በላይ፣ ከምንም ምድራዊ የሰው ልጆች ልዩነት በላይ በሁላችንም ውስጥ ያለውን፣ በሕይወት የሚያቆየንን ደምን በምሳሌነት መርጦ – ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ሲል – ደሙን በመስቀሉ ላይ በመርጨት ፍቅሩን ያሳየበት፣ የሰው ልጆች እኩልነትና አንድነት የተገለጸበት ዘለዓለማዊ ምልክታችን ነው!
መስቀሉ ጌታችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ከሞት ባሻገርም ሕይወት እንዳለ ታላቅ ተስፋን ያኖረበት፣ በሞት ሸለቆ ውስጥ እንኳ ብንጓዝ ሕይወት እንዳለን እያሰብን የምንጽናናበት፣ የዘለዓለም ህይወት ሰገነታችን ነው፡፡ መስቀሉ ብርታትና ኃይላችን ነው፡፡ መስቀሉ ወድቀን የመነሳታችን ተዓምራታችን ነው፡፡ መስቀሉ ሕይወታችን ነው፡፡ መስቀሉ ለማያውቁት ሞኝነት፣ ትርጉሙን ለሚያውቁትና በላዩ የተጻፈላቸውን ዘለዓለማዊ መልዕክት ለሚረዱት ሁሉ ደግሞ ህይወት ነው፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቸነከረው፣ ታላቅ ሥቃይንና መከራን የተቀበለው፣ የሞተው፣ የደማው፣ የተራበው፣ የተጠማው፣ የሚሠሩትን በማያውቁት እጅ ጎኑን በጦር ፍላጻዎች የተወጋው፣ የከበረ ደሙን ያፈሰሰው፣ ‘አባት ሆይ ብትወድ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ’ ብሎ እስኪለምን እጅግ የበረታ ፈተናን የተቀበለው፣ የሰው ልጆች ሁሉ ይድኑ ዘንድ ነው፡፡ በመስቀሉ ሥር የማንችለው የለም! ስለ መስቀሉ ክብር የማንሆነው የለም! መስቀሉ የህይወታችንም፣ የሞታችንም፣ የትንሣዔያችንም አዕማድ ነው፡፡
የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ደቀመዛሙርት ይህን ታላቅ እውነት የተረዱ እንደነበሩ የምናየው፣ ለመስቀሉ እውነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት ስንመለከት ነው፡፡ ሁሉም ሰማዕታት ከመስቀሉ እውነት ፈቅ አንልም ብለው ታላቅን ስቃይ ተቀብለዋል፡፡ ከሞት ወዲያ ላለው ህይወት ታምነው፣ የምድሩን ሕይወት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በማይታመን መከራ ውስጥ፣ በሚገርም የእምነት ፅናት ቆመዋል፡፡ የሰማዕታት ደቀመዛሙርቱን ፍፃሜ-ህይወት እንይ!! በእውነት የማንንም ሰብዓዊ ፍጥረት ልብ በሐዘንና በፍቅር ይነካሉ፡፡ የእየሱስ ደቀመዝሙሮች ፍጻሜ-ሕይወት እንደሚከተለው ነበር፡-
1ኛ. ጴጥሮስ (ስምዖን)፡- ሮምን በእሳት እያቃጠለ እርሱ በቤቱ በደስታ ጊታሩን ይጫወት በነበረው፤ ምነው አንዴ ቀንጥሼ እንድጥለው የዓለም ሰዎች ሁሉ አንገት ምነው አንድላይ ሆኖ ቢሰራልኝ! ብሎ በተቆጨው በጨካኙ የሮማ ንጉስ በኔሮ በ66 ዓ.ም. በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፡፡ ጴጥሮስ ሊሰቀል ሲል ሰቃዮቹን ‹እኔ ከክርስቶስ እኩል ወደላይ ልሰቀል ስለማይገባኝ ዘቅዝቃችሁ ስቀሉኝ› ስላለ፤ ተዘቅዝቆ እንዲሰቀል ሆነ፡፡
2ኛ. ጳውሎስ፡- ልክ ስምዖን ጴጥሮስ በተሰቀለበት ዕለት (በ66 ዓ.ም.) በሮም በንጉስ ኔሮ አንገቱ ተሰይፎ እንዲገደል ተፈርዶበት ሞተ፡፡ (ሆኖም ይህን የማይቀበሉ ሌሎች፡- ጳውሎስ ሮማዊ ነው፤ ስለዚህ ሞት አልተፈረደበትም፤ ታስሮ ተፈቷል፤ ከዚያም 2ኛ ጢሞቲዎስን መልዕክት የጻፈው እኮ በ68 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ አይደለም ወይ? ይሉና ቆይቶ ግን የሰማዕት አሟሟት እንደተቀበለ ይናገራሉ፡፡)
3ኛ. እንድርያስ (የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም)፡- በግሪክ የሮማ ቆንሲል አሳሰረው፤ ተከራከረው፤ ዕድል ሰጠው፤ እየሱስን ተውና የእኛን ተቀበል ብሎ ለመነው፤ እንድርያስ ግን አሻፈረኝ አለ፡፡ ስለዚህ ተገረፈ፤ በህይወት ረዥም ጊዜ እንዲቆይና ከህመሙ የተነሳ እንዲሰቃይ በምስማር ሳይሆን በገመድ በመስቀል ላይ ታስሮ ተሰቀለ፤ ለ2 ቀናትም በህይወት ቆየ፤ ህይወቱ ከማለፏ በፊት በእነዚያ 2 ቀናት ከህመሙ ጋር እየታገለ በአጠገቡ ለሚያልፉት ‹እየሱስ ከሞት ተነስቷል› እያለ ይሰብክ ነበር፡፡
4ኛ. ያዕቆብ (የእልፍዮስ ልጅ)፡- በምድረ ሶርያ በመጀመሪያ በድንጋይ ተወገረ፤ ቀጥሎም ጫፉ እንደቅልጥም በዶለዶመ በትር ተቀጥቅጦ ህይወቱ አለፈች፡፡
5ኛ. ዮሐንስ (የያዕቆብ ወንድም)፡- ከ12ቱ ደቀመዝሙሮች ብቸኛው በህይወት ተራፊ ነው፡፡ በምድረ-እስራኤል ቆይቶ የኤፌሶንን ቤተክርስቲያን አቋቋመ፤ የእየሱስን እናት ማርያምንም ሲንከባከብ ቆየ፤ ከዚያ ግን ሊገድሉት አሳደዱት፤ እና ‹ፓትሞስ› ወደተባለች ደሴት በግዞት ተሰደደ፡፡ እዚያም ሳለ የመጽሐፍ ቅዱስን የመጨረሻ ክፍል (የዮሐንስ ራዕይን) ጻፈ፡፡ (በአንዳንድ የላቲኖች ተረኮች መሠረት ግን ዮሐንስ ወደ ፓትሞስ ከመሰደዱ በፊት በሮማ በፈላ ዘይት ውስጥ ከነህይወቱ ተጨመረ፤ እርሱ ግን ምንም ሳይሆን ወጥቶ ተሰወረባቸው፤ እና ከዚያ በኋላ ነው ወደ ፓትሞስ ደሴት የሄደው ይላሉ)፡፡
6ኛ. ፊልጶስ፡- በካርቴዥያኖች፣ በሰሜን አፍሪካ፣ እና በትንሹ እስያ በስፋት ሲሰብክ የቆየው ፊልጶስ በመጨረሻ የሮማውን ቆንሲል ሚስት ስለክርስቶስ እንድትቀበል አሳመናት፡፡ ይህንን የተረዳው የሮማ ቆንሱል ፊልጶስን በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደል አደረገው፡፡ (አንዳንድ ድርሳናት ደግሞ ህይወቱ እስክታልፍ በድንጋይ ተወግሮ እንደሞተ ጭምር ይናገራሉ፡፡)
7ኛ. በርቶሎሚዎስ፡- ከጠርጣራው ከቶማስ ጋር ወደ ህንድ ሄዷል፤ ወደአርሜኒያ፤ ወደኢትዮጵያ፤ ወደደቡብ አረቢያ ሁሉ ክርስትናን የሰበከ ነው፡፡ በርቶሎሚዎስ በመጨረሻ የአርሜንያውን ንጉስ ፖሊሚየስን ክርስቶስን እንዲያምን ያሳምነዋል፡፡ ይህንን የሰማው የንጉሱ ወንድም በርቶሎሚዎስን በበትር ተቀጥቅጦ በመጨረሻ አንገቱ በሰይፍ እንዲቀነጠስ አስደረገው፡፡
8ኛ. ቶማስ፡- ቶማስ የእየሱስን ከሞት መነሳት ካላየሁ አላምንም ብሎ አይቶ ዳስሶ ያመነ ነው፡፡ ካየና ካመነ ግን ከቶውንም ምንም ነገር ምንም መከራ ምንም ስቃይ እምነቱን ሊቀለብሰው አልተቻለውም፡፡ ቶማስ በሶሪያ እና እስከ ህንድም ድረስ ሄዶ ስለክርስቶስ ሰበከ፡፡ ከዚያ ግን በኢአማኒዎች እጅ ተያዘ፡፡ የእየሱስን ከሞት መነሳት ካድና በህይወት እንለቅሃለን እያሉ ለመኑት፤ አሰቃዩት፡፡ ሹል የተሳሉ ጦሮች በተተከሉበት አውድ ላይ እየተበሳሳ እንዲንከባለል አደረጉት፡፡ ህይወቱ አላለፈችም፡፡ እየሱስ ተነስቷል ወይ? ብለው ጠየቁት፡፡ መልሱ ‹አዎ ተነስቷል›! ነበር፡፡ ከዚያ ደግሞ ሰውነቱን ሁሉ በእሳት ብዛት ፍም እስኪሆን ድረስ በጋለ ትሪ እየጠበሱት የክርስቶስን ከሞት መነሳት እንዲክድ አሰቃዩት፡፡ ቶማስ ግን አሁንም በእምነቱ ፀና፡፡ በመጨረሻም በቃ ከነህይወቱ በእሳት አቃጠሉት፡፡
9ኛ. ማቴዎስ (ቀራጩ)፡- ማቴዎስ በፐርሺያ (አሁን ኢራን አካባቢ) እና በኢትዮጵያ ነው የሰበከው፡፡ የጥንት ድርሳናት ላይ ማቴዎስ ልክ እንደዮሐንስ ሞትን በሰማዕትነት እንዳልተቀበለ ይናገሩ ነበር፡፡ ሆኖም ሌሎች ምንጮች ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ሳለ ህይወቱ እስክታልፍ ድረስ በጦር ፍላፃዎች ተወጋግቶ ተገደለ በሚል ስለሞቱ ተፅፎ እንደተገኘ ደግሞ ይናገሩለታል ተብሎለታል፡፡ ሆኖም አሁንም ሌሎች የድርሳናት ምንጮች ደግሞ ማቴዎስ የሞተው ከኢትዮጵያ ወደ እየሩሳሌም ሄዶ በዚያው በእየሩሳሌም ተይዞ በድንጋይ እንዲወገር ከተደረገ በኋላ አንገቱ ተቀልቶ ሞትን እንደተቀበለ ይናገራሉ፡፡
10ኛ. የዘብድዮስ ልጅ ያዕቆብ፡- ያዕቆብ ደግሞ በሄሮድ እንዲገደል እንደተደረገ ተጽፎለታል፡፡ (እዚህ ላይ የእልፍዮስ እና የዘብድየስ ያዕቆቦች የትኛቸው እንደሆኑ በትክክል መለየት አዳጋች ስለሆነ በጥንቃቄ መለየት ያሻል፡፡)
11ኛ. የአስቆሮቱ ይሁዳ፡- ይሁዳ እየሱስን በሰላሳ ብር ለአይሁድ ካህናት ከሸጠው በኋላ፤ በእየሱስ እንደተፈረደበት ሲያይ ፀፀቱን ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ የደሙን ገንዘብ (30 ብሩን) ለካህናቱ በመካነጉባዔ ሄዶ ወረወረላቸው፤ እየሮጠም ሄዶ ራሱን በራሱ በገመድ አንቆ ነፍሱን አጠፋ፡፡
12ኛ. ቀነናዊው ስምዖን፡- ስምዖን ደግሞ በፐርሺያ ሄዶ ነበር፡፡ እዚያም ሳለ ለፀሐይ አምላክ መሥዋዕትን እንዲሰዋ ሲጠየቅ አላደርገውም አለ፡፡ እጅጉን ቢለመንም አሻፈረኝ አለ፡፡ ከዚያ ወደ ሱዓሚር ወሰዱት ገዳዮቹም የተሳለ መጋዝን ይዘው ወደታሰረው ስምዖን ቀረቡ፡፡ በመጋዙም ከራስፀጉሩ እስከ እግርጥፍሩ ሁለት ቦታ ቆርጠው ጣሉት፡፡
13ኛ. ማቲያስ (ታዲዮስ ልብድዮስ)፡- አስራሁለተኛ ሆኖ ይሁዳን እንዲተካ የተመረጠው ደቀመዝሙር ነው፡፡ ማቲያስ ደግሞ በሶሪያ ከእንድርያስ ጋር ሄዶ ነበር፡፡ ከዚያ ግን የደረሰበት ዕጣ አሳዛኝ የኢአማኒዎች ዕጣፈንታ ነው – ከነህይወቱ በእሳት እንዲቃጠልና ሞትን እንዲቀበል ሆነ፡፡
የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስ ቅድስናና ክብር፣ የደቀመዛሙርቱ ሰማዕትነትና በረከት በልባችን ያድርብን ዘንድ፣ ሁሉ የማይሳነውን የሠማዩን አምላክ በመስቀሉ ሥር ተደፍተን እንለምነዋለን!
የማይቋረጥ ምስጋናና ክብር በመስቀሉ ላይ ስለ ኃጢያታችን ዋጋ ከፍሎ ዘመነ-ምህረትን ላመጣልን ጌታችንና መድሃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ይሁን፡፡ ምስጋና ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁንልን፡፡ በዚህ የመፈተኛ ዘመናችን ላይ ቸሩ የሰማይ አምላካችን ከኢትዮጵያውያን፣ ከትውልዶቻችንም ሁሉ ጋር ይሁንልን፡፡
መስቀል የነፍሳችን መድኃኒት ነው!
የምኅረት ደጅ፣ የእምነት ምኩራብ፣ የመስቀሉ ቃልኪዳን ምድር ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም በፍቅር ትኑር!
መልካም ጊዜ ለሁላችን፡፡
__________________________
ስዕሉ፦ የሠዓሊ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ «ጎልጎታ» ወይም «ስቅለት» (“Crucifix”) የተሰኘ ታዋቂ የቀለም ቅብ ሥራ፣ (1969 ዓም)፡፡