>

ጋሽ ታዲዮስ፣ አርበኞች እኩዮቹ፣ ሶልዲው ህገ-መንግሥት እና እኛ!  (አሰፋ ሀይሉ)

ጋሽ ታዲዮስ፣ አርበኞች እኩዮቹ፣ ሶልዲው ህገ-መንግሥት እና እኛ!

 አሰፋ ሀይሉ

 

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ነፍሳቸውን ይማርና አሁን በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ተብዬ ብዙ ጊዜ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ እጅግ ተገቢ የሆኑ ቅጽል ስሞች በመስጠት በአደባባይ ወርፈውታል፡፡ ከሁሉም የምወደው ‹‹ህገመንግሥቱ ከተጻፈበት ወረቀት በላይ ዋጋ የማያወጣ ርካሽ ሰነድ ነው›› ያሉት ሁልጊዜ ይመጣብኛል፡፡
እነ አብይ አህመድ ደም የተከፈለበት ነው እያሉ የሚፎክሩበትና በእጃቸው ጨብጠው የማሉበት የወያኔ ህገመንግሥት፣ በአንቀጽ 19 ላይ በወንጀል የተከሰሰ ሰው በዋስትና የመለቀቅ መብት እንዳለው ጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ግን ይህ መብት በተግባር ይሠራበታል ወይ? ይህ መብት ዋጋ አለው ወይ? መልሱ የሶልዲ ያክል ዋጋ የለውም የሚል ነው፡፡ የሶልዲ ያህል ዋጋ የሌለው አርቲቡርቲ ነው! በጋሼ ታዲዮስ ታንቱ ማየት ይቻላል፡፡
አብይ አህመድ የአማራን ታሪክ በአደባባይ ሲናገሩ፣ የሀገር አርበኝነታቸውን እየገለጹ ሲጽፉ ተቆጣ፡፡ እና ደህንነቶቹን ልኮ ከአርበኞች ድል በዓል ላይ አሳፈናቸው፡፡ መታፈናቸው ቶሎ ባይሰማ አስገድሎ አንዱ ትቦ ውስጥ ጥሏቸው እናገኛቸው እንደነበር በበኩሌ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ጋሼ ታዲዮስ ቃላቸውን ለፖሊስ ሰጡ ተባለ፡፡ ፍርድ ቤት ቀረቡ ተባለ፡፡ ክስ ተመስርቶባቸዋል፣ ወይም ገና ሊመሰረትባቸው ነው፡፡ ተከሰሱ ማለት፣ ተያዙ ማለት፣ ግን፣ ወንጀለኛ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
ያው የወያኔ ሶልዲ ህገመንግሥት አንድ ሰው በነጻና ገለልተኛ የፍርድ ሂደት በወንጀል ተከሶ ጥፋተኛነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ እንደ ንጹህ ሰው የመቆጠር የማይገሰስ መብት እንዳለው ያወራል፡፡ ያወራል ነው ያልኩት፡፡ ያው የሶልዲ (እጅግ የረከሰ) ወሬ ነው ግን፡፡ እና ጋሽ ታዲዮስ – በዋስትና ከእስር የመለቀቅ መብትም አላቸው፡፡ እንደ ንጹህ ዜጋ የመቆጠር መብትም አላቸው፡፡ ታዲያ የዋስትና መብታቸው ለምን ተገፈፈ?
እኚህ የ70 ዓመት ሽማግሌ – በዋስትና ቢለቀቁ ሮጠው ከሀገር ሾልከው ያመልጣሉ ተብሎ ተፈርቶ ነው? መቼም ወንጀላቸው ነው የተባለው በነጻነት መናገርና መጻፍ ነው፡፡ እንደ አብይ አህመድና ግብረአበሮቹ እጃቸው በሰው ደም የተነከረ አይደለምና መቼም ሀገር ጥለው የሚጠፉበት ምድራዊም ሰማያዊም ምክንያት የላቸውም፡፡
ወይስ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ በዋስትና ከእስር ቢለቀቁ – ልክ እንደ አይዛክ ኒውተን ወይ እንደ ስቴፈን ሃውኪንግ ወይ እንደ መጪው ዘመን የአይዛክ አሲሞቭ ልብለወዳዊ ሳይንቲስቶች ሁሉ – አንዴ የተናገሩትን ቃል ወይ አንዴ የጻፉትን ሆሄ – በታይም ትራቭል ማሽን ወደ ኋላ ጊዜ ተምዘግዝገው ተጓጉዘው – የአብይ አህመድ አቃቤ ህግ በማስረጃ እንዳይቆጥርባቸው – ሊያጠፉት፣ ሊያድበሰብሱ፣ ሊሰርዙ፣ ወይ ሊደልዙ፣ እና የጻፉትን እንዳልተጻፈ፣ የተናገሩትንም ከቫኪዩም ላይ ከነገደል ማሚቶው ሳይቀር ጥርግ አድርገው እንዳልተናገሩት ማድረግ አይሳናቸውም ተብሎ ነው?
ወይስ እንደምን ያለ ምድራዊ ወይ ሰማያዊ ምክንያት ይሆን እኒህን የሰባ ምናምን ዓመት አረጋዊ አዛውንት (ጋሼ ታዲዮስ ታንቱን) ከእስር በዋስትና እንዳይለቀቁ የሚያደርጋቸው ምክንያት?
ጋሼ ታዲዮስን በዋስትና የመለቀቅ መብታቸውን የሚሽር ምንም ዓይነት ምድራዊ ምክንያት ኖሮ ወይም ይኖራልም ታስቦ አይመስለኝም፡፡ ወይም ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ በሰባ ዓመታቸው እንደ አባባ ታምራት ወደ ሰማይ ዘልለው አርገው ይሰወራሉ ተብለው ተጠርጥረውም አይደለም፡፡ ወይ እንደነ ኒውተን በታይም ትራቭል ወደ ኋላ ሄደው የወንጀል ማስረጃዎቻቸውን ያጠፋሉ ያድበሰብሳሉ፣ ምስክር ያማልላሉ፣ ይደልላሉ ተብለው ተገምተውም አይደለም፡፡
ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ በዋስትና ከእስር ቢለቀቁ፣ ዕድሜ ልካቸውን ደረታቸውን ነፍተው በኩራት የኖሩባትን በአርበኝነት የቆሙላትን ሀገራቸውን ጥለው፣ ከተረፈ ወያኔ ደህንነቶችና ጆሮጠቢዎች የእይታ ቀለበት ተሰውረው ሀገር ጥለው ይጠፋሉ ተብለው ተጠርጥረውም አይደለም፡፡
ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ በወያኔ የሶልዲ ህገመንግሥት ላይ የተጻፈላቸውን የዋስትና መብት ተነፍገው በእስር እየተንገላቱ ያሉት – እሳቸውን ያየህ ተቀጣ በሚል ጥጋብና ተረኛ ባለጊዜነት በወለደው መንግሥታዊ ሽብርተኝነት የተነሳ ነው፡፡
ትናንት ገመቺስ (አማኑኤል) ወንድሙን በደምቢዶሎ በአደባባይ ያስረሸነው አብይ ነው፣ ዛሬ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱን በአደባባይ ጠፍንጎ ማንአለብኝነቱን የሚያሳይህ፡፡ ምን ታመጣላችሁ – ነው ቋንቋው፡፡ ምንም ስለማታመጡ አርፋችሁ ተቀመጡ! ነው መልዕክቱ፡፡ ያሻኝን ባደርግ ከልካይ እንደሌለብኝ እወቁት! ነው እወጃው፡፡
ይህን ባለጊዜነት አስረግጦ ለመናገር፣ የግድ እንደ እነ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ የመሰሉ አንጋፋ የሀገር ሀብቶች፣ በመከበሪያቸውና በመሸለሚያቸው፣ እንክብካቤና ጥንቃቄ በሚያስፈልጋቸው በእርጅና ዘመናቸው ላይ – በሶልዲው ህገመንግሥት ላይ የተጻፈው የዋስትና መብታቸው ተገፍፎ፣ እስርቤት ተወርውረው፣ ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው ተገፍፎ፣ ያለማንም ከልካይ በአህዮቹ ይረጋገጣሉ፡፡ ይህን የአብይ አህመድ አራጅ መንግሥት መቀጣጫ ሆነው ሌላውን ለማስፈራራት የግድ እንደ ገመቺስ ወንድሙ ያሉት ንጹሃን ወጣቶች በአደባባይ በእናቶቻቸው ፊት ይረሸናሉ፡፡ እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡
ይህን ሁሉ በጥሞና ሳስተውል ደግሞ ደጋግሞ የሚመጣብኝ አንድ በሰለጠነው የምዕራቡ ዓለም በአሁኑ ወቅት ሰፊ ተቀባይነትን ያገኘ የፕራግማቲክ ሥርዓተ መንግሥታዊ የህብረተሰብ ፍልስፍና አለ፡፡ ‹‹በያንዳንዱ የዓለም ሀገር፣ እያንዳንዱ የሀገሬው ህብረተሰብ የሚያገኘው ሥርዓተ መንግስት – ያንን ህብረተሰብ የሚመጥነውና የሚገባው (በልኩ የተሰፋለትን) ሥርዓተ መንግሥት ነው›› የሚል፤ ከተግባር ተሞክሮ በዓለም ዙሪያ ሁሉ ካሉ ነባራዊ ተሞክሮዎች ተጠንቶ የተቀመረ እጅግ ተቀባይነት ያገኘ የጊዜያችን ፍልስፍና ነው፡፡
በዚህ ፍልፍና መሠረት ለምሳሌ ሳዑዲዎች በአራጅ ፈላጭ ቆራጭ ዘውዳዊ ሼሆች የሚተዳደሩት – ሳዑዲዎች ያላቸው ንቃተ ህሊና ከዚያ በላይ የዘመነ ሥርዓትና የተሻሉ መሪዎች እንዲኖራቸው ስለማይፈቅድላቸው ነው፡፡ ኢራቆች ሳዳምን በሚያህል ደም በተጠማ አምባገነን ሥርዓት ሥር ሲተዳደሩ የኖሩት የኢራቅ ህዝብ ንቃተህሊናና ዝግጁነት ከዚያ የተሻለ ሥርዓትን ለማዋለድ የሚያበቃ የሰለጠነ የዝግመተ ለውጥ ደረጃ ስለሌለው ነው፡፡
በተመሳሳይ መንገድ፣ የራሳችንን ነገረ-ሥራ ካየን፣ በዚህ ፍልስፍና ትንታኔ መሠረት የምናገኘው ማብራሪያ እያጨድን ያለነው ከየራሳችን ጎታ አውጥተን የዘራነውንና የሚገባንን ነው ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔና ኦነግ በተቀረጸለት ሶልዲ ህገመንግሥት ሥር በተዋቀረ ሰው-በላ ሥርዓት እየተዳደረ የምናገኝበት ምክንያት – ሕዝቡን የሚመጥነው ይሄው ዓይነቱ ስርዓት ስሰሆነ ነው ማለት ይሆናል፡፡
ሕዝባችን እንዲህ ዓይነቱ የዘቀጠ የጋርዮሽ ዘመን የጎሳና የሜንጫ ሥርዓት አይገባኝም ብሎ ባይቀበለው ኖሮ፣ ከላዩ ላይ ገፍፎ ጥሎት የተሻለ ሥርዓትና መሪዎችን ይፈጥር ነበር፡፡ ያ ያልሆነበት ምክንያት አብዛኛው ማህበረሰብ በዚህ ዓይነቱ መንገድ መገዛትን እሠየሁ ብሎ ስለተቀበለው፣ ስለተስማማው፣ ስለሚመጥነው ነው፡፡ እና ያው የሚመጥነንን፣ በልካችን የተሰፋልንን፣ የሚገባንን ዓይነት መንግሥት እየኖርነው ነው፡፡ እኛኑ የመሰለና የሚገባንን ምስ የሚሰጠን መንግሥትም በሶልዲ ህገመንግሥቱ እስኪበቃን እየገረፈ ሰጥ ለጥ አድርጎ እያስተዳደረን ነው ማለት ነው፡፡
ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ፣ እና እንደ ፕ/ር አሥራት ወልደየስ፣ እንደ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም፣ እንደ ፕ/ር ምንዳርአለው ዘውዴ፣ እንደ እስክንድር ነጋ፣ እንደ ተመስገን ደሳለኝ፣ እንደ ጎቤ መልኬ ያሉ ሌሎችም በርካታ ከማህበረሰባቸው ንቃተ-ህሊና ልቀው የወጡ አብረቅራቂ ኢትዮጵያውያን ግን ከዚህ ጋርዮሻዊ አገዛዝ ከመጠነው የጋራ ሥፍር ይለያሉ ማለት ነው፡፡ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ ያንን ዓይነቱን የወረደ ሥርዓት አይገባኝም ብለው በአደባባይ ስለቆሙ በሥርዓቱ አጋፋሪዎች ተረጋግጠው በስተርጅና እየማቀቁ ነው፡፡
እንደሚገባኝና ከልቤ እንደማምንበት፣ እሳቸው የሚገባቸውን በመናገር እና ለሚገባቸው በልበ ሙሉነት በመቆም፣ ለህሊናቸው ታምነው ለቃላቸው በመገኘት – ራሳቸውን ከማይመጥናቸው ሶልዲ አገዛዝ በሚገባ ነጻ አውጥተዋል፡፡ ከሚገባኝ በታች አልኖርም ብለው የሚደርስባቸውን ግፍ እየተቀበሉመ ነው፡፡ ለዓለምም የጎፈየውን ሥርዓት እውነተኛ ማንነትና አረመኔ ቁመና  እርቃኑን አውጥተው እያስጣጡት ነው፡፡
ሌላው ሰውስ? ሌላው ሰው ወይ በሚገባውና በልኩ በሚመጥነው ሥርዓት ረክቶ በደስታና በተድላ እየኖረ ነው፡፡ ማለት ነው፡፡ ወይም ሶልዲው ሥርዓተ መንግሥትና ክብረነክ ሰብዓዊ አያያዙ የማይገባኝ (የማይመጥነኝ) ነው ብሎ ቢያምንም፣ እንደ ሰባ ዓመቱ አዛውንት እንደ ጋሼ ታዲዮስ ታንቱ በልበ ሙሉነት ቆሞ የሚገባውን ለመጠየቅ ወኔው ከድቶታል ማለት ነው፡፡
ጋሼ መስፍን ወልደማርያምን በአንድ ነገራቸው ከልቤ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ እውነቱን ፊትለፊት መናገርን አስተምረውኛል፡፡ ስለሆነም እየተናገርኩት ነው፡፡ በምንም ተቀባባ፣ በምንም ተሟሸ፣ በምንም ታጀለ፣ እውነቱ ይኸው ነው፡፡
እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ፈጣሪን የምለምነው አንድን መከናወን ብቻ እንዲሰጠን ነው፡፡ ፈጣሪ የልባችንን ምኞት እንዲሞላልን፡፡ ሥርዓቱ በልካችን ለተሰፋልን ነው ብለን ለምናምነው፣ ሃጃችን ወጥቶልናልና እንግዲህ ጭንቀት የለብንም፣ ደስ ይበለን፡፡ ቅር የሚያሰኝ ነገር አያግኘን፡፡
የለም ይህ ጉልበተኛው በውሻ ክራንቻው አቅመቢሱን ባደባባይ እየዘነጣጠለ የሚኖርበት፣ የበዪና ተበዪ ህገአራዊት ሥርዓት አይመጥነንም፣ ከልካችን በታች በዋለ ሥርዓትና የሰው ደም መጥጠው በማይበቃቸው ቫምፓየር አንጋቾቹ እየተገዛን ለመቀጠል አንፈቅድም ብለን ለምናስበው፣ እና በቁጭት ለምንደብነው ኢትዮጵያውያን ደግሞ፣ በሶልዲው ሥርዓተ መንግሥት ፊት በልበ ሙሉነት ለመቆምና፣ የሚመጥነንን ሥርዓት ለመጠየቅ – የጋሼ ታዲዮስ ታንቱን አንድ ሚሊዮንኛዋን ወኔ በልባችን ይዝራብን ብዬ ነው የምለምነው የኢትዮጵያን አምላክ፡፡
‹‹ለምኑ ይሰጣችኋልም፤ ፈልጉ ታገኛላችሁም፤ ደጅ ምቱ ይከፈትላችኋልም፡፡››
       — ማቴ 7፥7
ፈጣሪ ልመናችንን ይስማን፡፡ 
የሻትነውን ይስጠን፡፡ 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በክብር ትኑር፡፡
Filed in: Amharic