>

የኢሳታውያን የምድጃ ዳር ወግ ...!!! (ዲ/ን ታደሰ ወርቁ)

የኢሳታውያን የምድጃ ዳር ወግ …!!!

 ዲ/ን ታደሰ ወርቁ 

አንድ የብዙኋን መገናኛ ተቋም፥ ተቋማዊ እና ሕሊናዊ ሰውነቱን ሊያጣ አይገባም፡፡ አንድ የብዙኋን መገናኛ ተቋም፥ በዋናነት ተቋማዊ ሰውነቱን አጣ የሚባለው፥ ርቱዓዊ የሕዝብ ደምፅ መሆኑን አቁሞ፥ የአፋኞች የፕሮፖጋንዳ የዘውትር ቀለም ሆኖ ሲያገለግል ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሕሊናዊ ሰውነቱን አጣ የሚባለው፥ የተቋሙ የሥራ ሓላፊዎችና ጋዜጠኞች ሚዛናዊነትንና እውናዊነትን ዕለታዊ ድርጎ በሚሰፍሩላቸው፥ አፋኞች ኪስ ውስጥ የሚያስቀምጡ ከሆነ ነው፡፡
በዚህ ንድፈ አሳባዊ ትንታኔ መሠረት፥ ኢሳት ቴሌቪዥን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፥ ተቋማዊ ሰውነቱን ብቻ ሳይሆን፥ ሕሊናዊ ሰውነቱንም አጥቷል፡፡ በተቋም ደረጃ እንደመንግሥታውያኑ የብዙኋን መገናኛዎች ሁሉ፥ የአየገዛዙ የጭቆናና የአፈና ተቀላቢ የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው፡፡ በዚህ ተቋማዊ ሰውነቱን አጥቷል፡፡ የዕለት አደር ጋዜጠኞቹም፥ ለአገዛዙ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች፥ በተናቦሻዊ አእምሯዊ ስሪት ሚዛናዊነትንና እውናዊነት ደፍቀው፥በዕለታዊነት እያገለገሉት ይገኛሉ፡፡ በዚህ ደግሞ ሕሊናዊ ሰውነቱን አጥቷል፡፡
በእንዲህ ዐይነት መልኩ፥ በኢትዮጵያ ዲሞክራሳዊ የፖለቲካ ሥርዐት በማዋለድ ሂደት ላይ ለውጡን በመጠበቅና በመከባከብ ሽፋን መቆመራቸው ሳያንስ፥ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ለመተርተር እየተደረገ ባለው አደገኛ እንቅስቃሴ ውስጥ በግልጽ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ደግሞ ፓትርያርኩ ላይ የያዙት የኪራይ ፖለቲካ (Client Politics) አቋም ነው፡፡ ከእነዚህ የኪራያዊ የፖለቲካ አቋሞቻቸው ውስጥ አደገኛው ደግሞ፥ “ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ከመንበረ ሥልጣናቸው አውርዶና እንደራሴ በመሾም ቤተ ክርስቲያኒቱን በብፁዕ ወቅዱስ አበኑ መርቆሪዎስ እንድትመራ ማድረግ የሚለው ፕሮፖጋንዳቸው ነው፡፡” ይህን ሲሳይ አጌና ግንቦት 3 እና 4 ቀን 2013 ዓ.ም፥ በኢሳት ቴሌቪዥን በተላለፈው ዕለታዊ መርሐ ግብር ላይ እንዲህ ሲል ያረጋግጣል፡፡
• “. . . አቡነ ማትያስ በቃኝ ቢሉ እኮ የሚቀየር ፓትርያርክ የለም፤ አዲስ ፓትርያርክ አይመረጥም፤ . .  . የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ሕጋዊው ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስ አሁንም በመንበራቸው አሉ፤ በሕወይት አሉ፤ በሥራቸው ላይ ናቸው፤ የሚፈጠር ክፍተት አይኖርም ፡፡ . . . “
ይህን መልእክት ከሰሞኑ ቤተ ክህነት ውስጥ እየተደረገ ካለው አደገኛ እንቅስቃሴና ኤርትራ ዳግም በፖትርያርክ ላይ ፓትርያርክ መሾሟና ይህንንም ኢቀኖናዊ ድርጊት ሲሳይ አጌና ከማወደሱ ጋር አዛምደን ከተመለከትነው ደግሞ፥ አንድ ነገር ይነግረናል፡፡ይኽውም ሕ.ወ.ሓ.ት. አራተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አበኑ መርቆሪዎስን በቃኝ እንዲሉ በማስገደድ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ እንደ አደረገው ሁሉ፥ ስድስተኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን በቃኝ እንደሉ በማድረግ ከሥልጣናቸው በማውረድና ለብፁዕ ወቅዱስ አበኑ መርቆሪዎስ እንደራሴ በመሾም ቤተ ክርስቲያኒቱን ለፖለቲካዊ ፍትወት ማሳፈጸሚነት የማዋል ውጥን መኖሩን ይገልጥልናል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳንም ይህን አደገኛና ከፋፋይ ውጥን በመረዳቱ፥ በመግለጫው ‹‹ . . . ይዘቱ ምንም ይሁን ምን ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ ሰው የሚሰማቸውን ስሜትና አሳባቸውን መግለጽ መቻላቸው ተፈጥሮአዊ መብት ሆኖ እያለ፥ የእርሳቸውን ንግግር ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት እንደ ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ፥ ሲኖዶሱን ለመከፋፈልና ለማዳከም ብሎም ተቋማዊ አንድነትዋን ለማናጋት የሚደረገው ርብርብ በእጅጉ የሚያሳዝን ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ . . .  በቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጣችሁ የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅና ምእመናንን ለመጠበቅ የተሰጣችሁን አደራ ለጊዜያዊ ጥቅምና የፖለቲካ ፍላጎት መጠቀሚያ ያደረጋችሁ አካላት ከዚህ ድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ በተጨማሪም ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በተያያዘ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅናና መመሪያ ውጭ እና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ባልተከተለ መልኩ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ›› ሲል በመቃወሙ እሳታውያንን በእጅጉ አስቆጥቷል፡፡ በዚህም የተነሣ ለማኅበረ ቅዱሳን ያለስሙ ስም ለመስጠት እና በማኅበሩ አባላት መካከል ልዮነትን ለመዝራት ሲጥሩ ታይተዋል፡፡ መንግሥትም በማኅበሩ ላይ ርምጃ እንዲወስድም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
 ኢሳታውን አንድ ነገር ልብ እንዲሉ ግን ያስፈልጋል፡፡ ትላንት ለፖለቲካዊ ፍላጎታቸው ማኅበሩን ደግፈው እንደዘገቡለት ሁሉ፤ ዛሬም ለፖለቲካዊ እና ጥቅማዊ ፍላጎታቸው ተቃውመውታል፡፡ ከዚህ ውጭ ማኅበረ ቅዱሳን እነርሱ የገለጹቱን ዐይነት በጥቂቶች የሚዘወር ማኅበር አይደለም፡፡ ዛሬ ያለው ኢሳት ተቋማዊ እና ሕሊናዊ ሰውነቱን እንደአጣ፤ ዘሬ ያለው ማኅበረ ቅዱሳንተ ቋማዊ እና ሕሊናዊ ሰውነቱን አላጣም፡፡ ዛሬ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን የትላንቱ ነው፡፡ ትላንት ለየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛ እንዳልነበረ ሁሉ፥ ዛሬም ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኛ አይደለም፡፡ እናም ሰሞነኛው የቅጥረኝነት ክሳቸው አደገኛ ቢሆንም፥ የምድጃ ዳር ወግ ከመሆን የዘለለ፥ርቱዕ በሆነው የማኅበሩ አገልግሎት ላይ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ሊያመጣ እንደማይችል እሙን ነው።  ይልቁንም ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ ለመሆኗ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የትላንቱን ሰደት በትላንት ዕንቍ ልጆቿ ተጋድሎ እንደ ተሻገረችው ሁሉ፤ የዛሬ ስደቷንም በዛሬ ዕንቍ ልጆቿ ትሻገራለች፡፡
Filed in: Amharic